አዲስ አበባ፡- ሙስና የሀገራችን ትልቁ ችግር በመሆኑ ሙስናን ለማቆም ሰዎችን መቀያየር ሳይሆን ወደ ሙስና የሚያስገቡ ምክንያቶችን ከምንጩ ማድረቅ እንደሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። ፍርድ ቤቱ በፌዴራል ደረጃ የሚገለገልበትን አዲስ አርማ ይፋ አድርጓል፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሶስት ዓመት የማሻሻያ እቅድ ማስተዋወቂያና ማስጀመሪያ መድረክ ትናንት በጠቅላይ ፍርድ ቤት አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ እንዳሉት ሰውን በመቀያየር ሙስናን ማቆም አይቻልም፤ ይልቁንም ወደ ሙስና የሚመሩ መንገዶችን መዝጋት ይገባል፡፡
“ማንም ሰው ፈልጎ ወደ ሙስና አይገባም” ያሉት ወይዘሮ መዓዛ ሰውን ወደ ሙስና የሚገፋፉ አሰራሮች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት ለማሻሻል ካልተሰራ ሰው በመለዋወጥ ሙስናን ማስቆም አይቻልም ብለዋል። ምናልባትም ሰዎች ወደ ሙስና የሚገቡት የፍርድ ውሳኔውን ቶሎ አላገኝም ከሚል ግምት ወይንም ህጋዊ ውሳኔ አይሰጠኝም ከሚል ስጋት ሊሆን ስለሚችል መንገዱን ለመዝጋት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመስራት ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሶስት ዓመት የማሻሻያ እቅዱን በተመለከተ የተናገሩት ወይዘሮ መዓዛ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚያስባቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለማሳካት ከመደበኛ በጀት ውጪ ከልማት አጋሮችና ለጋሾች ድጋፍ በማሰባሰብ ለመስራት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። የማሻሻያ እቅድ ሥራዎቹ የሚሰሩት ከዋና ሥራዎች ጎን ለጎን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
“ የፍርድ ቤት ችግሮች ብዙ ናቸው” ያሉት ወይዘሮ መዓዛ ዋናው ግን ለየትኞቹ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት መፍትሄ ያስፈልጋል የሚለው ምላሽ የሚሻው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በእቅዱ ለማካሄድ የታሰቡት ዋና ዋና ሥራዎችን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ በዋናነትም ዳኞችና የማብቃት ሥራ፣ የፍርድ ቤቶች ራስን የማስተዳደር ስልጣን ፣ የፍርድ ቤት አደረጃጀት ይገኙበታልም ብለዋል፡፡
የፍርድ ቤቶች ራስን የማስተዳደር ስልጣን ለፍርድ ቤቱ ነፃነትና ለጥንካሬው ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ የፍርድ ቤቶች አደረጃጀት እንደገና መመለከትንና አዋጅና ህጉን ማሻሻልን ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ ዜናም በዕለቱ ፍርድ ቤቱ በፌዴራል ደረጃ የሚገለገልበትን አዲስ አርማ ይፋ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ዳግማዊት ግርማ