“ሌሎች ሀገራትን በመለመንና ርዳታ በመጠየቅ መኖር ኢትዮጵያን አይመጥናትም” – ቄስ ቶሎሳ ጉዲና(ዶ/ር) በአትላንታ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና መጋቢ

የትውልድ ሥፍራቸው ምዕራብ ወለጋ ዞን ኢናንጎ ወረዳ ደንጎሮ ዲሲ ከተማ ሲሆን፣ እድገታቸው ደግሞ ባቦ ጮንጌ ቀበሌ (በድሮ አወሣሰን) ውስጥ ነው – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ቄስ ቶሎሳ ጉዲና (ዶ/ር)፡፡ ቄስ ቶሎሳ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በቦጂ ድርመጂ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ደግሞ በቢሾፍቱ ወንጌላዊት ኮሌጅ ተብሎ በሚጠራው ውስጥ ነው፡፡

እንግዳችን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም የመንግሥት ሥራ ያዙ፤ ሥራው መረጃ መሰብሰብ ሲሆን፣ ለአራት ዓመት ያህል ከሠሩ በኋላ ለቅቀው በመምህርነት ተቀጠሩ፡፡ ይሁንና በመምህርነቱ ብዙም ሳይቆዩ ወደመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ ገቡ፡፡ በዚያም ለአራት ዓመት ያህልም የነገረ መለኮት (Theology) ትምህርታቸውን ተከታተሉ፡፡ እናዳጠናቀቁም ያቀኑት ወደባህር ማዶ ሲሆን፣ መዳረሻቸውን ያደረጉትም ስዊድን ሀገር ነው፡፡

ወደስዊድን ያቀኑበት ምክንያት ለትምህርት ሲሆን፣ የኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲን (Uppsala University) የተቀላቀሉትም ወዲያውኑ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲው ነገረ መለኮት (Theology) አጠኑ፡፡ ቅስናን ተቀብለው በዚያው በስዊድን ለሁለት ዓመት ሠሩ፡፡ በነበራቸው ቆይታም ሀገሩን በጣም ወደዱት፡፡ በዚያም ማገልገል ጀመሩ፡፡

በስዊዲን ጥቂት እንደቆዩም ጉዟቸውን በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው ካሊፎርያ አደረጉ፡፡ በዚያም ፉለር ሥነ መለኮታዊ ሴሚናሪ (Fuller Theological Seminary) ሚሲዮሎጂ (Missiology) የሚባል የቤተክርስቲያን ሚሽን ጥናት የሚመለከት ማስተርስ ኦፍ አርትስ በሚባል ላይ ሠሩ፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውንም እዚያው ሠሩ፡፡ እኤአ እስከ 1986 ድረስም በካሊፎርኒያ ቆዩ፡፡ የካሊፎርኒያ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ አትላንታ ያቀኑ ሲሆን፣ እኤአ ከ1986 ጀምሮ በዚያው በአሜሪካ አትላንታ ኑሯቸውን አደረጉ፡፡

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ከሀገር ከወጡ አራት አስርት ዓመት ሊሞላቸው የቀረው የአንድ ዓመት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ወደእናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ቢያንስ በዓመት አራቴ ለአገልግሎት ይመጣሉ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የጀመሩት አንድ ሥራ ያላቸው ሲሆን፣ ሥራውንም ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአትላንታ በምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በዋና መጋቢነት በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የትናንቱን ችግር ለመፍታት እርቅና ውይይት ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው? ይህን ከኃይማኖታዊ እሴት አኳያ እና ከማኅበረሰብ ባህል አኳያ እንዴት ይገልጹታል?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር):- እንደ አንድ ሕዝብ በእውነት እንታረቅ፤ እንፈወስ፤ እንያያዝ፤ በአንድ ላይ እንቁም ከተባለ ተቀራርቦ መወያየትና መመካከር የግድ የሚለን ጉዳይ ነው:: የችግራችንን ምንጭ በጋራ ማወቅና በጋራ ማስወገድ እጅግ ወሳኝ ነው::

ተቀራርቦ የማይወያይና የማይመካከር ሕዝብ፣ የማይተዋወቅና ከሩቁ የሚጣላ፣ በግል ፍላጎትና ስግብግብነት የሚነዳ፣ ለእውነትና ለአንድነት ቦታ የሌለው፣ የዛሬ እንጂ የነገ የማይታየው ራሱን በውስን ነገር ውስጥ ያጠረ ነው:: ስለሆነም ከዚህ ውስንነት ውስጥ በመውጣት በሀገር ደረጃ ቀርቶ ከጎረቤት ጀምሮ ተቀራርቦ መጠያየቅ፣ መወያየትና መመካከር ለምድራችን ችግር ትልቅ መፍትሔ ነው::

በኢትዮጵያ አለን የምንል ኃይማኖቶች በሙሉ የራሳችንን የውስጥ ችግራችንን አስወግደን በሀገሪቱ አንድነትና ሕብረትን ማጉላት ይጠበቅብናል:: ያንን ማድረግ ካልቻልን ራሳችን ሸክም ነንና እምነታችን መመርመር አለበት:: ዛሬ ለምድራችን መፍትሔ የኃይማኖትንም ሆነ የብሔርን ድንበር አልፈን መቀባበል መወያየት፣ ሕዝቡንም ወደ አንድ መወያያ መድረክ ማምጣት እጅግ ወሳኝ ነውና ይታሰብበት እላለሁ::

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ከሰላም እጦት መውጣት ያልቻልነው ለምንድን ነው? ከኋላ ቀርነታችን ጀርባ ያለው እውነታስ ምንድን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- ከሰላም እጦት መውጣት ያልቻልነው ሁሉ ነገራችን በግል እና በብሔር ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሀገር ተኮር የሆነ ፍላጎትና ርዕይ ጎድሎናል፤ ስለዚህም የሰላም እጦት ችግር አብሮን የዘለቀው ለዚህ ነው:: የርዕያችን አድማስ እጅግ ውስን ነው፤ ሁሉም በዕለታዊ ስሜቱ ተጠምዶ ለሌላው ላስብ፣ ለሌላው ልኑር የሚል ጽኑ ፍላጎት በውስጣችን ወይም በመካከላችን ስለሌለ ነው::

የእግዚአብሔር ቃል ‘ሰላም ሕይወቱን የማይገዛው ግለሰብ ሆነ ሕዝብ ሰላም ምን እንደሆነ አያውቅም::’ ይላል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ቁጥር 27 ላይ “ሰላም እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” ሲል ስለሰላም ያስቀምጣል:: ዓለም የሚሰጠው ጊዜያዊና ውጪያዊ ሰላም አለ፤ እውነተኛ ሰላም ግን ፈጣሪ የሚሰጠው፣ ሁሉን ከጥላቻ፣ ከንቀት፣ ከዘረኝነት የሚታደግ፣ እውነተኛና የሚያስተማምን አንድነት የሚያመጣ ነው::

ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ በእውነት ተያይዞ በሰላም ይኖር ዘንድ ወደፈጣሪው መመለስ አለበት:: ያለበለዚያ በምድረበዳ ውሃ ፍለጋ በከንቱ እንደሚንከራተት ማንነቱን እንደማያውቅ እንስሳ ይሆናል::

ከኋላቀርነታችን ጀርባ ያለው እውነታ አለመሠልጠን፣ አለመቀባበል፤ አለመኖር፣ አለመከባበር መጥፋት ነው:: አብሮነት መሸርሸሩና በጋራ ለመሥራት አለመፈልጉ ያመጣው ችግር ነው፤ ውግንናችንን ለሀገራችን ሳይሆን ለራሳችንና ለብሔራችን ስለምናስቀድም ኋላቀርነት ይፈታተነናል:: የሀገር የሚል እምነት ወይም አቋም የለንም::

ለዚህ መፍትሔው ማንም ከቋንቋው፣ ከብሔሩ፣ ከማንነቱ፣ ከኃይማኖቱ ከጾታው ወደኋላ እንዳይቀር ወስኖ ተያይዞ የዘመኑን ፈተና በጋራ መመከት መቻል ነው:: ወደ አንድነት ካልመጣን በምንም አይነት ለዘመናት ከሰጠምንበት ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ድህነት፣ መለያየት መውጣት አንችልም:: ስለሆነም ለራሳችንም ለተተኪ ትውልድም ለሀገራችንም ሲባል እንቀባበል፣ እንያያዝ፤ አብረን እንቁም፤ አብረን ለመቆም እንደጋገፍ እላለሁ::

አዲስ ዘመን፡- ዛሬ ስለለውጥ እና ብልጽግና ስናወራ ምን ላይ ቆመን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- ዛሬ ስለለውጥና ብልጽግና የምናወራው በከንቱ አይደለም:: በዘመናችን እውነተኛ ለውጥና እውነተኛ ብልጽግና ስለሚቻል ነው:: እኔ የማወራው በዘመናችን እጅግ እየባሰ በመጣው በማታለል፣ በማጭበርበር፣ በጉቦ፣ በሙስና ስለሚመጣው ጊዜያዊ እና የግለሰብ ብልጽግና ሳይሆን ይልቁንስ ሁሉን ያካተተ የትኛውንም ብሔሰረብ ወደኋላ የማያስቀር በሀገር ደረጃ ስለሚቻል እውነተኛ ብልጽግና ነው::

የዚህ አይነቱ ብልጽግና አንድነትን፣ ሰላምን፣ ትዕግስትን፣ መግባባትንና መደጋገፍን ለአንድ ዓላማ ተግቶ መሰለፍንና መሥራትን ይጠይቃል:: ስለሆነም በዚህ እምነት ላይ ቆመን ብንቀላቀል፣ ብንወያይና ብንመካከር መጥፎ የሆነው ልዩነታችንን ብናስወግድ በሁሉ ነገር የተባረከች ምድር አለችንና በእርግጥ ይቻላል፤ እንበለጽግማለን ብዬ አምናለሁ፤ ሆኖም ለብልጽግና የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን::

አዲስ ዘመን፡- የተጀመሩ ለውጦችን ለማስቀጠል እንደ ትልቅ ሀገርነታችን ትልቅ እሴት ሆኖ መበረታታት ያለበት ምንድን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- ትልቅ እሴት ሆኖ መበረታታት ያለበት መተዋወቅ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ትጋት ሲሆን፣ የማይረባ የዘረኞችና የጽንፈኞች ጫጫታን ማስወገድ ደግሞ ያስፈልጋል:: በሁሉም መንገድ በትምህርት በልማት በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ጤናማ ወድድር ላይ ማተኮርና መሳተፍ ወሳኝ ነው::

ትውልዱ ከመንደርና ከክልል ውስን ፖለቲካና አስተሳሰብ ወጥቶ አድማሱን በዓለም ደረጃ ማስፋፋት ይጠበቅበታል:: ቴክኖሎጂ እያመጣ ያለውን ለውጥና ዓለምአቀፋዊነት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል:: ይህ መበረታታትና መደገፍ ያለበት ዘመኑ እያመጣ ያለ ኃላፊነት እና ግዴታ ነው እላለሁ::

አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ ትውልዱ የሚያዳምጠው መንፈሳዊ አባትም ሆነ የሀገር ሽማግሌ እያጣ ያለበት ጊዜ ነው፤ ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡– ለዚህ ተጠያቂው በምድሯ ያሉ ኃይማኖቶች ናቸው:: ማንኛውም ኃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችንም ሆነ አስታራቂ የሀገር ሽማግሌዎችን የማፍራት ኃላፊነት አለበት ብዬ አምናለሁ:: ባለፉት ዘመናት በትምህርት፣ በማስተዋል፣ በእውቀት ማደግና ማሳደግ በምድሪቱ አጥረት ነበረ:: ይህም ደግሞ የራሱን ሚና ተጫውቷል ብዬ አስባለሁ:: ስለሆንም ማንም በማንም ላይ ጣቱን መቀሰር አቁሞ የእኔ ሚና ለሕዝቤ እና ለሀገሬ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅና ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ባይ ነኝ::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከልመና መውጣት አለባት ብሎ መንግሥት ግብርናን መሠረት አድርጎ በመሥራት ላይ ነው፤ በርዳታ መኖር ደግሞ ኢትዮጵያን እንደማይመጥናት ይታመናል፤ ከዚህ አንጻር ያልዎ አመለካከትና መፍትሔ ምንድን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- ለአንድ ሀገር ሕልውና እና እድገት ከልመና ወጥቶ ራስን መቻል ምንም ጥያቄ የለውም:: ለዚህ ደግሞ ግብርና ወሳኝ ነው:: እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነተት የተባረከና ለም መሬትና ሀገር እያለን ለልመና እና ለርዳታ ባህርን አቋርጦ መሔድ እጅግ የሚያሳፍር ነው:: ስለሆነም መንግሥት ለግብርና ልማት ቆራጥ ርምጃ መውሰዱ ትልቅ ማስተዋልና መፍትሔ እንደሆነ በሙሉ ልቤ አምናለሁ::

ሌሎች ሀገራትን በመለመንና ርዳታ በመጠየቅ መኖር ኢትዮጵያን አይመጥናትም:: ስለዚህ መፍትሔው የእኔ የሚል ብሔርና ክልል ተኮር አስተሳብ ከኢትዮጵያ ምድር ማስወገድ የግድ ነው:: በምዕራብ ሆነ በምስራቅ፣ በሰሜን ሆነ በደቡብ ያሉን ለም መሬቶች ያለገደብ ለሀገሪቱ ጥቅምና ኩራት መልማት አለባቸው:: ለዚህ ደግሞ ሰላም፣ አንድነት፣ መቀባበልና መከባበር ወሳኝ ስለሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የድርሻውን መወጣት አለበት:: በእኔ በኩል ቢያንስ ቢያንስ ይህ ለመፍትሔው ትንሽ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ::

አዲስ ዘመን፡- በብዙዎች ዘንድ ሥራ መናቅ ከመስተዋሉ የተነሳ ጊዜያችንን የምናባክነው ያለሥራ ነው፤ የሥራ ባህላችንም ገና አልጎለበትም፤ ከዚህ አኳያ እርስዎ ምን ይላሉ?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡– እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን በፈጠረ ጊዜ ያስቀመጣቸው ገነት ውስጥ ነው:: እግዚአብሔር ሥራን ያከብራል:: ሥራ የሰው ልጅ ጤናማ ሕይወት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው:: ሥራ የማይሠራ ሰው በሽተኛ ይሆናል:: ስንፍና ደግሞ በሽተኛ ያደርጋል::

ስለዚህ ሕዝባችን የሥራን ጠቃሚነት፣ የሥራን ኃይልና የስራን ክቡርነትን ማወቅ ይኖርበታል:: ሥራን በትጋት የመወጣት ባህል በምድራችን ቢዳብር፣ ልጆቻችንም ሥለሥራ ባህል ጠንቅቀው ቢያውቁ ካለንበት ስንፍና፣ ድህነት፣ ጉስቁል እና ውርደት እንወጣና ራሳችንን የምንችል ሌሎችንንም የምንረዳ እንሆናለን::

አዲስ ዘመን፡- ወጣቶች ለሀገር ፍቅር ኖሯቸው መሥራት እንዲችሉ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡– በአሁኑ ጊዜ በጣም የሚያሳዝነው አብዛኛው ወጣት ያልሠራውን ሥራ ለማፍረስ ድንጋይ ማንሳቱ ነው:: ድንጋይ ካነሳም ማንሳት ያለበት ለመገንባት እንጂ ለማፍረስ መሆን የለበትም:: ስሜትን ተከትሎ መቆጣትና ዘራፍ ማለት ለኢትዮጵያ ወጣቶች ምንም የማይጠቅምና ፋይዳ የሌለው አካሔድ ነው::

ይህንን እንዲህ ያኛውን ደግሞ እንዲያ አድርጉ ብለው ውጭ ሀገር ቁጭ ብለው አሊያም በሀገር ውስጥ ተቀምጠው አፍላ ወጣቶችን የሚገፋፉና የሚያደፋፍሩ ትውልድ ላይ የፈረዱ ወንጀለኞች ናቸው:: እንዲሁ መማርና መሥራትን ወደጎን አድርገው ጫካ በመግባት ሰላማዊውን ሰው ሰላም የሚያሳጡና የሚዘርፉ ጥይታቸው አንድ ቀን የሚያልቅ መሆኑን እንዳይዘነጉ::

ምንም ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ የሚያልፍላት መሆኑ ነው:: ኢትዮጵያ በሚያልፍላት ጊዜ ለሰነፍ ተማሪዎችና ለሰነፍ ወጣቶች ቦታ አይኖርም:: ከዚህ በኋላ ደግሞ ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑን ተከትሎ የጥበቃ ሠራተኛ ለመሆን እንኳ ትምህርት እና እውቀት የግድ የሚልበት ጊዜ ነው:: የኢትዮጵያ ወጣቶች ከስንፍና ወጥተው በትምህርት ላይ ማተኮር አለባቸው::

ወጣቶቹ ጥያቄ አለን ይላሉ:: ያልተማረ፤ መልስ ያለው ጥያቄ መጠየቅ አይችልም:: ጥያቄ ለመጠየቅ እንኳን መማር አለብን:: ለዚህም ነው ንዴት፣ ቁጣ የሚያበዛው፤ ንዴትና ቁጣ ደግሞ የሚያመጣው ጥፋት እንጂ ፋይዳ የለውም:: ስለዚህ ልጆቻችን አንደኛ መማር አለባቸው፤ ሁለተኛ የሥራ ፈጣሪዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል:: በመንግሥት ላይ እያጉረመረሙና ዝም ብለው ተቀምጠው መልካም ዘመን እንዲመጣ ከመጠበቅ መልካም ዘመን እንዲመጣ ራሳቸው መፍጠር ይችላሉ:: ከዚህ አንጻር ትምህርት ላይ ማተኮር ግዴታም እጅግ አስፈላጊም ተግባር ነው::

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ እንዴት ያዩታል? የሚቀሩ ነገሮችስ ምንድን ናቸው ይላሉ? የተጀመረው ለውጥ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማን ምን ይጠበቃል?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- በሀገራችን እየተጀመረ ያለው ለውጥ ለእኔ ተዓምር ነው:: በሕይወት ዘመኔ በኢትዮጵያ ምድር መልካም የሆነ ለውጥ እንዲመጣ እንደማንኛውም ሰው ጸልያለሁ፣ በእግዚአብሔር ፊትም ጮክያለሁ፤ ኢትዮጵያን አስባት ብዬ በእግዚአብሔር ፊት ወድቄያለሁ:: አሁንም በመጸለይ ላይም እገኛለሁ:: ነገር ግን እንዲዚህ አይነት ፈጣን የሆነ ለውጥ በኢትዮጵያ ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም::

ባለፈው ከአሜሪካ እንደመጣሁ በአዲስ አበባ አስገራሚ የሆኑ ለውጦችን አስተዋልኩ:: ይህንኑ ተግባር ለመመልከት ከሳር ቤት እስከ አራት ኪሎ ተንቀሳቅሼ ሥራዎቹን ተመለከትኩ፤ ባየሁትም ተደነቅኩም:: እኔ ውጭ ሀገር ወደ 40 ዓመት ያህል ኖሬያለሁ:: በቅርቡ የተሠራው የዓድዋ ሙዚየምን ያህል የሚያስደንቅ ነገር አላየሁም:: ሌላው ቀርቶ መስቀል አደባባይ ስር የተሠራው የተሽከርካሪዎች ማቆሚያም አስገራሚ የሆነ ሥራ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የሳይንስ ሙዚየም በራሱ በዚህ ደረጃ መሠራቱ ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት ወደ አውሮፓ ተሻግራ ከአውሮፓ ደግሞ በአንድ ምሽት ወደ ሌላኛው ዓለም ያለፈች ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል:: ከዚህ የተነሳ በእኔ አተያይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ያለው ትልቅ ትጋት ነው::

ስለዚህ ወሬ ትተን ስለተሠራው እያመሰገንን፤ ያልተሠራውን ደግሞ አለመሠራቱን እያሳወቅን ገንቢ የሆነ ትችት በማቅረብ መሞገት እንጂ ያልተገባ ንግግር ማድረግ ተገቢ አይደለም:: በሀገራችን ዋና መዲና የፈነጠቀው ብርሃን በየክልሉ እየተሰራጨ ስለመሆኑም ይበል የሚያሰኝ ነው:: በቅርቡ በጎርጎራ የተሠራውን ሥራ አይቼ በጣም ስገረመም ነበር:: በሌሎቹም ክልሎች የተሠራው ሥራ በእጅጉ አስገራሚ ነው:: እንዲሁ በሁሉም ቦታዎች ያለው እንቅስቃሴ ትልቅ ነው:: ይህ ትልቅ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ወጣቶችም ሆነ የእያንዳንዳችን ኃላፊት ነው:: ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለምና ከዚህ በኋላ ድንጋይ መወርወር ዘመኑ የማይፈቅድ ነው፡።

ስለዚህ የእኛ ተማሪዎች ማወቅ ያለባቸው መማርን ነው፤ ሰው ካልተማረ ከጨለማ መውጣት አይችልም፤ የትምም መድረስ አይችልም:: ካልተማርንና እውቀት ካልጨበጥን መጨረሻችን የሚሆነው ልመና ነው:: ከዚህ መውጣት አለብን:: እንደሚባለው ኢትዮጵያ ሶስት ሺህ ዘመን ያስቆጠረች ሀገር ናት፤ ይህን ያህል ዘመን ስንኖር ስለምን ለውጥ አላየንም? ስለምን ሥራችን ልመና እና ብድር ሆነ? ሶስት ሺህ ዓመት እርስ በእርስ ተደጋግፈን ቢሆን ኖሮ ዛሬ እጃችንን ለልመና ባልዘረጋን ነበር::

አንዱ የተሻለ ሰርቶ ካየን እርሱን እንዴት ይበልጥ እንደግፈው ሳይሆን እንዴት እንድፈቀው የሚል አስተሳሰብ ካለን ቅንነት የጎደለን ነን:: እኛ በሀገራችን ቅንነትን አስወጥተን ምቀኝነትን ቤት ለእምቦሳ ስላልነው ምድሪቱን የለማኝ እና የጦርነት ምድር አደረግናት:: አሁን የሚያዋጣን የቅንነት ዘመን ነውና በቅንነት እርስ በእርስ በመተባበርና በመከባበር፣ በሰላም መኖር ነው::

አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያና በአማራ ክልል ጥቂት የማይባል ቡድን ከመንግሥት በተቃራኒ በመቆም ሰላም እየታጣ ይገኛል፤ እነዚህ አካላት ወደሰላማዊው ትግል እንዲመጡ ምን መደረግ አለበት?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- አሁን የሚስተዋለው ጦርነት የሚያዋጣ ጦርነት አይደለም፤ ይህ እየተካሔደ ያለው ጦርነት ኢትዮጵያ ከሌላ ሀገር ጋር እካሔደች ያለ ጦርነት አይደለም:: ያለው የብሔር ወይም የግለሰብ ጦርነት ነው ባይ ነኝ:: ጦርነቱ ለምሳሌ በሱማሊያ፣ በኬንያ እንዲሁም በሱዳንና በሌላ ሀገር የተቃጣብን ጦርነት ቢሆን ስለሀገር የሚከፈል መስዋዕት ሊኖር ይችላል::

ይህ አሁን በአንዳንድ ቦታዎች እየተካሄደ ያለ ሰላም መንሳት ግን የራስ ወዳድነት ወይም ደግሞ እኔ ብቻ ካልተሳካልኝ ወይም ካልኖርኩ ብሎ የሚደረግ ነው:: ኑሮው ከእጅ ወደአፍ የሆነውን ሰው መግደልና ሰላም ማሳጣት የትም አያደርስም:: እና ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት፣ ፖለቲካና ብሔር ተኮር ጦርነት፣ ብሔር ተኮር አስተሳሰብና አጀንዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ ወዲህ አይሠራም:: ይህንን ኦሮሞው፣ አማራው ትግሬውም ሆነ ሌላውም እንዲያውቅ አያስፈልጋል::

ስለዚህ አሁን የሚያስፈልገን ብሔር ተኮር ፖለቲካ ሳይሆን ሀገር ተኮር ፖለቲካ ነው:: ብሔር ተኮር አስተሳሰብ ሳይሆን የሚያስፈልገን ሀገር ተኮር አስተሳሰብ ነው:: አሁን የሚያስፈለገን ሀገር ተኮር ርዕይና ሀገር ተኮር አጀንዳ ነው:: ብሔር ተኮር አስተሳሰብ የመንደር አስተሳሰብ ስለሆነ የትም ሊያድርስ አይችልም:: ከዚህ በኋላ ለልጆቻችን የምንሠራው መድረክ በብሔራቸው ዙሪያ የኦሮሞ፤ የአማራ እያሉ ልዩነትን የሚማሩበትን ሳይሆን ከሌሎች የበለጸጉ ሀገራት ጋር የሚወዳደሩበትን መድረክ ነው::

በብሔር ዙሪያ መነታረኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይጠቅምም:: በ21ኛው ክፍለ ዘመን እርስ በእርሳችን እየተጣላንና ጦርነት ውስጥ እየገባን ወደአዝቅት መሄድ የሚያዋጣ አይሆንም:: ከዚህ ይልቅ እርስ በእርስ መደጋገፍና አንዱ ለሌላው መኖር አለብን:: ሰሜኑ ወደ ደቡብ፣ ደቡቡ ወደ ምስራቅ፣ ምስራቁ ወደ ምዕራብ በመሔድ ምድራችንን ማልማት አለብን:: ሰፊ መሬት እና ምቹ የአየር ንብረት አለን:: በዚህ የታደልን ሆነን ሳለ በሥራ ልንገለጽ ሲገባ በሰላም መታጣትና በልመና ልንፈረጅ አይገባም:: የሚያዋጣን እየተወያየን፣ እየተቀባበልን በሰላም መሥራት ነው::

አዲስ ዘመን፡- አባቶቻችንን የመስማት፣ ታላላቆችንን የማክበርና የአብሮነት እሴታችን እየተሸረሸረ መጥቷል፤ ወደቀደመው መከባበር ለመመለስ ምን መሠራት አለበት?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- እኔ ወደኢትዮጵያ የመምጣቴ ዋና ዓላማ ይህን የተሸረሸረውን መልካም እሴት እንዴት መመለስ አለብን የሚለውን አጀንዳ ሰንቄ ነው:: በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ላይ መሥራትን እንደ ዋና ጉዳይ አድርጌ ከያዝኩ ዓመታት ተቆጥረዋል::

አሁን አሁን ኢትዮጵያ ቅንነትን አስወጥታ ምቀኝነትን በማስገባቷ የጦርነትና የውርደት ምድር እየሆነች ነው፤ ስለዚህ ቅንነትን ማስተማር አለብን፤ በአሁኑ ወቅት አንዱ ሌላውን ለመጣል ሲል ተኝቶ ማደር ተስኖታል:: አንዱን ለማደናቀፍ ያለእንቅልፍ ማደር ተለምዷል:: ይህን አይነቱን ምቀኝነት ከትልልቆቹ እንደ እኔ እድሜያቸው ከገፋው ውስጥ ማውጣት ብዙ እድሜም ስለሌላቸው ከንቱ ልፋት ነውና የሚቻል አይመስለኝም:: መርዘኛ የሆነውን ዘረኝነት ያስተማረ አካል ብዙም በሕይወት የመቆየት እድል ስለሌለው ማሸለቡ አይቀሬ ነው::

ነገር ግን ከሕጻናትና ወጣቶች ጀምረን የምንሠራባቸው ከሆነ መልካሙ ጊዜ የማይመጣበት ምክንያት አይኖርም:: ለምሳሌ አንድ ሕጻን ሲያጠፋ “አጠፋሁ፤ ይቅርታ” ብሎ መጠየቅን ማስለመድ አለብን:: በሌላ በኩል ደግሞ መልካም የሆነ ነገር ሲደረግለት “ስለተደረገልኝ አመሰግናለሁ” ብለው ማመስገን እንዲችሉ ማለማመድ ይገባል:: ወላጆች ሲያሳድጓቸው፣ ልብስ ሲያለብሷቸውም ሆነ ምግብ ሲያበሏቸው ማመስገንን መለማመድ አለባቸው::

አስተማሪዎቻቸው ከጨለማ እንዲወጡ የሚያስተምሩ መሆናቸውን ተረድተው ማከበር አለባቸው:: የሀገሪቱ መንግሥት ሀገርን በተቻለው ሁሉ ለመምራት ይለፋልና ማክበርንና መደገፍን ባህላቸው ማድረግ አለባቸው::

ከዚህ በተቃራኒ ሆነው ወጣቱ ያለምንም ምክንያት ቁጭ ብሎ ወላጆቹን፣ የሀገር ሽማግሌውንና ታላላቁን ሲተች ያስገርመኛል:: በምንም ነገር ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሳያበረክቱና የራሳቸው አነስተኛ ጎጆ እንኳን ሳይቀልሱ የተሰራን ትልቅ ህንጻ ለማፍረስ የየራሳቸውን ድንጋይ ሲወረውሩ መስተዋሉ ያለመማርና ያለመሠልጠን ነው እንድል ያስገድደኛል::

ስለዚህ ከዚህ አይነቱ አካሔድ መውጣት እንዲችሉ ልጆቻችንን ግብረ ገብ ማስተማር አለብን:: ስለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ላይ ለመሥራት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የስምምነት ውል መፈራረም የቻልነው:: ይህ ሥራ መምህራንና ተማሪዎችን የሚመለከት በመሆኑ ከሚኒስቴሩ ጋር በመሥራት ላይ እንገኛለን::

በተለይ ትኩረታችን ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የየክልል ተማሪዎች ላይ ነው:: ምንም የማየት እድሉ የሌላቸውን ተማሪዎች ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት አንዱ ሌላውን በማወቅ አብሮነትን እንዲያጎለብቱ ለማስቻል ነው:: እነዚህ ከየክልሉ የተለያየ ቦታ የሚመጡ ተማሪዎች ወዳጆች እንጂ እርስ በእርስ ጠላቶች የሆኑ አይደሉም:: ስለሆነም ከተለያየ አካባቢ የተውጣጡትን ተማሪዎች በአንድ ላይ አስቀምጠን ስለሀገር ፍቅር፣ አንድነትና ክብር በሚል ጽንሰ ሃሳብ ዙሪያ የምናስተምራቸው ይሆናል::

ማስተማር ብቻ ሳይሆን በሀገራቸው እየተከናወነ ስላለው ልማት እናስጎበኛቸዋለን:: ነገ የሚረኩበት የእነርሱ ሀገር ስለመሆኑ አስረግጠን እንገልጽላቸዋለን:: የእነርሱም በመሆኑ የሀገራቸውን ልማት በጥንቃቄ እንዲይዙት እንመክራቸዋለን:: ተግተው እንዲማሩ እናሳስባቸዋለን:: በአሁኑ ወቅት ይህን መሰል ሥራ በመሥራት ላይ ነን::

ይህ ሥራችን ዋና ዓላማው ደግነት፣ ርህራሄና አንድነትን በውድ ሀገራችን ላይ መዝራት እንችላለን በሚል ዙሪያ ያጠነጠነ ነው:: የቅንነትና የታማኝነት ምንነት በሀገር ግንባታ ላይ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ የመተሳሰብንና የአንድነትን ባህል ለማስፈን እየተጋን ነው:: ይህ ጉዳይ የራሱ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑም የብዙዎቹን ድጋፍ እንሻለን::

በቀጣይ የሚደረገውን ሴሚናር ለመከታተል ከየክልሉ የሚመጡ ተማሪዎችም መምህራንም ወደየ አካበባቢያቸው ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ ይፈለጋል:: ወጣቱን ወደአንድነት የምናመጣበት ጊዜ ስለሆነ ለዚህ በጎ ተግባር የየበኩላችንን ብንወጣ መልካም ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- ይህን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ የተነሳሱበት ምክንያት ምንድን ነው?

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡– ጉዳዩ “ቅን ኢትዮጵያ” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ ባለራዕይና መሥራችም ነኝ:: ይህ ሃሳብ ኃይማኖትን፣ ዘርንም ሆነ ፖለቲካን አይመለከትም:: ይህ ሃሳብ የተጀመረው በኢትዮጵያ ውስጥ የመደናነቅ ባህል ቢኖር መልካም ነው ከሚል ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ የመደናነቅ ቀን ቢኖርስ ከሚልም የመነጨ ነው:: ይህን ምንም እንኳ ትክክለኛ የአማርኛ ቃል እስካሁን ባላገኝለትም “የመደናነቅ” የ(appreciation) ቀን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምጣት ያሰብኩት በዓመት አንድ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እንዲደናነቁ በሚል አስቤ ነበር::

ይህን ሃሳብ ይዤ አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ስጀምር መደናነቅ እንደሌለ ተረዳሁ:: በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርንም ከዛሬ አስራ ሶስት ዓመት በፊት ጠይቄ የመደናነቅ ባህል ያለመኖሩንም ተረዳሁ:: የሀገር መሪዎችን መጠየቅ ይሻላል ሲሉኝ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ወደሆኑት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ዘንድ ሔጄ ጠይቅኳቸው፤ እርሳቸው፤ “አዎ! አለ” ሲሉ ዲፕሎማሲያዊ መልስ ሰጡኝ:: ነገሩ ስላላረካኝ ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማምራት ከተለያየ ትምህርት ክፍል ሀገርን በሚመለከት ከሰባት ፕሮፌሰሮች ጋር በመሆን አንድ መድረክ ፈጠርኩ:: ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ጠየቅኩ፤ ምላሻቸውም “የለም” የሚል ነበር::

