አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ አሁን ባለው የጸጥታ ስጋትና ጫፍ የረገጠ ብሔርተኝነት ምክንያት የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ መጪው ምርጫ መራዘም አለበት የሚል አቋም እንዳለው ኢህአፓ ገለፀ።
የኢህአፓ ከፍተኛ አመራርና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ቆንጅት ብርሃን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ጫፍ የረገጠበት ደረጃ ደርሷል።
አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ ምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ አዳጋች በመሆኑ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ፓርቲያቸው ምርጫውን በአግባቡ ማካሄድ ይቻላል ብሎ አያምንም።
በተለይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጫፍ የረገጠ ዘረኝነት እንደሚስተዋል ገልጸው፤ በዚህ ሁኔታ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች እንዴት አድርገው ነው ከህዝቡ ጋር የሚገናኙት፤ የት ሄደው ነው ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚቀሰቅሱት ሲሉ ጠይቀዋል።
«የመንግሥት የመጀመሪያው ስራ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን አለበት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶች የትም ተንቀሳቅሰው ከህዝቡ ጋር ተገናኝተው የራሳቸውን መራጮች የሚቀሰቅሱበትና ምርጫውን የሚሳተፉበት ሁኔታ ማስተካከል ያስፈልጋል» ብለዋል።
የሚቀድመው ነገር ኢትዮጵያን በሚገባ ማቆም እንጂ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ይካሄድ ማለት አገሪቱን ለጥፋት መጋበዝ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢህአፓ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር ውስጥ በመግባት አዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011