አዲስ ዘመን ድሮ

በሳምንታዊው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960ዎቹ በወቅቱ የተዘገቡ ዜናዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ለማስታወስ መርጠናል። ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ ወቅቱን ተከትሎ የተከሰቱ አደጋዎችና ሌሎች ጉዳቶችን የዳሰሱ ዘገባዎችን አካተናል።

በመብረቅ አደጋ ሁለት ሰዎች ተጐዱ

ዐሰበ ተፈሪ፤(ኢ-ዜ-አ-) በጨርጨር አውራጃ በዋጮ ቀበሌ በዘነbው ኃይለኛ ዝናም ምክንያት የጣለው መብረቅ በ፪ ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ። ዕድሜያቸው ፷ ዓመት የሆናቸው አቶ ነጋ አየለ በዚሁ መብረቅ አደጋ ምክንያት ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ እንዲሁም ፴ዓመት ዕድሜ ያላቸው አቶ ዑስማን አደም ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

(ነሐሴ 8 ቀን 1960 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

ድንገተኛ የወንዝ ሙላት የ8 ዓመት ልጅ ወሰደ

መቀለ፤(ኢ-ዜ-አ-) ታደሰ ገብረ መድህን የተባለ የ፰ ዓመት ልጅ ባለፈው ሰሞን ውቅሮ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ወንዝ ውስጥ ገብቶ ሲዋኝ በድንገት ደራሽ ውሃ ደርሶ የወሰደው መሆኑን የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ጽ/ቤት ገለጠ።

ይህ አደጋ እንደተሰማ የሟቹ ወላጆች በሥፍራው ደርሰው በሞት የተለያቸውን የልጃቸውን አስከሬን በሕዝብ ርዳታ እንዲወጣ አድርገዋል።

ይህንን የመሳሰሉትን አደጋዎች በሕፃናት ላይ ሊደርሱ የሚችሉት ከወላጆች ጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ መሆኑን ጽ/ቤቱ በመጥቀስ በዕድሜ ያልበሰሉ ሕፃናት በክረምት ወራት ወደ ወንዝ እንዳይሄዱ ወላጆች ብርቱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል። ( ነሐሴ 8 ቀን 1960 ዓ.ም አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

በሬው ባለቤቱን ከጅብ አዳነው

(ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)

በጨርጨር አውራጃ ጭሮ ወረዳ ያብዶ ኮሎሎ በተባለው ቀበሌ በአቶ ወጋየሁ ወንድማገኘሁ መሬት ላይ እያረሰ የሚኖር አቶ ሙሳ ቡቲ የተባለ ገበሬ፤ሰኔ ፲፭ ቀን ፲፱፻፷ ዓ/ም ከሌሊቱ ፰ ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በአንደኛው ቤት ውስጥ ካሉት ከብቶች መካከል አንዲት ፍየል ጅብ ጐትቶ ሲያወጣት ባለቤቱ ነቅቶ ጅቡን ሲከላከል ሆዱን ነከሰው፣ ሰውየውም የጅቡን አፍንጫውንና አገጩን አፍኖ ሲይዘው ሆዱን ለቆ የቀኝ ባቱን ነክሶ ፲፭ ሜትር ያህል ጐትቶ ሊበላው ሲተናነቅ የጥቁር ጋርማ ጐባ በሬ እውጭ ከታሠረበት ገመዱን በጥሶ ጅቡን ተከታትሎ በማባረር ባለቤቱን ከመበላት ያተረፈው መሆኑንና ሰውየውም በልዑል ሣህለ ሥላሴ ሆስፒታል ታክሞ የዳነ መሆኑን አቶ ወጋየሁ አስረድተውናል። (ሐምሌ 7 ቀን 1960 የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

ኃይለኛ ዝናም ፲፪ ቤቶችን አፈረሰ

አዋሳ (ኢ-ዜ-አ-) በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በአዋሳ ከተማ ሰኔ ፭ ቀን ፷ ዓ/ም/ ነፋስ አስከትሎ የጣለው ኃይለኛ ዝናም ፲፪ ቤቶች አፈረሰ ።በዚሁ ቀን ዝናሙ የዘነበው ከቀኑ ፲፪ ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ፩ ሰዓት ነበር።

ይኸው ኃይለኛ ዝናምና ነፋስ የቤቶቹን ክዳን ቆርቆሮውን ገነጣጥሎ በመጣል በባለንብረቶቹ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ከማድረሱም በላይ ፤በአንዳንድ ሥፍራዎችም የስልክ ሽቦዎችን ቆራርጧል።

