አዲስ አበባ፡- ለመንገድ ግንባታ ተብሎ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጨኪ በምትባል አካባቢ ላለፉት 11 ዓመታት በአንድ ስፍራ የተከማቹ ከባድ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች ባለቤታቸው በግልጽ እንደማይታወቅ ተገለፀ።የአካባቢው ነዋሪዎች ማሽኖቹና ተሽከርካሪዎቹ ለህገወጥ ሥራ እየዋለ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ማሽኖቹ በተከማቹበት ስፍራ በጋራዥ ባለሙያነት ከተቀጠሩት ውስጥ ብርሃኑ ደረሰ አንዱ ሲሆን፤ ማሽኖቹን ከመጠገን ውጭ በግልጽ ንብረቱ የማን እንደሆነ አላውቅም ብሏል። በግቢው ውስጥ ስካቫተሮች፣ ዶዘሮች፣ የከባድና ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎችና ለኮንስትራክሽን ሥራ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው ማሽኖች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ማሽኖቹ በግምት ከ100 እንደማያንሱም ተናግረዋል። ይሁንና ማሽኖቹን በአሳቻ ሰዓት ለሌሎች አካላት እንደሚከራይና ከመንግሥት እውቅና ውጭ የሚፈፀሙ ውሎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
ይህንንም የሚያደርገው በግቢው ውስጥ ለ11 ዓመታት የቆየው አንድ ቻይናዊ ዜጋ መሆኑን ተናግረዋል። እርሳቸውም በጋራዥ ባለሙያ ተብለው ይቀጠሩ እንጂ ቻይናዊው ዜጋ የሚያዛቸውን ሁሉ ለመስራት እንደሚገደዱ ጠቁመዋል። በግቢው ውስጥ የዓሳማ እርባታ የተጀመረ ሲሆን፤ ምንም ፈቃድ እንደሌለውና ለዚህም የሚጠይቀው አካል አለመኖሩን አብራርተዋል።
ቻይናዊው ዜጋ ማሽኖቹ እንደማይሰሩ የሚናገር ሲሆን፤ ከቻይናውያን ውጭ ሌሎች አካላት ወደ ግቢው እንዲገቡ አይፈቅድም ብለዋል። በተደጋጋሚ ጊዜ ለወረዳ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት መረጃ ብንሰጥም የሚከታተለው አካል አጥተናል ሲሉ ምሬታቸውን ገልፀዋል።
ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላ ቸው፤ ማሽኖቹና ተሽከርካሪዎቹ ጨለማን ተገን አድርገው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው፣ መንግሥት ክትትል እንዲያደርግ ተደጋጋሚ ጥቆማ ብንሰጥም ሰሚ አጥተናል ብለዋል። ማሽኖቹ የተከማቹበት ቦታም ምርት የሚሰጥና ሰፊ ቦታ የያዘ ነው።
ይሁንና በየዓመቱ ለመሬት ካሳ ተብሎ ለአርሶ አደሮች ብር እንደሚሰጥና በህጋዊ ውል ያልታሰረ እንደሆነም አብራርተዋል። ንብረቱ የመንግሥት ነው ከሚለው አሉባልታ የዘለለ ምንም መረጃ እንደሌላቸውም አመልክተዋል።
በአንድ ስፍራ የተከማቹ መሳሪያዎችን ላለፉት 11 ዓመታት ሲጠብቁ የነበሩት አቶ ያደቴ ፈይሳ በበኩላቸው፤ ባለቤቱን በግልጽ እንደማያውቁና ለምን ዓላማ እንደሚውልም ግንዛቤው እንደሌላቸው አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደብረብርሃን ወደ መቀሌ የሚያልፈውን መንገድ በአስፋልት ሲገነባ ሥራ ላይ የነበሩ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎች አንድ ቦታ እንዲቀመጡ ተደርጓል ከሚለው ተባራሪ ወሬ ባሻገር ምንም መረጃ የለኝም ብለዋል። ይሁንና አንድ ቻይናዊ ግቢው ውስጥ እንደሚኖርና ንብረቶቹን በበላይነት እንደሚቆጣጠር ገልጸዋል።
ቻይናዊው ማሽኖቹን ወደፈለገው ቦታ የማንቀሳቀስ መብት እንዳለውና ከእርሱ ውጭ ማንም ሰው የመቆጣጠር መብት እንደሌለው ጠቁመዋል። እርሳቸውም ላለፉት 11 ዓመታት የጥበቃ ሠራተኛ ይሁኑ እንጂ ማሽኖቹ ስንት እንደሆኑ በቁጥር አልተነገራቸውም። የቅጥር ሁኔታቸውም በህጋዊ መንገድ የተከወነ ሳይሆን በቃል ስምምነት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮርዳኖስ ተከስተ በበኩላቸው፤ ማሽኖቹና ተሽከርካሪዎቹ ለረጅም ዓመታት በአንድ ቦታ ስለመቀመጣቸው ብቻ ጥሬ መረጃ እንዳላቸውና ዝርዝር የሆነውን ነገር እንደማያውቁ ጠቁመዋል። ንብረቱ በግልጽ የማን እንደሆነም መረጃ የለኝም ብለዋል።
ይሁንና ቀደም ሲል የነበሩ የወረዳው አስተዳዳሪዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ እንደቀረበላቸው በመግለፅ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑና ጉዳዩን የሚከታተለው ሌላ አካል በመሆኑ ጥልቅ ግንዛቤ የለኝም፤ የንብረቱ ባለቤትም ከወረዳውም ጋር የገባው ውል ስለሌለ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። በህገ ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ ይውላል ስለሚለው ነገርም መረጃ እንደሌላቸው አስገንዝበዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደብረብርሃን አካባቢ መንገድ ጥገና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ሀብቴ በበኩላቸው፤ ማሽኖቹ ለረጅም ዓመታት ስለመቀመጣቸው እንደሚያውቁና ነገር ግን ባለቤቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።
ምናልባትም መንገዱን ሲሠራ የነበረው የቻይናው ሲ.አር. ቢሲ የተሰኘ ኩባንያ አሊያም ደግሞ ሌላ ተቋራጭ ሊሆን እንደሚችል ከመገመት በዘለለ በውል እንደማያውቁት አብራርተዋል።
ይሁንና ማሽኖቹ ለ11 ዓመታት በአንድ ስፍራ የተቀመጡበት አግባብ ግልጽ ባይሆንም በመንግሥት አሠራር መሰረት እንዲህ ዓይነት ተግባር ቦታ የለውም ብለዋል። ምናልባትም አካባቢውን የሚያስተዳድረው አካል ጉዳዩን በዝርዝር ሊያውቀው እንደሚችል ጠቁመው፤ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡን የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኝ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ቢደወልም ስልክ ባለማንሳታቸው መረጃ ማግኘት አልተቻለም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር