አንዳንዶቻችን ዓለም የተፈጠረችው አሁን ባለችበት ቅርጽና ሁኔታ ይመስለናል። ዓለም ግን አሁን ካለችበት ቅርጽና ሁኔታ በተፈጥሮም፣ በሰው ልጅ የአኗኗር ዘይቤም እጅግ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ያላት ነበረች። ይህ በሃይማኖትም በሳይንስም ያለ እውነታ ነው። እነ ዩቫል ኑዋህ ሃራሪ እንደሚሉት ደግሞ ዓለም ከ13 ቢሊዮን በላይ ዕድሜ አላት፤ ልብ በሉ ቢሊዮን ነው የተባለው።
የቢሊዮን እና ሚሊዮኑን ዓመታቱን እንተወውና የተጻፉ ሰነዶች የተገኙበትን የሰው ልጅ ታሪክ እንኳን ብናየው ከዛሬው ጋር የሰማይና ምድር ያህል የተራራቀ ልዩነት አለው። ከ100 እና 200 ዓመታት በፊት የነበረውና የዛሬው በጣም ሰፊ ልዩነት አለው። ከዛሬ 10 ዓመት በፊት የነበረውና የዛሬው ራሱ ብዙ ልዩነት አለው። ብዙዎቻችን ግን የዘመን ዓውድ ትዝ አይለንም። በዚህ ምክንያት አግባብ ያልሆነ ንፅፅር ውስጥ እንገባለን፣ ይህ አግባብ ያልሆነ ንፅፅር ወደ ፍረጃ ይሄዳል። ፍረጃው ደግሞ የጭቅጭቅ መንስኤ ይሆናል ማለት ነው።
ከዓመታት በፊት አንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር ፖለቲከኛ በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ቀርቦ ‹‹ለምንድነው 100 እና 200 ዓመታት ወደኋላ እየተመለሳችሁ የድሮ ዓፄዎችን የምትኮንኑት?›› ተብሎ ተጠየቀ። የሰጠው መልስ ‹‹ዴሞክራሲያዊ አልነበሩም›› የሚል በመሆኑ መሳቂያ ሆኖ በማኅበራዊ ገጾች ሲዘዋወር ነበር።
የሰውየው መልስ በብዙ መንገድ ዓውድ የሳተ ነበር። ከ100 ምናምን ዓመታት በፊት እንኳን በአፍሪካና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ፈጣሪ ናቸው በሚባሉትም ዴሞክራሲ አልነበረም። ዴሞክራሲ እንኳን ከ100 እና 200 ዓመታት በፊት፣ ዛሬ ራሱ ‹‹አለ›› ‹‹የለም!›› ክርክር ላይ ነው እኮ! እንኳን በአፍሪካ የዴሞክራሲ መሪ ናቸው የሚባሉት አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ላይ እያየን ነው። በነገራችን ላይ ዴሞክራሲ ማለት እንደነአሜሪካ ማንም ጎረምሳ ክላሽ እየያዘ ሕዝብ የተሰበሰበበት ቦታ እየሄደ ጥይት የሚተኩስበት ከሆነ ይቅርብን!
ዋናው ነጥባችን የዘመን ዓውድ ነው። ብዙ አባቶች ‹‹ድሮ ቀረ!›› ሲሉ እንሰማለን። ድሮ እና ዛሬ አንድ አይደለም። እንኳን ስሜት ያለው የሰው ልጅ ይቅርና ግዑዝ አካል ራሱ የጥንቱ እና የዛሬው አንድ አይደለም። ተፈጥሮ ራሱ ይቀያየራል። አሁን የምናየው መልከዓ ምድር ከሺህ ዘመናት በፊት የነበረው አይደለም። በእርግጥ ምክንያቱ የሰው ልጅ ነው ሊባል ይችላል። የሰው ልጅ ብቻ ግን አይደለም። መልክዓ ምድር የተፈጠረው በራሱ በተፈጥሮ ኃይል ነው። ስለዚህ ተፈጥሮም በዘመናት ሂደት ሌላ ቅርጽ ይይዛል ማለት ነው።
አንዳንዶቹ ደግሞ የአሁኑን ዘመን ሲኮንኑ ድሮ ችግር ያልነበረ ያስመስሉታል። ለምሳሌ፤ የዚህ ዘመን ትውልድ በጨዋነትና ሥነ ምግባር እየተበላሸ ነው ብለው ያማሉ። እውን ሱስ ድሮ አልነበረም? እውን ዝሙት እና ሴሰኝነት ድሮ አልነበረም? እንዲያውም በጥናት አልተረጋገጠም ይሆናል እንጂ ጉዳቱን የተሻለ በመረዳት የአሁኑ ትውልድ ሳይሻል አይቀርም።
ያም ሆነ ይህ ዋናው ችግር የድሮውን በአሁኑ መነጽር ማነጻጸር ነው። በየራሱ ዓውድ ነው መታየት ያለበት። አንድ ነገር ድሮ ይደረግ ከነበረ ያንን ነገር ለማድረግ የዘመኑ ነባራዊ ሁኔታ ያስገድድ ነበር ማለት ነው። ተፈጥሯዊ ሁኔታውም ሆነ ማኅበራዊ ሁኔታው ገፊ ምክንያት ነበር ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ያ በነባራዊ ሁኔታዎች ግፊት የሚደረግ ነገር ሲደጋገም ባሕል ይሆናል። ቀላል ምሳሌ እንውሰድ።
ለምሳሌ ድሮ ሴቶች ውሃ በእንስራ ይቀዱ ነበር። አሁንም በገጠሩ አካባቢ ይኖር ይሆናል። ይህን ለማድረግ አስገዳጅ ምክንያቶች አሉ። በአቅራቢያቸው የቧንቧ ውሃ የለም። ስለዚህ የወንዝ ውሃ ይቀዳሉ። የፕላስቲክ አማራጮች አልነበሩም፤ ስለዚህ በአካባቢ የሚሠራው የሸክላ ዕቃ (እንሥራ) ይጠቀማሉ። ይህ የዕለት ከዕለት ሕይወት ሲሆን ባሕል ሆነ ማለት ነው።
የማንነት መገለጫ ነው ተባለ። ለዚህም ይመስላል በባሕል ዘፈኖቻችን ውስጥ ተዋናዮቹ ከከተማ ሄደው፣ ሲኪኒ (ጠባብ) ሱሪያቸውን በሽንሽን ቀሚስ ቀይረው በእንሥራ ውሃ እየቀዱ ይታያል። ይሄ ነገር እንደ ዘጋቢ ፊልም የቀደሙን ዘመን አኗኗር ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ‹‹አኩሪ ባሕላችን›› ለማለት ግን አያስደፍርም። አኩሪም አሳፋሪም ሳይሆን ቀደም ሲል በነበረው ዘመን የነበረ የአኗኗር ዘይቤ ነው። አዲስ አበባም ከዛሬ 137 ዓመታት በፊት እንደዚያ ነበረች!
አንድ ነገር ‹‹ባሕላችን ነው አይነካ!›› ሲባል በዘመን ዓውድ መታየት አለበት። ዛሬ ላይ ብናደርገው ይጠቅማል ወይ? ተብሎ መታሰብ አለበት። ለምሳሌ የሴቶችን ሱሪ መልበስ የማይደግፉ ብዙ ወገኖች አሉ። ሱሪ መልበስ ጉዳቱ ምንድነው? ለቅልጥፍና እና ሰውነት እንዳይታይ ላለመሳቀቅ ምቾቱ አይበልጥም ወይ? ድሮ በቀላሉ የሚሠራው ከጥጥ የሚሠራ ልብስ ነበር፤ አሁን ደግሞ በዘመናዊ መንገድ የሚሠራ አማራጭ ከተገኘ በቀሚስ ባይገደቡ ምን ችግር አለው? ስለዚህ ነገሮችን በዘመን ዓውድ ማየት አለብን።
ይሄ ማለት ግን የግድ ሁሉም ነገሮች መቀየር አለባቸው ማለት አይደለም። ዋናው ነገር የትኛው ምቾት ሰጠን የሚለው ነው። ለምሳሌ፤ መሰንቆ፣ ክራርና ዋሽንት የመሳሰሉት የባሕል የሙዚቃ መሣሪያዎች የድሮ ናቸው። ዛሬ ብዙ ዘመናዊ የውጭ መሣሪያዎች አሉ። አንድ የዚህ ዘመን ወጣት መሰንቆና ዋሽንት ካስደሰተው ከኪቦርድ ይልቅ በዋሽንት ወይም መሰንቆ መዝናናት ይችላል ማለት ነው። አማራጩ አለ። አንዲት ሴት በጠባብ ሱሪ ከምጨናነቅ የአያት ቅድመ አያቶቼ ሽንሽን ቀሚስ ይመቸኛል ካለች ትችላለች ማለት ነው። አማራጩ አለ። ለዚህም ነው አንዳንድ የድሮ ነገሮች እንደገና የተጀመሩት፤ ወይም ተሻሽለው በዘመናዊ መንገድ የተጀመሩት።
ነገሮችን በዘመኑ ዓውድ ማየት ጠቃሚና ጎጂውን እንድንለይ ይጠቅመናል። ከዘመኑ ጋር እንድንራመድ ይሆነናል። ዓለምን እንድንከተል ያግዘናል። ‹‹ድሮ እንዲህ ነበርና!›› ብለን አንድ ቦታ እንዳንቸነከር ያደርገናል። ወይም ‹‹ዛሬ እንዲህ ነው!›› በሚል መሠረት የሆነንን ነባር ማንነት ሁሉ እንዳናወድም ያደርገናል። ምክንያቱም ማንነትን ሳያፈርሱ፣ ማንነትን እያስታወሱ፣ መሠረትን ሳይለቁ መዘመን ይቻላልና!
ለአድናቆትም ሆነ ለወቀሳ፣ ለስድብም ሆነ ለሙገሳ ድሮና ዘንድሮን ስናነፃፅር ዓውድን መዘንጋት የለብንም። ያኔ የነበሩ እና አሁን ያሉ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ነባራዊ ሁኔታዎችን መዘንጋት የለብንም። በነገራችን ላይ ተፈጥሮ የሰውን ልጅ ባሕልና አኗኗር ለመበየን ከፍተኛ ድርሻ አለው። ተፈጥሮን ተከትሎ የሚመሠረቱ የሰው ልጅ ባሕሪያት አሉ። የአየር ንብረትም ሆነ መልክዓ ምድር (ለምሳሌ ቆላማና ደጋማ አካባቢ) የአኗኗር ዘይቤን ይቀርጻሉ፤ ይህ ደግሞ ባሕል ይሆናል። ስለዚህ በዘመናት ሂደት ለውጥ ይመጣል ማለት ነው።
በአጠቃላይ ድሮና ዘንድሮን ስናነፃፅር የዘመን ዓውድ አንዘንጋ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም