አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች በአርሶ አደሩና ዩኒየኖች መካከል የምርት ወቅት የግዥ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ።
በአሠራሩ ዘመናዊነትን የተከተለውና በአርሶ አደሩና በዩኒየኖች መካከል መተማመንን፣ በገበያው በኩል መረጋጋትን፣ ከአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት አኳያም ፍትሀዊ አሰራርን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቀው የግዥና ሽያጭ የንግድ ስምምነት የክልሉ፣ የዞኑ፣ እና የወረዳው ባለስልጣናት፣ በክላስተሩ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተወካይ እንዲሁም በርካታ አርሶ አደሮችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ማክሰኞ ተፈፅሟል።
ዘመን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያነጋገራቸው የአርሲ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆ እንደ ተናገሩት ይህ የግዥ ስምምነት ከዚህ በፊት ገብስ አምራች አርሶ አደሮች ከቢራ ጠማቂ ፋብሪካዎች ጋር በመፈራረም ተግባራዊ ያደረጉት ሲሆን ውጤታማነቱም በተደጋጋሚ ተረጋግጧል።
አቶ አባቡ እንደሚናገሩት በመጀመሪያ ኩታ ገጠም መሬቶች ይዘጋጃሉ፣ ሰፊ ምርት ለማምረት እንዲያስችል በክላስተር ይደራጃሉ፤ ይህ ክላስተር በተመሳሳይ ሰዓት በተመሳሳይ ማሽን ይታረሳል፣ ተመሳሳይ ዘር ይዘራል፣ ተመሳሳይ እንክብካቤም ይደረግለታል። ይህ እስከ ገበያ ትስስር ድረስ የሚዘልቅ አሰራር ነው።
ከስንዴ፣ በተለይም አሁን እየተዘራ ካለውና ለፋብሪካ ግብዓት ተመራጭ ከሆነው ኦጎልቾ ስንዴ ምርጥ ዘር አኳያ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው የዘር መሬቱ በማሽን መዘጋጀቱና መዘራቱ ነው።አርሶ አደሩ የገበያ ስጋት እንዳይገባው ከወዲሁ ከዩኒየኖችና ዱቄት ፋብሪካዎች ጋር ስምምነት መፈራረሙና ውል መግባቱን የሚናገሩት አቶ አባቡ ይህ አሰራር በዋናነት የአርሶ አደሩን የገበያ ስጋት እንደሚያስወግድም ይናገራሉ።
በአርሲ ዞን፣ ዲገሉና ጢጆ ወረዳ፣ በፊቴ ከታራ እና ገረንቦታ ሎሌ ቀበሌዎች ውስጥ በክላስተር የተደራጁት አርሶ አደሮች በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከመካከላቸው አቅመ ደካሞችና የገንዘብ እጥረት ያለባቸው እንደሚገኙበት ኃላፊው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ዞኑ ለሁሉም እኩል ዘር፣ እኩል ማዳበሪያ፣ እኩል አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ስራው አንድ ወጥ በሆነ ሁኔታ እንዲሰራ እያደረገ እንደሚገኝ፤ አንድ ክላስተር በርካታ አርሶ አደሮችን ያቀፈ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ ገረንቦታ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘውና ምርቱ ሲደርስ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ለመገበያየት የሚያስችል የገበያ ስምምነት የተፈራረሙበት ክላስተር 107 አርሶ አደሮችን የያዘና 316 ሄክታር መሬት እንደሚሸፍን የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ነግረውናል።
በአጠቃላይ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙት 25 ወረዳዎች 17ቱ ወደዚህ ዘመናዊ አሠራር ገብተዋል።106 ሺህ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው ውጤታማ በመሆን ላይ ሲሆኑ በዘንድሮው የምርት ዘመንም ከዞኑ 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ኃላፊው አስረድ ተዋል።
ከዩኒየኖችና ፋብሪካ ባለቤቶች ጋር መፈራረሙ አርሶ አደሩን በደላላ ከሚመራ ገበያ በመከላከል የልፋቱ ተጠቃሚ እንደሚ ያደርገው፣ ህገ-ወጥ የግብይት ስርዓትን እንደሚያስቀር፣ ማሳው ድረስ እየገቡ ምርቱን በማጭበርበር በርካሽ ዋጋ በመግዛት እራሳቸውን ብቻ ከሚጠቅሙ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እንደሚከላከል እና ጤናማ የአምራችና ሸማች ስርዓት በአገሪቱ እንዲፈጠር የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ኃላፊው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ግርማ መንግስቴ