የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ- በባለሀብቶቹ እይታ

የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እውን ለማድረግ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ እድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው:: ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል::

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ:: ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚከፈልባቸውን የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል::

በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል:: በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አበርክተዋል:: በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በሥራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ::

በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች (Integrated Agro-Industry Parks)፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ይታመናል፤ በተለይ የግብይት ሰንሰለቱን በማቅለል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩም የሚጠበቅ ነው::

ባለሀብቶችም የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ:: መንግሥት በሀገሪቱ ሶስት የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወቃል:: ለግንባታቸውም እስካሁን ድረስ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ታልሞ የተደረገ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ::

በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ከባቱ ከተማ በ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የ‹‹ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› ከእነዚህ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው:: ፓርኩ በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር የተመረቀ ሲሆን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የማር፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሠማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው::

በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ በ271 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችሉ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላትም አሉት። በሻሸመኔ፣ መቂ፣ ዶዶላ፣ ባሌ ሮቤ፣ ኢተያ እና ኦለንጪቲ የሚገኙት እነዚህ ማዕከላት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የተከናወኑላቸው ሲሆን፣ ዋና ተግባራቸው የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትና በብዛት ሰብስቦ ለፓርኩ አምራቾች ማቅረብ ነው:: ወደ ፓርኩ የሚገቡት ባለሀብቶች ከሽግግር ማዕከላቱ ጋር በሚፈጥሩት ትስስር አርሶ አደሩን ጨምሮ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል::

የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰናይት መብሬ ፓርኩ በቅርቡ በፌዴራል መንግስትና በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በተጎበኘበት ወቅት እንደሚገልፁት፣ 276 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 42 ባለሀብቶች ወደ ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተው ለማምረት ከኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ፈጽመዋል። ከነዚህም መካከል 35 ባለሀብቶች መሬት ወስደው በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ። ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ለ16ሺህ 100 ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም ይጠበቃል። አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ፓርኩ አምስት ኩባንያዎች ግንባታዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ሦስት ፕሮጀክቶች (የምግብ ዘይት፣ የጥቁር አዝሙድ ዘይትና የእንስሳት መኖ) ደግሞ ማምረት ጀምረዋል::

እንደዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ፣ ወደ ፓርኩ የገቡ ባለሀብቶች በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሠማራት የሚያስችሏቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ:: ባለሀብቶቹ የሚሠማሩባቸው የአግሮ-ፕሮሰሲንግ (ግብርና ማቀነባበር) ዘርፎች የማርና ሰም፣ የምግብ ዘይት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ (ቲማቲም፣ ድንች፣ ጭማቂ… )፣ የቡና፣ የአቮካዶ ዘይት፣ የስጋ፣ የወተት፣ የቅመማ ቅመም፣ የእንስሳት መኖ፣ የፓስታና ማካሮኒ፣ የህፃናት ምግቦች ማምረትና ማቀነባበር ሥራዎች ናቸው:: ሌሎቹ ድርጅቶች ደግሞ መሬት ተረክበው የባንክ ብድር ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ:: አንዳንዶቹም የባንክ ብድር ተፈቅዶላቸው ማሽን ማስገባት ጀምረዋል::

‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኩ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም፣ የውሃ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ነው:: ማራኪ ገፅታን የተላበሰና ውብ ተፈጥሮ ባለው አካባቢ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የግብርና ምርቶችን ከማቀነባበር በተጨማሪ ወደፊት እንደ ቱሪዝም መዳረሻ ሊያገለግል ይችላል:: ፓርኩ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆኑ ዘርፎችን አስተባብሮ የያዘ በመሆኑ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ::

የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና ኢንዱስትሪያላይዜሽንን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ያሉትን እድሎች በመጠቀም ወደ ፓርኮቹ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ መሰማራት እንደሚኖርባቸው ይናገራሉ::

የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርውን ዘርፍ ለማሳደግ ታልሞ የተገነባ በመሆኑ ለምርት ሥራው የሚጠቀመው ግብዓት የሀገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን ነው:: በፓርኩ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አርሶ አደር ነው:: የፓርኩ አምራቾች የሚጠቀሙት ጥሬ እቃ የአካባቢውን የግብርና ምርት ነው:: አርሶ አደሩ ግብርናውን በማዘመንና አምራችነቱን በመጨመር ለምግብና ለገበያ ከሚያውለው ምርት በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ትርፍ ምርት እንዲያመርት እየተሠራ ነው:: በቀጣይ አምራቾች በማር፣ በስጋ፣ በዶሮ፣ በወተት፣ በጥራጥሬ፣ በዘይትና በሌሎች ዘርፎች ወደ ሥራ ሲገቡ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል:: ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የአካባቢው ኅብረተሰብ የገበያ እድል እንዲያገኝም ያደርጋል::

የ ‹‹አብዮት ቸርነት ኩባንያ›› ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ቸርነት፣ ኩባንያቸው ወደ ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ጥራጥሬ፣ አቮካዶና የጥቁር አዝሙድ ዘይት ወደ አውሮፓና ቻይና ለመላክ የማሽን ተከላ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይገልፃሉ::

እሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው በፓርኩ ውስጥ በ2500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካ እየገነባ ሲሆን፣ የፋብሪካው ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቋል:: ፋብሪካው በ2017 ዓ.ም በቀን ሦስት ሺ ሊትር ዘይት ለማምረት አቅዷል፤ ፈጣን የብድር አሠራር ከተመቻቸለት ደግሞ በቀን 10 ሺህ ሊትር ዘይት የሚያመርቱ ማሽኖችን የመትከል ፍላጎት አለው::

‹‹የምርት ግብዓቶችን ከአካባቢው አርሶ አደር ስለምንገዛ እና የአካባቢው ነዋሪ በፋብሪካው ግንባታ ላይ ተቀጥሮ እየሠራ በመሆኑ ወደ ፓርኩ መግባታችን የገበያ ትስስርና የሥራ እድል እንድንፈጥር አስችሎናል:: በሥራ ላይ ሲያጋጥሙ የነበሩት ችግሮች ከኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር መፍትሄ አግኝተዋል:: በቀጣይም ሥራችንን በማስፋፋት ተጨማሪ የሥራ እድሎችን የመፍጠር እቅድ አለን›› ይላሉ:: ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በፓርኮቹ ውስጥ ያለውን እድል እንዲጠቀሙም አቶ አብዮት ይመክራሉ::

‹‹ቲኬ ቢዝነስ ግሩፕ›› በቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከገቡ ድርጅቶች መካከል ምርት ማምረት የጀመረ ኩባንያ ነው:: የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚና የቦርድ ሊቀ መንበር ሃጂ ቶፊቅ ከድር ድርጅቱ በፓርኩ ውስጥ የሚያከናውናቸውን ግንባታዎች በአራት ወራት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ይናገራሉ:: ግንባታቸው ሲጠናቀቅም ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ ይፈጥራሉ:: በኩባንያው የምርት ግብዓቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ለማግኘት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ትስስር እየፈጠረ እንደሆነ ይገልፃሉ::

የ ‹‹ዩኒክ ትሬዲንግ›› ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፣ ወደ ኢንዱትሪ ፓርኩ ገብተው በመሥራታቸው ብዙ ጥቅሞችን እንዳገኙ ይገልጻሉ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የተሻለ የመሠረተ ልማት እና የግብዓት አቅርቦት እንዳለው ጠቅሰው፣ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ እንዲገቡና በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ ተሞክሯቸውን ይናገራሉ:: ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኩ በጣም ምቹ ነው:: መሠረተ ልማቶች ተሟልተውለታል:: ከአዲስ አበባ ቅርብ ነው:: የምርት ግብዓቶችንም ከቅርብ ማግኘት ይችላል:: ሥራውን ስንጀምር በአምስት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ነበር፣ አሁን ወደ 10ሺህ ካሬ ሜትር እያሳደግነው ነው:: ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ቢገቡ ተጠቃሚ ይሆናሉ›› ይላሉ::

የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ:: ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም:: ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል::

የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው:: ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል:: ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል::

አንተነህ ቸሬ

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You