በኢትዮጵያ ሕጎችን በተግባር ለማዋል በሚደረገው ሥራ ውስንነትና ተያያዥ ምክንያቶች ሙስናና ሌሎች ወንጀሎች እየተበራከቱ ስለመምጣታቸው ምሁራን ይናገራሉ።በወቅቱ መፍትሄ ካላገኘም የጎበዝ አለቆችን በማበራከት በሕዝቦች አብሮነትና በአገር አንድነት ላይ አደጋን እንደሚጋብዝ፤ የፖለቲካ ጥያቄው ወደ ዳቦ ጥያቄ የሚሸጋገርበትን እድሜም እንደሚያፋጥን ያስገነዝባሉ፡፡
ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሥርዓት ለማስያዝ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚሠራው ሥራ በተዳከመ ቁጥር የወንጀል ተግባራት ይበራከታሉ።ሥርዓት ሲጠፋ ደግሞ የመንግሥት ሥራም በአግባቡ አይከናወንም። ወንጀልን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ ደግሞ ሙስና ነው፡፡
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሙስና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት፤ በመቶ ሚሊየንና ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በግለሰቦችና በተወሰኑ ቡድኖች የሚወሰድበት ነው። ይሄ በራሱ ቅሬታን በመፍጠር የወንጀል ድርጊትን ያባብሳል። ሙሰኞች ደግሞ እውቀቱም፣ ገንዘቡም፣ የመንግሥት መዋቅሩም ስላላቸው ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የሕግ ሥርዓቱ በአግባቡ እንዳይሄድ ለማደናቀፍ ባላቸው ገንዘብ፣ ጉልበትና አቅም ተጠቅመው ተጨማሪ ወንጀል ይሠራሉ፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ፍሰሃ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ከልማታዊ መንግሥት ባህሪ አንጻር ሰፊ የልማት ሥራ ስለሚከናወንና ብዙ ሀብትም ስለሚንቀሳቀስ በአገሪቱ ሙስና አንድ መገለጫ ሆኖ ታይቷል። ዛሬም ድረስ የመንግሥት አሠራር ግልጸኝነት አለመኖር ከግዢ፣ ከፕሮጀክቶች የጨረታ ሂደት፣ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ፣ ብድር አከፋፈልና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አሠራሮች ለሙስና በር የሚከፍቱ ናቸው፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን ገለፃ፤ በዚህ መልኩ ከሚገለፀው የሙስና ወንጀል ባለፈ አጠቃላይ ወንጀሎችም በስፋት ይስተዋላሉ።በየቦታው ሰዎች ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ፤ ባንኮች ይዘረፋሉ፤ የኢኮኖሚ ሻጥሮች ይፈጸማሉ፤ የመሬት ወረራውም ተበራክቷል።እነዚህ ወንጀሎችም በተደራጀ መልኩ ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡
ለእነዚህ ወንጀሎች መባባስ የሕግ ማዕቀፍ ችግር ኖሮ ሳይሆን፤ የወጡ ሕጎችን በተግባር አለመፈፀም፤ በሕዝቡ ዘንድም ያላቸው ቅቡልነት ነው።ከክልል ጀምሮ ያለው መዋቅር የሕግ የማስከበር ተግባር መላላት፤ እንዲሁም የፀጥታ አካሉ በሚፈለገው ልክ እየሠራ አለመሆን ዘረፋና የጎበዝ አለቆችን አበራክቷል።ሰዎች በስነልቡናና አዕምሮ እንዲዘጋጁ፤ ወንጀል መፈፀም ኢ-ሰብዓዊ ተግባር መሆኑን እንዲገነዘቡ፤ ሞራላዊ እሴቶቻቸውንም እንዲያጎለብቱ አለመደረጉም የሙስናና የወንጀሎች መበራከት ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ባለው ሁኔታ የጎላ የሕግ ክፍተት አለመኖሩን የሚናገሩት ዶክተር ሲሳይ በበኩላቸው፤ መንግሥት ያሉትን ሕጎች በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ ካዋለ ሊያሠሩ የሚችሉ ሕጎች መኖራቸውን ይገልጻሉ።በዚህ ረገድ የወንጀል ሕጉም ሰፊና ብዙ ነገሮችን የያዘ፤ ሙስናን የሚመለከቱ ሕጎችም ወደ ወንጀል ሕጉ ሲካተቱ ያንኑ ታሳቢ አድርገው መሆኑን፤ ሌሎች የወንጀል አይነቶችም በአንድም በሌላ መልኩ ከወንጀል ሕጉ ጋር የተያያዙና የተካተቱ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፤ ምንም እንኳን ፍፁምና ምሉዕ ነው ባይባልም አሁን ያለውን ችግር ያመጣውም የሕጉ ክፍተት ሳይሆን የሕጉ በአግባቡ ሥራ ላይ አለማዋል ነው።አስፈጻሚው አካል በተለይ መንግሥት ሕግና ሥርዓትን የማስከበር፤ ሕግ ጥሰውና ወንጀል ፈጽመው የሚገኙትን አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ መንግሥት መኖሩን ማሳየት መቻል አለበት።በዚህ መልኩ ሕግ የበለጠ ተግባራዊ እየተደረገ ሲኬድ ነው የሕጎች ክፍተትም እየተለየ የሚሄደው፡፡
ለዚህ ደግሞ ከምርመራ ጀምሮ እስከ ፍርድ ባለው ሂደት የአፈፃፀም ክፍተት ይስተዋላል።ለምሳሌ፣ የወንጀል ድርጊቶች ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዳቸው በፊት ፖሊስ በአግባቡ መመርመር አለበት።የፖሊስ የምርመራ ሂደት ታክቲካዊም ሆነ ቴክኒካዊ፣ በሰነድና በሰው ምስክርነትም የሚተላለፉ የምርመራ ሂደቶችን በደንብ በመሥራት ጠንካራ መረጃና ማስረጃን ይዞ ለዓቃቤ ሕግ ክስ ከማቅረብ አኳያ የሚኖሩ ክፍተቶች አሉ።ይህም ሕግን ተከትሎ ከመሥራት፣ ከቁርጠኝነት፣ ከባለሙያ እጥረትና ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ጋር በተያያዙ ችግሮች ይፈተናል፡፡
ሁለተኛው፣ የፖሊስ ምርመራ ወደ ዓቃቤ ሕግ ከተላከ በኋላ ዓቃቤ ሕግ የደረሰውን መዝገብ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ባስቀመጠው መርህ መሰረት ካለመሥራት ጋር ይያያዛል።በዚህም ከፖሊስ ምርመራ ጋር በተያያዘም ሆነ ዓቃቤ ሕግ መረጃው ተሟልቶ እንዲቀርብለት ካለማድረግ የመነጨ ከእኔ እጅ ይውጣና ፍርድ ቤቱ እንዳደረገ ያድርገው በሚል ወደ ፍርድ ቤት የመጣል ነገርም ነው።በዚህ መልኩ ጠንካራ ክርክር ለማድረግ የሚያስችል የተሟላ ማስረጃ ይዞ የማይከራከር ከሆነ፤ በዳኞችም ሆነ በተቋም ደረጃ ካሉ ክፍተቶችና ጫናዎች ጋር ተዳምሮ ፍርድ ቤት ምንም ሊያደርግ ስለማይችል ወይ በዋስ ይለቅቀዋል፤ ወይም ነፃ ያደርገዋል፤ ማስረጃው ከደከመበትም በዝቅተኛ ቅጣት ሊለቀው ይችላል፡፡
ይህ ሂደት ደግሞ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።ምክንያቱም ፖሊስ ባለመሥራቱ፤ ዓቃቤ ሕግም በተገቢው መልኩ ሥራውን ሠርቶ ውጤት ባለማስገኘቱ፤ ፍርድ ቤትም የመጨረሻው ፍትህ የማስፈን ሥራ ሂደት ውስጥ ከእርሱ የሚጠበቅበትን ሚና ባለመወጣቱ ምክንያት ህዝቡ በፍትህ አካላትም ሆነ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፤ ፍትህንም በራሱ ለማግኘት በሚያደርገው ጉዞ የመንጋ ፍትህ እንዲመጣ፤ ሥርዓት አልበኝነቱ በየቦታው ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል፡፡
ዶክተር ሲሳይ እንደሚሉት፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ጠንካራ መንግሥት የነበራትና በተሻለም የሰለጠነ አገር ተብላ ትወሰድ የነበረችውን ሶሪያ፤ እንዲሁም ዴሞክራሲን ለመተግበር በመልካም ሂደት ላይ የነበረችው የመን አሁን በከፋ ችግር ውስጥ ናቸው።በሊቢያ የሆነውና ሱዳን ላይ እየገጠመ ያለው ችግርም የዚሁ አይነት ነው።ኢትዮጵያም ውስጥ ሥርዓት አልበኝነቱ ሥር እየሰደደ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያም ውስጥ እንዲህ አይነት ሥርዓት አልበኝነት እየተጠናከረ ከሄደ ወደነዚህ አገራት መስመር የማይገባበት ምክንያት አይኖርም።በዚህ ሂደት የሲቪል አስተዳደሩ በብቃት መምራትና ሕግን ማስከበር ካልቻለ፤ በሥርዓት አልበኞች ላይም እርምጃ የማይወስድ ከሆነ፤ የፍትህ ችግር እየተባባሰ ከሄደ በየቦታው የጎበዝ አለቃን በመፍጠር በአገር አንድነትና ሕልውናም ላይ አደጋን፤ አጠቃላይ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይም ተጽዕኖን ይፈጥራል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር መኮንን እንደሚሉት ደግሞ፤ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካና በሌሎች አካባቢዎች የማፍያ ቡድኖች ከመንግሥት በላይ ጉልበት ሲያበጁና ሕግን ከማስቀየር ጀምሮ የፈለጉትን ሲያደርጉ ማየት ተለምዷል።በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የጎበዝ አለቆች መበራከትም በዚሁ ከቀጠለ ወደዚህ ከመሄድ የሚያግድ አይኖርም።ይህ ደግሞ ህዝቡ እንዲሰጋና እንዳይረጋጋ ያደርጋል፤ የታየው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስም የንግድና ኢንቨስትመንት መዳከምን ስለሚያስከትል ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሸጋገር ያደርጋል።የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥያቄም ወደ ዳቦ ጥያቄ የሚሸጋገርበትን ዕድሜም ያፋጥናል፡፡
እንደ ምሁራኑ አባባል፤ አሁን ያለውን የሙስናና የተለያዩ ወንጀሎችን ለመከላከልና ቀጣይ የሚያሳድሩትን አደጋ ለማስቀረት መንግሥት ራሱን በመፈተሸ ጭምር ለሕግ ለበላይነት መከበርና ለሕጎች ተፈፃሚነት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት።የትኛውም የአገሪቱ ክፍል ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉና የሚፈጠሩ ወንጀሎችን መከላከልንም የመጀመሪያ ሥራው ማድረግ አለበት።የሕግ አስከባሪ አካላት (ፖሊስንና ሌሎች የሕግ አስከባሪ አካላት) ቁርጠኛ እንዲሆኑ ሙሉ ሃላፊነቱን መስጠት፤ አደረጃጀቱንም መፈተሽ፤ ርዕስ በርዕሳቸውም ተቀናጅተው እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል።
ህብረተሰቡም ወደ ሕግ ማክበር ሂደት ውስጥ እንዲመለስ ማድረግ፤ የሻከሩ ግንኙነቶችን መፍታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር፤ ፍርድ ቤቶች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ፤ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችና ሃላፊዎችን በየተቋማት ማስገባት፤ በሁሉም አካባቢዎች በተለያዩ አካላት ለሚፈጠሩ ችግሮች እኩል ትኩረት በመስጠት ያለ አድሎ ተገቢውን የሕግ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡
በተመሳሳይ በክልል መንግሥታት ያለውን የአስተዳደር መላላት መመልከት፤ ሥጋቶችን መቀነስ፤ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በመገምገም አጠቃላይ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስመሮችን ከቃል ባለፈ ወደተግባር መቀየር ይገባል።ከአሸናፊና ተሸናፊ፣ ከንትርክና ቂም በቀል አካሄድ በመውጣት ያሉ ችግሮችን በመለየት ለመፍትሄ መሥራት ያስፈልጋል።ለዚህ ደግሞ ሁሉም በየደረጃው የበኩሉን መወጣትና ሥራውን መሥራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ወንድወሰን ሽመልስ