የክረምት ፀጋ

ክረምት ይወዳል..ክረምት የነፍሱ ደስታ ነው:: ሰማይ ሲደማምን ጉም ሲውጠው የቀዬው ትዝታ ይወስደዋል:: አብዛኞቹ የልጅነት ትዝታዎቹ በክረምት የተፈጠሩ ናቸው:: አድጎ እንኳን የክረምት ፀጋ አልሸሸውም:: ትላንትም ዛሬም በክረምት ፀጋ ውስጥ ነው….

እየዘነበ ነው..:: እጆቹን ደረቱ ላይ አጣምሮ እትት ይላል:: በዝናብ ውስጥ ሆኖ እንደ እማማ ተዋበች አረቄ የሚናፍቀው የለም:: ከአንድ ሕንጻ በር ላይ እንደቆመ ከፊት ለፊቱ ጥላ የያዘች አንድ ሴት ተመለከተ:: ሳቀ..ብዙ አይነት ሳቅ:: ምስጋናን..አሜንታን የሚናገር ሳቅ:: ክረምት ሁሌም ለእሱ ፀጋው ነው..በዘነበ ቁጥር ፈጣሪ አብሮ ከዝናቡ ጋር መና የሚጥልለት ይመስለዋል:: የዛሬው የክረምት ፀጋው ከፊት ለፊቱ የምትመጣው ሴት መሰለችው:: ከዝናቡ ለመሸሽ..በጊዜ ወደ ቤቱ ለመድረስ ያለው አማራጭ ሮጦ ወደ እሷ መሄድ ነው::

እሺ ትለኝ ይሆን? በግድም ቢሆን አብሬያት እሄዳለሁ እንጂ ፀጋዬን የትም አልጥልም..እያለ ከራሱ ጋር እያወጋ ተጠጋት:: አለባበሷ በዝናቡ ውስጥ ወንድነቱን ተፈታተነው:: ከዝናቡ ሽሽት ቦርቃቃ ሸሚዙን ወደ አናቱ ስቦ ‹እናት! እባክሽን አስጠልይኝ…› አላት አይኗን በአይኑ እየተማፀነ::

ወደ ጎን አየት አድርጋው በአይኗ ወደ ጃንጥላው እንዲገባ ጋበዘችው::

እትት እያለ አጠገቧ ቆመ..ጃንጥላው ስር:: አጠገቧ ሲቆም መጀመሪያ ያገኘው ሽቶዋን ነበር፡ ከዛ አለባበሷን..ከዛ ቀይ ፍም መሳይ ሰውነቷን:: እንደዛ ቀን በሴት ልጅ ጠረን ተማርኮ አያውቅም:: ጥሩ ይቀባሉ የሚላቸው ኤደንና ሜሪ እንኳን የእሷን ያክል አልጠረኑበትም:: በአለባበሷ የምታስቀናው ቤቲ እንደ እሷ ለብሳ አይቷት አያውቅም:: ዝናብ ብሎ በገባበት ሌላ እንግዳ ስሜት ተጠናወተው:: በሽቶዋ እየታጠነ መሄድ ብቻ አልፈለገም ወሬ መጀመር አለበት:: ይሄን መልካም ዕድል ዝም ብሎ ማሳለፍ አልፈለገም:: የክረምት ፀጋ በሕይወቱ ሁሉም ቦታ መና ሆኖ ይከተለዋል የዛሬው ግን ከሆነው ሁሉ ሌላ ሆነበት::

ማውራት አለበት…ተዋውቆ..ስልኳን ተቀብሎ፣ የሆነ ያልሆነውን ቀባጥሮ የሆነ ነገር መፍጠር አለበት::

‹በጣም ነው የማመሰግነው….:: አላት

‹ምንም አይደል:: ከቬቶቨን ዜማ የላቀ ድምፅ ከአንደበቷ ተሰማ:: እየቆየ የሚሰማ..እየቆየ የሚሞዝቅ ድምፅ::

እዚህ ጋ መዋሸት አለበት..ያገኛትን ሴት ሳይዋሽ ቤቱ ገብቶ አያውቅም:: ለኃጢዓት የሚሆን ብዙ አቅም፣ ብዙ ጉልበት አለው:: ‹መኪናዬ ጋራጅ ገብታ ሰሞኑን ተቸገርኩ:: እንዲህ አላት::

‹አንዳንዴ ያጋጥማል..ሕይወት ሁሌም እንዳሰብናት አትሆንም:: መለሰችለት በቅድሙ ሙዚቃዊ ድምፅ::

ብዙ ሴቶችን የመኪና ስም ጠርቶ አደናብሮ ያውቃል:: ይቺኛዋ ግን ሌላ ሆነችበት:: እስካሁን ፊቷን አላየውም..በአለባበሷና በድምፅዋ እንደተዋጠ ነው::

‹የት ሰፈር ነሽ? አላት ወደ ሚሄድበት መሄዷ እያስገረመው::

‹እዚሁ አካባቢ ነኝ…

‹እዚህ አካባቢ ማለት? አንድ ሰፈር እንዳይሆኑ እየሰጋ::

‹ለጊዜው እዚህ ነኝ.. ሰሞኑን ነው ከለንደን የመጣሁት::

‹ኦ በጣም ደስ ይላል:: እንደዛ ከሆነማ በደንብ መተዋወቅ አለብን:: ለንደን ሁለተኛ ሀገሬ ናት..ብዙ ጊዜ እመላለሳለሁ:: እያወራ አየት አደረጋት:: ከዝናቡ መብረቅ ጋር ተመሳሰለችበት:: ቀይ እንደ ምድጃ እሳት የሚንበለበል ፊት ታየው:: በላቀ ሰማይ ስር የቆመ ይመስለዋል..በማያባራ ሐሴት ውስጥም::

‹ለሥራ ጉዳይ ነው የምትመላለሰው? ጠየቀችው::

‹አዎ! አስመጪ ነኝ..ከሥራ ባለፈ አንዳንድ የቢዝነስ ሚቲንጎችን እዛ ነው የምናደርገው:: የሕይወቱን ትልቁን ውሸት ዋሸ::

‹በጣም ደስ ይላል::

በወሬ መሐል ጎኗን ታከከው..እንደ ረመጥ የሚፋጅ ገላ ወደ ነፍሱ ሰረገ::

‹አንተ እዚህ ሰፈር ነህ?

‹እዚህ የምረዳቸው ድሆች አሉ..እነሱን ጠይቄ ልመለስ እየሄድኩ ነው::

‹ኦ! በጣም ደስ ይላል:: መልካም ሰው ይገዛኛል::

‹ጥሩነት ለራስ ነው:: ደሞ ሁሉም ሰው ሌላው እንዲያገለግል የተፈጠረ ነው:: ይሄን አባባል የት ነበር ያነበበው? ትዝ አለው ታክሲ ውስጥ ነው:: በየንግግሮቹ መሐል የታክሲ ላይ ጽሑፍ ሳይጠቀም አልፎ አያውቅም:: የታክሲ ላይ ጥቅሶች ሴት በማደናገር ላይ ትልቁን አስተዋፅዖ አድርገውለታል:: ሙቀት ፍለጋ ወደ ዳሌዋ ተሳበ..ነካት:: ነዘረው..ዘላለማዊ ንዝረት:: ገፋው ዝንታለማዊ ግፊት::

እስካሁን አብረው ናቸው…በአንድ መንገድ ወደ አንድ ሰፈር መሄዳቸው እያስገረመው ነው:: ቤቱ ደርሷል..ቤት ከመግባቱ በፊት ስልኳን ተቀብሎ ሊለያት ፈልጓል:: እንዳሰበውም ስልኳን ተቀብሎ ነገ እንደሚገናኙ ነግሯት ተለያዩ:: ዝናቡ አባርቶ ስለነበር ራሱን ችሎ ለመሄድ አልቸገረውም:: በመንገዱ ሁሉ ቀይዋ ሴት ነበረች:: ነገ ደርሶ ዳግም እስኪያገኛት ድረስ ተናወጠ:: የክረምት በረከት ሁሌም እንዳረሰረሰው ነው:: በልጅነቱ ውስጥ የተጻፉ በርካታ ክረምት ወለድ ትዝታዎች አሉ:: ከሁሉም ዛሬ ይበልጣል..:: በባለ ጃንጥላዋ ሴት ድምፅና ውበት እየተገፋ ከሚያውቀው አንድ ጠጅ ቤት ደረሰ:: ከእማማ ተዋቡ ጠጅ ቤት:: ማታ ሲሆን እዚች ቤት ጠፍቶ አያውቅም:: ጀምበር ወደ ምዕራብ ስታገድም መገኛው ይሄ ቤት ነው::

ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲል የአከራዩ የጋሽ ፍስሐ ማስጠንቀቂያ ትዝ ስላለው ወደ ቤቱ አመራ:: ጋሽ ፍስሐ ሁሉንም ተከራይ ጠርተው ከሁለት ሰዓት በላይ ማምሸት እንደማይቻል ከመናገራቸው በፊት ከዛ ጠጅ ቤት ታዝሎ ነበር የሚወጣው:: እኩለ ሌሊት ሳይሆን ቤቱ ገብቶ አያውቅም ነበር::

የተከራየበት ግቢ ሲደርስ ከአከራዩ ከጋሽ ፍስሐ ቤት ሞቅ ያለ የሳቅና ጨዋታ ድምፅ ተሰማው:: ወደ ቤቱ ሊገባ ሁለት ርምጃ ሲቀረው የጋሽ ፍስሐን ድምፅ ከኋላው ሰማው::

‹ምን ሆነህ ነው የጠፋህው..ቤትህ ስንት ጊዜ ተመላለስኩ መሰለህ? ጋቢያቸውን ወደ ትከሻቸው እያጣፉ::

‹ያው ሥራ አይደል…እዛው አምሽቼ ገና እየገባሁ ነው:: አላቸው:: በለመደው ውሸት::

‹ና በዚሁ ቤት ግባ..ሁሉም ተከራይ አሉ:: አንተ ብቻ ነው የጠፋህው:: አሉ ቆመው እየጠበኩት::

‹ዛሬ ቀኑ ምንድነው? ወሩን..ዓመቱን አሰበው ፕሮግራም ሊዘጋጅበት የሚችል ምንም የለም:: በቃ እንደለመዱት ወይ ቤት ኪራይ ሊጨምሩብን ነው አሊያም ደግሞ ሁለት ሰዓቱን ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ ሊያደርጉት ነው እያለ በማሰብ ወደ ቤቱ ሊገባ ያለውን ትቶ ተከተላቸው::

እሳቸው ከፊት እሱ ከኋላ እየተከተለ ወደ ቤት ገቡ:: ቤት ሲደርስ በድንጋጤ ክው ነበር ያለው:: መንቀሳቀስ አቅቶት ውሀ ሆነ..:: ቀይዋን ባለጃንጥላዋን ሴት አያት::

‹ይቺ ልጄ ናት..ሰርካለም ትባላለች:: ትላንት ነው ከለንደን የመጣችው:: ተዋወቃት አሉ ወደ ልጃቸው እየጠቆሙ::

በቆመበት ደርቆ ቀረ..

‹ምን ይገትርሃል ና እንጂ:: ጋሽ ፍስሐ ቆጣ አሉ::

ፊቷን ለማየት አቅም አጥቶ ሄዶ በሁለት ጣቱ ሠላም አላት::

‹ትንሳኤ ይባላል:: እንዴት ያለ..ድንቅ አናጢ መሰለሽ:: አረቄ ይወዳል እንጂ ማለፊያ ልጅ ነው:: እዛች ትንሿ ክፍል ነው የሚኖረው..:: አሉ ለልጃቸው እያስተዋወቁት::

ትንሳኤ በተቀመጠበት ላብ አሰመጠው::

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You