“ለውጡ ለሲዳማ ሕዝብ ከፍተኛ ትሩፋት ይዞለት መጥቷል” አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና ሕዝብ ከለውጡ በፊት ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች ጋር ተጨፍልቆ ማንነቱ ተደብቆና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ተነፍጎ ኖሯል፡፡ ይህ በመሆኑም ሲዳማ ተገቢው ትኩረት ተነፍጎት፣ ሰላምና መረጋጋት እርቆት፣ ልማት ጠምቶት ቆይቷል። ሆኖም ከስድስት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ተቀይዶ የተያዘበት ገመድ በመበጠሱ፤ የሲዳማ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄው ምላሽ ማግኘት ችሏል፡፡ ዛሬ ላይ እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ተከብሮለት፤ የራሱን ምቹ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግቶ ወደ ልማት ገብቷል፡፡

ሲዳማ ይህን እድል አግኝቶ እንደ ክልል ከተዋቀረ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመንገድ፣ በውሃ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎችም ዘርፎች ስኬታማ የልማት ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን በክልሉ ባደረግነው የመስክ ምልከታ ታዝበናል። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ብልጽግና ቢዘገይ እንጂ አይቀሬ መሆኑን፤ ሲዳማ እንደ ክልል ከተዋቀረ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያስመዘገባቸው ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶች ማሳያ ናቸው።

ከዚህ አኳያ በዋናነት በ2013 ዓ.ም ሲዳማ እንደ ክልል ከተዋቀረ ወዲህ በክልሉ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች እንዴት ተመሩ? ምን ግብ ታሳቢ ተደርጎ ምን ውጤት ተገኘ? በሲዳማ ሰማይ ሥር ሠላም የሰፈነበት ሚስጥሩ ምንድን ነው? የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የታገለለት አጀንዳ ግቡን መቷል ወይ? … ወዘተ በሚሉት አጠቃላይ ስለክልሉ ሠላምና መረጋጋት፣ ልማት እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቃለ ምልልስ አድርጎ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡ ሰናይ ንባብ!

አዲስ ዘመን፦ የሲዳማ ሕዝብ ለረጅም ዘመናት ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የታገለበት ዋና ዓላማ ምን ነበር? የታገለለት አጀንዳስ ተሳክቷል ማለት ይቻላል?

አቶ ደስታ ፦ የሲዳማ ሕዝብ ክልል ሆኖ ለመደራጀት ረጅም ጊዜ የፈጀ ትግል አድርጓል። ትግል ያደርግ የነበረውም በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ሲዳማ ቀድሞም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት መዋቅር፣ ሥርዓትና ልምድ ነበረው። ስለዚህ ይህ መዋቅር ተመልሶለት በሀገሪቱ ፖለቲካ በንቃት የሚሳተፍበት አደረጃጀት ይፈልግ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ክልል ሆኖ መደራጀቱ የሲዳማ ሕዝብ ይበልጥ እንዲታወቅና ማንነቱ እንዲጠበቅ ስለሚረዳው ነው።

ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል የደቡብ ክልል ሳይከፋፈል በነበረው አደረጃጀት፤ የሲዳማ ሕዝብ ተደብቆ ነበር። ሕዝቡም በአካባቢው ያለውን ሀብት ራሱ በራሱ ወስኖ ለማልማት፣ ለማስተዳደርና ውሳኔ ለመስጠት ተጽኖ ነበረው። በመሆኑም ሕዝቡ የታገለው ሕግና ደንብ አበጅቶ እንዲሁ ሥርዓት ዘርግቶ እጁ ላይ ያለውን ሀብት ማስተዳደር፣ መወሰንና መጠቀም እንዲችል ነው። እንደሀገር በጋራ ውሳኔ በሚሰጥባቸው ጉዳዮችም ሲዳማ ሚዛናዊ ውክልና ኖሮት የጋራ ውሳኔ ማሳረፍ እንዲችል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ወይም ተገቢ ምልከታና ትኩረት እንዲኖረው ለማስቻል ነው።

በሀገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የሲዳማ ሕዝብ የዘመናት ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። ይህንን ተከትሎ የሲዳማ ሕዝብ ለዘመናት ከታገለለት አጀንዳ ቱርፋት እየተቋደሰ ነው። ይህም ሲባል ክልል በመሆኑ በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲዳማ ጎልቶ እየታየ ነው። በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲዳማ ሚዛኑን የጠበቀ የውሳኔ ሰጭነት ሚናና ውክልና አግኝቷል። ከዚህ አንጻር በሚፈለግ ደረጃ ደርሷል የሚል እምነት ባይኖርም ጅማሮው ጥሩ ነው።

ሌላው የሲዳማን ማንነት የሚያንጸባርቁ ባህላዊ እሴቶቹ፣ ቋንቋው …ወዘተ ይበልጥ የመታወቅ፣ የመልማት እድል አግኝተዋል። ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ገጽታ አንጻር ሲታይ ደግሞ፤ ሲዳማ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ከጀመረ በኋላ በእጁና በአካባቢው ያሉ ጸጋዎች በአግባቡ ተለይተዋል። ያለውን ጸጋ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሊቀይር የሚችል ስትራቴጂካዊ እቅድ ተዘጋጅቶ ሕዝብና መንግሥት እጅና ጓንት ሆኖ እየተገበረ ይገኛል። በዚህም የክልሉ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

በድምሩ የሲዳማ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎቹና ፍላጎቶቹ እየተመለሱለት ነው። በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት … ወዘተ መሠረተ ልማቶች በስፋት እየተጠቀመ ይገኛል። ከዚህ በላይ ተጠቃሚነቱን ለማስፋት መንግሥትና ሕዝብ በቅንጅት እየሠራን ነው። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ ተጠቃሚነቱ እያደገ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ሲዳማ ክልል ለመሆን፤ በውስጡ አንግቧቸው ሲታገልባቸው የነበሩ አጀንዳዎች ከሞላ ጎደል ተሳክቷል ብሎ መውሰድ ይቻላል። በመሆኑም የሲዳማ ሕዝብ በጣም ደስተኛ ነው።

እንደሀገር ደግሞ “እህትና አጋር ድርጅት” በሚል አንዱ ውሳኔ ሰጪ፤ ሌላው ውሳኔ ተቀባይ የነበረበት ሥርዓትና አስተሳሰብ አክትሞ፤ ዛሬ ላይ መላው ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው ባለቤት የሆኑበት ሥርዓት እየተገነባ ነው። እውነተኛ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በዚህ ማዕቀፍ የሲዳማ ሕዝብ የዘመናት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄው ተመልሶለት፤ ሲዳማ በሁለንተናዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ጥሩና ሚዛናዊ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

አዲስ ዘመን፦ ሲዳማ እንደክልል ከመቋቋሙ በፊትና ከተቋቋመ በኋላ የተከናወኑ መሠረተ ልማቶችን እያነጻጸሩ በአጭሩ ቢነግሩን? የሕዝቡን ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ፍላጎትና የበጀት እጥረት ለማጣጣም የክልሉ አመራር የተጓዘበትን ጥበብ ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ቢገልጹልን?

አቶ ደስታ፦ ሲዳማ ራሱን በራስ የማስተዳደር የዘመናት ፖለቲካዊ ጥያቄው ተመልሶለታል። ይህ አጀንዳ አሁን ላይ ተቋጭቷል። አሁን ላይ የሲዳማ ሕዝብ የትግል አጀንዳ ልማት ነው። ክልሉም ከተደራጀ በኋላ በትኩረት እየሠራ ያለው ልማት ላይ ነው።

ከዚህ አኳያ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት መሠረት በማድረግ ቅድሚያ ጥያቄውን ለመመለስና ለማስደሰት፤ ልክ ክልል ከሆንን በኋላ ከሕዝቡ ጋር ሰፊ የምክክር መድረክ አካሂደናል። በዚህም መሠረት የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለመዳሰስ ተሞክሯል። የሕዝቡም አንገብጋቢ የልማት ጥያቄ የነበረው አንደኛ መንገድ ነው። ሕዝቡም “የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥታችሁ መንገድ ሥሩልኝ” ነው ያለው። እውነትም ሲዳማ ክልል ውስጥ የመንገድ መሠረተ ልማት አልነበረም ማለት ይቻላል። በሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ያነሳው ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመብራት አገልግሎት ነው። እነዚህ መሠረተ ልማቶች ለማህበረሰቡ ተደራሽ ባለመሆናቸው በውሃ ወለድ በሽታ በተለይ እናቶችና ህፃናት ይጠቃሉ። ሴቶች ረጅም ኪሎ ሜትር አቆራርጠው ውሃ ለመቅዳት ሲሄዱ ለጾታዊ ጥቃት ይጋለጣሉ። እንዲሁም መንገድ ባለመኖሩ ወላድን ወደ ሃኪምቤት የሚያደርስ የአምቡላንስ መሄጃ መንገድ አንኳን የለም ነበር። አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ለገበያ የሚያቀርበው በጋማ ከብትና በሸክም ነበር።

ስለዚህ እነዚህን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄ ለመመለስ የረጅም ጊዜ ወይም 10 ዓመት እቅድ አዘጋጀን። ከዚህ ደግሞ የመካከለኛ ጊዜ ማለትም የአምስት ዓመት እቅድ፤ ከዚያም የአጭር ጊዜ ማለትም የሦስትና የአንድ ዓመት እቅድ ነደፍን። በዚህ እቅድ መሠረት ቢያንስ በአምስት ዓመት ውስጥ የአስፓልት መንገድ ማቅረብ ቢያቅተን ክረምት ከበጋ ዓመቱን ሙሉ ሊያገለግሉ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የጠጠር መንገዶችን በከፍተኛ ትኩረት ለመሥራትና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት አቅደን ተነሳን። ሕዝቡም ይህንን እንድናሳካለት ነው ፍላጎቱ። ይህንን አደራ ከሕዝቡ ተቀብለን ፊታችን ወደ ልማት አዞርን።

ነገር ግን ሲዳማ እንደክልል ሲቋቋም ተጨማሪ ወጪዎች መጥተውበታል። ያለችውን ጭማሪ በጀትም አስተዳደራዊ ወጪው ወስዷታል። በመሆኑም ሕዝቡ ያሳየውን የልማት ፍላጎት መልስ ለመስጠት በጀት ማነቆ ሆነ። የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ሀብት ያስፈልጋል። ሀብት ለማሰባሰብ ደግሞ ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተዋቀረ በኋላ የዞን መዋቅር ሳይደራጅ ለሦስት ዓመት እንዲቆይ አደረግን። ዞን አደራጅተን ቢሆን ይወጣ የነበረውን ሀብት፤ ሕዝቡ ለጠየቀው ለልማት አጀንዳ አዋልነው።

ለአብነት ሲዳማ ክልል ከሆነ በአራተኛ ዓመቱ በጥናት አስደግፈን ወጪና የሰው ኃይል በሚቆጥብ መልኩ አራት የዞን መስተዳድሮችን ከፍተናል። ዞኖቹን ለማደራጀት የተገደድነው አንዳንድ የፌዴራል ተቋማት ተልዕኳቸውን ለማስፈጸም ከክልል ጀምሮ እስከ ዞንና ወረዳ አደረጃጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው እንዲሁም ህብረተሰቡ የዞን ከተሞች ሲመሠረቱ ሊያገኘው ከሚችለው ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ተጠቃሚነት አንፃር ነው። ህብረተሰቡም ይህንን ሲጠይቅ ስለነበረ ነው። ስለዚህ እነዚህን ዞኖች ካደራጀን በኋላ በመጀመሪያው ዓመት ለዞኖቹ “ትንሽ ገንዘብ” ብለን ለሥራ ማስኬጃ የሠጠነው 240 ሚሊዮን ብር ነው። አሁን ደግሞ ለመኪና ግዥ ብቻ 200 ሚሊዮን ብር የክልሉን መንግሥት ጠይቀዋል። ክልሉ ሲቋቋም ጀምሮ ዞኖቹ ቢደራጁ ወጪው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ልብ ሊባል ይገባል። በትንሹ በአንድ ዓመት ውስጥ ለዞን መዋቅሮች 300 ሚሊዮን ብር ወጪ ቢደረግ፤ በሦስት ዓመት ውስጥ በጥቂቱ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ይወጣ ነበር።

በተመሳሳይ ሲዳማ እንደ ክልል ከተዋቀረ በኋላ ለክልል ቢሮዎች የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ምን ያህል እንደሆነ መዋቅር ተሠርቷል። ለአብነት አንድ የዞን ትምህርት መምሪያ ጽዳትና ጥበቃውን ጨምሮ በድምሩ 50 ሠራተኞችን ያቅፋል። ክልል ሲሆን ይህ የዞን ትምህርት መምሪያ ወደ ክልል ቢሮ ሲያድግ፤ በመዋቅሩ መሠረት 280 ሠራተኞች ያስፈልጉታል። ይህ ደግሞ አንድ ቢሮ ላይ ብቻ ከ50 ሠራተኞች ተጨማሪ 230 ሠራተኞች የሚቀጠሩ ከሆነ፤ ሁሉም ቢሮ ላይ የሰው ኃይሉ በተመሳሳይ ሲሰፋ ለሠራተኞች የሚወጣው ደመወዝ እጅግ ከፍተኛ ነው።

መዋቅሩ ተግባራዊ ተደርጎ ሠራተኞች ቢቀጠሩ አዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች ብቻ በዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለደመወዝ ይወጣ ነበር። እውነት ለመናገር የተቋማቱን የሰው ኃይል መዋቅር የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ፤ ኮሚቴው ጥናቱን በሦስት ወር ውስጥ አጠናቆ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን ወጪ ለመቆጠብ በመዋቅሩ መሠረት የሰው ኃይል ሳይቀጠር፤ ባለው የሰው ኃይል ሥራዎችን ተግቶ በመሥራት በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለደመወዝ ይወጣ የነበረን ወጪ ማዳን ተችሏል።

ታዲያ የበጀት እጥረት እንኳን ቢያጋጥም እነዚህን ወጪዎች በማስቀረት የሕዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ ተችሏል። ለአብነት በአሃዝ ለመግለጽ ያህል ሲዳማ እራሱን ችሎ ክልል ሆኖ ከተቋቋመ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት ዓመት ውስጥ የመንገድ ተደራሽነት ባልነበረባቸው አቅጣጫ ጫካ መንጥረን፣ ገደላ ገደሉን ሰንጥቀን፣ ወንዞች ላይ ድልድዮችን ገንብተን አዳዲስ መንገዶችን ሠርተናል።

እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሳይጠገኑ ቆይተው ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ መንገዶችን እንዳዲስ ገንብተናል። በዚህም ህብረተሰቡ መግቢያ መውጫ አጥቶ ይቸገር በነበረበት አካባቢዎች ላይ የህብረተሰቡን የዘመናት ችግር ያቀለሉ 2 ሺ 170 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ በክልሉ መንግሥት ተሠርቷል። ከዚህ በተጨማሪ በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ 210 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሦስት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች አሉ። እነዚህ ተደምረው ሲዳማ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የመንገድ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ተቀርፏል።

ዛሬ ላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ በሲዳማ ውስጥ ጥያቄ አይደለም። ሲዳም ክልል ከሆነ በኋላ በሦስትና አራት ዓመት ውስጥ የተሠራው የመንገድ መሠረተ ልማት በ30 ዓመት እንኳን አልተሠራም። ስለዚህ ለውጡ ለሲዳማ ሕዝብ ከፍተኛ ትሩፋት ይዞለት መጥቷል ማለት ነው። ክልል መሆኑ ደግሞ በዚህ ትኩረት ልማቱን እንዲያከናውን አስችሎታል። ሌላው እንደ ብልጽግና ፓርቲ አንዱ ትኩረት የሚሰጠው የሕዝብ ደስተኝነት ነው። ከዚህ አንጻር ሕዝቡ ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር አነጻጽሮ ሲያየው፤ በተሠራው የመንገድ ሥራ በጣም ደስተኛ ነው። ይህንን ደስታውን ባገኝው አጋጣሚ ይገልጽልናል።

ሌላኛው በከፍተኛ ትኩረት ከተሠሩ መሠረተ ልማቶች ውስጥ አንደኛው ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማስፋፋትና ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሳደግ አንጻር ብዙ ተዋናዮች አሉ። እነዚህን አካላት በማቀናጀትና በማስተባበር ቅድሚያ ችግሩ በጥልቀት የሚስተዋልባቸው ቦታዎች ላይ የውሃ ፕሮጀክቶች በስፋት ተሠርተዋል። ከጥቃቅኖቹ ውጭ በከፍተኛ መጠን የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ የሚመልሱ 38 አንኳር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ዓመት ውስጥ ተከናውነዋል።

እነዚህ የውሃ ፕሮጀክቶች ወጪያቸው በጣም ከፍተኛ ነው። እያንዳንዳቸው ከ376 እስከ 25 ሚሊዮን ብር ድረስ ዋጋ ያላቸው ናቸው። ከ38ቱ ውስጥ 28ቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ነው። ወደ ሚቀጥለው ዓመት ግንባታቸው የሚዞረው 10 ፕሮጀክት ብቻ ናቸው። በድምሩ የ38ቱ ፕሮጀክቶች የግንባታ ውል ሁለት ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ግንባታውን ለሚያከናውኑ ተቋራጮች ተከፍሏል። ቀሪው ክፍያ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቁ ድረስ ይፈጸማል።

ስለዚህ በተመሳሳይ ክልሉ ከተመሠረተ በኋላ ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ዓመት ውስጥ ከንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አንጻርም አመርቂ (አኩሪ) ውጤት ተገኝቷል። ሲዳማ እንደክልል ሲቋቋም የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑ 38 በመቶ ነበር። ይህም ለ40 ዓመት ተሠርቶ የተገኘ ውጤት ነበር። ሆኖም ከክልል ምስረታ በኋላ በተሠራው ሥራ አሁን ላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ወደ 60 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሽፋኑን በእጥፍ ማሳደግ ተችሏል። በተጨማሪም በግንባታ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ እንዲሁም በቀጣይ ለመሥራት በዕቅድ የተያዙት ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ሲገቡ፤ በክልሉ የንጹህ ውሃ መጠጥ ሽፋን 75 እና 80 በመቶ ይደርሳል።

እንዲሁ የህብረተሰቡን አንገብጋቢ የልማት ጥያቄ የሆነውን የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያላለሰለሰ ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥያቄ በክልሉ አቅም ብቻ የሚፈታና የሚወሰን አይደለም። ይህንን አገልግሎት የሚያቀርቡ ተቋማት አደረጃጀታቸውና ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት ነው። የህብረተሰቡ አሰፋፈርም የተበታተነ ስለሆነ በየመንደሩ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ከባድ ነው። ሆኖም በተቻለ መጠን በአካባቢው ካሉት የፌዴራል ተቋማት ጋር በመቀናጀት፤ ክልሉም ተጨማሪ በጀት በመመደብ የህብረተሰቡን የመብራት ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እያደረግን ነው።

ሕዝቡ በ4ኛና በ5ኛ ደረጃ ያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ትምህርትና ጤና ናቸው። “ለምን እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ወደ 4ኛና 5ኛ ደረጃ ሄዱ?” የሚል ጥያቄ ከተነሳ በኢህአዴግም ሆነ ከዛ በፊት የትምህርት ጥራትና የጤና አገልግሎት ጥራት ላይ እንጂ ሽፋንና ተደራሽነት ላይ የጎላ ችግር ስላልነበረ፤ ሕዝቡ የትምህርትና የጤና መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ወደ ኋላ አስቀምጧቸዋል። ነገር ግን ክልሉ እንደክልል ከተቋቋመ በኋላ በትምህርትና ጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ለአብነት በጤናው ዘርፍ በሽታን ቀድሞ ከመከላከል አኳያ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር በፓኬጅ ደረጃ ተቀርጾ በተናጠል እንዲሁም በቤተሰብ ወይም በጎረቤት ደረጃ በቡድን በሽታን ቀድሞ የመከላከል ተግባራት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በትኩረት እየተመራ ነው። በአንጻሩ በሽታው ገፍቶ ሲመጣ ደግሞ አክሞ ማዳን ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ 138 ጤና ጣቢያዎች ቀደም ብሎ የተገነቡ አሉ። ክልል ከተሆነ በኋላ ደግሞ አገልግሎቱ ተደራሽ ያልሆነባቸው አካባቢዎች ላይ 15 ጤና ተቋማት ገንብተናል። ከነዚህ ውስጥ ስምንቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ ሰባቱ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ዳዬ ሆስፒታል በዙሪያው ላሉ የጤና ተቋማት እንደሪፈራል አገልግሎት መስጫ ሆኖ እንዲያገለግል፤ ግብዓት በማሟላትና የማስፋፊያ ግንባታ በማከናወን ሆስፒታሉን ወደ ጠቅላላ ሆስፒታልነት በማሳደግ የአገልግሎት ደረጃውን ከፍ ማድረግ ተችሏል። እንዲሁም ሆስፒታል ባልተዳረሰባቸው ወረዳዎች አማካኝ ቦታ ላይ ክላስተር ሆነው እንዲያገለግሉ ሦስት አዳዲስ ሆስፒታሎች ተገንብተዋል። እነዚህ ሁሉ የጤና ተቋማት ተዳምረው የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ተደራሽ ሆኗል ብሎ መናገር ይቻላል። በቀጣይ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ከማንዋል አሠራር አላቆ ወደ ዲጂታል በመቀየር እጅግ ዘመናዊ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ሁለት መሠረታዊ ሥራዎች ተሠርተዋል። አንደኛው የመድኃኒት እጥረቱን ለመቅረፍ ክልሉ በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ብር ለመድኃኒት ግዥ ፈንድ ያደርጋል። በዚህም ዘንድሮን ጨምሮ ወደ 110 ሚሊዮን ብር ለመድኃኒት ግዥ ወጪ ተደርጓል። በዚህም በጤና ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እየተፈታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የጤና ተቋማት የበጀት እጥረት ሲገጥማቸው ለመድኃኒት ግዥ የተመደበውን ገንዘብ በሌላ ሥራ ላይ ያውሉታል።

በጀቱ ከታለመለት ዓላማ ውጭ እንዳይውል ለመቆጣጠር እንዲሁም መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን የማቅረብ አቅምን ከፍ ለማድረግ ከሆስፒታሎችና ከጤና ጣቢያዎች በጥቅሉ ከጤና ተቋማት ባለፈ መድኃኒት አቅራቢ የሕዝብ መድኃኒት ቤቶችን እያደራጀን ነው። እስካሁንም ከ36 የገጠር አስተዳደር ወረዳዎች ውስጥ በ15ቱ የወረዳ ማዕከላት ላይ የሕዝብ መድኃኒት ቤት ተደራጅቷል። መድኃኒት ቤቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ትርፍ እያስገኙ ነው።

በዚህም የመድኃኒት ዋጋን ነጋዴው እንደፈለገ የማይዘውርበትና የማይበዘብዝበት፤ በአንጻሩ ደግሞ ሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርበት መድኃኒት የሚያገኝበት ሥርዓት በጤና ተቋማት ውስጥና ውጭ የመዘርጋት ሥራ እየሠራን ነው። አስተማማኝ የመድኃኒት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ብሎ መናገር ይቻላል።

ከትምህርት ሽፋን አኳያ ደግሞ ሁሉም ቀበሌ ላይ ትምህርት ቤት አለ። ነገር ግን ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ጉድለት አለ። ጥራቱ የተጓደለበት የራሱ በርካታ ምክንያቶች አሉት። ይሄንን በጥናት የመለየት ሥራ ተሠርቷል። ከምክንያቶቹ አንዱ፤ ከክልሉ የሕዝብ ቁጥር 80 በመቶ የሚሆነው የገጠሩ ማኅበረሰብ ልጆቹ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ ማለትም ፊደል ሳይለዩ፣ ማስላት፣ ማንበብ፣ መጻፍ ሳይለማመዱ ነው። ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ ቀጥታ ጥሬ እንደሆኑ 1ኛ ክፍል ሲገቡ ደግሞ፤ ሥርዓተ ትምህርቱ የሚያዘው “አንብቡ፣ አስሉ፣ ጻፉ” ብሎ ነው።

በዚህ ምክንያት ይቸገራሉ። ውጤታማ አይሆኑም። ይህንን ችግር በመሠረታዊነት ለመቅረፍ “በገጠሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ማስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ አንደኛው መፍትሔ ነው” በሚል እንደ ክልል በትኩረት እየተሠራ ነው። በዚህም ከክልልነት በኋላ 100 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በመቶ ቀበሌዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆኑ፤ እያንዳንዱ ትምህርት ቤቶች ስድስትና ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል። በክልሉ 500 ቀበሌዎች ያሉ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ጊዜያት በሁሉም ቀበሌዎች ላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ እናደርጋለን።

ከዚህ በተጨማሪ የቅድመ መደበኛ መምህራንን በስፋት እያሠለጠንን ነው። የሠለጠኑ ቅድመ መደበኛ መምህራን አመችና ደረጃውን በጠበቀ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ሲገናኙ፤ ብዙ በገጠር አካባቢ የተወለዱና የሚወለዱ ልጆች ልክ በከተማ እንደሚወለዱ ልጆች እኩል ትምህርት ቀስመው የሚያድጉበት ዕድል ያገኛሉ። ይህም የትምህርት ጥራት ላይ የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

ከዚህ ባሻገር የትምህርት ጥራቱን ለማስጠበቅና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በርካታ ፓኬጆች ተነድፈው ወደ መሬት ወርደዋል። በዚህም በሕዝብ ተሳትፎ ትምህርት ቤቶችን የማደስና ደረጃቸውን የማሻሻል፣ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት፣ የመምህራንን ተነሳሽነት የማሳደግና የሙያ ብቃታቸውን በሥልጠና የማጎልበት እንዲሁም ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ የሥነ-ልቦና ምክር አገልግሎት መስጠት … ወዘተ የመሳሰሉ የትምህርት ጥራት ጉድለቱን ሊሞሉ የሚችል ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ ይገኛል። በጥቅሉ ክልል ከተሆነ በኋላ የመጣውን ልማት ስንመዝነው፤ ሕዝቡ ለዘመናት ሲታገልለት የነበረው አጀንዳ በደንብ ተሳክቷል ማለት ይቻላል። ይህም የለውጡ መንግሥት ትሩፋት ነው።

አዲስ ዘመን፦ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራትን ቢነግሩን?

አቶ ደስታ፦ ሲዳማ እንደ ክልል ከተመሠረተ በኋላ የጋራ ብልጽግናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል። በዚህ ፍጥነት ከቀጠልን በአጠረ ጊዜ ብልጽግናን ማረጋገጥ፤ ሲዳማን ማበልጸግ ይቻላል። ነገር ግን የእያንዳንዱ ሕይወትና ጎጆ ምን ይመስላል የሚለውን ወረድ ብለን ስንገመግም፤ ኑሮው ተቀይሮ የተሻለ በልቶ፣ ለብሶ፣ መኖሪያውን አዘምኖ፣ ልጆቹን በጥሩ ሁኔታ የሚያስተምርበት አቅም ፈጥሮ አላገኘነውም።

ኑሮው ለምን እንዳልተሻሻለ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ጥናት ሲገባ፤ 80 በመቶ የክልሉ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነው። ይህ ሰፊ ሕዝብ የኑሮ መሠረቱ ደግሞ ግብርና ነው። አርሶ አደሩ ያለው የመሬት ስሪቱ ምን ይመስላል የሚለውን ኮሚቴው ሲያጠና፤ ከጠቅላላ የክልሉ ሕዝብ 27 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር 0 ነጥብ 25 ወይም ሩብ ሄክታር መሬት ነው ያለው። እንዲሁም 0 ነጥብ 5 ወይም የሄክታር ግማሽና ከዛ በታች ያለው በድምሩ 49 በመቶ ሕዝብ ከግማሽ ሄክታር በታች ነው መሬት ያለው። በዚች ስንዝር መሬት ላይ ደግሞ ቤት ሠርቶበት፣ የመውጫ መግቢያ ሥፍራ አስቀርቶ… ወዘተ ለግብርና ሥራ የሚተርፈው መሬት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለዚህ እያንዳንዱ አርሶ አደር ያለው የመሬት ሥሪት ጠባብ ነው። አርሶ አደሩ በዚህ የመሬት ሥሪት ላይ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ቡና … ወዘተ ለማምረት እየሠራ ውሎ ቢያደር ትርጉም ያለው ምርትና ሀብት ሊያፈራ አይችልም።

ስለዚህ በእርሻ ላይ የሚሠራው ሥራ በትኩረት ይሠራል። ነገር ግን ካለው የመሬት ጥበት አኳያ በእርሻ ብቻ የአርሶ አደሩ ሕይወት አይለወጥም። በመሆኑም በትንሽ ቦታ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፤ ሰፋፊ መሬት የማይጠይቁ የአመራረት ዘይቤ ውስጥ እንግባ ብለን ዘርፎችን ለይተናል። ከዚህ አንጻር የሲዳማ ሕዝብ ካለበት የመሬት ጥበት አኳያ ለምርትና ምርታማነቱ ፍቱን መድሃኒት አንደኛው የእንስሳት ሀብት ልማት ነው። በ2014 ዓ.ም የእንስሳት ሀብት ልማት ሥራው የሚመራበት ልዩ ስትራቴጂ በመንደፍ፤ አደረጃጀቱን አጠናክረን፣ ብቁ የሆኑ አመራር መደብን፤ በስፋት ሙያተኞችን ቀጥረን፣ በጀት መድበን፣ ግብዓት አሟልተን እንዲሁም ስትራቴጂውን ለማህበረሰቡ ካስገነዘብን በኋላ ፊሽካ ነፍተን በቅንጅት ስትራቴጂውን ወደ መተግበር ገባን።

የመጀመሪያው ርምጃ ቀደም ሲል የተጀመረ ቢሆንም ቁጥራቸው ያልበዙ፤ ነገር ግን ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ የተሻሻሉ የላሞች ዝርያ የማባዛት ሥራ በስፋት ተሠርቷል። በዚህም አሁን ላይ በእያንዳንዱ በአርሶ አደር ቤት ሀገር በቀል ላሞች ቁጥራቸው እየተመናመነ፤ በአንጻሩ ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞች ደግሞ እየተስፋፉ መጥተዋል። በሂደት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ዝርያ የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞችን ከሀገር በቀል ላሞች ጋር በማዳቀል ዝርያቸውን በማሻሻል አንጻራዊ የወተት ምርት የማሳደግ ተልዕኮ ይዘን ሠርተናል። በዚህም አርሶ አደሩ ከሀገር በቀል/ ሀገረሰብ ላሞች ከሁለት ሊትር በታች ወተት ያገኝ ከነበረበት፤ ዝርያቸው በተሻሻሉ ላሞች አራትና አምስት ሊትር ወደሚያገኝበት ተሸጋግሯል። በክልሉ ከፍተኛ የወተት ምርት ዕድገት ታይቷል። አስተማማኝ የገበያ እድልም አለ። ከዚህ በላይ ምርት ለማግኘት አሁንም ቀሪ የቤት ሥራዎች በትኩረት ይሠራሉ።

እንዲሁም እያንዳንዱ ቤተሰብ በትንሽ ቦታ በዶሮ ርባታ ልማት ላይ እንዲሠማራ አድርገናል። በኋላም ይህ አጀንዳ እንደሀገር “የሌማት ቱርፋት” በሚል ሲመጣ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በተደራጀ ሁኔታ እየሠራንበት እንገኛለን። በመሆኑም የማር፣ የዓሳ፣ የሀር ምርት … ወዘተ ሰፋፊ ቦታዎችን የማይፈልጉ ልማቶች በስፋት እየተከናወኑ ነው። ክልሉም የዶሮና የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል፤ እንደማህበረሰብ እና ቤተሰብ “በሌማት ቱሩፋት” ፕሮጀክት ተጠቃሚነትና ምርታማነት አንጿር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት ለመሆን በቅቷል። የተማሩ ወጣቶች ጭምር በዘርፉ የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው ነው። በመሆኑም ዛሬ ላይ የመሬት ጥበትና ስፋት ለምርትና ምርታማነት ተጽኖ የማይፈጥርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የመሬት ጥበት አጀንዳ ወደማይሆንበት የአስተሳሰብ ደረጃ ተደርሷል። የመሬት ጥበት ማነቆን በዚህ ደረጃ ተሻግረናል። የእያንዳንዱን ቤተሰብ ገቢ የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በአጠቃላይ ሲዳማ የመሬት ስሪቱ ጠባብ ቢሆንም ምርታማነቱ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ እርሻን በሚመለከት ዘመናዊ ቴክኖሎጂና የኤክስቴንሽን ግብዓቶችን ተጠቅሞ ከትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት በሚገኝበት አግባብ ላይ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ይህም በምግብ ዋስትና እራስን ከመቻል አልፎ ገበያን በማረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በማስገኘት ግብርናው ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ለአብነት ክልሉ ከ30 ሺ ቶን በላይ ቡና በዓመት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኛል። በአሁኑ ጊዜ የቡና ምርታማነት በአማካኝ 10 ኩንታል በሄክታር ሲሆን፤ እንደ ሀገርም ከፍተኛው 20 እና 21 ኩንታል በሄክታር ምርታማነት እየተመዘገበ ያለው በክልሉ ነው።

እንዲሁም ለይርጋዓለም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በሀዋሳ ከተማ ዙሪያ ለሚገኙ ሁለት የአቮካዶ ዘይት ጨምቀው ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ፋብሪካዎች፤ አርሶ አደሩ የአቮካዶ ፍራፍሬ ምርት በማቅረብ በተመሳሳይ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ገቢያ ያስገኛል። በሌላ በኩል ከሰብል ልማት አኳያ ደግሞ በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ65 ሺ በላይ ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል ብቻ ተሸፍኗል። ሙሉ የኤክስቴንሽን ፓካጆችን ተጠቅሞ የበቆሎ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ሲሆን፤ በአማካኝ 50 ኩንታል በሄክታር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ስለዚህ ከግብርና አኳያ በእርሻምና በእንስሳት ሀብት ልማት በትኩረት እየተሠራበት ነው።

 አዲስ ዘመን፦ በክልሉ የመስኖ ልማት ሥራ ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው? በተሠራው ሥራስ ምን ያህል ተጨባጭ ውጤት መጥቷል?

አቶ ደስታ፦ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ በዝናብ እጥረትና በድርቅ የማይበገር ኢኮኖሚ ተግባራዊ በማድረግ ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ እድገት ለማስመዝገብ ታስቦ እየተሠራ ነው። ከዚህ አንጻር ግብርናውን በማዘመንና ትራንስፎርም በማድረግ ክረምት፣ ከበጋ በዓመት ሶስትና ሁለት ጊዜ ማምረት የሚቻልበትን እድል ለመፍጠር ሰፋፊ ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተሠርተው ወደ ሥራ ገብተዋል። እንዲሁም በመሠራት ላይ ያሉ አሉ። በተሠራው ሥራም ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።

ይህ ሲባል ሲዳማ እንደክልል ከመቋቋሙ በፊት በዘመናዊ መስኖ ይለማ የነበረው ከ500 ሄክታር መሬት የማይበልጥ ነበር። ክልል ከተሆነ በኋላ በክልሉ መንግሥት ብቻ ወንዝ በመጥለፍና በከርሰ ምድር ውሃ 4,500 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ ለምቷል። ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የግዳቦ ግድብ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ገንብቶ ወደ ሥራ አስገብቷል። በዚህ ፕሮጀክት ብቻ 3,000 ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ ለምቷል።

በጥቅሉ ክልል ከመሆኑ በፊት በዘመናዊ መስኖ ይለማ ከነበረው 500 ሄክታር መሬት፤ አሁን ላይ ወደ 7,500 ሄክታር መሬት ማሳደግ ተችሏል። በዚህም በክልሉ በድምሩ 67 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊና ባሕላዊ መስኖ ለምቷል። በዚህ መልኩ የተገኘውን ውጤት አጠናክረን ከቀጠልን በአንድ አምስት ዓመት ውስጥ ሰፋፊ የመስኖ ልማት መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ እንችላለን። ይህም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ግብርናን እውን በማድረግ ክረምት ከበጋ አምርቶ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ገበያን ለማረጋጋት፣ ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠርና ከድህነት ለመውጣት ያስችላል።

አዲስ ዘመን፦ ሲዳማ በአንጻራዊነት ጥሩ ሠላምና መረጋጋት የሰፈነበት ነው። ይህ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ሠላምና መረጋጋቱ ለክልሉ ኢንቨስትመንትና ቱሪስት ፍሰት እድገት እየተጫወተ ያለው ሚና ምን ይመስላል?

አቶ ደስታ፦ “ትንፋሽና ሠላም ጣዕሙ በሰላም ጊዜ አይታወቅም” ይባላል። የሠላም ጣዕሙ የሚታወቀው ሠላም ሲጠፋ ነው። ስለዚህ የሠላም ትርጉሙ ገብቶን ሠላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራን ነው። የሕዝቡ የቆየ ባህልና እሴት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዚህም ክልል ከተሆነ በኋላ በሲዳማ ውስጥ እስካሁን የሰላም ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። ምክንያቱም የወጣቱ ጥያቄ የሥራ ዕድል ነው። ህብረተሰቡ የሚፈልገው ልማት ነው። ከዚህ አኳያ ወጣቱ ተደራጅቶ የሚሠራበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ግብዓት በማሟላት ዛሬ ላይ ወጣቱ በሥራ ተጠምዷል። የህብረተሰቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ በአጭር ዓመታት ውስጥ በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ ተችሏል። ስለዚህ ድንጋይ የሚወረውር፣ መንገድ የሚዘጋ የለም። ሕዝቡ ለዚህ ፊትና እድል አይሰጥም።

እንዲሁም ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ለሠላሙ ዘብ ቁሞ እየሠራ ይገኛል። ህብረተሰቡ የራሱን ሠላም እራሱ በመጠበቅ በሠላም ወጥቶ እየገባ ነው። በዚህ ሁኔታ ሕዝቡ ተጠቃሚ ሆኗል። ሲዳማ ውስጥ ከሰላም አንፃር ሁሉም በአንድ ልብ መካሪና ተናጋሪ ነው። ሠላምን በማስፈን እረገድ ወጣቶች፣ ሴቶቹ፣ ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣… ድርሻ ድርሻ አላቸው። በዚህ አጋጣሚ ሕዝቡን፣ በዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ያሉ የፀጥታ አመራሮችና አባላቶችን እጅግ በጣም ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።

እንደሚታወቀው ቱሪስት ኮሽታ አይወድም። ሠላም ባልተጠበቀበት ቦታ ቱሪስት ዝር አይልም። ሠላም በመጠበቁ በክልሉ የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ ነው። በተለይ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት እጅግ ጨምሯል። ለኮንፈረንስ ቱሪዝምና ለጉባኤዎች፣ …የክልሉ ዋና ከተማ ሀዋሳ ተመራጭ ናት። ቅዳሜና እሁድ ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ከተማዋ ለመዝናናት ብዛት ያላቸው እንግዶች ይመጣሉ። በዚህም ከቱሪዝሙ የከተማው ማኅበረሰብ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቀመ ነው። በተመሳሳይ በዘርፉ የገጠሩ ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማልማትና የማስዋብ፣ መሠረተ ልማት የማሟላት፣ አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን እንዲሁም ክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ ነው።

ሌላው አንድ አልሚ ኢንቨስት ከማድረጉ በፊት የራሱ መስፈርቶች አሉት። የመጀመሪያው ሠላም ነው። ቀጥሎ ኢንቨስት የሚያደርግበት ማኅበረሰብ ባሕል “ተባብሮ የሚሠራ ነው ወይስ ቆሞ የሚያይ ነው፤ ኢንቨስትመንቱን እንደራሱ ንብረት የሚንከባከብ ነው ወይስ ዘራፊ፣ አውዳሚ ነው” የሚለውን ያጠናል። ስለዚህ በቢሊዮንና ሚሊዮን ሀብት ይዞ የሚመጣው አልሚ እምነት ሊያድርበት ይገባል። በመሆኑም አልሚዎች እምነት ጥለው ወደ ክልሉ መጥተው መዋለነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል ሥራ ከፀጥታና ሠላም አንጻር ተሠርቷል።

በዚህም በየዓመቱ በርካታ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶችን እያስተናገድን ነው። ቀደም ብለው የገቡትንም የማበረታታት ሥራ በትኩረት ይከናወናል። ከዚህ ባሻገር በርካታ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ሼልፋችን ላይ ይገኛሉ። ሆኖም በዝግጅት ጉድለት ባለው ልክ የኢንቨስትመንት ፍላጎቱን አላስተናገድንም። በቀጣይ ያለውን ፍላጎት ለማስተናገድ የኢንዱስትሪ ኮሪደር እያዘጋጀን ነው።

የኢንዱስትሪ ኮሪደር ልማቱን በስፋት ለማከናወን፤ ቀደም ብሎ ለአልሚዎች የተሰጡ ቦታዎች “ምን ያህል እየለሙ ነው?” የሚለውን ኦዲት አድርገናል። በኦዲቱም ሳይለሙ ታጥረው የተቀመጡ በርካታ መሬቶች መኖራቸው ተረጋግጧል። ከዚህ አንጻር በማስጠንቀቂያ እንዲያለሙ የማበረታታት ሥራ ተሠርቷል። ነገር ግን በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያና ማበረታቻ መሠረት ወደ ልማት ባለመግባታቸው የሚነጠቁ በሃዋሳ ከተማ ብቻ ሰባት የኢንቨስትመንት ቦታዎች ተለይተዋል። በዚህ መልኩ ካስተካከልን በኋላ አዳዲስ ለኢንዱስትሪ አመቺ አካባቢዎችን የበለጠ ለማደራጀት እየሠራን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፦ የቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አሁን ላይ ወደ አራት ክልል ተከፋፍሏል። ይህንን ተከትሎ ፍትሃዊ የሀብት ክፍል ለማድረግ የሽግግር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ትግበራ ላይ ነው። የሀብት ክፍፍል ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅና በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በሠላም እንዲኖሩ ከማድረግ አኳያ ምን ተሠርቷል?

አቶ ደስታ፦ ቀድሞ ክልል ሆኖ የወጣው ሲዳማ ነው። ያኔ ሲዳማ ክልል ሆኖ ሲወጣ የደቡብ ክልል እጣፈንታ አልተወሰነም ነበር። በዚህም ደቡብ ክልልና ሲዳማ ክልል በአንድ ከተማ የታጠቀ ሠራዊት ይዘው ለሶስት ዓመት በሠላም ተቀምጠዋል። ይህ በብዙ አካባቢ የሚቻል አይመስለኝም። ብዙ ግጭት ይፈጠር ነበር። ብዙ የሚያጋጩ ጉዳዮችም ነበሩ። ለአብነት ሲዳማ ቀድሞ ክልል ሆኖ ሲወጣ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መቀመጫ ተብሎ የተሰጠው፤ አነስተኛ ህንፃ ነው።

ነገር ግን ቀድሞ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ የነበረበት ህንፃ እያለ፤ “አነስተኛ ህንፃ ተሰጥቶን ስንወጣ፤ ድርሻችን ይሄ ብቻ አይደለም፤ ድርሻችን ስጡን” ብለን አስወጥተን መግባት እንችል ነበር። ያላፈናቀልነው ለማስከን፣ ለማረጋጋት ነው። ምክንያቱም ያኔ ቢያንስ ሲዳማ ጥያቄው ተመልሶለታል። የደቡብ ግን እጣፋንታው አለየለትም ነበር። በዚህ ላይ ግፊት ሲታከልበት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ያ ሕዝብ የኛ ሕዝብ ነው። አብሮ የመኖር፣ የመብላት፣ የመጠጣት… ወዘተ የሕዝቦች የቆየ ትሥሥር አለ። ስለዚህ የዛ ሕዝብ አለመረጋጋት ጦሱ ለሀገር ነው። ሀገር ደግሞ በጋራ የምንገነባው ነው። የነበረው ጤናማ ግንኙነት እንዳይሻክር ከፍተኛ መስዋትነት ተከፍሏል። ብዙ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ሲዳማ ለሦስት ዓመት፤ ዝቅ ብሎ አገልግሏል ብዬነው የማስበው።

በኋላ ላይ ደቡብ ክልልም የራሳቸውን ምርጫ ወስነው ወደ ሦስት ክልል ተከፋፍለዋል። ይህንን ተከትሎ ሃዋሳ የነበረው የጋራ ቤት ሲፈርስ፤ የሀብት ክፍፍሉን በሠላማዊ መንገድ ለመቋጨት መረጃ ላይ የተመሠረተ ድርድርና ውይይት ሲደረግ ቆይቷል። በመጨረሻም “አንተ ትብስ አንቺ” በሚል መርህ የሀብት ክፍፍሉ በስምምነት ወደ መቋጨት ተደርሷል።

በአሁኑ ጊዜ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በሚመለከት ኮሚቴ ተቋቁሞ በተደረገ ክፍፍል፤ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ሁሉም የየድርሻውን ይዞ ሂዷል። ጥቂት ቀሪ የተንጠባጠቡ ጉዳዮች ካሉ እየታየ በጋራ ውይይትና ውሳኔ፤ እልባት ያገኛል።

ሌላው ህንፃን በሚመለከት ደግሞ፤ ደቡብ ክልል፣ ክልል ከሆነ እና መቀመጫውን ሃዋሳ ከተማ ካደረገ በኋላ በሀዋሳ ከተማ በጋራ የተገነቡ ንብረቶች ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አሉ። እነዚህ ህንፃዎች ተቆጥረው ተይዘው፤ “የቱ ወዴት ይሂድ?” የሚል ምክክር ተደርጓል። በዚህም በተመሳሳይ “አንተ ትብስ አንቺ” በሚል በሰጥቶ መቀበል መርህና መቻቻል ህንፃዎቹ ምን መሆን እንዳለባቸው እጣ ፋንታቸው ተወስኗል። የሲዳማ ድርሻውን ተለይቶ ተሰጥቶታል። ነገር ግን ሲዳማ “ይገባኛል” የማይላቸው፤ ለተቀሩ ለሦስቱ ክልሎች የደረሷቸው ህንፃዎች ሀዋሳ ከተማ ውስጥ አሉ። እነዚህን ህንፃዎች እንደራሳችን ንብረት እየጠበቅንና እየተንከባከብን ለባለቤቶቹ ማስረከብ ነው። ስናስረክብም ከሙሉ ሰነዱ፣ መብቱ፣ … ወዘተ ጋር ነው የሚሆነው።

ህንፃዎቹ ግምት ዋጋ ስለወጣላቸው፤ “ያስፈልገናል” ብለን የምናስበው ህንፃ ካለ፤ የሚያጨቃጭቅ ምንም ነገር የለውም የወጣላትን ዋጋ ግምት ከፍለን ህንፃውን ገዝቶ የሲዳማ ማድረግ ነው። የተከፋፈሉ ክልሎች ህንፃውን ሽጠው ገንዘብ ይዘው መሄድ ስለሚፈልጉ፤ አቅሙ ካለን ገዝተን የራሳችን ስለምናደርግበት አግባብ ተነጋግረን ተስማምተናል። ምክንያቱም በየክልል ርዕሰ መዲናቸው ግንባታ ለማከናወን ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ከዛ ውጭ የንብረታቸው ደህንነትና መብት ተጠብቆ ሁሉም ባለቤት ንብረቱን ለኛ ጥሎ በሠላም ይገለገልበታል።

በጥቅሉ የሽግግራችንና የንብረት ክፍፍላችን ሂደት፤ መሰል ሂደት ለሚገጥማቸው ተምሳሌት በሚሆን መልኩ፤ ፍጹም ኮሽታ በሌለበት በሠላማዊ መንገድ ተጠናቋል። ሁሉም ወደየመረጠበት ማዕከሉ ንብረቱን ይዞ ሂዷል። እያንዳንዱ ክልል ንብረቱ ተለይቶ ተሰጥቶት እያስተዳደረ ነው። ሲዳማ ክልልም የራሱን ንብረት በፈለገው መንገድ የሚያስተዳድርበት ደረጃ ላይ ይገኛል። ሌላው ከክልሎቹ ሕዝቦች ጋር ጤናማ ግንኙነት አለን። ይህ መልካም ወንድማማችነት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የሲዳማ ሕዝብ እንደ “አፊኒ” ያሉ ግጭትን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ የበለፀገ ባሕልና እሴቶች ባለቤት ነው። እንደ “አፊኒ” ያሉ ባሕላዊ እሴቶች ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬት የድርሻቸውን እንዲወጡ እንደክልል ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ደስታ፦ አጠቃላይ ሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከችግር እየወጣች ነው የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን አሁንም ተግባቦት ያልፈጠርንባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከትናንት የወረስናቸው፤ በኛ ጊዜም የተፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች አሉ። ይህንን ውስብስብ ችግር ልንፈታው የምንችለው ቁጭ ብለን በተረጋጋ ሁኔታ በመመካከር ነው። መንግሥት ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ፤ የምክክር ዕድል አመቻችቷል። ኮሚሽኑም የአጀንዳ፣ የተሳታፊ ልየታ … ወዘተ ሥራዎችን እያገባደደ ይገኛል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ለአለመግባባት መነሻ የሆኑ አጀንዳዎች ለውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ ይቀርባሉ ብዬ አስባለሁ። በዚህ የምክክር ሂደትም የተለያዩ ርዕዮት ዓለምና አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሳተፋሉ። እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሑራን፣ … ወዘተ ተሳታፊ ናቸው።

እንደሀገር አላግባቡ ያሉ አጀንዳዎችን በብቃት ሊያቀርቡ የሚችሉ አካላት ሁሉ የሚሳተፉበት ነው። ስለዚህ ሀገራዊ ምክክር መድረኩን በሰከነ ሁኔታ ከተጠቀምንበት ለችግሮቻችን መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን አንዴ ፋይላቸውን ዘግተን የምናልፍበት ነው። ይህም ኢትዮጵያ የሁላችን ሆና፤ ሁላችነም በጋራ አልምተን ለሁላችነም የተመቸች ሀገር ለመፍጠር ያስችለናል። ሀገራችንን በጋራ የምናበለፅግበት ዕድል ይፈጠራል።

ከዚህ አኳያ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ደግሞ እንደ “አፊኒ” ያሉ ግጭትና አለመግባባትን በሠላማዊና በሰከነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ ባሕልና እሴቶች ሚናቸው ከፍተኛ ነው። የሲዳማ ሕዝብ እስካሁን ተረጋግቶ፣ አንድነቱን ጠብቆ እንደ ማኅበረሰብ ተጠናክሮ ዛሬ ላይ የደረሰው “በአፊኒ” ባሕላዊ እሴቱ ነው። ለአብነት ምድር ላይ ከባዱ የሰው ሞት ወይም ደም መፋሰስ ነው። በሲዳማ ባሕል አንድ ሰው ተገድሎ ቢገኝ የሟች ቤተሰብ አስከሬኑን ጨርቅ እንኳን ቢጠፋ ቅጠል አልብሶ “አፊኒ” ይላል። “አፊኒ” ማለት ምን እንደሆነ፤ ምን እንደተከሰተ፤ አያችሁ፣ ሰማችሁ ወይ እንደማለት ነው። ከችግሮች በላይ ሆኖ መሻገርን የሚያመላክት ነው። “አፊኒ” ከተባለ በኋላ የሟችና የገዳይ ቤተሰብ ቢገናኙ እንኳን መረጋጋት ነው እንጂ አካኪ ዘራፍ አይባልም። በተለይ ሽማግሌ የሟች ቤተሰቦች፤ የገዳይ ቤተሰብ እንዳይጎዳ ይከላከላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ “አፊኒ” ከተባለ በኋላ ሁሉም ለችግሩ የመፍትሔ ሀሳብ ለማፍለቅ እንዲሳተፍ ዓውድ ይፈጥራል። በዚህ ማዕቀፍ ሁሉም ተረጋግቶ ከእርምጃ ይልቅ በሰከነ መንገድ ስለሆነው ነገር ወደ ማስረዳትና ወደ መመርመር ይገባል። ወደ ንግግር ወይም ማስረዳት ከተገባ በኋላ መግባባት፣ መተማመን… ይመጣል። በዛ ደረጃ ቢቻል ወዲያውኑ ካልሆነ በይደር፣ በቀጠሮ እየተወያዩ ከባድ የሆነ ችግርን ይፈታሉ። ስለዚህ “አፊኒ” በሲዳማ ሕዝብ ውስጥ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች የመፍትሔ ቁልፍ የሆነ ሥርዓት ነው። ይህን ሥርዓት እንደ ክልል በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ሂደት በስፋት እንደግብዓት እንጠቀምበታለን።

አሁን ላይ እንደሀገር የመጣው ዕድል ተመሳሳይ ነው። ብንነጋገር ብዙ መፍትሔ አለ። ነገር ግን አንዳንድ የኢትዮጵያ ችግርና መከራ እንዳያልቅ የሚፈልጉ አካላት፤ “እንመካከር” መባሉን የሚያብጠለጥሉ አሉ። እንነጋገር መጥፎ አይደለም። በቁርሾ፣ በቂም፣ በትርክት … ወዘተ ተነሳስቶ መገዳደሉ ነው መጥፎው። በመሆኑም በኃይለኝነትና በእልህ የፈለግነውን እናሳካለን የሚለው አያዋጣም። በዚህ መንገድ ስንት ሺ ዓመታትን በጋራ መጥተናል። እየተጨራረስን ነው የመጣነው።

ውጤቱም ቢሆን በድህነት ውስጥ ነው ያቆየን። ከዚህ በኋላ ይብቃን ልንል ይገባል። ለችግሮቻችን መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በመነጋገር መፍትሔ እንፈልግላቸው። ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሕይወት የምናስብ ከሆነ፤ “በዳይ፣ ተበዳይ” ብለን በየጊዜው የምንጨቃጨቅበትን ያለፈውን ፋይል በእርቅና በይቅርታ ልንዘጋው ይገባል። ለአብነት ከኛ ሀገር በላይ በሕንድ ሀገር ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ሀገር ተዋቅረው በፍቅር ይኖራሉ። ሀገራቸውንም ይጠብቃሉ። ብልፅግናንም አረጋግጠዋል። እኛም ያለችን ሀገር አንድ ናት። በፍቅር ልንኖርባት ይገባል። ከድህነት አዙሪት ወጥተን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመጪው ትውልድ ልናስረክብ ይገባል።

አዲስ ዘመን:- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ይህን ሰፋ ያለ ቃለምልልስ ስለሰጡን እናመሰግናለን።

አቶ ደስታ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You