የልዩ ፍላጎት ስኬትና የማታ ትምህርት ድክመት

በትምህርቱ ሴክተር ትኩረት ተነፍጓቸው ከቆዩ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ አንዱ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ነው። እንዲያ ሲባል ግን በየዘመኑ በመጡ መንግሥታት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ ምንም ሥራ አልተሠራም ማለት አይደለም ። ነገር ግን በዚህ ትምህርት ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። ከመንግሥት ለውጥ በፊት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ የተሠሩ ሥራዎች አበረታች የነበሩ ቢሆንም አዲሱ የለውጥ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ሥራዎቹ ተጠናክረው በመሠራታቸው በብዙ መልኩ ለውጦች መጥተዋል።

በተለይ ትምህርት ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አመቺ ሆነውና ለነሱ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በመሟላታቸው ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ ማሳለጥ ተችሏል። በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ የሚፈለገው ውጤት ስለመጣም ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን ባደረገበት ወቅት ይህንኑ የመሰከሩት።

በሌላ በኩል ደግሞ በደርግ ዘመንም ይሁን በኢሕአዴግ ከመደበኛው ትምህርት ባልተናነሰ መልኩ ለማታ ትምህርት ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ጥሩ ለውጥ መጥቷል። በማታ ትምህርት ዘርፍ ትኩረት በመደረጉ በተለይ በቀኑ ክፍለጊዜ ለመማር የማይመቻቸውና ጊዜያቸውን በሥራ ለሚያሳልፉ ዜጎች ራሳቸውን በትምህርት እንዲለውጡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህም ቀላል የማይባሉ ዜጎች ቀን እየሠሩ ማታ እየተማሩ ራሳቸውንና ኑሯቸውን ማሻሻል ችለዋል ።

ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ምንም እንኳን በማታ ትምህርት ላይ የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም በሚጠበቀው ልክ ባለመሆኑ በተለይ በዚህ ዓመት አፈፃፀሙ ደካማ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህንንም የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) የከተማ አስተዳደሩ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም በቀረበበት ወቅት አረጋግጠዋል። በመደበኛው ትምህርት የተሠራውን ያህል ሥራ በማታውም መደገም እንዳለበት አፅንዖት ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዚህ ሳምንት መጨረሻ አካሂዷል። በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚገኘው የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ የምክር ቤቱ አባላት፣ አስፈጻሚ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በጉባኤውም የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል። ውይይት ከተደረገባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ትምህርት ሲሆን በዚህ ዘርፍ በ2016 ዓ.ም የተከናወኑ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በሪፖርት ቀርበዋል።

ከአዲስ አበባ ትምህርት ዘርፍ ጋር በተገናኘ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በማስፋፋት የተማሪዎችን ቅበላ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል። በሁሉም ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በማስፋፋት የተማሪዎችን ቅበላ ከዕቅድ በላይ ማድረስ የተቻለው በአዲስ አበባ ከተማ የትምህርት ፍትሐዊነትን ለማስፈን በተደረገው ጥረት መሆኑንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

በዚሁ የማጠቃለያ ጉባኤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን አቅርበዋል። ከንቲባዋ በሪፖርታቸው የትምህርት ተሳትፎ፣ ፍትሐዊነት እና ጥራትን በማሳደግ በዕውቀት እና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን ለማፍራት በተሠራው ሥራ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላን ከ291 ሺ 392 ወደ 316 ሺህ 931 ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላን በተመለከተ ደግሞ ቅበላውን 626 ሺህ 647 ማድረስ መቻሉን እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ቅበላን 232 ሺህ 30 ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የትምህርት ቅበላ ሥራውን 1 ሚሊዮን 175 ሺህ 608 አድርሰናል ያሉት ከንቲባዋ፤ የትምህርት ፍትሐዊነትን ለማስፈን በተደረገው ጥረት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ትምህርትን በማስፋፋት የተማሪዎችን ቁጥር 39 ሺህ 640 ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል። ትምህርት ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግ በ52 ትምህርት ቤቶች ራምፕ ጥገና እና ራምፕ በሌላቸው 15 ትምህርት ቤቶች በአዲስ መልክ የመገንባት ሥራ መሠራቱንም አመልክተዋል።

የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል በ“ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ በገንዘብ 360 ሚሊዮን ብር፣ በግብዓት 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ በጉልበት 154 ሚሊዮን 596 ሺህ 195 ብር እና በዕውቀት 99 ሚሊዮን 384 ሺህ 667 ብር በአጠቃላይ ከ6 ነጥብ 44 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ መቻሉንም አብራርተዋል።

በተሰበሰበው ሀብትም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና በተማሪዎች ምገባ 779 ሺህ 231 በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ የተደረገ መደረጉን እና የተማሪ ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የመምህራን ጋዋን ማቅረብ መቻሉን ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በመደበኛው የቀን ትምህርት የተመዘገበውን ውጤት በማታው መርሐ-ግብር ለመድገም ሁሉም በትብብር ሊሠራ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገልፀዋል። ኃላፊው ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በቀረበው ሪፖርት ላይ የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መልስ ሲሰጡ ነው።

ትምህርትን በተመለከተ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)ዘርፉ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው፣ ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ለውጥ ለማምጣት ከወትሮው በተለየ መልኩ ጠንካራ ሲሠራ እንደነበር ተናግረዋል። በከተማዋ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከተተገበረ ጀምሮ የመጽሐፍት ኅትመት ትልቅ በጀት የጠየቀ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች 1 ለ 1 መጽሐፍት ማዳረስ መቻሉን ጠቁመዋል። ይህም ለትምህርት ጥራት ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎች በተለይም የተማሪ ክፍል ጥመርታን ለማስተካከል ‹‹በትምህርት ለትውልድ›› እንቅስቃሴ እና በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት መማሪያ ክፍሎች ተገንብተው የተጨናነቁ ትምህርት ቤቶችን የማስተካከል ሥራ መሠራቱንም አስረድተዋል። ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በታችኛው እርከን ላይ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑንም አንስተው፤ ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነው የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ይህንን ያመላክታል ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት የ8ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት 50 እና ከዚያ በላይ በማምጣት ወደ ቀጣዩ የክፍል እርከን ማለፋቸውንም ኃላፊው አስታውሰዋል። የተማሪዎችን ውጤት በተመለከተ ኃላፊው በሰጡት ማብራሪያ የ8ኛ ክፍል የቀን የመንግሥት ተማሪዎች 50 እና ከዚያ በላይ ያመጡት 82 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆኑ የቀን የግል ትምህርት ቤት 96 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች 50 እና ከዚያ በላይ በማምጣት ማለፋቸውን ገልጸዋል። በዚህም በድምሩ 87 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ሚቀጥለው የትምህርት እርከን አልፈዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል የ8ኛ ክፍል የማታ ተማሪዎች በጣም አነስተኛ ውጤት ማሳየታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል። የመንግሥት የማታ ተማሪዎች 16 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ 50 እና ከዚያ በላይ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ ሲሆን የግል የማታ ተማሪዎች ደግሞ 6 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ማለፋቸውን አንስተዋል። እንዲሁም በርቀት የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና 5 በመቶ ተማሪዎች ብቻ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፋቸውን ተናግረዋል።

በመደበኛ የቀን ትምህርት የተመዘገበውን ውጤት በማታው የትምህርት መርሐ-ግብር ለመድገም በልዩ ትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ያነሱት ኃላፊው ለዚህም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል። በውጤት ብቻ ሳይሆን በሥነ-ምግባር የታነጸ ሁለንተናዊ ስብዕና ያለው ትውልድ ለመገንባት ትምህርት ቤቶች ከአዋኪ ድርጊቶች ነፃ እንዲሆኑ በተሠሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል መታየቱንም ኃላፊው አብራርተዋል።

ከዚህ አንፃር የከተማ አስተዳደሩ በቅድሚያ በልዩ ፍላጎት ትምህርት የመጣውን ለውጥ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል። በዚህ ትምህርት ዘርፍ ለውጥ ስለመጣ ሁሉም ነገር ተስተካክሎ አልቋል ማለት ስላልሆነ ቀሪ ክፍቶችን በማረምና ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት የመጣውን ለውጥ ይበልጥ እንደሚያስጠብቅ ይገመታል።

ከዚህ ባለፈ የማታ ትምህርት ላይ በቂ ሥራ ባለመሠራቱ አፈፃፀሙ ደካማ ሆኖ ተመዝግቧልና ጠንካራ ሥራ በመሥራት በመደበኛው ትምህርት የተመዘገበውን ውጤት በማታው ትምህርት መድገም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከወረዳ እስከከተማ ድረስ ያለው የትምህርት መዋቅርና አመራር ሥራውን በኃላፊነትና በጥንካሬ እንደሚሠራ ይጠበቃል።

በልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ የመጣው ለውጥ እንዳለ ሆኖ ከአምናው ትምህርት በመውሰድ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን ለማማሻሻል ዘንድሮ ጠንካራ ሥራዎች ከወላጅ ጀምሮ እስከፍተኛ የትምህርት ሚኒስቴር ድረስ ሥራዎች ተሠርተዋል። ከዚህ አንፃር በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ጥሩ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል። የትምህርት ጥራትንና መሠረተ ልማትን ለማሻሻልም በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። የዛኑ ያህል ውጤት ያልመጣባቸው ሌሎች የትምህርት ዘርፎች አሉና በነዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ይጠበቃል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You