አዲስ አበባ:- በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና በአመራሮች ግድያ ዙሪያ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ አካላትን ይዞ ለህግ የማቅረቡ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አስታወቀ።
አዴፓ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የኢትዮጵያ ህዝቦችንና አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥልና በአማራ ክልል ብቻ የተቃጣ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ ጥፋት ነው። ስለዚህም ይህ ሁኔታ እንዳይቀጥል ለማድረግ የፀጥታ መዋቅሩን መልሶ በማጠናከርና መላ ህዝቡን በማስተባበር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ በልዩ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል፤ ህጋዊ እርምጃም እንደሚወሰድ አስታውቋል።
ወቅቱ ለድርጅቱ፤ ለመንግሥትና ለህዝቡ ፈታኝ እና ጠንካራ ውስጣዊ አንድነትን የሚጠይቅ መሆኑን የገለጸው መግለጫው መላ የድርጅቱ አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎች፤ የክልሉና የአገሪቱ ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መቆምና የገጠመውን ፈተና በብቃት ማለፍ ይጠበቅበታል። አገሪቱንም ለመታደግ መስራት ያስፈልጋል ብሏል።
መስዋዕት ከሆኑት ግንባር ቀደም መሪዎችና ከተፈፀመው ድርጊት ጋር ተያይዞም የሚናፈሱ አሉባልታዎችን ወደ ጎን በመተው ውስጣዊ ጥንካሬን በማጎልበት አንድነቱን ጠብቆ በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላትን ማጋለጥ ላይ ማተኮር እንደሚገባም ገልጿል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ አካላትም በእንዲህ አይነት አገርና ህዝብ ችግር ላይ በወደቁበት ሁኔታ መረጋጋትን፤ ሠላምና አንድነትን ማጠናከር ላይ መስራት እንዳለባቸው ጠቁሞ፤ ይህንን በማያደርጉ ላይ ግን ለህዝብና ለአገር ደህንነት ሲባል ማንኛውም አይነት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክቷል።
ወንጀሉን ለመሸፋፈን እና ለማሳነስ ሆን ተብሎ አሉባልታ በመንዛት ህዝቡን በሚያደናግሩትና አቅጣጫ ለማሳት በሚሰሩት ላይ ከዚህ ዕኩይ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ በህግ እንደሚጠይቅ አሳስቧል። በቀጣይ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ዋጋ እንዳያስከፍሉ ወንጀለኞችን ሙሉ በሙሉ በህግ ቁጥጥር ስር የማዋል እና ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባራትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርቷል።
የፀጥታ መዋቅሩና መላ ህዝቡ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ክልሉን ለማረጋጋት ይሰራል ያለው መግለጫው፤ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ ለማክሸፍ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ ሁሉ የፈፀሙት ገድል በደማቅ ታሪክ ተፅፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ይሆናል ብሏል። ድርጊት ከሞራል፤ ከህግና ፖለቲካዊ አቋም ተቃራኒ የሆነ ከባድ ክህደት መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ፤ ድርጊቱ የአማራ ህዝብን ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እና መንግሥት እንዳይኖረው እና በአገራችን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀለበስ እንዲሁም አገር እንዲፈርስ የማድረግ ጥፋት በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው እንደሚገባ አስገንዝቧል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር