“ሰላምን ሻት ተከተላትም !”

ዓለም አቀፉ የእርቅ፣ የሰላም፣ የግልግልና የሽምግልና ረቡኒ (መምህር ) ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ «የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች» በሚለው ማለፊያ መጽሐፋቸው የሰላም የእርቅ አድማሶች በማለት በመጀመሪያ ሰው ከራሱ ጋር ከዚያ ከጎረቤቱ፣ ከማህበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ፣ ሰላም ማውረድ እንዳለበት ይተነትናሉ። በፕሮፌሰር የሰላም አድማስ እይታ መሠረት ሦስት የሰላም አለባውያን አሉ፦

1ኛ . ከራስ ጋር ሰላም

ዓለም አቀፍ አሸማጋይ እና የሰላም አባት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ በዚሁ መጻሐፋቸው ገፅ – 102 ላይ «ውስጣዊና መንፈሳዊ ሰላም ከራስ ጋር ሰላም ማውረድ፣ መታረቅ ነው። ከፈጣሪ ጋር ሰላም ከማውረድ ጋር ትስስር አለው። ውስጣዊ ሰላም ከሌሎች ጋር ለሚመሰረት ሰላም ወሳኝ ነው። ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው ምን ያህል ከሌሎች ጋር በሰላም እንደሚኖር እና ሰላም እንደሚያካፍል ይታወቃል። ውስጣዊ ሰላም ያላቸው ሰዎች አስታራቂና ሰላም ገንቢም ናቸው። ሰላማቸው ወደሌሎች ይፈሳል። ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሰላም ያለው ሰው የሕይወትን መስተጋብር የተገነዘበ ስለሆነ ከማህበረሰቡና ከተፈጥሮ ጋርም ሰላምና እርቅን ያወረደ ነው። ከራስ ጋር የሚፈጠር ሰላም ለሰላም አድማሶች መነሻም ውጤትም ነው። …»

2ኛ . ማህበራዊ ሰላም

ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ስለ ሁለተኛው የሰላም አድማስ ገፅ – 103 ላይ «ማህበራዊ ሰላም ከራስ ጋርና ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረግ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ይህ ማለት ግን ማህበራዊ ሰላም ከሌለ ውስጣዊ ሰላም አይኖርም ወደሚል መደምደሚያ አያደርስም። ሆኖም ብጥብጥና ሁከት ባለበት ውስጣዊ ሰላምን ማስፈንንም ሆነ ማስቀጠልን ፈታኝ አያደርገውም ማለት አይደለም።

ሌላው ማህበራዊ ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረገው ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን መገንዘብ ነው። ግጭትና ጦርነት በተደጋጋሚ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሚጎዳ ደኑም ስለሚጨፈጨፍ አካባቢው ይራቆታል። በዚህም ሥነ ምህዳሩ ስለሚዛባ የከባቢ አየር ለውጥን ያስከትላል። ለዚህ ነው የማህበራዊ ሰላም መኖር ለፍጥረትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና ተደርጎ የሚወሰደው።»

ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከራስ ጋር የሚፈጠር ውስጣዊ ሰላም ከጎረቤት፣ ከማህበረሰብ ጋር የሚደረግ እርቅ መሠረት ነው። በኢሬቻ ለመታደም ከራስ ጋር መታረቅ ማህበራዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከራሱ ጋር ሰላም ያለው ደግሞ ከጎረቤቱ ጋር የመጋጨት አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው። ለዚህ ነው የሥነ ማህበረሰብ አጥኚዎች መጀመሪያ ከራስ በመቀጠል ከጎረቤት ጋር የሚፈጠር ሰላም ከተፈጥሮ ጋር ለሚደርስ ሰላም መደላድል እንደሆነ የሚያስረዱት። ታላቁ መጽሐፍስ «እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።» አይደል የሚለው ! ?

3ኛ . የተፈጥሮ ሰላም

ፕሮፌሰር በገፅ – 104 ላይ «የተፈጥሮ ሰላም ከማህበራዊ እና ከውስጣዊ ሰላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ፣ እርቅ ማውረድ አካላችን ከታነፀበት ምድር ጋርም መታረቅ ነው። ከተፈጥሮ፣ ከዩኒቨርስ ሥርዓትና ኃይል ጋር መንሰላሰል የውስጣዊ ሰላም ምንጭ ነው።

የተፈጥሮ ፍቅርና እንክብካቤ ለማህበራዊ ሰላም መስፈን የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። …«ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ «…በተለያዩ ማህበረሰቦች ሀገር ግንባታ Nation Building በመሀላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ግድግዳዎችን አፍርሶ የጋራ ማንነት መገንባት ነው ። …» ይላሉ።

የሀገር በቀል እውቀቶችና የባህል ተመራማሪው አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ይሄን የፕሮፌሰር ሃሳብ ይጋራሉ። የጋራ የሆኑ እሴቶችንና ባሕሎችን እያጎለበትንና እያሳደገን በሄድን ቁጥር መተዋወቅ፣ መከባበር፣ መቀባበል ስለሚጨምር እኔነት በእኛነት እየተተካ ስለሚሄድ ለሀገርም ሆነ ለሀገር መንግሥት ግንባታ እርሾ እንደሚሆን ተመራማሪው ያስረዳሉ። ዛሬ ከምንገኝበት መንታ መንገድ ላይ የደረስነው ባህሎቻችንን እሴቶቻችንን ለሀገር መንግሥትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ባለማዋላችን ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታህ ይሞግታሉ። እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓሎቻችን ፣ ኢሬቻ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጨምበላላ ፣ ወዘተ. .. አንድ የሚያደርጉን ባሕሎች በብዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊነታችንን ያጠናክራል። ከተገኘንበት ብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነታችን እየገዘፈ ይሄዳል። እየተዋሀድን፣ እየተቀባበልን፣ እየተከባበርን በሄድን ቁጥር እየተዋደድን እንሄዳለን አንድነታችንም በዚያው ልክ ይጎለብታል ሲሉ ይጠቁማሉ።

መምህር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ በበኩላቸው ሰላም ማለት ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል ይሉናል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሰላምን ሻት ተከተላትም” ብሎ ከመናገሩ አስቀድሞ የመጽሐፉን ክፍል ወደ ኋላ መለስ ብለን የተነሳንበትን ኃይለ ቃል ሙሉ አሳቡን ለመረዳት ስንመለከተው እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን። “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካንም አድርግ ሰላምን ሻት ተከተላትም” ይላል።

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሰላምን የምንሻበትን ምክንያት በዚሁ በተመለከትነው ኃይለ ቃል ላይ ገልጦታል። እንደ አባትነቱ እግዚአብሔር ልጆቹ ለምን ይሆን ለእኛ ሊያስተምረን የፈቀደለትንና እርሱ በሕይወቱ ገንዘብ አድርጎት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተመረጠበትን ጥበብ ለእኛም ሲያካፍለን “እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ አለ። ምክንያቱም እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ይልቅ ቀዳሚ ነውና። ለዚህም ነው አባትና ልጅ ተባብረው (ተቀባብለው) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የነገሩን (መዝ. 111፥10፣ምሳ.1፥7፣9፥10)።

ከሁሉ አስቀድሞ በሕይወታችን እግዚአብሔርን መፍራት ትርጉም ላለው ሕይወት አስፈላጊ ነው። ሰላምን የምንሻበት መንገድ እሱ ነውና። ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን መፍራት ሕይወትን የሚያስገኝና በጎ ዘመንን ለማየት የምንችልበት የጥበብ (የዕውቀት) ሁሉ መሠረት ነው። ይህንንም ከገለጸ በኋላ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? ብሏል። ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው። በመሆኑም ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ቀጥለን በዝርዝር እንመለከታቸዋለን።

1ኛ. አንደበትን ከክፉ መከልከል፤

የሰው ልጅ በልቡ ያሰበውን በአንደበቱ ይናገራል። በልብ የታሰበውን መልካምም ይሁን ክፉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ነገር ግን የታሰበው ነገር በውጫዊ ሰውነት ላይ በሚታዩ ምልክቶች (ገጽን በማየት) መታወቅ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም በአንደበት ቢነገርና በሥራ ቢተገበር ሰዎች ይረዱት ይሆናል።

ይሁንና አንደበትን ከክፉ ካልከለከሉት ሰዎችን የሚጎዳና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የማለፍ በዚያም ሰበብ ተናጋሪውን ሳይቀር ሁለተኛውን አካል በቁጣ በመጋበዝ ለሞት የማብቃት ዕድል አለው። ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ምላስ እሳት ናት እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት ሥጋችንን ትበላዋለች ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች” ይላል። ስለዚህ ሕይወትን የሚፈቅድና በጎ ዘመንን ለማየት የሚፈልግ ሰው አንደበቱን ከክፉ ነገር መከልከልና መጠበቅ ያስፈልጋል። ተናግሮ ሰውን ላለማስቀየምና ላለማስከፋት መጠንቀቅ አለበት። ሌላውንም ሰው ወደ ጥፋት ላለመምራት ማስተዋል ተገቢ ነው። አንደበት ኃያል ነውና ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል የሚል አባባል እንዳለ እናስታውሳለን። አንደበትን ከክፉ ካልከለከልነው ስድብንና ሐሜትን እናበዛለን። ይህ ደግሞ ከሕይወት ጎዳና የሚያወጣ ክፉ ተግባር ነው። በጓደኛ መካከል፣ በባልና ሚስት መካከል፣ በአንድ ሀገርና በሌላው ሀገር መካከል፣ በጎሳና በጎሳ መካከል፣ በጎረቤትና በጎረቤት መካከል ሐሜትና መነቃቀፍ፣ ስድብና ጥላቻ ካለ በጎ ዘመንን ማየት አይቻልም። ነገር ግን ሕይወትንም ሆነ በጎ ዘመንን ለማየት አንደበትን ከክፉ መከልከልና በጎ ነገርን ማውራት አስፈላጊ ነው።

2ኛ. ከክፉ መሸሽ፤

ከክፉ መሸሽ ማለት ክፉን ከማድረግ መቆጠብና ክፉ ከሚያደርጉት ጋር በክፋታቸው አለመተባበር ነው። የእግዚአብሔር ሰው ሁልጊዜም ቢሆን ከክፉዎች ጋር ኅብረት የለውም አባታችን ያዕቆብ ልጆቹን በሚመርቅበት ጊዜ ክፉ ሥራ ከሠሩ ከልጆቹ የክፋት ሥራ ጋር እንደማይተባበርና ከክፋት ጋር ኅብረት እንደሌለው ገልጧል። “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው። በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመጽን ፈጸሟት በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው አሳቤም በአመጻቸው አትተባበርም በቁጣቸው ሰውን ገድለዋልና በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቆርጠዋልና ቁጣቸው ርጉም ይሁን ጽኑ ነገርና ኩርፋታቸውም ብርቱ ነበርና በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ” (ዘፍ.49፥5)

ያዕቆብ ምንም እንኳ በሥጋ የወለዳቸው ልጆቹ ቢሆንም በፈጸሙት ክፉ ሥራ ግን እንደማይተባበር ከክፉ ሥራቸው የራቀና ከክፋት የተለየ መልካም አሳብ እንዳለው ገልጧል። ዛሬም ቢሆን የሰው ልጆች ክፋትና በደል እየበዛ ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔር ልጆች ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከውሸት፣ ከሌብነት፣ ከቅሚያ፣ ከዝርፊያ፣ ከጭካኔ፣ ከሴሰኝነት፣ ከዘማዊነት፣ ከዘረኝነት በአጠቃላይ ለራስም ለሀገርም ከማይበጁ እኩይ ምግባራትና ከሚፈጽሟቸው ሰዎች ጋር መተባበር የለብንም። ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ሕይወትን ለማግኘት የምንሻና በጎ ዘመን ለማየት የምንፈልግ ሁሉ ከክፉዎች ጉባኤ መለየትና አለመተባበር ያስፈልጋል።

3ኛ. መልካም ማድረግ፤

ሕይወትን ለማግኘትና በጎንም ዘመን ለማየት የሚሻ ሰው ሁሉ መልካምን ሁሉ ሊያደርግ ያስፈልገዋል። ከክፉ መሸሻችንና ከከፉዎች ጋር አለመተባበራችን መልካም ሥራ ለመሥራት መሆን አለበት እንጂ ከሥራ ርቀን እንዲሁ እንድንኖር አይደለም። ያለ በጎ ሥራ መኖር ስንፍና ነውና።

እግዚአብሔር የሰውን ውድቀቱንና መጥፋቱን የማይሻ አምላክ ስለሆነ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በክፉ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ሁሉ ሊመለስና በሕይወት ሊኖር ይገባዋል። በቀደመው ስሕተቱ ወንድሙን ያሳዘነ፣ ሰው የገደለ፣ አካል ያጎደለ፣ ግፍን የፈጸመ፣ የድሃውን ገንዘብ በተለያየ ሰበብ የዘረፈ፣ ጉቦ የተቀበለ፣ በነዚህና መሰል እኩይ ሥራዎች ሀገሩን የጎዳ፣ እግዚአብሔርን የበደለ ሁሉ ከልብ በመጸጸት በልቅሶና በዋይታ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያስፈልገዋል። ለዚህም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ አድሮ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንዳለበት አስገንዝቦናል።

“እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው (በደለኛው) ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከከፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለምንስ ትሞታላችሁ? (ሕዝ.33፥11) እንዲል።

እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮ እንደ ነገረን በደለኛ ሰው በበደሉ ቀጥሎ መጥፋት የለበትም። መመለስና በሕይወት መኖር ያስፈልገዋል እንጂ። እሱም እንደ በደሉ ዓይነት የቅርታ ጠይቆ፣ ንስሓ ገብቶ፣ የበደለውን ክሶ፣ የሰረቀውን መልሶ፣ የሰበረውን ጠግኖ፣ ያጎደለውን መልቶ በፍጹም መጸጸት ሊመለስና መልካም በመሥራት ሌት ተቀን ከሚተጉት ጋራ በመልካም ሥራ ሊተባበር ያስፈልገዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ስለዚህ ሐሰትን ተውአት ሁላችሁም ከመንገዳችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ እኛ አንድ አካል ነንና አትቆጡ አትበድሉም ፀሐይ ሳይጠልቅም ቁጣችሁን አብርዱ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም” (ኤፌ. 4፥25) ይላል።

ሰላምን መሻት፦

ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው። ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል። በዓይነቱ ሰላምን በሁለት መልኩ እናየዋለን። እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ብለን እንመድበዋለን።

የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል። ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሐት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋትና ወዘተ ነፃ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል። ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል። ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ከሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን መኖር ነው። በመሆኑም ሰላም ከጥል፣ ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው። ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው።

የሰላም መገኛ፦

ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከፈጣሪ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል። እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ. 15፥33)። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል። “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥6) እንዲል። ዓለም ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ይኖር የነበረ ሲሆን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ መሞትና መነሣት እውነተኛውን ሰላም አግኝቷል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ሞት ምክንያት ፍርሐት ጸንቶባቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት “ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም (ዮሐ.14፥27) በማለት ፍርሐትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን፣ ሁከትን፣ መረበሽን የሚያርቀውን (የሚያስወግደውን) እውነተኛውን ሰላም አደለን።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል። ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው። ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል። መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው። ለዚህም ነው ሰላምን ሻት ካለ በኋላ ተከተላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት የራሳችን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የነገረን።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You