ከዚህም ሌላ ዛፎችን ከሥራቸው ነቃቅሎ የጣለ ሲሆን ፤በሰው ሕይወትና በእንስሳት ላይ ግን የደረሰ አደጋ አለመኖሩን የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ረዳት ዋና አዛዥ ኰሎኔል አየለ ወልደ ሥላሴ ገልጠዋል።

(ሰኔ13 ቀን 1960 የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

ባለ አንድ እግሯ ፍየል በሕይወት ትገኛለች

ዓድዋ (ኢ-ዜ-አ-) ባለፈው ፲፱፻ ፶፱ ዓ.ም. የተወለደችው ባለ አንድ እግር የፍየል ግልገል እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት ትገኛች።ግልገሏ የአቶ በሪሁን ምራጭ ንብረት ናት።

ይህችው አስገራሚ ፍጥረት የተወለደችው በዓድዋ አውራጃ ግዛት በዓዲ አበና ወረዳ በእንዳማሪያም ሸዊት ቀበሌ መሆኑን የአውራጃው ጽሕፈት ገለጠ። (ነሐሴ 8 ቀን 1960 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

፫ ሺ ፫ መቶ ጅቦችና ቀበሮዎች ተገደሉ

መቀሌ፤(ኢ-ዜ-አ-) በትግሬ ጠቅላይ ግዛት በራያና አዘቦ አውራጃ ግዛት በበረሀሌና በጸሎም ወረዳ ውስጥ ፪ሺ ፬፻፺፩ ጅቦችና ፰፻፸፬ ቀበሮች መገደላቸውን የትግራይ ልማት ድርጅት የመንገድ ሥራ አላፊ አቶ ገብረክርስቶስ ገብረ እግዚአብሔር ገለጡ።

አቶ ገብረ ክርስቶስ እንደገለጡት ልዑል ራስ ሥዩም ተገኝተው የሸዊትንና የጨርጨር ወረዳ ግዛቶች በጐበኙበት ወቅት በአገሩ ላይ የጅብና የቀበሮ መንጋ ተነሥቶ በሰውና በእንስሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን ሕዝቡ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ሁኔታውን ከመረመሩ በኋላ ፤የጅብና የቀበሮው መንጋ በየጊዜው እንዲጠፋ ካልተደረገ ወደፊት ከፍ ያለ ጉዳት እንደሚያስከትል በመገንዘብ ፤ጉዳዩ ከሚመለከተው መሥሪያ ቤት ጋር ተነጋግረው ባስፈቀዱት መሠረት ፤ በትግራይ ልማት ድርጅት አማካይነት የሚመረጡ በየወረዳዎቹ ተቋቁሞ በተደረገው ዘመቻ ከላይ የተጠቀሱት አውሬዎች በመድኃኒት ርዳታ ተገድለዋል።

(ሰኔ 12 ቀን 1960 የታተመው

አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተሠራ የጣሳ ሥጋ ወደ እንግሊዝ ይላካል

ድሬዳዋ ፤(ኢ-ዜ-አ-) ቻንድረስ አፍሪካ የተባለው የሥጋ ፋብሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የታሸገ ሥጋ ወደ እንግሊዝ አገር ሊልክ ነው።

ድሬዳዋ ከተማ ያለው ይህ የሥጋ ፋብሪካ ከእንግሊዝ ወታራዊ ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፤ በጣሳ የታሸገ የኢትዮጵያ የቀንድ ከብቶች ውጤት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደዚህ አገር ይሰድዳል።

በኢትዮጵያ የተሠራው የታሸገ ሥጋ በውጪ አገር ዘንድ በጣም ተፈላጊነት ያለውና ከሌሎች የዓለም ሥጋ ፋብሪካዎች የሚወዳደር መሆኑን የሥጋው ፋብሪካ አላፊ ገለጡ።

አሁን ወደ እንግሊዝ አገር የሚሄደው የታሸገ ሥጋ፤ በቻንድራ አፍብሪካ ገና ተሠርቶ ያላለቀ ሲሆን፤ከሥር ከሥሩ ወደዚሁ አገር እንደሚላክ አላፊው ሲገልጡ፤ ምን ያህል ጣሳ ሥጋ እንደሚላክ ለመጥቀስ አልፈቀዱም።

ይሁን እንጂ ብዛት ከፍ ያለ ሥጋ በልዩ ቅመም ተቀምሞ ወደ እንግሊዝ አገር የሚላክ መሆኑ ተገምቷል።

(ሰኔ 2 ቀን 1960 የታተመው አዲስ

ዘመን ጋዜጣ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You