የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት

የዓለም ልዕለ ኃያል የሆነችው፣ የዓለም ሀገራትን እኔ ቅኝ ካልገዛኋቸው ስትል የነበረችው ማለት ብቻም ሳይሆን ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ በርካታ ሀገራትን ቅኝ የገዛችው፣ በዚህም ምክንያት ቋንቋዋ ዓለም አቀፍ ቋንቋ የሆነው እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ በተጻፈ ሰነድ መተዳደር የጀመረችው በ13ኛው ክፍለ ዘመን (1215) ነው። ይህም ‹‹ማግና ካርታ›› የሚባለው ሲሆን፤ ታላቁ ስምምነት (ሜጋ ቻርተር) የሚል ትርጉም ይይዛል። ከዚህ ከእንግሊዝ ሰነድ በፊት ሌላ የዓለም ሀገር የገዥዎችን ብዝበዛ የሚገድብ መተዳደሪያ ያላት የለችም።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ፤ ፍትሐ ነገሥት (የነገሥታት ሕግ) የሚባል ነበር። ነገሥታት የሚመሩበት የሕግ ሰነድ ነው። ማግና ካርታ የሚባለውም ሕጉን ያወጡት የእንግሊዝ ነገሥታት ናቸው። በእርግጥ የፍትሐ ነገሥት ሥረ መሰረቱ የግብጽ ኮፕቲክ ነው። ሆኖም ግን ቃሉንም እሳቤውንም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ፍትሐ ነገሥት ለሺህ ዘመናት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሲመሩበት ኖረዋል። ዛሬ ላይ ማግና ካርታም ሆነ ፍትሐ ነገሥት ተቀይረው ሌላ ቅርጽ ይዘዋል። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 93 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ።

ከ7 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ዘመናዊ መልክ እንዲይዝ ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱት አንጋፋ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የነበሩት ጋዜጠኛና ደራሲ ነጋሽ ገብረማርያም አረፉ። ነጋሽ ገብረማርያም በኢትዮጵያ የእንግሊዘኛ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው የ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ›› የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ነበሩ።

ከ106 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 11 ቀን 1910 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ጁላይ 18 ቀን 1918) ‹‹ማዲባ›› እየተባሉ የሚጠሩት የጸረ አፓርታይድ አብዮተኛው፣ የደቡብ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይና የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላ (ማዲባ) ተወለዱ።

ከ89 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም የአንጋፋው የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት መሰረት የነበረው ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር›› ተመሰረተ።

ከ8 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ የዘመናዊ ትያትር አባት›› በመባል የሚታወቀው አንጋፋው የጥበብ ሰው፣ አባተ መኩሪያ አረፈ።

በዝርዝር ወደምናየው የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት እንለፍ። በነገራችን ላይ ‹‹ዘመናዊ›› የሚለው እና ‹‹የተጻፈ›› የሚለው አወዛጋቢ ናቸው። የመጀመሪየው የተጻፈ የሚለው አይገልጸውም የሚሉ አሉ፤ ምክንያቱም ፍትሐ ነገሥትም ቢሆን የተጻፈ ነበር። ‹‹ዘመናዊ›› የሚለው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ከፍትሐ ነገሥት ብዙም የማይሻል እና ሃይማኖታዊ ይዘት ያለበት የንጉሡንና መሳፍንቱን ቤተሰብ የሚያስቀድም ስለሆነ ‹‹ዘመናዊ›› ለማለትም አያስደፍርም፤ ምናልባት በዘመኑ ‹‹ዘመናዊ›› የሚለው ይገልጸው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ‹‹ሕገ መንግሥት›› በሚባል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀውን ሕገ መንግሥት እናስታውስ።

ኢትዮጵያ እንደ ብዙዎቹ የአውሮፓና ሌሎች ዓለም አገራት በንጉሣዊ ሥርዓት ስትተዳደር የኖረች ሀገር ናት። በእነዚህ ንጉሣዊ ሥርዓቶች ዘመን የነበረው አስተዳደር ብዙውን ዘመን በተጻፈ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት አልነበረም።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ የተጻፈ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት የጀመረችውም በዚያው በንጉሣዊ ሥርዓቱ ዘመን ነው። ምንም እንኳን ከሥርዓት ለውጥ በኋላ የሚመጣው መንግሥት ቢቀያይራቸውም የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት የጀመረችው ግን በንጉሳዊ ሥርዓቱ ዘመን ነው።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ ባለሙያ የሆኑት ሚኪያስ በቀለ በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ የጻፉትን ጥናታዊ ጽሑፍ፣ የታሪክ ጸሐፊው ፍስሐ ያዜ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዘመን ታሪክ ቅጽ 2›› መጽሐፍ እና ከልዩ ልዩ ድረ ገጾች ያገኘናቸውን መረጃዎች ዋቢ አድርገን እናስታውሰው።

ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ዘመናዊ (የተፃፈ) ሕገ መንግሥት ያጸደቁት ከ93 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም ነው። ሕግ መንግሥቱ ሲጸድቅ ንጉሱ የተናገሩትን የፍስሐ ያዜ መጽሐፍ እንዲህ ይነግረናል።

‹‹…ሕግ ለሰው ከሁሉ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑን ማንም አይስተውም። መከበርም መጠቀምም የሚገኙት በሕግ መተካከል የተነሳ ነው። መዋረድም መጎዳትም የሚመጡት በሕግ መጓደል የተነሳ ነው። ግፍ እና በደልም የሚበዙት ሕግ ባለመቆሙ ነው….››።

በንጉሣዊ ሥርዓቱ ዘመን በሕይወት የነበሩ አባቶች ሲያወሩ እንደምንሰማው በዘመኑ ‹‹በሕግ አምላክ!›› የሚባል ነገር ነበር። ‹‹በሕግ አምላክ!›› ከተባለ ምንም ዝንፍ አይልም። ወደታች የሚወርድ የወንዝ ውሃ ‹‹በሕግ አምላክ!›› ሲባል ይቆማል ይላሉ አባቶች። አባባሉ ግነት እንዳለው ግልጽ ነው፤ ዳሩ ግን የሕግን ሃያልነት ለመግለጽ የተጠቀሙት ነው። በዚህ እሳቤ ውስጥ ነው የመጀመሪያው ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት የጸደቀው።

የፍስሐ ያዜ መጽሐፍ እንደሚነግረን፤ ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በመሳፍንቱ እና በመኳንንቱ መካከል ከፍተኛ ክርክር ነበር። ጠቅለል ሲደረግ፤ የመሳፍንቱ ሀሳብ ኢትዮጵያ በአውራጃ ተከፋፍላ የመሳፍንቱ የበላይነት እንዲቀጥል ነው። ሥልጣንም ለልጅ ልጆቻቸው እንዲተላለፍ ነው፤ ዳሩ ግን ወንጀል ሰርተው ከተገኙ ከርስታቸው እንዲነቀሉ የሚል ነው።

የመኳንንቱ ሃሳብ ደግሞ፤ በአጭሩ ሹመት በዘር መሆን የለበትም የሚል ነው። ንጉሱም አስታራቂ ሃሳብ ሰጥተው መሳፍንቱንም መኳንንቱንም ያካተተ እንዲሆን ተደረገ። በንጉሰ ነገሥቱ ይሁንታ ማንም ሊሾም እንደሚችል ተነገረ። በዚህ መንገድ ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ሚኒስትሮች አብረው ሆነው ነው።

የሕግ ምሁሩ ሚኪያስ በቀለ ጥናታዊ ጽሑፍ ደግሞ ስለዚሁ ሕገ መንግሥት የሚከተለውን ይነግረናል።

‹‹… ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀው በንጉሡ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሲሆን፣ ያረቀቁትም በሩስያ የተማሩ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም የሚባሉ ግለሰብ ነበሩ። ደጃዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅ አጼ ኃይለሥላሴ በቀጥታ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው፣ ውይይታቸውን በማካተት ስለ ግለ ሕይወት ታሪካቸውን በጻፉት መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል…››።

ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ለማስረቀቅ እና ለማውጣት ምክንያት የሆናቸው ሀገሪቷ ተራማጅ እና ሥልጡን መሆኗን ለዓለም ለማሳተዋወቅ ነው። የሚኪያስ በቀለ ጥናት ተከታዮቹን መረጃዎችም ይነግረናል።

ደጃአዝማች ተክለሐዋሪያት ሕገ መንግሥቱን ከጃፓኑ (የመጂ ስርወ መንግሥት) ሕገ መንግሥት ላይ በመገልበጥ ቢያረቁትም፤ ከሚኒስትሮች እና የክፍለ ሀገር መኳንንቶች የተውጣጣ 11 አባላት ያሉት የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። ኮሚቴው የእንግሊዝና የጃፓን ሕገ መንግሥቶች ተተርጉመው ቀርበውለት ተወያይቶበት እንደነበር እና በቀጥታ ወደ ንጉሡ ተልኮ ነው የጸደቀው።

ንጉሡ ሕገ መንግሥቱን ከማጽደቃቸው በፊት ብላቴን ጌታ ሕሩይ እና ራስ ካሳ ከሚባሉ አማካሪዎቻቸው ጋር መክረዋል። ሕዝብ አልተወያየበትም በሚል የሕገ መንግሥቱ ሰነድ ከንጉሡ ለሕዝብ የተሰጠ ሥጦታ ተደርጎም ይቆጠራል።

ይህ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዊ ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ንጉሡን ሲያስተች የቆየ ነው። በዚያ ንጉሳዊ ዘመን ቢያንስ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ማስጀመራቸው ያስመሰግናቸዋል እንጂ ይዘቱ ግን ለንጉሡ ያደላ ነበር። እነዚህን አንቀጾች እንጠቃቅስ።

አንቀጽ ሁለት፡- የኢትዮጵያ መሬትም፣ ሕዝብም፣ ሕጉም በጠቅላላው የንጉሠ ነገሥት ነው።

አንቀጽ ሦስት፡- የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ከሰለሞን እና ንግሥት ሳባ ከተባለችው ኢትዮጵያዊ ንግሥት ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሳህለሥላሴ ዘር ከተወለደው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዳይወጣ በሕግ ተወስኗል።

አንቀጽ አምስት፡- ንጉሰ ነገሥቱ የነጋሲ ዘር በመሆኑና ቅብዓ መንግሥት በመቀባቱ ክብሩ የማይቀነስ፣ ማዕረጉ የማይገሰስ ኃይሉ የማይደፈር ሆኖ በቆየውም ልማድ በአዲሱም ሕግ በሚገባው ሁሉ ይከበራል። ክብሩንም ለመንካት በድፍረት የተነሳ ሰው በሕግ እንዲቀጣ ተወስኗል።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አንቀጾች ንጉሱን በሕግ ባለሙያዎች እነሆ ዛሬ ድረስ ተወቃሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በታሪክ ጸሐፊዎች ግን የዘመኑ እና የሥርዓቱ ባህሪ ነው የሚል ሙግት አለ። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ለሺህ ዘመናት የኖረ ንጉሣዊና ልማዳዊ ሥርዓትን ነው አዲስ መንገድ ያስጀመሩት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈ ሕግ እንዲኖረው ያደረጉት… የሚሉ አሉ።

ያም ሆነ ይህ፤ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ነው። ለዛሬው የምናስታውሰው የመጀመሪያው የጸደቀበትን ስለሆነ እንጂ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎች አንቀጾች ባስነሱት ቅሬታና ሙግት በ1948 ዓ.ም ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሏል።

የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሕገ መንግሥት ለዘውዳዊ ሥርዓቱ ያደላ ቢሆንም ያመጣቸው ለውጦችም በታሪክ በበጎ ተጽፈውለታል። ለምሳሌ፤ ማንኛውም መሳፍንት እንዳለፈው ዘመን በግሉ ከውጭ ሀገራት ጋር መጻጻፍ አይችልም። መሳሪያ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በግሉ መቀበል አይችልም። መሳፍንቱን በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ ችሏል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፓርላማ የተመሰረተውም በዚሁ በመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት ነበር። ይሄው ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም የጸደቀው የንጉሡ ሕገ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶችን አቋቁሟል። ምክር ቤቶቹም የሕግ መወሰኛ (ላዕላይ) ምክር ቤት እና የሕግ መምሪያ (ታህታይ) ምክር ቤት የሚባሉት ናቸው። በዛሬው ዓውድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደማለት ነው።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ንጉሡን ለረዥም ጊዜ ካገለገሉ መኳንንት፣ ሚኒስትሮች፣ ዳኞች እና የውትድርና መኮንኖች ውስጥ በቀጥታ በንጉሡ የሚመረጡ ናቸው። አባላቱ የመሳፍንት ዘር ባይሆኑም መንግሥትን ያገለገሉ ከሆነ ከተራ ዜጎችም ይመረጣሉ። ይሄውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 31 ላይ ተቀምጧል።

የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አባላት ደግሞ ‹‹ሕዝቡ የራሱን እንደራሴ መምረጥ እስከሚችል ድረስ›› በሚል በመኳንንቱ እና በሹመኞች ተመርጠው እንደሚላኩ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 32 ይደነግጋል።

አንድ አባል በተመሳሳይ ጊዜ የሁለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን አይችልም። ምክር ቤቶቹ አራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ሥራቸውን አቁመው ቆይተው በድጋሚ ሥራቸውን የጀመሩት በ1933 ዓ.ም መሆኑን አቶ ቃልዓብ ታደሰ ስለ ሕገ መንግሥት ታሪክ በጻፉት መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።

ረቂቅ ሕጎች ከተለያዩ ሚኒስትሮች የሚቀርቡ ሲሆኑ የመጨረሻው ሕግ የማውጣት ሥልጣን ግን የንጉሡ ነበር። ረቂቅ ሕጎች ግን በሁለቱም ምክር ቤቶች ውይይት ይደረግባቸዋል። የትኛውም ምክር ቤት በሚመጡ ረቂቅ ሕጎች ላይ ሃሳብ ካለው በፕሬዚዳንቱ (አፈ ጉባኤ) አማካኝነት ለንጉሡ ያቀርባል። በሁለቱ ምክር ቤቶች መካከል በረቂቅ ሕጎች ላይ አለመግባባት ካለም የሚፈታው በንጉሡ የመጨረሻ ቃል ነው።

በነገራችን ላይ የንጉሡ ሕገ መንግሥት በ1948 ዓ.ም ሲሻሻል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በቀጥታ በሕዝብ የሚመረጡ እንዲሆን ደንግጓል። የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት በመኳንንትና ሹመኞች መመረጣቸው ቀርቶ በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ ሲደረግ፤ በሕዝብ የሚረጡት የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱ አባላት ከ25 ዓመት በላይ መሆን፤ የራሳቸው ርስት ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲኖራቸው ይገባል። የሥራ ዘመናቸውም ለአራት ዓመታት ነው። ይህንንም ተከትሎ በሀገሪቷ የመጀመሪያው ምርጫ በ1949 ዓ.ም ተደርጓል።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባላት ግን አሁንም በንጉሡ ነው የሚመረጡት፤ የሚያገለግሉትም ለስድስት ዓመታት ያህል ነው።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ 17 ኢትዮጵያውያን እና 13 የውጭ ዜጎችን ያካተተ የሕጎችን ጥራዝ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አቋቋሙ። ኮሚቴው የሚሰበሰበው እና ሥራውን ይሰራ የነበረው በጊዜው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር።

ከተረቀቁት የሕግ ጥራዞች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።

የ1952 ዓ.ም ፍትሐ ብሔር፣ የ1958 ዓ.ም የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት፣ የ1949 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ፣ የ1954 ዓ.ም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት፣ የ1952 ዓ.ም የንግድ፣ እና የ1952 ዓ.ም የባህር ሕጎች ናቸው። ሕጎቹ የጸደቁትም ከ1949 ዓ.ም እስከ 1958 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።

በዚያን ጊዜ ከተረቀቁት ስድስት ሕግጋት አምስቱ የተለያዩ ማሻሻዎች እየተደረገላቸው እስከ ዛሬ ተፈጻሚ ሲሆኑ አንዱ (የወንጀለኛ መቅጫ) ሕግ ግን በ1997 ዓ.ም በሌላ እንደተተካ የሕግ ምሁሩ ሚኪያስ በቀለ ጥናታዊ ጽሑፍ ያመለክታል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ከላይ የጠቃቀስናቸውን ይመስላል። ለመሆኑ ከዚህ ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት በፊት የነበረው ምን ነበር የሚለውን ከሕግ ምሁሩ ሚኪያስ በቀለ ጥናታዊ ጽሑፍ ጥቂቱን እናካፍላችሁ።

ማህበረሰቡ ለዘመናት ሲተዳደር የቆየው ከአስተዋይ (አመዛዛኝ ሰው/ዳኛ) ውሳኔ በሚመነጭ ሕገ ልቦና፣ ከአይሁድ፣ ክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች የሚመነጩ ሕገ ሃይማኖት፣ በሕጎች ዙሪያ ከሚሰጡ የሊቃውንት ትምህርት፣ በስምምነት ከሚገኙ እና በተስማሚዎቹ ላይ ብቻ ከሚፈጸሙ ልማዳዊ ወጎች፣ አንድ ዓይነት አሠራር ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ በመዋሉ ምክንያት በተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ በስምምነት የሚፈጸሙ ልማዳዊ ሕግጋት፣ እና የአፈ ንጉሥ ችሎት ፍርዶች ናቸው።

ኢትዮጵያን ከ1426 ዓ.ም እስከ 1460 ዓ.ም ያስተዳደሩት አጼ ዘርዐ ያዕቆብ የተጠረዘ እና ወጥ ሕግ ለሀገሪቱ እንዳበረከቱም የሚኪያስ በቀለ ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳያል። አጼ ዘርዐ ያዕቆብ በመጀመሪያ ‹‹ፈውስ መንፈሳዊ›› የሚባል በይዘቱ ሃይማኖታዊ የሆነ ባለ 68 አንቀጽ የሕግ ሰነድ በቤተ ክህነት ምሁራን እንዳስረቀቁ እና ለአጭር ጊዜ ሀገሪቷን እንዳስተዳደሩበት ይገልጻሉ።

ቀጥሎም ሀገሪቷን ለዘመናት ሲያስተዳድር የቆየው ‹‹ፍትሐ ነገሥት›› የሚባል በይዘቱ ሃይማኖታዊና ምድራዊ ሕግጋትን ያካተተ የሕግ ሰነድ ለአገሪቷ ያስተዋወቁት አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው። ፍትሐ ነገሥት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የሚያስተዳድር 22 አንቀጽ እና 801 ንዑስ አንቀጾች፣ ምድራዊ (ዓለማዊ) ኩነቶችን የሚገዙ ደግሞ 29 አንቀጾች እና 1033 ንዑስ አንቀጾችን ያከተተ ነው።

በእነዚህ ልማዳዊ፣ ሃይማኖታዊና ሕገ ልቦናዊ ሕጎች ሲተዳደር የኖረው የኢትዮጵያ የነገሥታት ሥርዓት በ1923 ዓ.ም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመናዊ የተጻፈ ሕገ መንግሥት አጸደቀ የሚለው ግን እነሆ በታሪክ ተቀምጧል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You