– በዞኑ ዘንድሮ 43 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ ተተክሏል
ዲላ፡-እንሰት ምርት ለማግኘት ይወስድ የነበረውን ጊዜ ወደ አንድ ዓመት ተኩል ዝቅ ማድረግ መቻሉን የጌዲኦ ዞን አስታወቀ። በዘንድሮው ዓመት 43 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ መተከላቸውም ተገልጿል።
የጌዲኦ ዞን አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፡- የእንሰት ምርትን ለማግኘት ይወስድ የነበረውን ከአምስት ዓመት በላይ ጊዜ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወደ አንድ ዓመት ተኩል ዝቅ ማድረግ ተችሏል።
እስከ ሰባት ዓመት ይወስድ የነበረውን የእንሰት ምርት የተለያዩ አካባቢውን መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ማድረስ ተችሏል።
በዞኑ በባለፈው ዓመት ከአርሶ አደሮች ጋር በመሆን ከ32 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ ተተክሏል ያሉት አስተዳዳሪው፣ ዘንድሮው ዓመት 43 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ ተተክሏል ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የእንሰት ምርት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ ዞኑ የእንሰትና ቡና ተክል በስፋት የሚገኝበት በመሆኑ ምርታማነትን ሊያረጋግጥ በሚችል ደረጃ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
እንሰት አምራች የሆነ አካባቢዎች ተለይተው በቴክኖሎጂ የተደገፈ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እየጠበቀ ምርት ይሰጥ የነበረውን እንሰት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ምርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በዞን ደረጃ እንሰትን በስፋት አምራች አካባቢዎች ተለይተው ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት ዝናቡ (ዶ/ር)፣ ከለውጡ በፊት አካባቢውን መሠረት ያደረገ የግብርና ድጋፍ ተደርጎ አያውቅም ብለዋል።
በጌዲኦ ከጭላንጭል ወደ የሚጨበጥ ብርሃን ለመሸጋገር የተያዘውን ሀገራዊ እቅድ ለማሳካት የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ የእንሰት ምርትና ምርታማነትን ሊያረጋግጥ በሚችል ደረጃ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በቡና ልማት ሥራ 75 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና መሸፈኑን ጠቅሰው፣ ከዞኑም በየዓመቱ እስከ 27 ሺህ ቶን ቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በለውጡ መንግሥት ለአርሶ አደሮች ትኩረት በመስጠት የቡናን ምርት ለማሳደግ መሠራቱን ጠቅሰው፣ ቡናን በሞዴል አርሶ አደሮች ደረጃ በሄክታር 19 ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል።
በዞኑ ከ780 በላይ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ወደ ገበያ እያቀረቡ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ 350 በላይ የእሸት ቡና ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም