ትንቅንቅ

ሕይወት ትንቅንቅ ናት፡፡ ከራስ ጋር፣ ከፈጣሪ ጋር፣ ከተፈጥሮ ጋር ከነዚህ ሁሉ ጋር፡፡ ከሁሉም ግን ከራስ ጋር የሚደረግ ትንቅንቅ ይከፋል፡፡ ከራስ ጋር ትንቅንቅ መልስን ደብቆ፣ እውነትን ሸሽጎ ነው። በማይገኝ መልስና በማይደረስ እውነት ውስጥ ቆሞ ላለመውደቅ ትግል እንደምን ይቻላል? ሰው ራሱን ታግሎ እስካላሸነፈ ድረስ ሁሌም ትንቅንቅ ውስጥ ነው፡፡ እናም ከራሱ ጋር እንዲህ ያስባል፡፡ በተለይ መኖር አፈር ከድሜ ሲያስግጠው፣ በተለይ እብድ እናቱ ፊት ቆሞ የማይነቃ ሴትነቷን ሲያስብ፡፡

አስራ አራት ዓመቱ ነው.. አስራ አራት የመከራ ቀንበሮች ጠይም ፊቱ ላይ ተስለዋል፡፡ ተስሞ ያልበቃው ጉንጭ፣ ቦርቀው ያልጠገቡ እግሮች ዛሬም ድረስ ልጅነት ያምራቸዋል.. ዛሬም ድረስ መሄድ ይናፍቃሉ። እንዳያልፈው ልጅነቱ ላይ የተጋደመ የሕይወት ሰንኮፍ አለ፡፡ ተናንቆ ያልተሻገረው.. ተፍገምግሞ ያላለፈው፡፡ ከዚህ ርቆ መኖር ይፈልጋል።

ስድስት ሰአት አለፍ ሲል ከእናቱ ሸሽቶ መንገድ ጀመረ፡፡ የምግብ ፔስታሉን እንደያዘ አንድ ሆቴል በር ላይ ቆመ፡፡ በሃሳቡ ሁለት ሴቶች ይመላለሳሉ፡፡ አንድ አይነት ተፈጥሮ፣ አንድ አይነት ሴትነት ተሸክመው ግን የተለያየ ልብ ያላቸው ሴቶች፡፡ አንዷ ደስታው ናት.. እንዲህ እንደ አሁኑ በሕይወት ትንቅንቅ በአደፈ ልብስና አካሉ ጋር የምግብ ፔስታሉን ይዞ በር ላይ ሲቆም መቼም በማይረሳው፣ በሕይወቱ ሙሉ በሚከተለው ትህትና ፔስታሉን በምግብ ሞልታ ትሸኘዋለች፡፡ ሩቅ ከደረሰ በኋላ እሷን ለማየት ዞሮ ያውቃል፡፡ ሲዞር እዛው በር ላይ ምግብ የያዘችበትን ሳህን እንደያዘች ትሁት በሆነ ፊት ወደ እሱ እያየች ያገኛታል፡፡ እናቱ ጋ እስኪደርስ ድረስ ሃሳቡ እሷ ናት። እና ደግሞ አንድ ሴት አለች.. ከዚች ሴት የራቀች፣ ማጣት ላገረጣት ነፍሱ መከራ የሆነች፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ የምግብ ፔስታሉን ይዞ በር ላይ ሲቆም ድንገት ትመጣና ‹ሂድ ከዚህ..! ትለዋለች፡፡ ከበር ሸሽቶ ሩቅ እስኪደርስ ድረስ እንዳይመለስ በአይኗ ትጠብቀዋለች፡፡ ወፍራም ናት..በእሷ ምክንያት ወፍራም ሴቶች ሁሉ ክፉዎች ይመስሉታል፡፡ እሷ ካባረረችው በኋላ ባዶ እጁን ወደ እናቱ ይሄዳል፡፡ እናቱ መጽናኛው ናት፡፡ እናቱ እንደዛች ወፍራም ሴት ሕይወትና ሁኔታዎች ሲያሰቃዩት ማረፊያው ናት። የምታደርገው ሳይገባው፣ የምትለው ሳይሰማው ተነስታ እስክታባርረው ድረስ ሄዶ አጠገቧ ቁጭ ይላል፡፡

ዛሬም ሁለት ሴቶች በሃሳቡ እየተመላለሱ ሆቴሉ በር ላይ ቆመ፡፡ ከሆቴሉ ውስጥ ብዙ ሳቆች ይሰሙታል፡፡ ጥጋብና ድሎት ጸንሶ የወለዳቸው ሳቆች፡፡ ደስታ ምን እንደሆነ አያውቅም.. ደስታ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባውም፡፡ ከሆቴሉ ውስጥ የሚሰማው ሳቅ ግን የነፍሱ ማረፊያ ሆነ፡፡ ሳቅ አማረው.. መከራውን ሁሉ ረስቶ እንደነዚያ ነፍሶች መሳቅ.. መፍነክነክ አማረው፡፡ በሕይወቱ ተመኝቶ ያጣው ይሄን ነበር፡፡ አስቆት የሚያውቅ የለም፡፡ የምታስቀው አንድ ነፍስ ነች.. እዚህ ሆቴል በር ላይ ቆሞ፣ ነጭ በጥቁር የመስተንግዶ ልብስ ለብሳ ፔስታሉን በምግብ የምትሞላለት ነፍስ፡፡ የምታስቀው እሷ ናት። ኀዘን በሚተናነቀው በማይስቅ ፊት፣ አቆፋዳውን በምግብ ትሞላለታለች፡፡ ያኔ ይስቃል..ያኔ እየሳቀ ወደ እናቱ ይገሰግሳል፡፡ በዚያች አስተናጋጅ ነፍስ ብዙ ጊዜ ስቋል፡፡ ግን ሰሞኑን አላያትም… ያለፉትን ሶስት ቀናት እየደነበረ ያለው በወፍራሟ ሴት ነው፡፡ ዛሬም ሳቅ አማረው.. ደጓን ሴት ሽቶ በር በር ያይ ጀመር፡፡

አይኖቹ የሚወጣውንና የሚገባውን እየቀላወጡ ብዙ ቆየ፡፡ ከዛ ሁሉ ሳቂታ ፊት መሀል ለእሱ የሚሆን አንድ ሰው መጥፋቶ አስከፋው፡፡ የሚያየው የለም.. የሚመጣው ሁሉ እየገፋው ያልፋል፡፡ መሞት ጀመረ.. በነፍሱ ላይ የለኮሳት የተስፋ ጭላንጭል መክሰም ጀመረች፡፡ ሆቴሉ በር ላይ እንደቆመ ጀምበር ሸሸችው፡፡ ከሆቴሉ የሚሰማው ሳቅ ግን አሁንም ይሰማዋል፡፡ ተንቆራጠጠ.. በዚህ መሀል ወደ እሱ የሚረግጥ ኮቴ ሰማ፡፡ ይሄን ኮቴ ያውቀዋል.. እዛ የሆቴል በር ላይ በተመላለሰባቸው ጊዜያቶች ውስጥ ከዚህ ኮቴ ጋር ተቆራኝቷል፡፡ የወፍራሟ ሴት ኮቴ ነው.. እንዲህ ትመጣና ነው ታግሎ ባልጣለው ራሱ ውስጥ የምትሸነቀረው፡፡ እንዲህ ትመጣና ነው ሳቅ የናፈቃት ነፍሱን የምታጸልምበት፡፡ እንዲህ ትመጣና ነው ከጠበቀው ከብዙ ተስፋው የምታቆራርጠው፡፡

