– የመንግሥት ሥራ በአንድ ለመምራት ያስችላል
– የስኬል ስሩልን ጥያቄን ይመልሳል
አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ሥራ አንድ ሆኖ እንዲመራ እና በእኩልነት እንዲስተናገዱ የሚያስችለው የሥራ ምዘና እና ደረጃ አወሳሰን ፕሮጀክት (Job evaluation and grading) በሐምሌ ወር እንደሚጀመር የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽነሩ አቶ በዛብህ ገብረየስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በነጥብ ምዘና ስርዓት የሚደረግበት የስኬል ሽግግር ትግበራ ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ይደረግ የነበረውን የሠራተኞችን ፍልሰት ያስቆማል። ሥራዎቹ ሲመዘኑ ደረጃ አወሳሰኑ አንድ አይነት ክፍያ ይኖረዋል።
ይህ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ መስሪያ ቤቶች የየራሳቸውን ስኬል ስሩልን ብለው ጥያቄ ማቅረብ አይችሉም። የመንግሥት ሥራ አንድ ሆኖ ይመራል፣ በእኩልነት የሚስተናገዱበት ስርዓት ይዘረጋል።
‹‹አንድ ለወጣ የሥራ መደብ የተሰጠው ዋጋ አንድ ላይ ስለሆነ ያኛው የተሻለ ይከፍለኛል በሚል እሳቤ የሚደረግ እንቅስቃሴ አይኖርም›› ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሥራ ተቋም በመልቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ለመኖሪያ ቤት ለመቅረብና የሥራ ከባቢ ምቹነት ምክንያቶች ካልሆኑ በስተቀር የተሻለ ክፍያ ፍለጋ እንቅስቃሴ እንደማይኖርም አስረድተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የሥራ አመዳደብ ፕሳ፣ ጽሂ፣ አስ በማለት ሰዎችን በመከፋፈል የነበረው መደብ ተቀይሮ አዲሱ ደረጃቸው ላይ የሚቀመጡ መሆኑን ኮሚሽኑ ጠቁመው፤ በአዲሱ ደረጃ በመመዘኛ ነጥቦች (point rating) ላይ በመመስረት በሚሰሩት ሥራ በወጣላቸው ደረጃ መሰረት በነጥቦች ተለክተው በተለዩ 21 ደረጃዎች እንደሚመደቡ ተናግረዋል።
እስካሁን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 18 ሺ በላይ መደቦች 99 በመቶ የወረቀት ሥራ መጠናቀቁን አመልክተዋል። አዲስ የተፈጠሩ ተቋማትን ጨምሮ የወረቀት ሥራቸውን ያላጠናቀቁ አንድ በመቶ ተቋማት እስከ ሰኔ 30 ድረስ እንደሚጨርሱም ገልጸዋል። የወረቀት ሥራውን ስለጨረሱ ተገበሩ የሚባሉ ተቋማት እንደሌሉም አስገንዝበዋል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቀቀ የሚባለው ሥራዎቹ ተመዝነው፣ ደረጃ ወጥቶላቸው ሲጨርሱና ሰራተኞች በመደብ መጠሪያ ሲቀመጡ ነው ያሉት አቶ በዛብህ፤ መንግሥት የቀረቡትን አማራጮች ተመልክቶ መወሰኑን አስታውሰዋል። ‹‹ይህ ማለት ቀጥታ የደመወዝ ጭማሪ መስጠት አይደለም፣ ነገር ግን መከልከልም አይደለም።
ሥራው እንደተመዘነው የሚመጥነውን ደመወዝ ያገኛሉ›› ብለዋል። ስለዚህ የደመወዝ ጭማሪ አይኖርም። ከሀምሌ ወር ጀምሮ ግን ሥራን በነጥብ ምዘና ስርዓት ወደሚደረግበት ስኬል ሽግግር እንደሚካሄድ አብራርተዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ አነስተኛ የደመወዝ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ደረጃው የሚያመጣው ልዩነት ቢኖር በእነርሱ ይጀመራል። ደመወዙ በደብዳቤ ተገልጾ ተሰጥቷቸው ልዩነቱ የሚከፈላቸው ኢኮኖው የተሻለ ሲያመነጭ ነው ተብሎ የሚታለፉም መደቦች ይኖራሉ።
በዚህ ለውጥ ሠራተኛው የተሻለ ደመወዝ አያገኝም የሚባልበት ዕድል ግን በጣም ያነሰ ነው። ሥራዎች በተለያዩ መመዘኛዎች በልጽገው፣ ፈታኝ ሆነው ቀርበዋል፣ የዛን ያህልም የሚጨምረውን ነገር ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም ለሰውየው ተብሎ የሚጨመር ሳይሆን ሥራው ይዞት የመጣው ነው የሚሆነው።
የምዘና ሥራው ከባድና ውስብስብ በመሆኑ፣ የመንግሥት መዋቅሩ መቀያየርና የባለሙያ እጥረት ለመዘግየቱ በምክንያትነት አንስተዋል። የወሰደውም ጊዜ ረጅም መሆኑን አመልክተዋል። የስኬል ሽግግሩ ቀድሞ አለመተግበሩም በብዙዎች ዘንድ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ፈጥሮ መቆየቱን አመልክተዋል።
ትክክለኛ ግንዛቤው ኦሮሚያ ክልል ይሁን አዲስ አበባ ከተማ፣ ትግራይ ይሁን ጋምቤላ ክልሎች የመንግሥት ሥራ ተብሎ በወጣለት ስም እና በውስጡ በያዙት ይዘቶች አንድ ሰው ተመድቦ እየሰራ የትም ቦታ ላይ፣ የትኛውም መስሪያ ቤት ላይ ሆኖ በሥራ እኩል ሰዓት ስለሚሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
«በየትኛውም ዓለም የሥራ ምዘና እና ደረጃ አወሳሰን ፕሮጀክቶች ሲሰሩ የሰራተኛን ደመወዝ ለመጨመር አይደለም» በማለትም በአገር ውስጥ የተሳሳተ ግንዛቤ እንደተያዘበትም ጠቁመዋል።
አነስተኛ ደመወዝ የሚባሉት አስ (የአስተዳደር አገልግሎት)፣ ጥጉ (ጥበቃና ጉልበት)፣ ጽሂ (የጽህፈትና ሂሳብ አገልግሎት) ሲሆኑ፤ እነዚህ መደቦች ደመወዛቸው አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ፕሳ (የፕሮፌሽንና ሳይንስ አገልግሎት) ደረጃ ላይም ሶስትና አራት መደቦች ዝቅተኛ መደቦች ተብለው እንደሚወሰዱ አመልክተዋል። በተለያየ ደረጃ የመንግ ሥትን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ተጠንቶ ቀርቧል።
ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊወስንባቸው የሚገቡ ትላልቅ የውሳኔ ሃሳቦች እልባት አግኝቶ ውሳኔው እንደደረሰ መመሪያው ለየተቋሙ እንደሚላክ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ዘላለም ግዛው