– 255 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
አዲስ አበባ፡- ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የደረሰው የጥቃት ሴራ እና ተከታታይ ግድያ በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምርም እርምጃዎችን ለመውሰድ የታቀደ እንደነበር ተገለጸ። 255 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውንና በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ሰኔ 20/2011 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ድርጊቱ በሀሳብ ልዕልናና በሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የማያምኑ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የተፈጸመ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው።
ድርጊቱ ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ወደማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥና እልቂት በማስገባት ስልጣንን በኃይልና በመሳሪያ አፈሙዝ ለመቆጣጠር የተደረገ ግን ደግሞ ያልተሳካ እኩይ ድርጊት ስለመሆኑ ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቀዋል ብሏል።
በሂደቱ የምንጊዜም የለውጥ ኃይሎች ውድ የህዝብ ልጆች በጥፋት ኃይሎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ላይም የህይወትና የአካል ጉዳት ደርሷል፣ የጥፋቱ ዋና አቀነባባሪ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌና ግብረአበሮቹ መሆናቸው በተጨባጭ መረጃዎች መረጋገጡን የግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል።
መንግሥት ለዘመናት በሀገሪቱ የቆየውን የዴሞክራሲ እጦት በማሻሻልና በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባና ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ቢገኝም ጥቂቶች የጥፋት መንገድን መርጠው ህዝቡን ለመከራና ለእንግልት ዳርገውታል ብሏል መግለጫው።
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የክልሉ የፀጥታና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ የነበረ በመሆኑ ለዕኩይ ድርጊቱም ህዝብና መንግሥት የሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የራሱን የስልጣን ጥማት ለማሳካት ጥቂት የፀጥታ ኃይሎችንና አመራሮችን በስሩ በማደራጀት እኩይ ተግባሩን ሊፈፅም እንደቻለ ገልጿል።
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል በነበረበት ወቅት በተመሳሳይ መንገድ በፌዴራል መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት በማካሄድ እያለ ከነ ግብረ አበሮቹ በቁጥጥር ስር ውሎ በህግ ፊት ቀርቦ የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶበት እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ በለውጡ ሂደት በምህረት ቢለቀቅም ግለሰቡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ጥቃቱን በመምራት ከፈፀመና ካስፈፀመ በኋላ መፈንቅለ መንግሥቱ እንደከሸፈና ምኞቱ እንዳልተሳካ ሲረዳ በመሸሽ ላይ እያለ በክልሉ የፀጥታ ኃይልና በህዝቡ እርምጃ ተወስዶበት ህይወቱ ማለፉንም ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
ሀገራዊ ለውጡን በግንባር ቀደምትነት እየመሩ በነበሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፀጥታ አባላትና ዜጎች የህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን የታሰበው የመፈንቅለ መንግሥት ቅዠት በፀጥታ ኃይሉና በህዝቡ ትብብር በጥቂት ሰዓታት ሊቀለበስ መቻሉን አስታውሷል።
በእለቱ መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ ሰዓታት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ላይ በኢታማዦር ሹሙ የቅርብ ጠባቂ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መኮንን የግድያ ጥቃት ሁለቱም አንድ ላይ በነበሩበት ወቅት በጀነራል ሰዓረ መኖሪያ ቤት መፈፀሙንም ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አትቷል።
የፀጥታና የፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል በመግለጫው ጥቃቱን የፈፀመው ግለሰብ በፌዴራል የፀጥታ ኃይል ቆስሎ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ይህ ሴራ ተከታታይ ግድያ በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጭምርም እርምጃዎችን ለመውሰድ የታቀደ እንደነበር ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ይፈልጋል ብሏል።
ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው በአጠቃላይ በአማራ ክልል 212 ተጠርጣሪዎች ከነሙሉ ትጥቃቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማ 43 ተጠርጣሪዎች 2 መትረየስ 27 ክላሽ ጠመንጃዎችና በርካታ ሽጉጦች ከነ መሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም ከተለያዩ የጥቃት ማስፈፀሚያ እቅዶችና ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጣራባቸው ይገኛል ተብሏል።
በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች የተፈፀመውን ጥቃት ግንኙነት ስለመኖርና አለመኖሩ በቀጣይ በምርመራ በመለየት እንደሚያሳውቅ የገለፀው ግብረ ኃይሉ፣ መላው ህዝብና መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ማንኛውም ዜጋ ሀሳቡን በነፃነት እንዲገልፅ መንግሥታዊ ስልጣን ከነፍጥ ይልቅ በሰለጠነ መንገድ በህዝቦች ይሁንታና ስልጣን ህዝብን ማገልገያ ብቻ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ድልነሳ ምንውየለት