አመራር ራዕይን፣ ተልዕኮንና ዕሴቶችን መሠረት በማድረግ መሪው ከሚመራቸው ሰዎች ጋር መግባባትን ከመፍጠር ይጀምራል። አንድ መሪ አንድን ተቋም ሲመራ የሚመራው ተቋም ግልጽ የሆነ ራዕይ፣ ተልዕኮና ዕሴቶች ሊኖሩት የሚገባ ሲሆን፣ ተከታዮቹም እነዚህን ራዕይ ተልዕኮና ዕሴቶችን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው።
ዕውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በበርካታ የመንግሥት መሥሪያቤቶች ራዕይ ተልዕኮና ዕሴቶች በሰሌዳ ላይ፣ በግድግዳ ላይ ወይም በቢሮ ውስጥ ተጽፈው የሚስተዋሉ ቢሆንም ቁም ነገሩ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ምን ያህል አውቀዋቸው የራሳቸው አድርገዋቸዋል የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። በየቦታው መስቀልና መለጠፍ ሣይሆን በመጀመሪያ መሪው የተቀበላቸውና የሚያውቃቸው ሊሆኑ ይገባል።
በመቀጠልም በተዋረድ ተከታዮቹ ቢቻል ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ መቀበላቸውንና ማወቃቸውን ማረጋገጥ ይጠበቃል። የየመሥሪያቤቱ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የመሥሪያቤቱን ራዕይ ተልዕኮና ዕሴቶች ማገናዘብና የዕለት ተዕለት ሥራቸው አካል አድርገው መንቀሳቀሳቸው ሊከሰት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ይቀንሳል፣ ብሎም ያስወግዳል፡፡
በመሠረቱ የአመራር ሥራ በየዕለቱና በየሰዓቱ በሚነሱት የእሣት ማጥፋት ሥራ ላይ ማሣለፍ አይደለም። የአመራር ዋነኛ ሥራ ከመሥሪያቤቱ ራዕይ ተልዕኮና ዕሴቶች ጋር የተያያዙ ቁልፍ ሥራዎች ላይ በማተኮርና በመከታተል የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጡ በማድረግ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት ነው። ሁሉንም ሥራዎች ለመሥራት የሚሞክር መሪ ውጤት አያመጣም ስለሆነም የውጤትና የስኬት ሚስጥሩ ያለው በተልዕኮና በዓላማ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና ማሰራት መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፡፡
ከአመራር ሁሉ አስቸጋሪውና ምናልባትም በሁሉም የበለጠ ትኩረት የሚያሻው የሰው ኃይል አመራር ነው። ለሠራተኞቹ /ለሰው/ ክብርና ፍቅር የማይሰጥ መሪ በሕይወቱም ሆነ በሥራው ላይ ችግር ይገጥመዋል። እንደዚህ ዓይነት መሪ ለድርጅትም ሆነ ለሀገር ውድቀት ምክንያት ነው፣ የጥሩ መሪ ዋነኛው መገለጫ የሚመራቸውን ሰዎች/ሠራተኞች/ተከታዮች/ ክብር በመስጠት ሕይወታቸውን በዕውቀትና በክህሎት ማብቃትና ለተከታዮቹ ግልጽ ሀቀኛና አርዓያ ሆኖ የመሥሪያቤቱን ዓላማ ማሣካት ነው፡፡
ጥሩ መሪዎች በመልካም ተግባራቸው በአርአያነት የሚቆሙ ባለ ራዕይና መልካም ተሞክሮ ያላቸው ንቁ ተከታዮችን የሚያፈሩና የሚያሰማሩ፣ ያላቸውን ዕውቀት ለተከታዮቻቸው የሚያስተላልፉ ሲሆን በተገላቢጦሽም በጣም ጥሩ ተማሪዎችና ሠልጣኞችም ናቸው። በመሪዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚዘነጋው በተከታዮች ዘንድ የመልካም ሥራ አፈጻጸምና ተሞክሮ ጅማሮው ቢኖርም የተገኘውን ጅማሮ ዕውቅና ሰጥቶ ምስጋና አለመስጠትና አለመሸለም ነው። ሆኖም ግን ለውጤት ዕውቅና መስጠትና ማበረታታት ሌሎች ተከታዮችም አርአያ የሆኑትን ሠራተኞች ፋና እንዲከተሉ የሚያበረታታ ከመሆኑም ባሻገር ለሠራተኞቹ/ተከታዮቹ ሞራል ቀስቃሽ በመሆኑ አስፈላጊ ነው፡፡
ጥሩ መሪ ከለውጥ ጋር አይታገልም፣ ከለውጥ አይሸሽም፣ ለውጥ ሲመጣ እጁን ዘርግቶ ይቀበላል፣ ለውጡን ለተሻለ ነገር/ሁኔታ ይጠቀምበታል። በመጨረሻም ለለውጥ እጁን ይሰጣል፣ ለለውጥ እጅን መስጠት ትክክለኛው የአመራር ዘዴ ነው፡፡ ያልተጠበቁ ክስተቶችን ማስተናገድ መቻል ለውጥን ማስተዳደር ነው። ስለሆነም መሪ ያልተጠበቁ ችግሮችን በድፍረት፣ በንቃትና በፍጥነት አጥንቶና ፈትሾ ወደ መልካም ሁኔታ መቀየር ይኖርበታል፡፡
በየቀኑ የተለመደውን ተመሣሣይ ሥራ ማከናወን አዲስ ውጤት አያመጣም፤ አዲስ ለውጥ/ውጤት ለማምጣት የሚሠራውን ሥራ መለወጥ ያስፈልጋል። ግትርነት ለለውጥ አደጋ ነው፣ ለውጥ ለማምጣትም ሆነ ለመቀበል ያስቸግራል። በአንጻሩ ተደማጭነትንና ግልፅነት ለለውጥ ያዘጋጃል፡፡ ስለዚህ ራስን ከለውጥ ጋር በማቆራኘት ለውጡን ማስተናገድ ጠቃሚ ነው። ከለውጥ ጋር ራስን ማስማማት የአንድ መሪ ትልቅ ችሎታ ነው። ለውጥን ከመቀበል ጋር ተያይዞ ውድቀት ወደ ስኬት የመሄጃ መለማመጃ መንገድ ነው፡፡
ለምሣሌ ከብስክሌት ሣይወድቅ ብስክሌት መንዳት የቻለ የለም፣ ከተወሰኑ ውድቀቶች በኋላ ግን ብስክሌትን ያለምንም ችግር መንዳት ይችላል። በተግባር ላይ ያልዋለ ዕውቀት ዋጋ የለውም፣ ስኬት የሚመጣው በምታውቀው ሣይሆን ዕውቀትን ተግባራዊ አድርገህ በምትሠራው ሥራ ነው። ለውጥ የሚፈራው ልጎዳበት እችላለሁ ከሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል፤ የፍርሃት መድሃኒቱ ዕውቀት ነው። ለመማር ስንፍናን ማስወገድ ያስፈልጋል ሰዎች ለማወቅ፣ ለመማር እና የመረጃ ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ ከሆኑ ለውጡን ለመቀበልና ለማስተዳደር ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡
ስለለውጥ ሲነሣ ሁልጊዜ የሚሰጠው የእንቁራሪቷ ምሣሌ ነው። ‹‹አንዲት እንቁራሪት ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ አድርገዋት ቀስ በቀስ ውሃውን ቢያፈሉት ከውሃው ሣትወጣ እዚያው ትሞታለች። ነገር ግን ውሃው ከፈላ በኋላ እንቁራሪቷን የፈላው ውሃ ውስጥ ቢጨምሯት አዲስ ለውጥ ስለሚሆንባት ወዲያው ዘላ ትወጣለች” ለውጥም እንዲሁ ነው። ከተውትና ከተደበቁት እያሣሣቀ ይገድላል፣ ከነቁበት ግን ሕይወት ያድናል፡፡
ለውጥ ስንል አንድ ተቋም አሁን ካለው ተቋማዊ አደረጃጀት አሠራርና አመራር ወደ አዲስ አደረጃጀት አሠራርና አመራር ለማሸጋገር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። የለውጥ መሪ ደግሞ ይህ እንቅስቃሴ ተግባራዊ እንዲሆን የሚታገል ነው። ለወጥ የለውጥ ካፒቴን ይሻል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
የለውጥ መሪ ለውጥን የህልውና ጉዳይ አድርጎ የሚወስድ ነው፣ የራሱን ማንነት በሚገባ የሚያውቅና ሌሎችን በቀላሉ የሚያነብ ጽኑ አቋም ያለው ትዕግስትን የተላበሰ፣ በራሱ የሚተማመንና ለሥራዎች ደረጃ / ስታንዳርድ/ የሚያመጣ ነው፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቀበል በሥራ ላይ የሚያውል እና ስለ ሥራው ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው፣ ለአዳዲስ ግኝቶች ቦታ የሚሰጥና የውጤትና ስኬት መሠረቱ የሰው ኃይል ነው ብሎ የሚያምን ነው፣ ለባልደረቦቹና ለሥራው ልዩ ፍቅር ያለውና ችግሮችን ለመፍታት የሚጥር ነው፣ ራሱን እንደ አገልጋይ የሚያይና ስህተትን እንደትምህርት ሰጪነቱ የሚወስድ ወዘተ. ነው።
ስለዚህም በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ አመራር እነዚህን መሠረታዊ መርሆች ተላብሶ በከፍተኛ ትጋት እና ቁርጠኝነት፣ ከሌብነት በፀዳ መንገድ፣ በኃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ በየዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት ይጠበቅበታል። በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ሕዝብን ለምሬት የሚዳርጉ እንቅፋቶችን ማስወገድ ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው። በዚህም አመራሩ ሕዝቡ ድረስ ወርዶ ችግር መፍታት መልመድ መቻል አለበት። ሁሉም አመራር የተሰጠው ጊዜ ሕዝብን የማገልገያ እድል መሆኑን ተረድቶ ለጠንካራ እና ፍሬያማ ለውጥ መትጋት ይኖርበታል።
ከአድሎአዊ አሠራር የፀዳች፣ ሁሉም የልፋቱን የሚቃርምባት የለውጥ ምሳሌ የሆነች ሀገር እንድትፈጠር በቀጣይ ከአመራሩ የሚጠበቀውም ይህ ነው፡፡
ሰለሞን ተስፋዬ ግድየለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 /2016 ዓ.ም