አዲስ አበባ፡- የ2012 በጀት ዓመት የግብርና እና መስኖ ሥራዎች የፌዴራል መንግሥት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገለፀ።
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት በፌዴራል መንግሥት 2012 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ውይይት ተካሂዷል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በወቅቱ እንደገለፁት፣ የ2012 በጀት ዓመት የግብርና እና መስኖ ሥራዎችና መሠረተ ልማት ግንባታ የፌዴራል መንግሥት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የመንግሥት ሰራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ ለመፈፀም በሰፊው ይሰራል። ይሁንና ይህ ሂደት በመሆኑ በአንድ ቅጽበት የማይፈታ ስለመሆኑም መግባባት ላይ መድረስ ይገባል።
የህዝብ ፍላጎትና አገሪቱ ያላት የፋይናንስ አቅም የተመጣጠነ ባለመሆኑ ጥያቄዎችን በፍጥነት መመለስ አለመቻሉን ዶ/ር እዮብ ገልጸዋል። ምንም እንኳን የ2012 በጀት ዓመት ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1ነጥብ6 ከመቶ ብልጫ ያለው ቢሆንም ክፍተቶችን በቀላሉ መድፈን አለመቻሉን አስረድተዋል። የሚጠበቅ ግብር በወቅቱ ባለመሰብሰቡም የወጪና ገቢ ማመጣጠን አልተቻለም ብለዋል። ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው። ለአብነትም በአሁኑ ወቅትም ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ላይም የዋጋ ግሽበቱ 16ነጥብ5 ከመቶ መድረሱን ገልጸዋል። ይህም በመሆኑ የገቢ አሰባሰብ ሥራውን ማሳደግና ከህዝብ ጋር በግልጽ መወያየት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሓድጉ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የህዝቡ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ሲሆን አገሪቱ ያላት አቅም ውስን ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያለባት ሀገር በመሆኗ ክፍተቶችን ለመድፈን አስቸጋሪ እየሆነ ነው።
የግብር አሰባሰብ ደካማ ከመሆኑ የተነሳም ገቢና ወጪ አልተመጣጠነም። ይህ በመሆኑም ያለውን በጀት ከብክነትና ሙስና በፀዳ መልኩ መጠቀም ይገባል። በአጠቃላይ ሚኒስቴሩ ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት አጽንኦት መስጠትና የኢኮኖሚውን አካሄድ በየጊዜው በመገምገም እልባት ማበጀት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር