አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን ለማስከበር ባደረገው እንቅስቃሴ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተገኘ 878 የጦር መሳሪያና 15ሺ24 ጥይቶችን መያዙን አስታወቀ። ህብረተሰቡ ከሰላም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ከፀጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በክልሉ እየተዘዋወሩ ያሉ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች ስልታዊ በመሆናቸው ያንን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትልቅ ጥረትን ጠይቋል። ይሁንና በክልሉ በተሰራው የተጠናከረ ሥራ 609 የጦር መሳሪያዎች፣265 ሽጉጦች፣አራት ክላሽ መያዝ ተችሏል። እንዲሁም 10ሺ297 ለተለያዩ መሳሪያዎች የሚያገለግሉ ጥይቶች፣ 4ሺ 583 የሽጉጥ ጥይትና 144 የክላሽ ጥይቶች እንደያዘ ገልጿል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ከተያዘው የጦር መሳሪያ በተጨማሪ ሸቀጥና የተለያዩ ንብረቶች ተይዘዋል። እነዚህም 932 ኩንታል ቡና፣ 400 ኩንታል ሰሊጥ፣ 2ሺ የሱማሌ ሽልንግ በአንድ መጋዘን ውስጥ የተያዘ ሲሆን 20ሺ ኩንታል ቡና፣ 3ሺ ኩንታል ሰሊጥ፣ 9552 የተለያዩ ተሽከርካሪዎች መለዋወጫ፣ 3ሺ ኩንታል አኩሪ አተርም ደግሞ በሌላ መጋዘን ውስጥ የተገኙ ናቸው። በተመሳሳይ ሁለት መጋዘን ሙሉ ገብስ፣ 1ሺ66 ኩንታል ቡና ተይዘዋል። ይሁን እንጂ ህገወጥ ናቸው አይደሉም የሚለው እየተጣራ ነው ብለዋል።
ክልሉ የጸጥታ አካላትን በማቀናጀትና ከህብረተሰቡ እገዛን በመጠየቅ የህግ የበላይነትን በማያከብሩ ላይ ተከታታይ ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት ኮሚሽነር ከፍያለው፤ በህገወጥ መንገድ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አካላት ለህግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል። በቅርቡ በአማራና አዲስ አበባ በተፈጠረው ችግር ዙሪያም ኦሮሚያ ላይ ትስስሩ ይኖራቸዋል ተብሎ የተጠረጠሩ ግለሰቦች መያዛቸውንም አስረድተዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በክልሉ ህዝብ ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን ህዝቡ በመግለጽ መንግሥት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብርለት በተለያየ መልኩ እየጠየቀ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች መደረጋቸውን አንስተዋል። ይህንንም ችግር ለመፍታት ክልሉ ይሰራል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ከሰላም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ከፀጥታ አካላት ጎን መቆምና መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል። ህዝቡ የሚያደርገው ርብርብ የማይተካ ሚና አለውና ይህንን በጎ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው