
– ከመኸር እርሻ 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በዘንድሮ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ከ278 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ዞኑ ገለጸ:: ከመኸር እርሻ 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል::
የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር መነሻ በማድረግ በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ ከ278 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ ነው::
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 35 በመቶ የሚሆኑት ለምግብነት የሚያገለግሉ የአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓዬ፣ ብርቱካን፣ ቴምርና ሌሎችም እንደሆኑ አብራርተዋል:: በፍራፍሬ ዛፎች ላይ ትኩረት መደረጉን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ የተቀረው ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለውበትና ለከብቶች መኖ የሚያገለግል መሆኑን ተናግረዋል::
እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፤ ዞኑ ለአቮካዶ ምርት ተስማሚ የአየር ሁኔታ ያለው በመሆኑ ከአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ጋር በማያያዝ በስፋት እየተሠራበት ይገኛል:: ዞኑ የአቮካዶ ምርትን ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ዘጠኝ ሺህ ኩንታል አቮካዶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል::
ምርታማነቱን ለማሳደግ አምና 900 ሄክታር መሬት ብቻ ለአቮካዶ ምርት አምራቾች ይሰጥ የነበረ መሆኑን አንስተው፤ በዘንድሮው ዓመት ወደ አንድ ሺህ 200 ሄክታር ከፍ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል:: የኢትዮጵያ አቮካዶ ምርት በሚደርስበት ወቅት የሌሎች አምራች ሀገራት ምርት ወደ ገበያ የሚወጣበት ወቅት ባለመሆኑ ይህንን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ገበያውን የማሳደግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል::
በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ ችግኝ ጣቢያዎች ላይ እራሱን የቻለ የአቮካዶ ችግኝ ማፍያ ሼድ ተዘጋጅቶ የምርት አሰጣጥ ሁኔታው በጥናት የተረጋገጠለት ሀስ የሚባል ዝሪያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል:: በዚህ ረገድም ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ከመቻል ባሻገር አርሶ አደሩም በቅርበት ችግኝ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል::
በዞኑ በመኸር እርሻ 583 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 19 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው አያይዘው ገልጸዋል:: ከዚህ ውስጥ ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ እንደሚለማና በተጨማሪም ሩዝ፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎና ጤፍ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል::
በአሁኑ ወቅት በስንዴ ልማት በተሰራው ከፍተኛ ሥራ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት እስከ 16 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል:: ከማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ከአምና የተሻለ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት አስተዳዳሪው፤ ከሁለት ዓመት በፊት አርሶ አደሮች 530 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ይጠቀሙ እንደነበርና ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ ዘንድሮ ለአርሶ አደሩ ብቻ 720 ሺህ ኩንታል ማዳረስ መቻሉን ተናግረዋል::
አንደ አቶ አባቡ ገለጻ፤ ከምርጥ ዘር ጋር በተያያዘ የስንዴ፣ የሩዝና የጤፍ ምርቶች ምርጥ ዘር በፍላጎቱ ልክ ማቅረብ ተችሏል:: በሌሎች በተወሰኑ ሰብሎች ላይ ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ማሟላት አልተቻለም:: ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት የሰብል ዘርን በዩኒየኖችና ከተለያዩ ማህበራት ጋር በመሆን የማባዛት ተግባር እየተከናወነ ነው::
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 /2016 ዓ.ም