– ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ ፦ በመጪው ዓመት በድሬዳዋ የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የሀገሪቱ የማዳበሪያ ፍላጎቱን ሙሉ ለሙሉ የሚመልስ መሆኑን የኬሚካልና ኮንስትራክሽን አምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።ፋብሪካው ወደ አገልግሎት ምዕራፍ ሲሻገር ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የግብርናን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ በተሟላ መልኩ ማምረት ያስችል ዘንድ በመንግሥት በርካታ እቅዶች ተይዘዋል።
ከዚህ መካከል በድሬዳዋ ከተማ የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ዋነኛው ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ያለውን የማዳበሪያ ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ ይመልሳል። በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በመጪው ዓመት ወደ ትግበራ ምዕራፍ ይገባል።
ድሬዳዋ ኢንደስትሪያል ፓርክ አጠገብ የሚገነባው ፋብሪካው በዋናነት ከኦጋዴን የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በግብዓትነት የሚጠቀም መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ዩሪያን እና ኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያን በስፋት የሚያመርት ይሆናል።
የፋብሪካ ግንባታው በአራት ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት መታሰቡን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ «የማዳበሪያ ፋብሪካው በዓመት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ዩሪያ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያን የማምረት አቅም ይኖረዋል። የአገሪቱን የማዳበሪያ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ከማሟላት አልፎ ወደ ውጭ የመላክ እድልን የሚፈጥር ይሆናል» ብለዋል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከውጪ እያስገባችው የምትገኘው ዩሪያ 1 ሚሊዮን ቶን አልደ ረሰም ። በሌላ በኩል ደግሞ 1 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ኤን.ፒ.ኤስ ታስገባለች። በቀጣይ ፍላጎቱ ቢያድግ እንኳ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ
ለማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል።
«ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን አክለው የገለጹት አቶ ሳሙኤል ፤ፕሮጀክቱ ኦሲፒ ከሚባለው የሞሮኮ ኩባንያ ጋር በመቀናጀት የሚሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሞሮኮው ኩባንያው ጋር በመሆን ስለ ፕሮጀክቱ በዋናነት መሰረታዊ የሚባሉ ጥናቶችን አከናውኖ በማጠናቀቅ ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች አስረክቧል። በዚህ መሰረት የኢንቨስትመንት መሰረታዊ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና ከሞሮኮ መንግሥት ጋር የሚፈራረሙበት ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ኮሚቴ ወደ መጨረሻው ደረጃ እያደረሰው ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያመለክ ተው፤ በ2012 ዓ.ም ግንባታው የሚጀመረው ዩሪያና ኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ፕሮጀክት ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረ መሆኑን ነው።ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውጪ ለምታስገባው ማዳበሪያ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ዳንኤል ዘነበ