የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ችግሮች እንዲሁም በሀገር ውስጥ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በእጅጉ መፈተኑ ይታወቃል። ፈተናዎቹ የቱንም ያህል ከባድና ውስብሰብ ቢሆኑም፣ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ሀገሪቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያሳዩ ካሉ ሀገሮች አንዷ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሀገሪቱ ላስመዘገባቸው እድገት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አስተዋጽኦ ተጠቃሽ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በቅርቡ ደግሞ ሁለተኛው ምእራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጸድቋል። ለእዚህ ትግበራ ደግሞ ሰሞኑን ወደ ሥራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምና እሱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ከተገነባባቸው አራት ምሰሶዎች መካከል ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትንና የንግድ ዘርፍ ከባቢና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚለው አንዱ ነው። ማሻሻያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት አስመልክቶ ያወጣው ማሻሻያ እንዳስታወቀው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ይሆናል።
በብሄራዊ ባንክ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ አሁን ያሉ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎች ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚደረግ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያበረታቱ፣ ላኪዎችና አስመጪዎች የሸቀጦችን ዋጋ ያለአግባብ ከፍ ወይም ዝቅ እንዲያደርጉ የሚገፋፉ፣ የካፒታል ሽሽትን የሚያጠናክሩ፣ በጥቅሉ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትንና በእጅጉ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያሳጡ ናቸው።
የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ በኢኮኖሚው ውስጥ ኢ-መደበኛነትንና ሕገ ወጥነትን ሲያበረታቱ የቆዩ በርካታ የንግድ አሠራሮችን ለማስቀረት ይረዳል። የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ ርምጃዎችን ለማጠናከር ይረዳል።
ማሻሻያው ለንግዱ ዘርፍ ምን መልካም እድል ይዞ መጥቷል? ምንስ ስጋቶች አሉት? ስጋቶቹን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማቅረብ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮግራሙና እሱን ተክትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል እንዲሁም ንግድን ለማሳለጥ እንደሚጠቀም ጠቅሰው፣ ትግበራው ግን ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ ዶክተር ሞላ አለማየሁ ስለማሻሻያው ለመናገር በቅድሚያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዚህ ቀደም ያለው ልምድ ምን ይመስላል? የሚለውን መመልከት ይገባል ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋናነት የንግዱን ዘርፍ ይደግፋል። በተለይም የውጭ ንግድን ያሳልጣል፤ የተሻለ ያደርጋል። በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲበረታታ ያደርጋል፤ በተለይም በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲሳቡ በማገዝ ትልቅ አቅም ይሆናል።
ማክሮ ኢኮኖሚው ወደ ተግባር ሲገባ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅርን መመልከት የግድ ነው ያሉት ዶክተር ሞላ፣ የውጭ ምንዛሪያቸውን ገበያ ተኮር ያደረጉ ሀገራት ውጤታማ የሆኑም፤ ያልሆኑም እንዳሉ ጠቁመዋል።
‹‹እርግጥ ነው ቢዝነስ ላይ ለተመሠረተና ለዳበረ ኢኮኖሚ የውጭ ምንዛሬን በገበያው እንዲመራ ማድረግ በጣም ጥሩ ነው›› ሲሉም አመልክተው፣ ማሻሻያው በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የውጭ ምንዛሪ በገበያ ሲመራ የወጪ ንግዱን በማሳለጥ ሀገርን ተወዳዳሪ በማድረግ የተሻለ አቅም ይፈጥራል። ይህም ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት። አንደኛው ላኪዎች ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥ ዋጋ ተምነው ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ትርፍ እንዲያገኙ ያስችላል። ሁለተኛው የውጭ ምንዛሪውን ራሱ በማግኘታቸው የተሳለጠ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር ይጠቅማቸዋል። ዶክተር ሞላ ማሻሻያውም ይህን ታሳቢ ያደረገና የወጪ ንግድን በጥሩ ሁኔታ በማሳለጥ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያጠባል በሚል የተወሰደ እርምጃ ነው ባይ ናቸው።
ይሁንና በኢትዮጵያ ያለው ኢኮኖሚ ከውጭ የሚገባው ንግድ ከሚወጣው ንግድ ጋር ሲነጻጸር አራት እጥፍ የሚበልጥ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ እንዲህ አይነት ኢኮኖሚ ላይ አሁን የተደረገው ማሻሻያ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ በመሆን የኑሮ ውድነቱን ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። የዚህ ምክንያትም ኢኮኖሚው በሀገር ውስጥ ንግድ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው ብለዋል።
መንግሥት ከዚሁ ጋር ተያዥ የሆኑ ጉዳዮችን በሚገባ ተከታትሎ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳያመዝን መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉም አስገንዝበው፣ ለእዚህም የማሻሻያ ፕሮግራሙን በየጊዜው እየገመገመ ማስተካከያ መውሰድ ይገባዋል ሲሉ ይመክራሉ።
ሕገወጥ ንግድን መከላከል እንደሚያስችል አመልክተው፣ የውጭ ምንዛሪው በገበያው መመራት ከቻለ ምንዛሪው ከመደበኛው ገበያ ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ይሆናል። ይህም ማንም ሰው በሕገወጥ ንግድ ለመሰማራት ተነሳሽነት እንዳይኖረው ያደርጋል። በመሆኑም ሕገወጥ ንግድ ሊጠፋ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ በማለትም አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ በዚህ ጊዜ መንግሥትም ኢኮኖሚውን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ወጪና ገቢ ምርቶችን እንዲሁም ካፒታልን መቆጣጠር ይችላል። ምክንያቱም ሕገወጥ ስምሪትን በስፋት መቀነስ የሚቻልበት አጋጣሚ አለ። መንግሥት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የሚያውቅ በመሆኑ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥም ሆነ ለማዘግየት የሚፈልገውን የፖሊሲ አቅጣጫ ማውጣት ያስችለዋል። ያወጣውን የፖሊሲ አቅጣጫም ተፈጻሚ ለማድረግ ጉልበት ይኖረዋል።
የውጭ ምንዛሪው በኑሮ ውድነት ላይ የራሱ የሆነ ድርሻ ቢኖረውም የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ በዋናነት በሀገሪቱ ያለው ግሽበት ዋናው መንስኤ ምንድን ነው? ብሎ መለየት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ ከቻለ የኑሮ ውድነቱ ላይባባስ እንደሚችልም ገልጸዋል።
መንግሥት የውጭ ምንዛሬን ማቅረብ ካልቻለና የውጭ ምንዛሬው አቅርቦት አሁንም በግለሰቦች ላይ የሚንጠለጠል ከሆነ ግሽበቱ በጣም ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስክትል እንደሚችል ጠቁመው፣ ለዚህም መንግሥት ድጎማዎችን በማድረግና በየጊዜው በመገምገም የድጎማውን መልክና ይዘት እየቀየረ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ማከናወን እንዳለበት ይናገራሉ።
አሁን እየተወሰደ ያለው ርምጃም ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ሞላ፤ ወደ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፍላጎትን ብቻ መሠረት ያደረገ ነው ሲሉም ይገልጻሉ። ከዚህ ይልቅ ዋናው መሠራት ያለበት አቅርቦት ላይ እንደሆነም ጠቁመው፣ አቅርቦቱን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት በማድረግ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማምጣትና የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግር መፍታት እንደሚቻል ያብራራሉ።
ዶክተር ሞላ እንደሚያስረዱት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ኢኮኖሚዊ ስብራቶችን ለመጠገን የአቅርቦት መዋቅሩን በደንብ ማስፋትና እዛ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን የሀገሪቱ ዜጎች በአቅርቦት በኩል የሚፈልጉትን ማርካት አልተቻለም። ለአብነትም የጤፍ ዋጋ እየናረ የሄደው ጤፍ ከውጭ የሚገባ ምርት ሆኖ ሳይሆን በሀገር ውስጥ ፍላጉቱን ማርካት ስላልተቻለ ነው። ተመጣጣኝ የሆነና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ዕድገት ለማምጣት በአቅርቦት መዋቅሩ ላይ መሥራት የግድ ይላል።
የውጭ ምንዛሬው በገበያ እንዲመራ መደረጉ በንግዱ ሥራ ላይ የሚያመጣው በጎ ተጽዕኖ እንዳለ ሁሉ አሉታዊ ጎንም አለው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ለእዚህ ዋና ምክንያት ኢኮኖሚው ያልዳበረና ገቢ ምርት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው ይላሉ።
‹‹መንግሥት የንግዱ ዘርፍ ነጻ ገበያን እንዲከተል በሚል ሙሉ በሙሉ ሊብራላይዝ ማድረጉን እንደ ባለሙያ አላምንበትም›› የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ከዛ ይልቅ በየደረጃው እየታየ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን ያመለክታሉ። የንግዱ ዘርፍ ቀስ በቀስ በየደረጃው ነጻ ገበያን እንዲከተል ቢደረግ ኢኮኖሚው እየተላመደ ይሄዳል ሲሉም አመልክተዋል።
አሁን ግን ከአዲስነቱም አንጻር የአሠራርና ሌሎች ችግሮች ሊገጥሙት ይችላሉ ይላሉ። ለዚህም መንግሥት ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለበት ሲሉም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ከመንግሥት ባለፈም በኢኮኖሚው ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ባለሙያዎችና ሌሎችም የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
ማህበረሰቡም ምንም ሳይረበሽ ሁኔታውን እያገናዘበ መመልከት እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ሞላ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ካለመረዳት ‹‹እንዲህ ሊሆን ይችላል›› በሚል ስጋት ውስጥ እንዳይጠመድም ይመክራሉ። ይሁንና ሕዝቡ ጉዳዩን በቅጡ ካለመረዳት መሯሯጥ ማሻሻያው ይልቅ ውዥንበሩ የሚፈጥረው ችግር ጎጂ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ። በመሆኑም ከመንግሥት በተጨማሪ ሕዝቡን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግና መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያመለክታሉ።
ዶክተር ሞላ እንዳሉት፤ የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ እንደመሆኑ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ የከፋም ሆነ የተሻለ የማድረግ አቅም አለው። ሕዝብ ሲባል መንግሥት፣ ባለሀብቱና ህብረተሰቡ ናቸው። ህብረተሰቡ እንደ አንድ አካል ሲሆን፤ ሻጭም ገዢም ነው። መንግሥትም በተመሳሳይ ሻጭም ገዢም ነው። ባለሀብቱ ደግሞ ሻጭ ነው። ስለዚህ የእነዚህ አካላት ተናብቦና ተሰናስሎ መሄድ ኢኮኖሚውን የተሻለ ያደርገዋል። በእነዚህ ሶስት አካላት መካከል ጠንካራ መተማመን ሊኖር ይገባል። ሁሉም አካላት እንደየአቅማቸውና ዕውቀታቸው ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ ቢያደርጉ የተሻለ ኢኮኖሚ መፍጠር ይቻላል።
ዶክተር ኤርሚያስ አበራ ኦዲተር፣ የፋይናንስ አማካሪና መምህር ናቸው። እርሳቸውም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ ሀገር ይዞ የሚመጣው ጠቀሜታ ትልቅ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ማንኛውም ሪፎርም ጠቃሚ ነገሮች እንዳለው ሁሉ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲሉ ጠቅሰው፣ የንግዱ ማህበረሰብ ከለመደው ውጭ መሆኑንና፣ የማይመች ነገር የሚኖረው ቢመስልም ለሀገራዊ ኢኮኖሚ መሻሻል ግን ወሳኝና የግድ ነው ብለዋል።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ርምጃ የውጭ ምንዛሪ በገበያው እንዲመራ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ተገቢነት ያለውና የዘገየ መሆኑን ዶክተር ኤርሚያስ ይናገራሉ። በመደበኛው ገበያና በጥቁር ገበያው ያለው ርቀት ሰፊ መሆኑን አመልክተው፤ ይህን ለማቀራረብ ግን ጊዜ እንደሚወስድ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረቱ የውጭ ምንዛሪ ላይ ነው፤ ለንግዱ ማህበረሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ተግዳሮት የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ቢመስልም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የአስተዳደር ችግሮችን በረጅም ጊዜ የሚፈታ ይሆናል።
‹‹በሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት ውስጥ አብዛኛው ምርት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባና የምንጠቀማቸው ምርቶች ናቸው። ይህም በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል›› ሲሉ ያብራራሉ። በሀገሪቱ ከወጪ ምርቶች ይልቅ ገቢ ምርቶች ከመብዛታቸው ባለፈ አብዛኞቹ ሰዎች መሠረታዊና የግድ ከሆኑ ቁሶች በተጨማሪ ቅንጡ ለሆኑ ቁሶች ጭምር የውጭ ምንዛሪን ይጠቀማሉ ሲሉም ጠቅሰው፣ መንግሥት የብዙሃኑን ፍላጎት ከግምት በማስገባት የውጭ ምንዛሪውን መጠቀም የሚቻልበት ዕድል አለ ብለዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሕገወጥ ንግድ መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል ብለዋል።
መንግሥት በዋናነት መዋቅር ውስጥ ያለውን ሕገወጥ ንግድ መከላከል እንዳለበት ያስገነዘቡት ዶክተር ኤርሚያስ፤ በተለይም በባንክ ውስጥ ያሉ አካላት ኤክስፖርት ካደረጉ አካላት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ ማስተዳደር ላይ ሰፊ ክፍተት እንደሚታይ ጠቁመዋል። በተለይም መንግሥት ትኩረቱን ባንክ ላይ ማድረግ እንዳለበትና የባንክ አሠራር መፈተሽ እንዳለበት ያስረዳሉ። የባንክ አሠራር ፍትሃዊ አለመሆኑን አመልክተው፣ መንግሥት የመቆጣጠር አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ ሀገር ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑት ዶክተር ኤርሚያስ፤ ማሻሻያው ግቡን መምታት የሚያችለው መንግሥት በቁርጠኝነት በመዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ሕገወጦችን መቆጣጠር ሲችል እንደሆነም ያመለክታሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ማሻሻያው ፖሊሲ እንደመሆኑ በየጊዜው መሻሻል የሚችል ነው። በመሆኑም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፋይዳው በመንግሥት ቁርጠኛ አካሄድ ላይ የሚወሰን ይሆናል። ሀገር ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንድትችል ምንም የፖለቲካ ዕይታ ሳያስፈልግ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል።
የውጭ ምንዛሪው በገበያ ይመራል በተባለበት ሁኔታ ላይም ሲያብራሩ፣ በውጭ ምንዛሬ ገበያው መካከል ያለውን ርቀት ማሰብ ያስፈልጋል ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ ለአንድ ዶላር በጥቁር ገበያ 120 ብር እየተመነዘረ በባንክ ደግሞ 57 ብር ሲመነዘር ቆይቷል። በመሆኑም በዚህ መካከል ያለውን ርቀት ለማስተካከል ጊዜ የሚወስድና ቆም ብሎ ማሰብንም የሚጠይቅ ነው።
‹‹ማሻሻያው በሂደት የሚያመጣው ሀገራዊ ፋይዳ ጉልህ ነው›› ያሉት ዶክተር ኤርሚያስ፤ አሁን ላይ የሚፈጥረው ስጋት እንደመኖሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው የፖሊሲ ማሻሻያውን መተግበር ላይ ጠንካራ አቋም መውሰድ መሆኑን ያመለክታሉ። ለእዚህም መንግሥት የቁጥጥር አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ይጠቁማሉ። ለእዚህ አይነቱ ተግባር ተቆጣጣሪ አካላትን ሳይቀር ከውጭ የሚቀጥሩ የአፍሪካ ሀገራት እንዳሉም ጠቅሰው፣ መንግሥትም ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።
በማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ሰነዱ ላይ እንደተመለከተው፤ መንግሥት ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ይሠራል። ከእነዚህም መካከል የማህበራዊ ሴፍትኔት ፕሮግራሞች ድጎማ ይደረግላቸዋል። ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ድጎማና ማሻሻያ ለተወሰነ ጊዜ ይደረግላቸዋል የሚሉት ይጠቀሳሉ።
የማክሮ ኢኪኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚ ውስጥ ትግበራ ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነትና ሕገወጥነትን ለመከላከል መንግሥት የነቃ ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ ይወስዳል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም