በኮሪደር ልማት በተሠሩ መንገዶች የትራፊክ ሕግን በሚተላለፉት ላይ ርምጃ ይወሰዳል

አዲስ አበባ፡– በኮሪደር ልማት በተሠሩ መንገዶች ላይ የትራፊክ ሕግ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች፣ ብስክሌተኞችና እግረኞች ላይ ተገቢውን ርምጃ የሚወስድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ለኢፕድ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ እና ደህንነቱን ለመጠበቅ በኮሪደር ልማቱ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሆኖም ይህን በሚያውክ መልኩ የሚንቀሳቀሱ እና በኮሪደር ልማቱ በተሠሩ መንገዶች ላይ የትራፊክ ሕግ በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች፣ ብስክሌተኞችና እግረኞች ላይ ተገቢው ርምጃ ይወሰዳል፡፡

በመንገዶቹ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ያለው መግለጫው፤ አሽከርካሪዎችም ለመጫንና ለማውረድ ከተፈቀዱ ቦታዎች ውጪ ማውረድና መጫን እንደሌለባቸው አሳስቧል፡፡

የኮሪደር ልማት በአንዳንድ ቦታዎች እግረኞችና ብስክሌተኞች በጋራ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች በመኖራቸው ብስክሌተኞች ለእግረኞች ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም ጠቅሷል፡፡

እግረኞችም በመንገዱ ላይ ብስክሌተኞች እንደሚጠቀሙበት በመገንዘብ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የትራፊክ ፍሰትና ደህንነት ሥራን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ከማድረጉም በላይ የሞተር አልባ እንቅስቃሴዎችን በማበረታታት የካርቦን ልቀትን እንዲቀንስ እያስቻለ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም የትራፊክ ፍሰቱን ለማዘመንና ደህንነቱ የተረጋገጠ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና አለው ብሏል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የመንገዶች ስፋት ከመጨመሩም ባሻገር የትራፊክ ምልክቶች እንዲሁም የቀለም ቅቦች መከናወናቸውም ለትራፊክ ፍሰቱ መዘመንና ደህንነት መረጋገጥ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ጠቁሟል፡፡ የመንገዱ ተጠቃሚዎችም ምልክቶችን በአግባቡ በመገንዘብ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

በኮሪደር ልማቱ ከ48 ኪሎ ሜትር በላይ የተሽከርካሪ መንገድ፣ ከ96 ኪሎ ሜትር በላይ ሰፋፊ የእግረኞች መንገድ እና 100 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ መሠራታቸውን መግለጫው አትቷል፡፡

በተጨማሪም አራት የመሬት ውስጥ የእግረኛ መንገድ፣ አምስት ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክና ሁለት ትልልቅ የተሽከርካሪ ድልድዮች በተመሳሳይ በኮሪደር ልማቱ ተሠርተዋል ብሏል፡፡

ስድስት ሺህ 369 ተሽርካሪዎችን የሚይዝ 32 ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች፣ ዘጠኝ የታክሲና የአውቶቡስ ዘመናዊ ተርሚናሎች እንደተሠሩ አመላክቷል፡፡

በአንድ ጊዜ 268 አውቶብሶችና ታክሲዎች ለአጭር ጊዜ መጫንና ማውረድ የሚችሉባቸው እንዲሁም ሌሎች ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ጠቁሞ፤ እነዚህን መሠረተ ልማቶች በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚያስፈልግ መግለጫው አሳስቧል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 20 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You