ብሔራዊ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ገንዘብ ለግል ባንኮች ማከፋፈሉ የፋይናንስ ተቋማትን ከመገንባቱም በላይ የተሻለ አሰራር በአገሪቱ እንዲመጣ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ዳባ እንደተናገሩት፣ የውጭ ገንዘብ እጥረት ባለበት በአሁኑ ወቅት መቶ ሚሊዮን ዶላር ለግል ባንኮች መከፋፈሉ በርካታ ጠቀሜታ አለው። የመጀመሪያው በግል ባንኮች ደንበኞችን ለመያዝ ያስችላል።እስካሁን በነበረው ሂደት ደንበኞች የውጭ ምንዛሪ ሲፈልጉ ገንዘባቸውን ይዘው ብሔራዊ ባንክ ይሄዳሉ። በዚያው ልክ ከግል ባንኮች ይልቅ ንግድ ባንክ ላይ ደንበኝነት ያላቸው ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆኑ ነበር። አሁን በተጀመረው መንገድ ደግሞ ደንበኞች በፈለጉት ባንክ ለመሄድ አማራጭ ያሰፋላቸዋል። የተከፋፈለው የዶላር መጠን አነስተኛ ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከመቀነስ አኳያ የማይተካ ሚና አለው።
ሌላው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባቸው ፋብሪካዎች፤ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትና አልሚዎች ያጋጠማቸውን ችግር አማራጭ ባንኮችን በመጠቀም እንዲፈቱ ያስችላቸዋል፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ እንዲመረት የማድረግ እድል እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ሌሎች የሥራ አማራጮችን ለማስፋትና የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ ያግዛል።
ለግል ባንኮች ዕድሉ መመቻቸቱ የአገር ውስጥ አልሚዎችን ለአዲስ ነገር ለማነሳሳት ያስችላል የሚሉት አቶ አዲሱ፤ የአገር ውስጥ አልሚዎች ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ፤ አዳዲስ የልማት ሥራዎችን እንዲሰሩና ሰዓታቸውን ጠብቀው ወቅታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል። የግል ባንኮቹም ሰፊ አማራጭን እንዲሰጡ እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ። ቱሪስቶችም የውጭ ምንዛሪያቸውን በግል ባንኮች ጭምር እንዲያዘዋውሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው ፤ ኤክስፖርት ላይ የሚሰሩ ሰዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ብዙ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ያነሳሉ። ይህ እድል መመቻቸቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሥራ ያቆሙ እንዲጀምሩ ያነቃቃል። ከብሔራዊ ባንክና ከንግድ ባንክ ብቻ የውጭ ምንዛሪ የማግኘቱን ሁኔታ ያስቀራል። የባንኮቹ ተገልጋዮችም እንዲሁ ደንበኝነታቸውን እንዲያጠናክሩ ከማድረጉም በላይ በፈለጉበት ቦታ ሄደው ገንዘቡን አግኝተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያግዛቸዋል።የግብዓት ማስገቢያ ገንዘብ በቀላሉ የሚያገኙበትን አማራጭ ያሰፋላቸዋል። በተለይ ለላኪዎች ሰፊ እድልን የሚያቀዳጅ ነው።
ከዚህ በፊት ብዙ ላኪዎች በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ሥራ ማስኬጃ ሲጠቀሙበት በመቆየታቸው ዶላሩን ተጠቅሞ የሚያመጣውን ትርፍ እንዳይልቅ አድርጎታል። በህጋዊ መንገድ የሚሰሩትም በህጉ በማይሰሩት አካላት ጋር ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። አሁን ግን በግል ባንኮችም ጭምር ይህ ሥራ በአግባቡ እንዲከወን ስለሚያደርገው በአሰራር የተስተጓጎለውን የላኪዎች ሁኔታ አቅጣጫ ያስይዘዋል። የሁለቱም የባንክ ተጠቃሚዎች በእኩል የላኪነት ሚናቸውን እንዲወጡና ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ ያደርጋል ብለዋል።
እንደ አቶ ሙሼ ገለጻ፤ አገሪቱ በመጀመሪያ ወደ ውጭ የምትልከው የሰብል ምርት ሲሆን፤ ሰላም ባለመረጋጋቱ የተነሳ ያልተመረተው ብዙ እንዲሆንና ያለሥራ የሚቀመጠው እንዲበራከት በር ከፍቷል።አሁን ይህ እድል መምጣቱ ሥራ አጡ ወደ ሥራ እንዲገባ ያበረታታል። አምራቾችም በጥሬ እቃ እጥረት ሥራዎችን መስራት እንዳይችሉ የሆኑበትን ችግር ይፈታል። ከግል ባንኮቹ የተሻለ ብድር እንዲያገኝም ያስችላል። ከሌሎች የውጭ ባንኮች ጋር አጋር ሆኖ የሚሰራበትንም አማራጭም ያጎለብታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር አጥላው አለሙ እንደሚናገሩት፤ እስከዛሬ ብሔራዊ ባንክ በአግባቡ ገንዘቡን አይጠቀሙትም ብሎ ከመከልከል ይልቅ ሥርዓት አበጅቶ ዶላር ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ብዙ የኢኮኖሚ እድገቶች በአገሪቱ ይመዘገብ ነበር ሲሉ ይቆጫሉ። ሆኖም አሁን መጀመሩ በርካታ ጥቅሞች እንደሚኖረው ይናገራሉ። ንግድ ባንክ ለራሱ ደንበኞች የሚሰጠውን ያህል ለሌሎች ደንበኞች ስለማይሰጡ ከግል ባንኮች ይልቅ እርሱ ብቻ ተመራጭ መሆኑ ይቀርና የግል ባንኮችም እኩል ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የሚሆኑበትን እድል ያሰፋል።
ለግል ባንኮች ዶላር መከፋፈል መጀመሩ ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻርም ትልቅ ሚና እንዳለው ይጠቅሳሉ፤ ደንበኞች በግል ባንኮች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲያገኙ እድል የሚፈጥርበት አማራጭ መሆኑን ያነሳሉ። የሥራ ክፍፍልንም ለማምጣት እንደሚጠቅም፤ በንግድ ባንክ ብቻ የሚሰለፈውን የውጪ ምንዛሪ ፈላጊ የግል ባንኩ ጋር ሄዶ በሰዓቱና በወቅቱ ገንዘቡን አግኝቶ ወደ ሥራው እንዲሰማራ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ።
መቶ ሚሊዮን ዶላሩ ለግል ባንኮቹ መከፋፈሉና ዶላር በእጃቸው መኖሩ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ማህበረሰቡ እንዲያገኝ ያስችላል የሚሉት ዶክተር አጥላው፤ እስከዛሬ በአገር ውስጥ ብር እንቅስቃሴ ላይ የተወሰኑት የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ተጨምሮበት የሚሰሩ ከሆነ ከውጭ አጋሮች ጋር የሚሰሩበትን እድል ያሰፋሉ።
የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት 23 በመቶ ወደ ውጭ በሚላክ ምርት ላይ የተመሰረተ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ይህ ሥራ ብዙ ጫናዎች እንዲያርፉበት ሆኗል። ስለዚህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ባንክ የተከፋፈለው መቶ ሚሊዮን ዶላር ብዙ ደጋፊ አማራጮችን ይሰጣል የሚል አስተያየት አላቸው።
አሁንም ክፍፍሉ በሥርዓት መመራት እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ሙሼ፤ በቀጣይ የአጠቃቀም ሥርዓት ተገንብቶ ሁሉም ባንኮች በእኩል ደረጃ እንዲወዳደሩ የሚደረግ ከሆነ የግል ባንኮች ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍ ይላል። በተለይም አዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ተወዳዳሪ የባንክ አገልግሎት በአገር ውስጥ እንዲኖር ያደርጋሉ።
ምሁራኑ እንዳሉትም ፣ የግል ባንኮች በውጭ ምንዛሪው ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ በቀጣይ የግል እና የመንግሥት ባንኮች በአሰራርም ሆነ በእድገት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በር ይከፍታል ። ከውጭ ባንኮች ጋር በጥምረት የመስራት እድላቸውንም ያሰፋል።ለደንበኞች ሰፊ ዕድል በመፍጠርም በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸውን ሚና ያጎለብታል ።በአጠቃላይ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የጎላ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው