አዲስ አበባ፡- ጀማሪ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ልምድ እና እውቀት ካገኙ በኋላ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች በከፍተኛ ክፍያ ሠራተኞችን እያስኮበለሉ በመሆኑ ሥራው ላይ ጫና መፍጠሩን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የ2011 በጀት ዓመት የ11 ወር እቅድ አፈፃፀም ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፤ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል። ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በቀለ ሙለታ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ጀማሪ ባለሙያዎችን ሲቀጥር ከ3ሺ500 ብር በላይ ስለማይከፍል በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች ተቋማት ከፍተኛ ክፍያ ስለሚፈጽሙ ባለሙያዎችን ለማግኘት ተቸግሯል።
በዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ተቀጥረው ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ደግሞ በሌሎች ተቋማት በ10ሺ ብር እና ከዚያ በላይ እየተቀጠሩ በመሆናቸው የሠራተኞችን ፍልሰት ለማቆም አለመቻሉን አስረድተው፣ችግሩ እንዲቃለል ቋሚ ኮሚቴው ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ለሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዜና ከመመገብ አኳያም ችግሮች መኖራቸውን አቶ በቀለ አብራርተዋል። ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዜናዎችን ለመጠቀም ክፍያ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልሆነም። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደግሞ አዳዲስ መረጃዎችንና በሌሎች ሚዲያዎች ያልተነገሩ መረጃ ዎችን በመፈለጉ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተዘገቡ ወሬዎችን ከመጠቀም መቆጠቡን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፤ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእቅድ አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኬሚያ ጁነዲ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በርካታ ጥንካሬዎች እንዳሉት በመግለፅ አገር አቀፍ የዜና ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል። በተለይም ደግሞ በክልል ባሉ ቅርንጫፎቹ ጠንካራ የመረጃ ምንጭ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ተቋሙበርካታ አበረታች ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ አያሌ ችግሮች እንዳሉበት ጠቅሰዋል።
ወይዘሮ ኬሚያ የቋሚ ኮሚቴውን አባላት ሃሳብ መሆኑን ዋቢ በማድረግ እንደተናገሩት፣ በወቅቱ ለሌሎች ሚዲ ያዎች መረጃዎችን በማድረስና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ትስስር በመፍጠር ረገድ ውስንነት አለበት። ለተቋሙ አስፈላጊ የተባሉ የሰርቨርና ኤሌክትሮኒክስ ግብ ዓቶችን በመግዛት ረገድም በግዥ በኩል መጓተት ይስተዋላል። የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን የማደራጀት ክፍተት አለበት።
ዋና ዳይሬክተሩ በቋሚ ኮሚቴ ለተነሱ ሃሳቦች በሰጡት ማብራሪያ፣ ተቋሙ አገራዊ እንደመሆኑ መጠን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት እንገነዘባለን ለዚህም እየሰራን ነው ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴው በድክመት የጠቀሳቸውን ችግሮች ለማስተካከል እንደሚሰራም አስገንዝበዋል። ሆኖም ተቋሙ በሠራ ተኞች ፍልሰት ክፉኛ እየተፈተነ መሆኑን አብራርተዋል። ከደመወዝ ማነስ የተ ነሳም በክልል በሚገኙ ቅርንጫፎችም ባለሙያዎችን ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር