አንዳንድ የማይቻል የሚመስሉ ምኞቶቼ ተሳክተዋል:: የማይቻል ይመስሉኝ የነበረው የማይቻሉ ሆነው ሳይሆን ባለን ኋላቀር አመለካከት ምክንያት ነበር:: ልጅ ሆነን ከአካባቢያችን በጣም የራቀ አካባቢ (የሰማይ አድማስ የሚታይበት) ቦታ እየጠቆምን ‹‹ክንፍ ቢኖረኝና ብርርርር ብየ እዚያ ባርፍ›› እንላለን:: ይህ በተፈጥሮ የማይቻል ስለሆነ (የሰው ልጅ ክንፍ ስለሌለው) ምኞት ብቻ ነው::
በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ ስመኛቸው የነበሩ ነገሮች ግን የሚቻሉ ብቻ ሳይሆን በጣም ግዴታ መሆን የነበረባቸው ነበሩ:: በዚህ በትዝብት ዓምድ ከተስተናገዱ ትዝብቶች ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአካባቢ ንጽህና እና በሥነ ምግባር ዙሪያ ናቸው ስል ምንም ሳላጋንን ነው:: ይህ ለዓመታት ስንጮህበት የነበረ ጉዳይ ነው::
እነሆ አሁን ጊዜው ደርሶ በእነዚያ ስመኛቸው በነበሩ ጉዳዮች ላይ ቆራጥ ርምጃ ሲወሰድ ስሰማ ከልቤ ለማመስገን አልሰነፍኩም:: የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ቢሮ የሚሰጣቸው መግለጫዎችና ማስፈራሪያዎች ሊመሰገኑ የሚገባቸው ናቸው:: ለምሳሌ፤ መንገድ ላይ ሶፍት መጣል፣ ያለዜብራ መሻገር፣ የተንጣለለ የእግረኛ መንገድ እያለ በብስክሌት መሄጃው ላይ መሄድ…. የመሳሰሉት ያለምንም ማቅማማት ርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ናቸው:: በተለይ የንፅህና ጉዳይ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው:: ሶፍት መጣል ቀላልና ተራ ነገር ሊመስለን ይችላል:: ዳሩ ግን ይህ ዝርክርክ ልማድ ነው ከተማዋን ቆሻሻ አድርጓት የቆየው::
ሥነ ሥርዓትን ለማለማመድ ብዙ ዋጋ ይከፈላል፤ ብዙ አድካሚና አሰልቺ ነገሮች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው:: ሰዎችም ነገሩን እንደ ማካበድ እንደሚያዩት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይባስ ብሎም እንደ ጭቆና የሚያዩትም ይኖራሉ:: እንደፈለገው ሲዝረከረክ የኖረ ሰው ድንገት ሥነ ሥርዓት ያዝ፣ ሰልጥን ሲባል እንደ ጭቆና ሊያየው ይችላል:: ዳሩ ግን ይህ መብት አይደለምና ማስተማሩ ብቻ ሳይሆን ቅጣቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል:: የምንለማመደው በቅጣት ካልሆነ በስተቀር በምክር የምንሰማ አልሆነም! እስከ መቼ የኋላቀርነት ምሳሌ ሆነን እንኖራለን?
ከዚህ ምስጋና በኋላ ግን አንድ ሊቀረፍ ያልቻለ፣ እስከ አሁንም አጀንዳ ሲሆን ያላየሁት፣ ብዙዎችም እንደ ችግር ያላዩት አንድ ትልቅ ኋላቀርነት አለ:: ይሄውም የአሽከርካሪዎች ቅጥ ያጣ ጡሩንባ (ክላክስ) መልቀቅ ነው! በተለይም እንደ ሃይገር፣ አንበሳ ባስ እና ሌሎች ከበድ ያሉ ተሽከርካሪዎች የሚያንባርቁት ክላክስ አካባቢ ያናውጣል፤ የጆሮ ታምቡር ይበጥሳል::
አንድ አሽከርካሪ ለምን ክላክስ እንደሚያርግ ይገባኛል፤ የክላክስን አስፈላጊነትም ጠንቅቄ አውቃለሁ:: መቼና የት እንደሚደረግ ግን ሕግና ሥርዓት አለው:: በትክክል በሕግና ሥርዓቱ መሠረት ብቻ ይሂዱ ባይባልም፤ ቢያንስ ክላክስ ለማድረግ የሚያስገድድ ምክንያት መኖር አለበት:: የትራፊክ መብራት የያዘው ተሽከርካሪ ላይ ያን ያህል ማንባረቅ ምን ይሉታል? የትራፊክ መብራት ጥሶ እንዲሄድለት ነው? ለመሆኑ ከፊቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች የቆሙት መሄድ ጠልተው መስሎት ይሆን? እዚያ የቆመው ሊዝናና ነው?
አንዳንድ ቸልተኛ አሽከርካሪ እንደሚኖር ግልጽ ነው:: መሄድ እየቻለ፣ ስልክ ሲጎረጉር ወይም አንገቱን አሾልኮ ከሌላ አሽከርካሪ ጋር እያወራ የሚቆም ሊኖር ይችላል:: ለዚህ ክላክስ ማድረግ ተገቢ ነው:: ዳሩ ግን በሆነ አጋጣሚ መንገድ ተዘጋግቶ፣ መሄጃ አጥተው የቆሙ ተሽከርካሪዎች ላይ በረጅሙ ማንባረቅ የጤና ነው?