ሆቴሉ በር ላይ አያት፡፡ ቁመቷን ከፍ ያደረገ ባለታኮ ጫማ ተጫምታለች፡፡ ጉልበቷ ላይ የቀረ ደረቷን የሚያሳይ ሰማያዊ ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ጸጉሯ በአጭሩ ተቆርጦ ለራስ ቅሏ በሚመች ሁኔታ ወዲያና ወዲህ ተለጥልጧል፡፡ ጫማዋ እንዳይጥላት ቀስ እያለች በመራመድ ወዳለበት ተጠጋች፡፡ ልትናገረው አፏን ስታሞጠሙጥ ከአንድ ወዳጇ ጋር ተገናኘችና ለእሱ ባሞጠሞጠችው ከንፈሯ ወዳጇን ጉንጮች ሳመቻቸው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ተሳሳቁ፡፡ ትቷት ወደ ሆቴሉ ሲገባ እሷም ወደ እሱ ተመለሰች፡፡ ሳቋን አክስማ ‹ስማ አንተ! አለችው፡፡

የሆቴሉን አንድ ጥግ ይዞ አያት፡፡

‹አትሰማም እንዴ! ሁለተኛ እንዳትመጣ አላልኩህም?

ዝም አለ.. ምን እንደሚልና ምን እንደሚባል አላወቀም፡፡ ሰዎች ሲናገሩት የኖረ ሰው ነው፡፡ ከእናቱ ጋር እያባረሩና እየገፉት የኖረ ነው፡፡ ሰዎች በእሱና በእናቱ ላይ እንደፈለጉ ናቸው.. ይቺንም ሴት ምን እንደሚላት አያውቅም፡፡ አይደለም ይቺን ቀርቶ ያቺን የነፍሱን ሳቅ አስተናጋጅ እንኳን በዛ ሁሉ ደግነቷ ውስጥ ምንም ብሏት አያውቅም፡፡ በእጁ ያንከረፈፈውን ፔስታል በመዳፉ እያሟሸሸ ዝም ብሎ አያት፡፡

‹ምን ይመስላል! አመዳም› አለችው፡፡

ዝም አላት.. በአይኖቹ እየሰረቀ ያያታል፡፡ የተጸየፉት አይኖቿ ይታዩታል፡፡ የገፉት.. የሸሸው ልቧም፡፡

‹ሁለተኛ ድርሽ እንዳትል..ሂድ አሁን ከዚህ› ስትል ፊቷን በጥላቻ ሞልታ፣ በእጇ መሄጃውን እየጠቆመች ተናገረችው፡፡

ከዛ በኋላ እዛ ሆቴል አልተመለሰም.. ሁለት ሴቶች በነፍሱ ላይ አፍርቶ ከዛ ስፍራ ተገለለ፡፡ ከዚህ እዛ እስኪደርስ፣ ይሄን ዘመን አልፎ ሌላ እስኪሆን ድረስ እኚህ ሁለት ነፍሶች አይረሱትም፡፡ በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል፡፡ ‹ሰው የሚሞተው ሰው ያጣ ቀን ነው፡፡ ሕይወት የሚታክተው ቀና ልብ ሲርቀው ነው› እንዲህ እያሰበ ራሱን አገኘው፡፡ ይሄ ሃሳብ እንዴት ወደ ልቡ እንደመጣ አያውቅም፡፡

ባዶ እጁን ወደ እናቱ ሄደ፡፡ ወደ እናቱ ሲሄድ ከፊት ለፊቱ ስሙን የማያውቀው ካቴድራል ይታየዋል፡፡ ርምጃውን አንቀርፍፎ ተጠጋው፡፡ ሕይወት ያስተማረችው ዝምታ አይደል? አሁንም ምን እንደሚል አያውቅም፡፡ እግዜር ፊት ቆሞ ዝም አለ፡፡

በርቀት ጀርባው ላይ የተቀደደ ነጠላ ለብሳ ያቺን መልካም አስተናጋጅ አያት.. እግዜር ለካ ዝምታ ይሰማል..

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You