አዲስ አበባ፡- የአገሪቱ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን በሰላምና በመነጋገር ብቻ ለመፍታት የተስማሙበትና መላ ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተው ቃል ኪዳን ተጥሶ ህዝብን የመምራት ኃላፊነት በተጣለባቸው የፖለቲካ መሪዎች ዘንድ ወደ ተለመደው የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ የሚያስገባ ድርጊት መከሰቱ በእጅጉ እንዳሳዘነው የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ትናንትና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች እና በአገር መከላከያ ጀኔራሎች ላይ በተፈጸመው ግድያ በእጅጉ ማዘኑን አስታውቋል። በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት በህዝብ ላይ በሚደርሱ መፈናቀሎችና ግድያዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል። ለችግሮች መፍትሔ ለማፈ ላለግ በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽን በአ ፋጣኝ ወደ ሥራ ለመግባት ተግቶ ሲሰራ መቆየቱንና ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጿል።
የብሄራዊ እርቅና ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል “ከህዝብ ቀድመው ግጭቶችን ያቆማሉ ባልናቸው የፖለቲካ መሪዎቻችን መካከል ወደተለመደው የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ የሚከት እንዲህ ዓይነት የእርስ በእርስ ግጭትና ግድያ መከሰቱ በእጅጉ አሳዝኖናል” ብለዋል። በመሪዎች ላይ የደረሰው ግድያ በማንም ላይ መፈጸም የሌለበትና ፍጹም መወገዝ ያለበት ተግባር መሆኑን ያሳሰበው ኮሚሽኑ፤ ድርጊቱን በማውገዝ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
በዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው ካለፈው ታሪካቸው በመ ማር ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይትና በህጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት የሚገባቸው መሆኑን አመላክቷል።
የፖለቲካ መሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ በተስፋና ስጋት መካከል ያለው መስመር ቀጭን መሆኑን በመገንዘብ ከመጠላለፍ፣ ከመገዳደልና ከመጠፋፋት ተቆጥበው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለውን ህዝብ ለመርዳት መረባረብ የሚገባቸው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል። በመንግሥት በኩልም ችግሩን ተከትሎ እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ የሚወሰደው እርምጃ ሌላ የቅራኔ በር እንዳይከፍት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሆን ኮሚሽኑ ጠይቋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ችግሮችን ለመፍታትና ኢትዮ ጵያውያን በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በንግግርና በውይይት ብቻ መፍታት እንዲችሉ፣ ፍትህ እንዲያገኙና እርቀ ሰላም እንዲያወርዱ በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለውጡን በሚመሩት አካላት ላይና አሁን ባለው የአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አልተደመጥኩም የሚል አካል ካለም ኮሚሽኑ ችግሩን አዳምጦ መፍትሔ ለመስጠት በሩ ክፍት መሆኑንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ይበል ካሳ