ደብረ ማርቆስ፡- ደብረ ማርቆስ ከተማ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር በከተማ አስተዳደሩ ሥራ ላይ ጫና መፍጠሩ ተገለፀ። የፌዴራል መንግስትም ችግሩን ተገንዝቦ የሰብ ስቴሽን ማሻሻያ በማድረግ ችግሩን ባፋጣኝ እንዲፈታም ተጠይቋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ አቶ ዳንኤል በላይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከተማዋ የሚለማ ሰፊ ሀብት ያላት እንደመሆኗ እያደገችና ኢንቨስትመንት እየሳበች ያለች ናት። ይሁን እንጂ በከተማዋ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር መኖሩ በአስተዳደሩ ሥራ ላይ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። የፌዴራል መንግሥት ይሄን ተገንዝቦ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ ደብረ ማርቆስ ምቹ የአየር ፀባይ፣ ሥራ ወዳድ ህዝብና የትርፍ አምራች ዞን ዋና ከተማ እንደመሆኗ ወደ ከተማዋ በርካታ ባለሃብቶች መግባታቸውና ኢንቨስትመንቱም እየተስፋፋ መሄዱ አይቀርም። ሆኖም በከተማዋ የመብራት አቅርቦቱ እጅግ የተጓደለ በመሆኑ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው፡፡
አሁን እየሰራ ያለው ሰብስቴሽን፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት የተገነባና ብዙ ችግር ያለበት፤ በትንንሽ ችግሮች የሚቋረጥና አቅሙም በጣም ደካማ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል ይህ ደግሞ በከተማዋ የውሃ አቅርቦት ሂደት ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል። በዚህም እንኳንስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ሊሰሩ ቀርቶ፤ በከተማዋ ያሉ ትንንሽ ፋብሪካዎችና ወፍጮ ቤቶችም ጭምር ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳንኤል እንደሚሉት፤ ይህ የመብራት ችግር እስካልተፈታ ድረስ የወጣቱ የሥራ እድል ፈጠራም ሆነ የከተማው ህዝብ ኑሮ ሊሻሻል አይችልም።የውሃ አቅርቦቱም ዘላቂ መፍትሄ አያገኝም።ማርቆስ ላይ ሆኖ ውሃ መጠማት ደግሞ፣ “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” የሚለውን ተረት በተግባር እንደማየት ነው።በመሆኑም የከተማዋን የመብራት ችግር የፌዴራል መንግሥት በአጽንዖት ይዞ የሰብ ስቴሽን ማሻሻያ በማድረግ ሊፈታው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ወንድወሰን ሽመልስ