ብዙ አሽከርካሪዎች አካባቢን የሚያናውጥ ክላክስ የሚያደርጉት በብስጭት ነው:: በመንገዱ መዘጋጋት በመናደድ ነው:: ልክ አንዳንድ ሰዎች ሲናደዱ ዕቃ እንደሚሰብሩት ማለት ነው:: ለረጅም ደቂቃዎች መቆሙ ስልችት ይለዋል፣ ይህኔ እልሁን የሚቆጣው በረጅሙ ክላክስ በማንባረቅ ነው:: በእግረኛ መንገዱ ላይ የሚሄዱ ሰዎች የጤና ጉዳይ አያሳስበውም:: አያሳስበውም ብቻ ሳይሆን ‹‹ምናባታቸው!›› ሊል ይችላል:: መንገዱን የዘጉበት እነርሱ የሆኑ ይመስል እልህ መወጫ ያደርጋቸዋል:: በተለይም አሁን በተሰራው የኮሪደር መናፈሻዎች ላይ ደግሞ ብዙ ሰዎች አሉ:: ሰላምና ፀጥታ ለማግኘት ብለው ነው ከዚህ ቦታ ላይ የሄዱ:: ስለዚህ ያንን ሰቅጣጭ የሚያንባርቅ ክላክስ ሁለቱንም ጆሯቸውን ሸፍነው፣ ፊታቸውን ጨፍግገው ለመከላከል ይሞክራሉ ማለት ነው:: ድንገት በጮኸው ክላክስ ጆሯቸው ላይ ‹‹ጭውውውው!›› ሲልባቸው ይቆያል ማለት ነው:: ‹‹ዋውው! ለካ ሀገራችንንን እንደዚህ ማሳመርና ማሠልጠን ይቻላል!›› እያሉ ሲያደንቁ የነበሩ ሰዎች በድንገት ‹‹ኤጭ!›› ለማለት ይገደዳሉ ማለት ነው:: ቀጥሎም ‹‹መቼ ይሆን የምንሰለጥን?›› እያሉ ለማማረር ይገደዳሉ ማለት ነው:: ምክንያቱም ንጹህ አየርና ፀጥታ ለማግኘት የሄደ ሰው የጆሮ ታምቡር የሚበጥስ ክላክስ ሲጮህበት ራስ ምታት ሁሉ ሊነሳበት ይችላል::
ይህ እንዳይሆን የማያወላዳ ቅጣት መጀመር አለበት:: ለሥልጣኔ ገና ብዙ ይቀረናል:: ነገሮችን የምንተወው በምክርና በማሰብ ሳይሆን በቅጣት ሆኗል:: የትራፊክ መብራት የያዘው ተሽከርካሪ ላይ የሚያንባርቅ አሽከርካሪ ቢቀጣ እስኪ ምኑ ያሳዝናል? ለምሳሌ፤ ሰው የገጨ አሽከርካሪ ያሳዝናል:: ምክንያቱም በግዴለሽነት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ችግር እንጂ ሆን ብሎ ሰው የሚገጭ አይኖርም:: ስለዚህ ‹‹እንዲያው ምን አዘዘበት?›› ብለን ልናዝንለት እንችላለን:: ሆን ብሎ አካባቢን የሚረብሽ ሰው ግን ምንም ቢቀጣ ሆን ብሎ ነውና ያደረገው አያሳዝንም::
ይህንን ስል ምናልባት ‹‹ክላክስ ማስጮህ ይህን ያህል ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ነው ወይ?›› ያሰኝ ይሆናል:: አዎ! ትልቅ ጉዳይ ነው:: አደገኛ የድምጽ ብክለት ያልታወቀበት አደገኛ ነቀርሳ ነው:: በዓይን የማይታይ የጤና ጉዳት ያለው ነው:: ሲቀጥል የትራፊከ መብራት የያዘው ተሽከርካሪ ላይ ማንባረቅ ቢከለከል ለአሽከርካሪው ምን ጉዳት አለው? ያለአግባብ ክላክስ የሚያደርግ አሽከርካሪ ቢተወው ምን ይጎዳል? በረጅሙ ክላክስ ስላንባረቀ ከፊቱ ያለው ተሽከርካሪ ክንፍ አውጥቶ ይበራል ወይ? ይሄ መጥፎ ልማድ ከወዲሁ መቀረፍ አለበት!
ቢቻል ቢቻል ነገሮችን ያለምንም ቅጣት ብንተዋቸው መልካም ነበር:: ለምሳሌ፤ በዜብራ ላይ መሻገር ለረጅም ዘመን የኖረ፣ ማንም ሰው ሊያውቀውና ሊተገብረው የሚገባ ነበር:: በእግረኛ መንገድ ላይ ባለመሄድ መቀጣት አሳፋሪ ነው:: ቆሻሻ መንገድ ላይ ጥለሃል ተብሎ መቀጣት ሊያሳፍረን ይገባል:: የተከለከሉ ነገሮችን ሁሉ ቅጣት በመፍራት ሳይሆን በጨዋነትና በሰዋዊነት ልንተዋቸው ይገባ ነበር::
ዳሩ ግን እዚህ ላይ መድረስ ስላልቻልን ልክ የሚያስገባን ቅጣት ሆኗል:: ስለዚህ ‹‹ዋው!›› የተባለለትን የኮሪደር ልማት፣ ‹‹አውሮፓን እዚሁ አየናት!›› የተባለለትን ንጹህ አካባቢ፤ አንዳንድ ኋላቀር ድርጊቶች ‹‹ኤጭ!›› ሊያስብሉን አይገባም:: ስለዚህ የአሽከርካሪዎች ቅጥ ያጣ አካባቢ የሚያናውጥ ክላክስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም