የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የኢንደስትሪው ትስስር

የዓለም የሥልጣኔ ዕድገት መለኪያው ኢንዱስትሪ ነው:: ለዚህም ነው ዘመናዊ የዓለም ታሪክ ሲወሳ መነሻውን ከኢንዱስትሪ አብዮት የሚያደርገው:: የኢንዱስትሪ አብዮት የአውሮፓ ሀገራትን ያነቃቃ፣ የዘመናዊ ሥልጣኔ መነሻ የሆነ፣ በአጠቃላይ አሁን ላለው የሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤ መሠረት የጣለ ነው:: ይህ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ እያደገ መጥቶ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለመካተት በቅቷል:: የበለጸጉት ሀገራት ደግሞ ይህንን የኢንዱስትሪ አብዮት በአግባቡ በመጠቀም ወደ ፈጣን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መገኛነት አሳደጉት:: ከዘመናነት ጉዞ በኋላም በተለያየ ባሕላዊ መንገድ ከትውልድ ወደትውልድ ሲሸጋገር የኖረውን እውቀት ‹‹ተግባር ተኮር›› ትምህርት ተብሎ ለሥራ ፈጠራ አጋዥ እንዲሆን አገልግሎት ላይ መዋል ጀመረ::

ለ19ኛው ክፍለ ዘመን የብልጽግና በረከቶች ፈር ቀዳጁም ኢንዱስትሪ መስፋፋት ሲሆን፤ የሀገራትን ኢኮኖሚ ማደግ ተከትሎም ለስልጣኔ ከፍተኛ ሚናን ለመጫወት በቅቷል:: እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣… የመሳሰሉ ሀገራት ላስመዘገቡት ፈጣን እድገት ተጠቃሽም ነው:: የኢንዱስትሪ ዘርፍ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ሚና ከመጫወቱም ባለፈ፤ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ቀጣይነት ያለው የገቢ ምንጭ በመሆንም እያገለገለ ይገኛል:: የዜጎችን አኗኗር በማሻሻልና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድም ያደጉ ሀገራት ከዘርፉ ብዙ ተጠቅመዋል:: በተጨማሪም ሰዎች በጉልበት ያከናውኗቸው የነበሩ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመተካት ድካምን ቀንሶ ቅልጥፍናን በመጨመር ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅቷል። በሥራ እድል ፈጠራውም ረገድ ዛሬም ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል::

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን የምናገኘው ታሪክ ካደጉትም ሆነ በማገድ ላይ ካሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ባጭሩ ከዘርፉ ከምንፈልገው ምርትና ምርታማነት እንዲሁም የሥራ እድል ፈጠራ መጠቀም የቻልነው እጅግ በጣም ትንሽ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱ ደግሞ የኢንዱስትሪው አለመስፋፋትና አለመጠናከር ሲሆን ይህንን ለመቅረፍ ደግሞ ከገንዘብ አቅም ባለፈ የተማረ የሰው ኃይል ማግኘት ትልቁ ጥያቄ ነው።

እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በሀገሪቱ ይሰጡ የነበሩት ትምህርቶች ከተግባር ይልቅ የወረቀት ላይ ሆነው መቆየታቸው በቂ የሰው ኃይል ላለመገኘቱ አንዱ ምክንያት ነው። በዚህም የተነሳ ከቴክኒክና ሞያ የትምህርት ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎችን ጨምሮ ‹‹የራሳቸው ሥራ ጀመሩ›› ከተባለ የሚሰሩት አያት ቅድመ አያቶቻቸው በልማዳዊ መንገድ የፈጠሩትን ሥራ ነው:: ይህ የሚያሳየን ኢንዱስትሪውና በመስኩ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች መካከል የተሳለጠ ግንኙነት አለመኖሩን ነው:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መስፋፋትና የዘርፉንም እድገት ተከትሎ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትኩረት አቅጣጫ ይህንኑ ማዕከል ያደረገ እየሆነ መጥቷል::

ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ሳይቀራረቡ በንድፈ ሃሳብ ትምህርት ብቻ ማተኮራቸው ሰልጣኞች ከተመረቁ በኋላ ወደ ኢንዱስትሪው ሲቀላቀሉ እንግድነት እንዲሰማቸው ሲያደርግ የነበረ ነው:: በርግጥ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው በሥራ ልምምድ (አፓረንትሺፕ) ኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ የመግባት እድል ይኖራቸዋል:: ይሁንና በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ሆነው የሥራውን ዓለም መቀላቀል ይሳናቸው ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ ተማሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ በወረቀት ትምህርት ላይ አሳልፈው ለምረቃ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው በውስን ሰዓት ከተግባራዊ ትምህርት ጋር የሚገናኙ በመሆናቸው ነው። በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር የሚፈጥሩት ትስስር ይህንን ክፍተት ሊሸፍን የሚችል ሆኖ አልተገኘም:: በአሁኑ ወቅት ግን እንደ መፍትሔ ሆኖ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራበት ያለው የትምህርት ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር ትልቅ ተስፋ የተጣለበትና የብርሃን ጭላንጭል ያሳየም ለመሆን በቅቷል።

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ኢንዱስትሪ ትስስር ታሪክ በአንጻራዊነት ገና ጅምር ላይ ቢሆንም እያደገ ከመጣው ሰፊ የኢኮኖሚ ልማት እና የቴክኖሎጂ እድገት ጋር እየተጣጣመ የመጣ መሆኑን የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር መረጃ ያመላክታል። የከፍተኛ ትምህርት እና ኢንዱስትሪ ትስስር ከታሪክ አኳያ በዋነኛነት ያተኮረው በንድፈ ሃሳባዊ እውቀት ላይ ውስን በሆነ የኢንዱስትሪ ትብብር ላይ ነው። በ1950 ዎቹ ዓ.ም የተቋቋመው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩት ኮሌጆችም ቢሆኑ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ አነስተኛ ነበር።

የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተቀምጠው በትምህርት ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ልዩነት የማጣጣም ሥራ የተጀመረው ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም በኋላ ነው። ከዚህ ጊዜ አንስቶም የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም በትምህርትና ስልጠና ተቋማትና በኢንዱስትሪው መካከል ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም:: ዛሬም ድረስ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለሀገራዊ ልማት ለማዋል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ የዩኒቨርሲቲ እና የኢንዱስትሪ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ የፖሊሲ ውጥኖችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። እነዚህን የትስስር ሥራዎች በይዘታቸው እና ከባህሪያቸው አኳያ ውጤታማ እንዲሆኑ አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል::

በመሆኑም የለውጡ መንግሥት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚኖራቸውን ትስስር ለማጠናከር እና ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በመገንዘቡ የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ቁ.1298/2015 የሕግ ማዕቀፍ አውጥቷል።

ይህንንም ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እና የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች አጋር አካላትን ለጋራ ጥቅም በትስስር ተግባራዊ ምርምር መሥራት ጀምረዋል። የትስስር አዋጁ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የሕግ ማዕፎችን የትስስር ፖሊሲዎችን እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዱ የተማሪዎች የተግባር ልምምድ፤ የኤክስተርንሽፕ /የሠራተኞች የተግባር ተሞክሮ፤ የትብብር ስልጠና ፤ የማማከር አገልግሎት። እንዲሁም የጋራ ተግባራዊ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መመሪያዎችን በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትና በኢንዱስትሪ መካከል ትስስርን የበለጠ ለማጥራት እና ውጤታማነት ለማሻሻል በመሰራት ላይ ይገኛሉ።

የትስስር መመሪያዎቹ የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ተደራሽ እና ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የተለያዩ የማበረታቻ ስልቶችን፣ የአእምሯዊ ንብረት አስተዳደርን እና ተግባራዊ የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ በጋራ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እና የፈጠራ ተግባራትን ጨምሮ ዝርዝር ሂደቶችን እና ደረጃዎችን ያስቀምጣል። በመሆኑም የትስስር አዋጁ የማህበረሰቡን ተግዳሮቶች የሚፈቱ የጋራ ተግባራዊ ምርምር፤ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የፈጠራ ሥራዎች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ በመሥራት ላይ ይገኛል ለማለት ያስደፍራል::

የትስስር አዋጁ ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ ምርምር አጀንዳዎቻቸውን ከሀገራዊ ልማት ግቦች እና ከኢንዱስትሪ ፍላጎቶች ጋር እንዲያቀናጁ እና ወጪ ቆጣቢ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር አግዟቸዋል። አዋጁ ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለምርምር ተቋማት የተሻሻለ ሥርዓተ ትምህርት፤ አግባብነት ላይ የተመሠረተና ከኢንዱስትሪዎች የገበያ ፍላጎትና ደረጃዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም አስችሎታል።

በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው ትስስር የምርምር ውጤቶችን ከገበያ ፍላጎቶች ጋር በማጣጣም የተግባር ስልጠናዎችን፣ የጋራ የተግባር ልምምዶችን በመስጠት የኢንዱስትሪውን ምርታማነት እና ተወዳዳሪነት ማሳደግም አስችሏል። ይህም መንግሥት በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት እና በኢንዱስትሪዎች ልማትና ፈጠራ ላይ በትስስር ንቁ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ ናቸው።

የትስስር አዋጁ በቀጣይ የትስስር ሥራዎችን ከማሳለጥ እና ውጤታማ ከማድረግ አንጻር የጋራ የምርምር መሠረተ ልማቶችን ለማሳደግ፣ የተሻሻሉ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ለጋራ የቴክኖሎጂ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የትስስር ሥራዎችን ለማጠናከር ብሎም ለተማሪዎች፣ ለኢንዱስትሪዎች እና ለዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ፈጠራና በኢኮኖሚ ዕድገት እና በህብረተሰብ ልማት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያግዛቸው ይሆናል::

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢንዱስትሪው ጋር ሰፊ ቁርኝት ካላቸው የትምህርት ዘርፎች መካከል አንዱ ቴክኒክና ሙያ መሆኑ ይታወቃል:: በተለያየ መስክ የሙያ ባለቤት እና የፈጠራ ምንጭ የሆነው ይህ ዘርፍ የሚያፈራው የሰው ኃይል ከኢንዱስትሪው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው:: የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የኢንዱስትሪ ትስስር ታሪክ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1942 ዓ.ም ተግባረ ዕድ የቴክኒክ ትምህርት ቤት ከመክፈት ጋር ጅማሬውን ያደርጋል። ከትምህርት ቤቱ መቋቋም በኋላም በአንጻራዊነት የቴክኒክና ሙያ አስፈላጊነት ላይ መጠነኛ የአመለካከት ለውጥ ሊመጣም ችሏል:: ከአስርት ዓመታት በኋላም በ1990ዎቹ አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተዘጋጅቶ የስልጠና ዘርፉ ሥርዓት ተዘርግቶለት መሰጠት ተጀምሯል::

እንደ ሀገር የተጀመሩ ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችን የማስፋት፣ ምቹና ዘላቂ የሥራ ዕድል እንዲሁም ሰላማዊ ኢንዱስትሪ የመፍጠር ዕቅዱን ለማሳካት የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል መኖር የግድ ነው። የኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት የሚወሰነው ደግሞ ብቃት ባለው የሰው ኃይል እንደመሆኑ ዘርፉ ያሉበትን ፈተናዎች ለማለፍ፣ የአመለካከት ችግሮችን መቅረፍ ከቻለ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ። ብሎም ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በራሳችን የማምረት አቅም ለመተካትና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና ለመጫወት ይረዳል:: አሁን ባለው ሁኔታም በየጊዜው እየጨመረ ለመጣው የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የሰው ኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የስልጠና ዘርፉን ማጠናከር አስፈላጊ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም:: ለዚህ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከላት በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማቅረብ የሚኖራቸው ሚና ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል።

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ተቋማት እንዲሁም ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በመሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራም ይገኛል:: የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በቅርቡ ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ወቅትም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ያነሱት ይህንኑ ነበር:: ሚንስትሯ በንግግራቸው «እንደ ሀገር በዘርፉ የጀመርናቸውን የሪፎርም ሥራዎችን ለማቀጣጠል የሚያስችል እንደሆነ እምነቴ የፀና ነው›› ብለዋል:: በመሆኑም በስልጠና ቆይታችሁ ባገኛችሁት ክህሎትና በቀሰማችሁት እውቀት ለመጣችሁበት ማኅበረሰብ፣ አካባቢ፣ ተቋምም ሆነ ኢንዱስትሪ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት ከወዲሁ እንድትዘጋጁ ሳሳስባችሁ ከአደራም ጭምር ነው::» የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህን ያነሳነው የቴክኒክና ሙያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተገቢውን ክብርና ትኩረት እያገኘ መሆኑን ለመጠቆም ነው:: ከዚህ በፊት በነበረው አመለካከት ቴክኒክና ሙያ ብዙም ትኩረት የሚሰጠው አልነበረም:: የቴክኒክና ሙያ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ከሚሰጥባቸው የትምህርት ተቋማት በተሻለ ለኢንዱስትሪ መሠረት የሆነ ተቋም ነው:: በተገቢው መንገድ ከተሠራበት ሀገር በቀል የሆኑ ሙያዎችን ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ማስደግ የሚቻልበት ነው:: ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ተሰጥኦዋቸውን የሚጠቀሙበትን ዕድል የሚፈጥርበትም ቦታ ነው:: በተጨማሪ ከመደበኛ ትምህርት ባለፈ ትስስሩ የባሕል አምራቾችንም ሊያጠቃልል እንደሚገባ ይነሳል። ሀገር በቀል የሆኑና በባሕላዊ መንገድ የሚመረቱ ብዙ ዓይነት ዕቃዎች አሉ:: እነዚህን ዕቃዎች የሚያመርቱ ሰዎችን በማምጣት የተግባር ተሞክሮውን ለተማሪዎች እንዲያሳዩ ማድረግም ይጠበቃል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You