ምክንያታቸው “ኢትዮጵያ በፊውዳል ሥርዓት ውስጥ ስለነበረች ሥርዓቱ ደግሞ ይህን ባህል ስለማያበረታታ መሆኑን ነገሩን:: ታዲያ እናንተ የሰጣችሁኝን መልስ በአደባባይ ጠቅሼ መጠቀም እችላለሁ? ስል ጠየቅኳቸው:: “አትችልም” አሉኝ:: ለምን? ስላቸው ጥናት ስለሚያስፈልገው ነው አሉኝ::

ከዚያ በኋላ ሰባቱንም ፕሮፌሰሮች ለሁለት ዓመት ምርምር እንዲያደርጉ ጠየቅናቸው:: ለሁለት ዓመት ምርምር አካሂደው ውጤቱን አቀረቡ:: በወቅቱ ለነበሩ የሀገሪቱ ባላሥልጣናትና ለኃይማኖት አባቶች ወረቀት አቀረቡ:: በኢትዮጵያ ውስጥ የመደናነቅ (appreciation) ባህል የለም ወደሚል ድምዳሜ ተመጣ::

ምን እናድርግ በሚል ስንወያይ ከቆየን በኋላ ይህን ንቅናቄ ስያሜውን “ቅን ኢትዮጵያ” እንበለው ተባባልን:: የእኛ እስተሳሰብ የነበረው በብሔራዊ ደረጃ የመደናነቅ (appreciation) ቀን ለማሳወጅ ነው:: ነገር ግን ያልኖረበት ምክንያት በየቦታው ሔጄ ታላላቅ የሆኑ አባቶችን “ለመሆኑ በየቤታችሁ የመደናነቅና የምስጋና ጊዜ አለ? የትዳር አጋራችሁ ጥሩ ምግብ ሲያቀርቡም ሆነ ጥሩ ሲለብሱ ማድነቅና ማመስገን ለምዳችኋል?” ብዬ ስጠይቅ “አይ” ሲሉ መልሰውልኛል:: አለማድነቃቸውም አለመውደዳቸውን እንደማይገልጽና ሙያ በልብ ነው በሚል የያዙት መሆኑን አጫውተውኛል:: ይህ ግን ለእኔ አሳዛኝ ሆኖ ነው የተገነዘብኩት::

ስለዚህ ይህ የመደናነቅ ባህል በእኔ እድሜ ባሉት ዘንድ የሌለ በመሆኑ በዚያ የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉት ላይ ከምደክምና ጊዜዬን ከማጠፋ ወደ ሙዓለ ሕጻናት ሔጄ ልጆችን ማሠልጠን ተመራጭ ነው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ:: ልጆቹ ከዛሬ 15 እና 20 ዓመት በኋላ ልዩ አዕምሮ ይዘው ያድጋሉ:: እርስ በእርስ መከባበር ይችላሉ:: አሁን ያለው ሕዝብ አፉ የተዘጋ ነው::

ስለዚህ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የስምምነት ፊርማ አካሒደን በዓመት አንድ ጊዜ ብሔራዊ የተማሪዎች ቀን እንዲኖርም እያሰብን ነው:: በመጀመሪያ ዓመት የተሠራው ትልቅ ሥራ ነው:: በወቅቱ በየትምህርት ቤቱ ፕላዝማ ቲቪ ይግባ በመባሉ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ተከፍሎ በየትምህርት ቤቶቹ እንዲገባ ተደረገ:: ከአዲስ አበባ ስታዲየም ስናስተላልፍ ጠቅላላ ለሁሉም ተማሪ ይደርስ ነበር:: ይሁንና ኮቪድና የሰሜን ጦርነት መጣ::

እኛ ደግሞ መርሃግብሩን በመስቀል አደባባይ እናደርጋለን ብለን ብናስብም፤ የደህንነት ጉዳይ በሚል በሚሊኒየም አዳራሽ አንድ አስር ሺህ ተማሪዎችን ከአስተማሪዎቻቸውና ወላጆቻቸው ጋር ከየክልሉ ጠርተን በማስተማር እንዲደናቀቁ አደረግን::

በዚህ ዓመት ደግሞ ያሰብነው ተማሪዎች አምጥተን ስለ ሀገር ፍቅርና ሰላም ብናስተምራቸው ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር መሆን ይችላሉ ብለን ነው:: ከተለያየ ክልል ከዘጠነኛ ክፍል 250 ተማሪዎችና 250 መምህራን እንዲመጡ እቅድ ተይዟል:: የቆይታ ጊዜያቸውም ለአምስት ቀን ሲሆን፣ ጠዋት ጠዋት ይማራሉ፤ ከሰዓት ደግሞ የተሠራውን ሥራ ያያሉ:: የሚመጡ ተማሪዎች በዘር፣ በኃይማኖት፣ በጾታ ልዩነት አይደረግባቸውም:: መልሰን የምንልካቸው ከሰነድ ጋር በመሆኑ ሲመለሱ በየትምህርት ቤቱ “ቅን ኢትዮጵያ” ክለብ እንዲመሠርቱ እናደርጋለን::

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ::

ቄስ ቶሎሳ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You