የጉለሌው ሰካራም

በ1941 ዓ.ም ነበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው አጭር ልቦለድ የተጻፈው:: ልቦለዱም “የጉለሌው ሰካራም” ነበር:: ደራሲ ተመስገን ገብሬ አስቀድሞ ተነስቶ ጻፈው። በወቅቱም ተአምር አያልቅ…አጃኢብ! ተባለለት። ታሪኩ የአንድ ተራ የጉለሌ ሰካራም ታሪክ ቢመስልም ከባህር ውሃው መሀከል አንባቢውንም እራሱን በመፈለግ ቀዘፋ ውስጥ እንዲንቦራጨቅ አድርጎታል። ደግሞም እንዲህ ዓይነቱ ቅልብጭ ቁልጭ ያለውን ልቦለድ አንብቦ አያውቅምና አዲስ ዓይነት ጥፍጥናም ነበረው።

በየአንባቢው ሁሉ “የጉለሌው ሰካራም!…የጉለሌው ሰካራም!” ተባለ። “የቱ የጉለሌው ሰካራም?” አለ አንዱም። “ ያ ተበጀ ነዋ!” ደግሞ እንደገና “ተበጀስ ማነው?” ይላል ሌላውም። ሁሉም አጠያይቆ የደረሰበት ነገር ቢኖር ተበጀ በጉለሌ ውስጥ የታወቀ ዶሮ ነጋዴና ታዋቂ ሰካራም መሆኑ ነው። ጥያቄም አያልቅ “ተበጀ ዶሮ ነጋዴ?” ኧረ ወዲያ!…

“…የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ ዶሮ ነጋዴው፤ ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል:: የሕይወቱ ታሪክ ፍፁም ገድል ነው:: ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው:: ራሱን ጠጉር ውሃ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም:: ማለዳ አይናገርም:: በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ሲራገም ወይም ሲሳደብ ሲፎክር ወይም ሲያቅራራ ድምፁ ከፈረንጅ ውሻ ድምፅ ይወፍራል:: ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኘው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል:: ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኘው ሁሉ ጋር ማታ ይስቃል:: ቢያውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው” እያለ የሚነግረን እውነታ የተበጀ የብቻው አይደለም። እዚህ ውስጥ የብዙ ሰካራሞች አንድ ዓይነት እውነት አለ:: ተበጀ ግን ከዚህም ሌላ አለው::

“…በፀባዩ ከተባለለት የባሰ ሰካራም ይሁን ወይም የጉለሌ ባህር ዛፍ ውስጥ ወጥቶ እንደ አዲስ እንግዳ ሰው ሆኖ ለአዲስ አበባ ታይቷል:: ከዱሮ የእንጨት ጉምሩክ አጠገብ ወደ ምሥራቅ ሲል ካለው ወንዝ ማዶ ድልድዩን ወደ ምሥራቅ ተሻግሮ መጀመሪያ የሚገኘው አነስተኛ ሳር ክዳን ቤት የተበጀ ቤት ነው።” ይለናል:: ተበጀ ሁሌም ይጠጣል:: ዝም ብሎም እንደጠጣ ነው:: ግን እንደ አብዛኛዎቹ ሰካራሞች የገንዘብ ችግር የለበትም:: እንዲያውም ባለጠጋ ነው ይለናል:: ከምንም በላይ ግን መድፈኛ ሰካራም ነው::

ታዲያ በስካር ውስጥ ብርሌውን ጨብጦ ጠጁን ከማንቃረር፣ መለኪያውን ይዞ አረቄና ውስኪውን ከማንዶቅዶቅ በስተቀር ምንስ ይኖርና? እንል ይሆናል። ብንልም ኩነኔ አይሆንብንም። በሰካራሙ ተበጀ ሕይወት ውስጥ ግን እልፍ ደግነቶችና የፍቅር መስዋዕትነቶች እፊቱ መሳ ለመሳ ቆመው በእንባ ይራጫሉ። “በዚያ በቤቱ በዚያ በጉለሌ በሠፈሩ ኖረ:: እንጨቱን ተሸክሞ አፈሩን ቆፍሮ ቤቱን የሠራው እርሱ ነው:: ዋጋ ከፍሎ አስከድኖታል:: ተበጀን ኩራት ተሰማው:: ቆይቶ ደግሞ አይኖቹ እንባ አዘሉ:: በጉንጩም የእንባ ዘለላ ወረደው:: በግራ እጁ መዳፍ ከጉንጩ የተንከባለለውን እንባ ጨፈለቀው:: …ሊነገር በማይችል ደስታ ልቡ ተለውሳል:: ዝናብ ያባረራቸውም ከቤቱ ጥግ ሊጠለሉ ይችላሉ:: ቤት የእግዚአብሄር ነውና ውሽንፍር እንዳያገኛቸው ከቤት ውስጥ ዝናቡ እስኪያባራ ይቆያሉ” በማለት ነበር ተበጀ ቤቱን በመሥራቱ ደስ ያለው።

“ሰካራም ቤት አይሠራም፤ ቢሠራም….” ቢልም ብሂሉ ተበጀ ግን ቤት ሠራ። በእርግጥ በጊዜ አይገባም ነበር። ሰካራም ሆኖ ሳለ ቤት የመሥራቱ ነገር ጸሀፊው አንዲት የፈለጋት ምልከታ ነበረችው። ሰካራሙን ተበጀን በአልኮል መለኪያው ለክተውት ቢያልፋና ባያውቁት ችግሩ የቀጂው እንጂ የተበጀ አይደለም። እንዴት? ካሉ የተበጀ የሚታየው ስካርና ሰካራምነቱን ይሁን እንጂ እንደሰው አስቦ ሰው ሠብዓዊ በመሆን ማንስ ደርሶበት? የሚወግር ድንጋዩን እንጂ መች ውስጡን ይመለከትና…ሰካራሙ ተበጀ፣ የጉለሌው ሰካራም እራሱን ሲገድል ይኖራል እንጂ ለሰውማ ሟች ነው። ያቺን ደሳሳ ጎጆውን ሲያቆም እንኳን ደስ ያለው ለራሱ አልነበረም። ታዲያ ከሰካራሙ ተበጀ ሌላ በጉለሌ መንደር ውስጥ እንደዚያ ያሰበ ማን ነበር? ማንም። ምግባሩ እንጂ ልቡ የእግዜር ማደሪያ ነበረች።

“የጉለሌው ሰካራም” በሀገራችን የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ አይደለም ብለው ደፍረው የሚናገሩ የሉም። የመጀመሪያውማ እሱው ራሱ ነው በማለት ከነማስረጃው ፈርጠም ብለው የሚመሰክሩለት ግን አያሌ ናቸው። ለአብነትም አስፋው ዳምጤ እና ዘሪሁን አስፋው ተጠቃሽ ነቃሾቹ ናቸው። በዚህም አሉ በዚያ የተመስገን ገብሬ “የጉለሌው ሰካራም” የአጭር ልቦለዶች እንጎቻ ነው። እሱን ያነበበና የተመለከተም ነበር ቀጣዩን የምናብ ምጣድ እያሟሸ ሌላ ሰበከታም የልቦለድ እንጀራ ያበላን። ከቡሀቃው እየተቀዳ ሲጋገር ተሰንብቶ አሁን የአጫጭር ልቦለዶቸ መሶብ ጢም ስላለ እንጎቻውን የዶሮ ፍርፋሪ አናደርገውም። በኩርነቱን ተቀብሎ የሚገባውን ዕውቅና መስጠት እዚያ አካባቢ ለነበሩ ለየትኛዎቹም አጫጭር ልቦለዶች ያለንን ቦታ አያጎድለውም። ለዚህ ታላቅ የሥነ ጽሁፍ ጀብዱ ጸሀፊው ተመስገን ገብሬ ዳጎስ ያለ ክብርን ላቅ ከላቀ ምስጋና ጋር ልንቸረው ግድ ይለናል።

እንግዲህ የጉለሌው ሰካራም ተበጀ እንደሆን ነገረ ሥራው አያልቅም። ጥንባዣም ሌቱም ነግቶ የሚነጋ አይደለም። ቢነጋ እንኳን ለአንድ ግብግብና ትርምስ ነው። ተበጀ የመሰለውንና ውስጡ የሚያዘውን ሕይወት ያለጭንቅ ይኖራል። በእርሱ የሕይወት ጎጆ ዙሪያ ተጠግጥገው በሀሜት ወሬ የሚጨነቁበት የመንደሩ ሰዎች ናቸው። በዕድርና በዕቁቡ ቢሰባሰቡ፣ ቡና አፍልተው ከጎረቤት ቢጠራሩ ያለ ተበጀ የወሬ ቡና ቁርስ ሲኒው አይነሳላቸውም:: ቡናውም አይጠጣላቸውም::

ትናንት፣ ከትናንት በስቲያና ዛሬም ያዩትን የስካር ጀብዱ እየተረኩ ማውካካት ነው። ስለ ስካሩና ሁኔታው የሚናገር ይኑር እንጂ አፉን ከፍቶ የሚያደምጠውስ አሸን ነው። በሰካራሙ ደካማ ጎን ሾልኮ ትኩስ ደሙን እያስመለከተ ቀልደኛና ጨዋታ አዋቂ በመሆን ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚጥረው ሰው ብዙ ነው። እየሰከረ ከሚወድቀው ተበጀ በላይ የተበጀን አወዳደቅ እያሳየ ካዳማዊን በሳቅ ገድሎ አፈሩን በተበጀ ላይ ይመልሰዋል። ተበጀ ምስኪኑ የጉለሌ ሰካራምስ? እሱማ በየሰው ልብና ቤት ውስጥ በቁም ሞቶ በቀልድ አፈር ያለበሱት ከንቱ ነዋሪ ነው::

በሕይወት እየኖረ እንዳለ እንደ አንድ የመንደሩ ነዋሪ ማንም እርሱን ከቁብ ቆጥሮ ለቁም ነገር ባይፈልገውም እርሱ ግን ለአንዲት ነብሱም ሳይራራ ፈጽሞ ያልጠበቁትን ታላቅ ግብር ፈጽሞ ይገኛል። ግን ይኼም ቢሆን ለማንም ከቁም ነገር የሚቆጠርለት ነገር አይደለም። እጁ አመድ አፋሽ ሥራውም ሳቅን ቀስቃሽ የፌዝ ጠርሙስ ሆኖ ይቀራል። እራሱ ወድቆ የሚያጣጥረው ሰው እንኳን፤ ተበጀ እየወደቀ እንዲያስቀው እንጂ ተነስቶ እንዲሸከመው የሚፈልግ አይመስልም። የተበጀ ልብ እንደ ብርሌው ሁሉ አንስተው ባፈረጡት ቁጥር እንክትክቱ የሚወጣ ቢሆን ኖሮ የሚሞተው ገና ያኔ በመጀመሪያ በሰከረበት ዕለት ይሆን ነበር። ግን እርሱም የዋዛ ሰካራም አይደለም። ልቡን እንጂ ጆሮውን አይከፍትላቸውም። እንዲሁ እንደልቡ ሆኖ እየኖረ ስሙ ከሰፈር አምልጦ መላውን አዲስ አበባን አካለላት። በየትኛውም ሰፈር ከማንም በላይ የጉለሌው ሰካራም ታዋቂ ነው። ሰው እንዴትስ በስካር እንዲህ ዝነኛ ይሆናል? ሰው በስኬቱ ብቻም ሳይሆን በውድቀቱም ዝነኛ ሟች ለመሆን እንደሚበቃ ይነግረናል። ምክንያቱም ጥሩ ነገሮችን ለመስማትና ለመናገር ከምናሳድደው በላይ ልብና ጆሮዎቻችን በመጥፎ ዜናዎች ፍቅር የተነደፉ በመሆናቸው ነው።

ለማየት የምንፈልገው ተበጀን ሳይሆን የጉለሌውን ሰካራም ስለሆነም ግርድ ማንነቱን ከፍሬው፣ ፍሬውንም ከግርዱ ነጥሎ ለማየትም ሆነ ለመቀበል አይቻለንም። በዚህ ምክንያትም እንደሰው ካለው ማንነትና ተሰጥኦ ቢያንስ አንዱን እንኳን ሳይሰጠንና ሳንቀበለው ደርሶ አፈር ይቀማዋል። “ጉለሌ ተኝቷልና ከዚሁ ከባሕር ዛፍ ሥር ቁጭ ብዬ ብጠጣ የሚታዘበኝ የለም” አለና አሰበ:: እውነቱን ነው:: ጉለሌስ ተኝቶ ነበር ነገር ግን አሁን እርሱ ጠጥቶ የሰከረ እንደሆነ ጉለሌን ሊቀሰቅሰው ነው እርሱ ከጠጣ በጉለሌ ማን ይተኛል?”

ሰዎችስ እኛን የሚፈልጉት ለምንድነው? ወዳጅነታችን የተገመደበትን ሀረግ የተመዘዘውስ ከወዴት ነው? ጥያቄው ለተበጀ ቢሆን ኖሮ ምናልባትም “ኧረ ወዲያ ደግሞ ስለእነርሱ ምን አገባኝና…እኔ ተበጀ ከወዴት እንደመዘዝኩት እንጂ ከወዴት አባታቸው እንደመዘዙት ለማወቅ ዴንታም የለኝ!” የሚል ይመስለኛል። ቅሉ ግን ወደደም ጠላም የእርሱ መፈለግና ወዳጅነቱ የሚቀዳበት ስፍራ ከጨዋታና ከቧልት ከበርቻቻው መንደር ነው።

የእርሱ ወዳጆች ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉት የጠጅ ቤቱ አጫፋሪዎቹ ብቻ ናቸው። እነርሱም ቢሆኑ ከመሀከላቸው በመተመዘዘው የወዳጅነት ቀለበት ውስጥ አንድ ስውር መሃላ ያለ ይመስላል። እንዲህ የሚል…”በኛና በአንተ መሀከል ያለው ወዳጅነት እስከ እድሜ ልክ መቆረጫችን ድረስ በእዚህ የጠጅ ቤት አግዳሜ ወንበሮች ፊት ብቻ ይሁን። ከዚህ ቃልኪዳን ያፈተለከም የፍቅር ማተባችንን በጥሷልና በሌት በማዕልቱ የቅዠት ዲን በላዩ ይውረድበት” ይኼኔ ብርሌዎቹ ተነስተው የጭብጨባ ኳኳታቸውን ተገጫጭተው አሰሙ። ይህን የአንድነት ማሰሪያ የሆናቸውን ልጥ መሃላ በአፋቸው አውጥተው አይበሉት እንጂ ልባቸው የሚያውቀው እውነታ ግን ይኼው ነው። ከጠጅ ቤቱ ከተለዩ በኋላ ተበጀ ትዝ የማይላቸው ሙት ነው::

“ወደ ውጭ እንደ እርም ወርውሮት የነበረውን የመጠጥ ጠርሙስ ሁሉ በጨለማው ዳብሶ አንድ በአንድ ለቃቀማቸው:: አንዱን ግን ቀና አደረገና ከአፍንጫው አስጠግቶ አሸተተው:: በጠርሙሱ ቅርፅ የመጠጡን አይነት አወቀው:: ዊስኪ ነበርና ስለዚህ ነው ሰው እንዳይሰማ ቀስ ብሎ ሳቀ:: የጠርሙሱን ግማሽ ከጠጣ በኋላ ግን በአፉ ቡሽ ቢወትፍበት ለሳቁ መጠን የለውም::

ቀጥሎ ከእግሩ በታች የወደቀውን ጠርሙስ እየቆጠረ ይህን ሁሉ እንደጠጣሁት አላምንምና በጉለሌ አፈርሳታ ይደረግልኝ እነናቄ እነተሰማ አጎቴም ይጠጣሉ አለ::”

በዚህ አጭር የልቦለድ ታሪክ ውስጥ ደራሲው ተመስገን ገብሬ ስለምንስ ነው እያወራን ያለው? “ስለሰካራሙ ተበጀ እንጂ ሌላ ስለምን ሊሆን?” እያልን ጥያቄውን በጥያቄ ብናዳፍነው ስህተት ላይሆን ይችላል። ትክክለኛ እውነት ግን አይደለም። ስለ ሚያወራው ነገር ሰሙ ስለ ጉለሌው ሰካራም ይሁን እንጂ ወርቁን ግን በፍለጋ ካልሆነ በቀር በዋዛ አናገኘውም። ከበስተጀርባው ሊነግረን የሚፈልገው አንድ ነገር እንዳለ መሀል መሀል ላይ አስታኮ ጣል የሚያደርጋቸው ቃላት ይጠቁሙናል። ሳይንሳዊ እውነታዎችን ከፍልስፍናው ጋር ጨምቆ አንድ የተለየ ቅመማ ሲያካሂድ ይታየናል።

ተበጀ እንደ ጉለሌው ሰካራምነቱ ሕይወቱ የድሎት አነበረችም። ሚስት ለማግባት ፈልጎ የጠየቃቸው ብዙ ሴቶች ምራቅ ተፍተው ተመናቅረውበታል። ትዳሩ እንኳን ቀርቶ ለቤቱ ገረድ ፈልጎ እንኳን አጥቷል። በሰንበቴና በእድር ማህበሩ እንኳን ንቀው ነፍሱን አርክሰዋታል። ታዲያ ለምንስ ይጠጣል? ካላችሁ ደግሞ “ተበጀ ለመስከር ይጠጣል። ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል። ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል” በማለት የሚነግረን ነገር ዞሮ ቀለበት ይሠራል። የዚህ ችግር ቁልፉ ቦታ ሰካራም በመሆኑ… ብለን አንዘጋውም። ምክንያቶቹ መጠጥን፣ መጠጥም ስካርን፣ ስካርም ሌላ ሲያጎርፍበት እንመለከታለን። በስካሩ ጢንቢራው ከመዞሩ የተነሳ መንገድ ላይ እንደወደቀ አድሮ ያውቃል። በወደቀበትም አውቶሞቢል እግሩን ድጦት አልፏል። እስር ቤት ውስጥ ገብቶ መግባቱን እንኳን ያወቀው ጠዋት ሲነጋ ነው። በእነዚህ ሁሉ ትርምሶች ውስጥ እየሆነም መጠጣቱን አያቆምም። እናም ተበጀ ከዚያ እንደራስ ቅሉ ከበቀለበት ሱስ ይወጣል ብሎ ማሰብ ከንቱ ድካም ይመስላል። ጸሀፊው ግን አንዳች ተአምር ለመሥራት እንደቀጠለ ነበር።

ደራሲውም በስተመጨረሻ አንድ ነገር አስቀመጠ:: ተበጀ በአንድ ዓመት፣ ከዘጠኝ ወር፣ ከዘጠኝ ቀንም በኋላ የሆነበት ይህ ነበር፤ “…አንዱ ሐኪም ከጉልበቱ ይቆረጥ አለ:: ሌላው ግን ሁለተኛ እንዳይሰክር ከቂጡ አስጠግቼ እቆርጠዋለሁ አለና ከቂጡ አስጠግቶ ቆረጠው:: የተቆረጠውን እግሩን ከፊቱ መዝናችሁ አስታቅፉት ብሎ አስታማሚዎችን አዘዘ:: እግሩን ከፊቱ መዘኑትና አሥር ኪሎ የሆነው እግርህ ይኸውልህ ታቀፈው ብለው አስታቀፉት:: በዚህ ጊዜ በአጥንት የተጣሉት ውሾች በላዩ ላይ ተረፈረፉበትና በድንጋጤ ከእንቅልፉ ነቃ:: ይህ ሁሉ የደረሰበት በሕልሙ እንደነበር ማወቅ አቃተው:: ከአልጋው ላይ ወረደና ገረዱን ወይዘሮ ጥሩነሽን ከመኝታቸው ቀስቅሶ እየጮኸና እየተንዘረዘረ ስንት እግር ነው ያለኝ ብሎ ጠየቃቸው:: ወይዘሮ ጥሩነሽም “ድሮ ስንት እግር ነበረዎ ጌታ?”

ተበጀ እግሩን አጎንብሶ ለመሳም ሞከረና ራቀው:: ወደ ሰማይ እያየ መጠጥ ማለት ለእኔ ሞት ማለት ነው አለ:: ጊዜውም ሌሊት ነበር:: እንደዚህ የሚሉበት ሌሊት ያልፋል ብለው ወይዘሮ ጥሩነሽ መለሱለት” በማለት ያሳርግልናል። ደራሲው በመጨረሻ የተበጀን የህልም ቅዠት የተናገረበት መንገድ እንዴት አድርገን በምን ቃላት ልናደንቀው እንደምንችል ይጠፋናል። “እነሆ ተበጀም ሱሱን አቆመ። ከዕለታት በአንዱም ቀን በህልሙ ሲጠጣ ታየው። በህልሙም ሐኪሞቹ እግሩን ቆርጠው ሲሰጡትም ተመለከተ” አላለንም። ቢለን ኖሮ ስሜታችንን እስከ ጫፍ ድረስ ቋጥሮ የያዘውን ውበት ባልተመለከትን ነበር። መጠጥ ያቆመበትን የጊዜ ርዝመት፣ ዓመትና ወሩን ሲያስቆጥረን እንኳን የነገረን ለዘብ አድርጎ ነበር። እንዲህ በማድረጉም እርገጠኛ ሆነን መጨረሻውን እንዳንገምተው አደረገን። በልቦለዱ ውስጥ ስለ ተበጀ ትረካውን ጀምሮ እስኪጨርስልን ድረስ ከሀ_ፐ በእረቂቅ የአዕምሮ ጨዋታ ውስጥ እንድንቆይ አድርጎ ተረከው። የጉለሌው ሰካራምም ከመጀመሪያም የመጀመሪያው ሆነ::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You