አዲስ አበባ፡- ቱሪዝም በባህሪው ውስብስብ እና ብቻውን ማደግ የማይችል በመሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ተጓዳኝ የሆነው የኢኮኖሚው ዘርፍ ማደግ እንዳለበት ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡ዘርፉ በሚጠበቅበት ልክ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ አስተዋጽኦ እያደረገ አይደለም።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት ረቂቅ እቅድን አስመልክቶ ትናንት በካፒታል ሆቴል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ዋና ዳይሬክተሯ ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንደገለፁት፤ ቱሪዝም በባህሪው ውስብስብና ብቻውን ማደግ የማይችል በመሆኑ ለዘርፉ ዕድገት መሰረተ ልማቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በተለይ ደግሞ መንገድ ፣የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ጥራት ያለው ሆቴል እንዲሁም የተለያዩ ተቋሞች በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ላይ አለመኖር ከቱሪዝም ማግኘት ያለብንን ጥቅም እንዳናገኝ አድርጎናል ብለዋል፡፡
ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠቱና በቅንጅት ሥራው ባለመሰራቱ ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል አስተዋፅኦ እያደረገ አይደለም፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያ የሀገርን ገፅታ መገንባት በዋናነት የተሰጠው ተልዕኮ ነው። ነገር ግን የቱሪስት መስህቦቻችንን ባ ለ መ ል ማ ታ ቸ ው ፣ የ ት ራ ን ስ ፖ ር ት ችግር መኖር፣ የአንድ ሀገር መታወቂያ
የሆነው ብራንድ በሀገርና በውጪም ባለመተዋወቁ፣ ለጎብኚዎች የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸውና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ባለመሰራቱ በሚፈለገው ልክ የሀገርን ገፅታ መገንባት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ቅርሶች ካላቸው ሀገሮች መካከል ብትሆንም በዘርፉ ላይ በትኩረት ከመስራት ይልቅ የተወሰነው ላይ ብቻ በማተኮራችን ለቱሪዝም እድገቱ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበት አስታውቀዋል። አሁን ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የ2012 የበጀት ዓመት ረቂቅ እቅዱ ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ቡድን መሪ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በቀጣይ በጀት ዓመት የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማነቃቃት ዝግጅት ተደርጓል። የራሱ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማድረግ፣ጠንካራ የሰው ኃይል በማሟላት የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት እየተሰራ ነው፡፡ እንዲሁም ያሉንን የቱሪስት ቦታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት ዘርፉን ለማሳደግ ከምን ጊዜውም በላይ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ሞገስ ፀጋዬ