ከተገለጡት – ገፆች…

  ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል። ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል። አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል። ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ። የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ። በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ። በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ። ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ።

እንደመነሻ …

በየቀኑ መልከ ብዙ ገፅታዎች የሚያልፍበት ሰፊ ጊቢ ኀዘንና ደስታ፣ ዕንባና ሳቅ ፣ ሞትና ውልደት ሲመላለስበት ኖሯል :: ይህ በርካታ ነፍሶች የረገጡት አጸድ ለዓመታት በመውደቅ መነሳት፣ በመሳቅ ማልቀስ፣ በማግኘት ማጣት የተቃኘን ታሪክ አሳልፏል::

በዚህ ሥፍራ ብዙዎች ያለቀሱ ስቀዋል:: ብዙዎች ያጡ አግኝተዋል:: ‹‹ቀን ጨለመብን ዙሪያው ገደል ሆነብን›› ያሉ ከደልዳላው ሜዳ ቆመው ፣ ከጨለማው መንገድ ወጥተዋል:: በየቀኑ ዕንባ በሚታበስበት፣ በየዕለቱ ቋጠሮ በሚፈታበት ጊቢ ደጋግ ልቦች ከመልካም እጆች ተጣምረው መላ መፍትሄ ሲያበጁ ቆይተዋል::

ዛሬም በዚህ መሰሉ ሻካራ መንገድ የሚያልፉ፣ የኑሮ ጫናቻውን፣ የሕይወት ስብራታቸውን የሚጠግኑላቸው ርህሩህ ልቦች ከጎናቸው ይቆማሉ:: አሁንም ጊቢው በኑሮ ለተገፉ፣ በሕይወት ለተከፉ ብዙሃን ክፍት ውሎ ያድራል::

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዙፋን ምትኩ ካለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት በላይ የበርካቶችን ነፍስ ከችግር ለመታደግ ስትታትር ቆይታለች:: እነዚህ ዓመታት በእሷና በድርጅቱ ሠራተኞች በውጤትና ፈናዎች የታለፉ ፣ በአይረሴ ትዝታና ታሪኮች የሚታወሱ ናቸው::

በግቢው ያለፉ እውነታዎችን ጠልቆ ለማውሳት የሙዳይን ጠንካራ ክዳን መክፈት ያሻል:: ሙዳዩ በውስጡ እንደአለላው ቀለም ደምቀው የታተሙ ግዙፍ ታሪኮችን ሰንቋል:: ይህ የተዘነቀ ገበታ ብዙዎች ኖረው ያለፉባቸው፣ የሕይወት ማስታወሻን እየጠቆመ ፣ እንደጥላ አልፈው ያላለፉ እውነታዎችን፣ የማንነት ታሪኮችን እንዲህ ያስታውሳል::

ሙዳይ ሲከፈት …

የዕለቱን ቆይታ በሙዳይ ጊቢ ለማድረግ ከጊቢው የደረስኩት ገና በማለዳው ነው:: በሥፍራው ያሉ ሠራተኞች ዛሬም እንደ ወትሮው ከሥራ ላይ ናቸው:: መለስ ብዬ ዙሪያ ገባውን ቃኘሁ:: ሁሉም በያዘው ተግባር ላይ አተኩሯል:: ለቀጠሮዬ በሰአቱ ከቢሮው ያገኘሁት የሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ታደለ አየለ ካለፉት የጊቢው ታሪኮች መሀል ጥቂቱን እየመዘዘ ያጫውተኝ ይዟል::

አንገት ደፊው ልጅ …

የባልና ሚስቱ ሰላም ማጣት ለኑሯቸው አልበጀም:: ንፋስ የገባው ትዳር ከታመመ ቆይቷል:: በውይይትና በሽምግልና ያልዳነው ጥምረት ፍቺ ተበይኖበት ከውሳኔ ደርሷል:: ባልና ሚስቱ ሰማንያ ቀደው፣ ንብረት ተካፍለዋል:: ከዚህ በኋላ ‹‹የእኛ›› የሚያስብል ጥምር ሕይወት የላቸውም::

የጋራ ልጃቸው ገና ተማሪ ነው:: በዚህ ዕድሜው የእናት አባቱ መለያየት፣ የቤተሰቡ መፍረስ ይጎዳዋል:: የሁለቱ አንድነት ለእሱ በሰላም ማደግ ቢበጅም ይህ መሆን አልቻለም:: ጥንዶቹ በአብሮነት መቀጠል ባይሹ መለያየት፣ መፋታት ምርጫቸው ሆኗል::

ከፍቺው ማግስት አባቱ ዘንድ እንዲቆይ የተወሰነበት ልጅ እናቱን ሸኝቶ ከአባቱ ጋር በቤት ቀርቷል:: እናት ልጇን ለወላጁ አስረክባ የራሷን ሕይወት ይዛለች:: አሁን ከጣራው ስር አባትና ልጅ በአብሮነት ሊኖሩ ግድ ብሏል:: አባት ከሥራው፣ ትንሹ ልጅ ከትምህርትቤት ይውላሉ::

አባትዬው ሥራ ውሎ ቤት ሲገባ ትንሹ ልጅ ይረበሻል:: ሁሌም በስካር የሚናውዘው አባወራ ለልጁ ተመችቶ አያውቅም:: ቤት በገባ ቁጥር ያንገላታዋል :: ያስፈራራዋል:: ይህ ልምዱ ስቃይ የሆነበት ታዳጊ ሁሌም ኀዘንተኛ ነው:: ፊቱ ፈገግታ የለውም:: በትካዜ፣ በዝምታ አንገቱን ደፍቶ ይውላል::

ትንሹ ተማሪ ቤት ሲገባ እንደልጅ የሚያይ፣ የሚያጎርሰው የለም:: የሰካራም አባቱ ግድ ማጣት ከርኃብ ቢጥለው ከሙዳይ ጊቢ እየዋለ ይመገባል:: በሙዳይ ገበታ እንደ እሱ ኑሮ የከበዳቸው ፣ ችግር ያንገላታቸው ወገኖች በየቀኑ በልተው፣ ጠጥተው ያድራሉ::

ታዳጊው ትምህርት ቤት የቅርብ ባልንጀራ ይሉት የለውም:: እንደ እኩዮቹ፣ መጫወት፣ መዝለል፣ መሳቅን አያውቅም:: ዝምታው የሚያስፈራቸው ጓደኞቹ ከእሱ መቅረብን አይሹም:: ዝም ሲል ፣ ዝም ይሉታል:: ሲሸሻቸው ይርቁታል::

የልጁ ዝምታ ፣ የሚያሳስባቸው የሙዳይ ቤተሰቦች ዘወትር ባህሪዩን እያጤኑት ነው :: ልጁ ከማንም አይቀርብም :: ማንም በተለየ እንዲጠጋው፣ እንዲያወራው አይፈልግም:: ከጊቢው ሲደርስ የቀረበውን ተመግቦ ይወጣል:: ማግስቱን ሲመለስ እንደትናንቱ በዝምታ ተውጦ ነው:: ዘወትር በትካዜ ተቀምጦ በኀዘን አንገቱን ይደፋል::

አንድ ቀን ወይዘሮ ሙዳይ ትንሹን ልጅ በፍቅር ቀርባ አናገረችው:: ዝምታው ያስጨንቃል፣ ትካዜው ያሳስባል:: ሙዳይ ይህ እውነት ያለምክንያት እንዳልመጣ ገብቷታል:: እንደእናት እያዋየች፣ እንደሀኪም መረመረችረው:: ትካዜ ኀዘኑን መዝና፣ ስለምን? ስትል ጠየቀችው::

ልጁ ለሙዳይ የውስጡን ችግር ፣ የልቡን ኀዘን ለመንገር አልዘገየም:: ቢጨነቅም፣ ቢፈራም ፣ ዕንባ እያነቀው የማይታመነውን እውነታ ዘረገፈላት::

ትንሹ ልጅ ከእናቱ ከተለየ ወዲህ የአባቱ ብቸኛ ልጅ ሆኖ ጊዜያትን ቆጥሯል:: እነዚህ ጊዜያት ለዚህ ምስኪን ልጅ የጨለማ ሕይወት ያወረሱ ናቸው:: ለእሱ እያንዳንዱ ለሊት እጅግ ከባድና አሰቃቂ ነው:: ሰካራም አባቱ አምሽቶ በገባ ቁጥር እያሰቃየ ግብረሰዶም ይፈጽምበታል:: ሲነጋ ምንም እንዳልፈጸመ ደረቱን ነፍቶ ወደ ሥራው ይሄዳል::

ትንሹ ልጅ ትምህርቤት ሲሄድ ያለፈውን ምሽት እያሰበ ፣ በሆነበት ሁሉ እየተከዘ ነው:: የአባቱ ክፉ ድርጊት ፊቱ በዞረ ቁጥር ውስጡ ይጨነቃል፣ ሰውን ይሸሻል ፣ ራሱን ከእኩዮቹ አርቆ አንገት ደፍቶ ይውላል:: ሙዳይ ጊቢ ሊመገብ ሲመጣ ከማንም አይቀርብም::

ያለፉት ጊዜያት ለትንሹ ልጅ ጥርሳማ፣ እሾሀማ ነበሩ:: የጀንበሯ መጥለቅ ፣ የምሽቱ መድረሰ በእጅጉ ያስፈራዋል:: አባትዬው ትናንት በፈጸመው ድርጊት ተፀፅቶ አያውቅም:: አምሽቶ በገባ ቁጥር በገዛ ልጁ ላይ ደጋግሞ ግብረሰዶም ይፈጽማል:: ልበ ሰባራው ታዳጊ በአባቱ ድርጊት ተሳቆ ይውላል:: የውስጡን ቁስል ፣ የቤቱን ችግር ቀርቦ የሚያዋየው የለም:: በዝምታ፣ በመገለል፣ በብቸኝነት ራሱን ደፍቶ ይውላል::

ወይዘሮ ሙዳይ ይህን እውነት የሰማችው በታላቅ ድንጋጤና ኀዘን ነበር:: አባት በልጁ ላይ የፈጸመው ድርጊት ፈጽሞ ያልተለመደና ለጆሮ የሚከብድ ነው:: አሁን ለትንሹ ልጅ አስቸኳይ መፍትሄ ያሻል:: የመጀመሪያው ርምጃ ልጁ ወደቤቱ እንዳይሄድና በሙዳይ ጊቢ እንዲቆይ ማድረግ ሆኗል::

ትንሹ ልጅ በጊቢው እንዲቆይ ሲወሰን የተናገረው እውነት በሚስጥር እንዲጠበቅ ተደርጓል:: አባት የፈጸመው ድርጊት እንደወጣበት ካወቀ በልጁ ላይ ጥቃት ሊያደርስ እንደሚችል ተገምቷል:: የታቀደው እንደታሰበው ሆኖ በደለኛው ልጅ ሰላማዊ የዕንቅልፍ ለሊቶችን በጊግቢው አሳለፈ:: ውሎ አድሮም የሥነልቦና ባለሙያዎችን ድጋፍ አገኘ:: ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አልታለፈም:: በደል የፈጸመበት ወላጅ አባቱ በሕግ እንዲጠየቅ ሆነ::

እነሆ ! ይህ ታሪክ ካለፈ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል :: ዛሬ የትናንቱ አንገት ደፊ ልጅ የልብ ስብራቱ ተጠግኖ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል:: በሙዳይ በጎ አድራጎት ጊቢ ከሚኖሩ ጠንካራ ቤተሰቦች መሃልም አንደኛው ነው::

በዚህ ልጅ ውስጠት የትናንቱ እሳት ፈጽሞ አይዳፈን ይሆናል:: የነገው ተስፋ ግን በእጁ ላይ እንደተቀመጠ ነው:: ያለፈው ጨለማ በወደፊት ጥረቱ ብሩህ ሆኖ ይደምቃል :: ይህ ይሆን ዘንድ የሙዳይ ጊቢ መላው ቤተሰቦች ሁሌም ከጎኑ እንደቆሙ ናቸው::

ከአቶ ታደለ ጋር ውይይቴን ቀጥያለሁ:: ታደለ አሁንም የሙዳይን ሰፊ ክዳን ከፍቶ የጊቢውን እውነታ እያሳየኝ ነው:: ባለፉት ዓመታት በሙዳይ አጸድ ፣ የተሻገሩ አሳዛኝና አስገራሚ ታሪኮች ፣ ያልፉ የማይመስሉ እውነታዎች በታሪክ መዝገብ በጉልህ ሰፍረዋል :: ዛሬን በምክንያት ሊኖሩት እስትንፋሳቸው የቀጠለ ፣ ነገን ለማየት ብሩህ ተስፋ ውስጣቸው የታሰረ በርካታ ነፍሶች በሙዳይ ጊቢ የግል ሚስጥርና እውነታን እንደያዙ መኖርን ቀጥለዋል::

ከአፍ ያመለጠች ጥሬ …

ገና በጠዋቱ እናት አባቷን በሞት ያጣችው ብላቴና ዕጣ ፈንታዋ ከአያቶቿ እጅ ወድቋል:: ትንሸዋ ልጅ በዕድሜ ከፍ ማለት ስትይዝ ከሁሉም ተግባባች:: ያየችውን የምትቅርብ ፣ የቀረበችውን የምትወድ ሆነች:: ትኩረት ያጣችው ልጅ ከቤት መውጣቷን እንጂ መዋያ ሥፍራዋን የሚጠይቃት የለም:: የትም ውላ፣ ተጫውታ ትመጣለች::

አያቶቿ አቅመ ደካማ ናቸው:: የእሷን በቅርብ መኖር እንጂ መግቢያ መውጫዋን አይጠይቁም:: በቤቱ ሌሎች ቢኖሩም እሷን እንደልጅ የሚያስብ፣ የሚያስታውሳት የለም:: አምሽታ ስትገባ እንደእናት የሚፈልጋት፣ እንደአባት የሚቆጣ፣ የሚቆነጥጣት ታዛቢ ኖሮ አያውቅም::

ገና ስድስተኛ ዓመቷን የተሻገረችው ህጻን ጠዋት ወጥታ ምሽቱን ትመለሳለች:: ማለዳ ከቤት ስትወጣ የእሷን መድረስ በጉጉት የሚጠብቁ ዓይኖች በርቀት ይቀበሏታል:: ውላ ስትገባ እንደተለመደው ነው:: ከነማን እንደነበረች የሚጠይቃት የለም:: እሷ ግን ለሚቀርቧት ጥቂት ሰዎች ውሎዋን መናገር ጀምራለች::

ትንሽዬዋ ልጅ ከቤት በወጣች ቁጥር ጎረምሶች ያገኝዋታል :: ባገኝዋት ጊዜ ልጅነቷ አያሳዝናችውም:: ወላጅ አልባ መሆኗ፣ ሰብሳቢ ማጣቷ ግድ አይሰጣቸውም:: እጃቸው ስትገባ ህጻንነቷን ይረሳሉ:: ሴት መሆኗን ብቻ ያስባሉ:: ሁሌም ያሻችውን ለማድረግ ፈጣን ናቸው:: ጎረምሶቹ ድርጊቱን ሲፈጽሙ መረጃን አይተውም:: በየቀኑ ያሻቸውን ሲፈጽሙ በድብቅ ነው::

ውሎ አድሮ ህጻኗ ለሌሎች ሰዎች የሆነባትን ሁሉ መንገር ጀመረች:: ሁኔታውን የሰማው የሙዳይ ድርጅት ዝም አላለም:: ተጠቂዋን ህክምና አድርሶ ለሚመለከታቸው የሕግ ክፍሎች ጉዳዩን አሳወቀ ::

በወቅቱ ጎረምሶቹ እነማን እንደሆኑ አልተለዩም:: ትንሸዋ ልጅ የበደሏትን፣ ደጋግመው የደፈሯትን ወጣቶች በስም መጥራት ፣ በአካል ማወቅ አልሆነላትም:: እንደዋዛ ከእጅ ወጥታ የትም ስትውል የነበረችው ህጻን በትኩረት ማጣት ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች::

ይህን እውነት መርምሮ የደረሰበት የሙዳይ ድርጅት የልጅቷ ሕይወት በነበረበት እንዲቀጥል አልወደደም :: ተበዳይዋን ከአሳዳጊዎቿ ተረክቦ በማዕከሉ መልካም ኑሮ፣ አዲስ ሕይወት፣ እንዲኖራት ዕድል ችሯታል::

እነዚህን ህጻናት የመሰሉ በርካታ ወገኖች በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ውስጥ ሕይወትን እንዲህ ቀጥለዋል:: በዚህ ሥፍራ ያለፈ በደል ተረስቶ አዲስ የኑሮ መስመር ፣ ሌላ የሕይወት ገጽ ይገለጣል:: ሁሌም ጥሩ ህሊና ፣ መልካም ልቦችና ፣ ቸር እጆች በእነዚህ በደለኞች ዙሪያ ሲሆኑ ሰፊ ትርጉም አላቸው:: ዕንባን ሲያብሱ ፣ ታሪክን ሲቀይሩ ፣ ተስፋን ሲያጭሩ መቼም ‹‹ደከመኝ፣ ሰለቸኝ›› አይሉምና::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You