የደበዘዘች ጽጌረዳ

የብዙ የሀገራችንን ዝነኞች ጓዳና ጎድጓዳ ተመልክተናል። እንደ ክብር ኒሻን ያንጠለጠሉትን የስኬት ቁልፎቻቸውንም ተመልክተን ከሥራዎቻቸው ጋር ምስጋናንም ችረናቸዋል። በታሪኮቻቸው ተደንቀናል። ከሕይወታቸው ተምረናል። በደፉት የታላቅነት ዘውድ፣ በደረቡት የዝና ካባ ላይ እጅግ ብዙ ብዙ ተመልክተናል። አንዳንዴ ግን እንዲህም አለ…የኑሮ ውብ ሸክላ ተሰንጥቆ የሞላው የሕይወት ውሀ ሲፈስ… ደግሞ ሲጎድል ሁሉን አጥቶም ባዶ ጥቁር ጋን ታቅፎም ይኖራል።

ከዝነኞቹ መንደር ዝናና ስኬት ብቻ ሳይሆን የፈራረሰ ደሳሳ ጎጆ፣ ከጎጆው በታችም ጥልቅ የሕይወት ጉርጓድ የሚታይበት ሌላ ምዕራፍ አለ። ከዚያ ወድቀው እኛም ደርሰን ያወጣናቸውና ዳግም ያቆምናቸው ምናልባትም አሉ። ግን ደግሞ የወደድናቸውን ያህል ዘንግተናቸው በማጥ ውስጥ ተዘፍቀው ማቅ የለበሱም በርክተዋል። የሙዚቃ ፍቅራችንን አለምልመው፣ ከስራዎቻቸው ጣፋጭ ፍሬን ካቀመሱን የ90ዎቹ ጽጌረዳዎች መሀል አንዷንም እንዲህ ናት… ከስኬቷ ማማ ላይ ብቻም ሳይሆን ከሕይወቷ ደረጃዎች ላይም ወድቃ ውስጧም ጭምር በመሰበሩ ከሁሉም በላይ አሳዛኝ ያደርጋታል። በጸደይ፣ በመስከረም በልምላሜ ፈክታ ከሁሉም አበቦች ውብ መስላ ትታይና ብዙም ሳትርቅ በበጋው ደረቀች። ንፋሱም ቅጠሎቿን አረገፈው። ታዲያ እንዲህ ስትጠወልግ ጽጌረዳ ለምንስ አታሳዝን?… በእንባ ስትታጀብ፣ ስትኮሰምን ጽጌረዳ እንዴትስ አንጀትን አትበላ?…ጊዜ ጌታው እንዳነሳ መልሶ ሲጥል ሕይወትም እንደበረዶ እየቀዘቀዘች አንሸራታ ስትጥል ያሳዝናል። ልብ ይሰብራል። ይኼ ሁሉም የድምጻዊቷ የቤተልሔም መኮንን ጥቁር ጥላ ነው።

ቤተልሔም መኮንን ሲባል ስንቱ እንደሚያስታውሳት አላውቅም። ስሟን የተሸከመውን ሥራዋን ጠርቼ “አነጋግረኝ” ብል ግን ሙዚቃን የሚወዱ ልቦች ሁሉ በደስታ አስታውሰው “አቤት ግሩም ሙዚቃ!” እንደሚሉ ጥርጥር የለውም። ያኔም ቢሆን አሁን በሙዚቃዋ ፍቅር ተለክፈው ለልባቸው ማሰሪያ ያጡ እንደሞሉ ናቸው።

“መውጫ መግቢያህን ጠብቄ፤

አይሀለሁ ከሩቅ ሠርቄ

ውስጥ ውስጤን ፍቅር ጨረሰኝ

መጥተህ ባክህ አንድ በለኝ…

እሂያ! ሂያ ሂያሂ… ሁ… ሁ”

ይህ ሥራዋ በጊዜው እንደ አንድ ቆንጆ የሙዚቃ ክሊፕ ታይቶ ብቻ የታለፈ አልነበረም። ይህ ሥራ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ክሊፕ ሥራዎች ውስጥ በሁሉም ነገሮች ፈር ቀዳጅ የነበረና ቀድሞ ከነበረው አንድ ከፍታ የተጨመረበት የተለየ ሙዚቃ ስለመሆኑ ብዙዎች ተናግረውለታል። ከቀረጻውና ከሙሉ የሙዚቃው ግብአት ጀምሮ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ታይተውበታል። እንዲያውም የዘመናዊው ሙዚቃ አብዮት የፈነዳበት ነው ሲሉ የሚያነሱም እንዲሁ ጥቂት አይደሉም። በሥራው ላይ ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የወጡ ወጣቶችን ጨምሮ ከ23 በላይ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ቅንብሩን በተለየ ሁኔታ አሳምሮና ከሽኖ ያዋሀደላት አቀናባሪ ደግሞ ባደግ በቀለ ነበር። ነገር ግን ባደግ ብዙም ሳይቆይ ከሀገር ወጣ። የድምጽዋን ሙያዊ ልኬት ተረድቶ በትክክለኛው ብቃቷ ላይ ያሳረፋት እርሱ ነውና ከሀገር መውጣቱ ለቤተልሔም ጥሩ አጋጣሚ አልነበረም። “አነጋግረኝ” እርሷን ከማሳወቅ አልፎ ተቀጽላ ስሟ ለመሆን የበቃ ቢሆንም ብቸኛው ሥራዋ ግን አይደለም። “ሀብል” የተሰኘ አንድ የአልበም ሥራም አላት። አልበሙን ጨምሮም በድምሩ 15 ያህል ሙዚቃዎችን ሠርታለች። ከ”አነጋግረኝ” በመቀጠልም “የት ነው” የተሰኘው ዜማዋም ተወዳጅነትን ያተረፈላት ሥራ ነው።

“የት ነው የማገኝህ

የት ነው የምፈልግህ

ለኔ የተባልክ ሰው

ለኔ የተፈጠርከው”

ዛሬም ድረስ እንደ ዓይን ብሌናችን እያየን ከምንሳሳላቸው የምን ጊዜም እንቁዎች ጋር ልንመለከታት ልትሆን የምትችል ባለተስፋ ወጣት የነበረች ቢሆንም ነገሩ እንዳልታሰበ ሆኖ ቆይቶ ነበር። መቼም ድምጽዋ እንደሆን ለሙዚቃ የሰጠ ነበር። ገና የ17 ዓመት አፍላ ወጣት ሆና በ90ዎቹ አጋማሽ ላይ “አነጋግረኝ”ን ስታወጣ ጆሮ ብቻም ሳይሆን አፍም ጭምር አስከፍታ ነበር። በጣም ተወዳጅ ከመሆኑ የተነሳ የሙዚቃ ቡፌ በተደረደረበት ገበታ ላይ ሁሉ ይገኛል። አሁን ላይ የ90ዎቹ ሙዚቃ ከምን ጊዜም በላይ እጅግ ተወዳጅና ተመራጭ ሆነዋል። ከዘመን ይልቅ እንደ አንድ የሙዚቃ ምድብ እየታዩ ያለ ይመስላል። የወይን ጣዕሙ እየተንጠፈጠፈ የሚወጣው እየቆየ በሄደ ቁጥር እንደ ሆነ ሁሉ የ90ዎቹም ይበልጥ እያስጎመዡ መጥተዋል። ቀዳሚውን ስፍራ ከያዙት መሀከልም ቤተልሔምና ሙዚቃዋ “አነጋግረኝ” ይገኙበታል። እንዲሁ ዓይነቶቹን ብዙ ልታስደምጠን እያሰበች ባለችበት ሰዓት ላይ ነበር ሕይወት እንደማይፈታ ትብታብ ተወሳስቦባት ከመንገድ የቆመችው። ገና ስትመጣ የነገውን ትልቅ ተስፋ ቢጣልባትም ነገር ግን ሳይሆን ቀረ።

ቤተልሔም መኮንን ወደ ሙዚቃው በተቀላቀለችበት ሰሞን ገና የ17 ዓመት ልጅ ነበረች። በፊት ተጫዋችና በሥራም ይሁን በሌላው ፈጣንና ተግባቢም ነበረች። ትንሽ ሳለች ጀምሮ በባህሪዋ ብዙዎችም ይወዷታል። ነገሮችን መሞከርና ሁሌም ማንጎራጎር ሥራዋ ነበር። ሙዚቃውን ሳትጀምር አስቀድሞ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥም የድምጽ ተማሪ ነበረች። ከዚያ በኋላ ነበር አብረዋት ከተማሩት ጋር “አነጋግረኝ”ን ለመሥራት የተነሱት። ሙዚቃው በተለቀቀ ማግስት ሕይወት ለቤተልሔም እንደ መስከረም ጸሐይ ወገግ ብላ ፈነጠቀች። በአንድ ጊዜ የዝና ማማ ላይ ተሰቀለች። ሙዚቃው ተደምጦ አያበቃም ከየአቅጣጫው ይደጋገማል። ምቱ ዛሬም ድረስ ከብዙዎች ልብ ላይ እንዳለ አለ። በዚሁ ቀጥሎ ብዙ ራዕይ ብዙ ተስፋ ሰንቃ ነገንም እያሰበች ነበር። ሕይወት ባዳ ተስፋና ሕልምም ከሀዲ ናቸው፤ አንድ ቀን ክህደትን ይፈጽማሉ። ሁሉም እንዳልነበረ ሆኖ ሲቀርም እጅግ ያማል። የወጡበት ከፍታ መልሶ ያንኑ ያህል ሲፈጠፍጥ የጭለማውን ገደል መውጣት እጅግ ፈታኝ። የማለዳ ጸሐይ ለመምሰል የሚቻላት ሕይወት ከዚያ በበለጠም የምሽት ድቅድቅ ጭለማ መሆንን ትችልበታለች። ይህች ዓለምም በወረት የናወዘች መጥፎ ወረተኛ ናት። ማሸርገድም መሸርከትም ለሷ ቀላል ነው። ያቺ ፍንድቅድቋ አፍላ ወጣት እምብዛም በዚያ ሳትቆይ በሌላ አስፈሪ የሕይወት እረመጥ ውስጥ ገባች። ሀገሩ ሙሉ በእርሷ ሙዚቃ ዳንኪራውን ሲመታ እርሷ ግን በከባድ የአዕምሮ ጭንቀት ውስጥ ነበረች። ዕለት ዕለት ስቃይዋ እየባሰ ሄዶ በጨለማው የሕይወት ዋሻ ውስጥ ወደቀች። በሙዚቃዋ በሰጠችው ደስታ ሌላው ሲፍነከነክ እርሷ ግን በመራራ የእንባና የሀዘን አጀብ ውስጥ ተሸጉጣ ነበር። አንዳችም ኑሮ ኑሮ፣ አንዳችም ሕይወት ሕይወት አይሸታትም ነበር። በዚያ ሰሞን የገጠማትን ነገር ማንም ልብ ብሎ ያስተዋለ አልነበረም። በማይነጋ የቀን ሌት ጭለማ ውስጥ መዘፈቋን ጠርጥሮ የፈለጋትም አንድም የለም። ከአቅሟ በላይ ሆነና ቤቲ የአዕምሮ ሕመምተኛ፣ የሕይወት ቁራኛ ሆነች።

“ቤቲ እኮ እየዘፈነች ነው አሉኝ። ደግሜ ብጠይቅ አዎ እየዘፈነች ነው አሉኝ። ከዚያም ዘሬን ተመልክተሽዋል የቄስና የመነኩሴ ልጅ ነኝ…ብዬ ብላት እማዬ በምትወጂው ገብርኤል ይዤሻለሁ እማዬ! ስትለኝ እኔም ተውኳት” አሉ የቤተልሔም ወላጅ እናት። አባቷ የሚኖሩት ከእነርሱ ተለይተው በመሆኑ ከልጅነቷ ጀምሮ ለማሳደግ በኑሮ ብዙ መከራን ያሳለፉባት ልጃቸው ናት። አሁን ደግሞ ቤተልሔም የሁለት ልጆችም እናት ናት። እናቷ ማንም የሌለበትን የሰቆቃ ዘመን ከእርሷ ጋር አሳልፈዋል። ድምጻዊቷን ከወዴት ገባች ምንስ ነካት ብሎ ፍለጋ የወጣ አልነበረም። ከረዥም ጊዜያት በኋላ ግን እናቷ ራማ በተሰኘ ሚዲያ ቀርበው የሆነችውን ሲናገሩ ተሰማ። በቃለመጠይቁም በአዕምሮ ሕመም ተይዛ ተኮራምታ ከቤት ውስጥ መቅረቷን ተናገሩ። ”ቤቲ እኮ ጥሩ ልጄ ነበረች። ልጅ ሆና እንኳን እንደ ልጅ ይህቺን ታህል! ጫፏን ነክቻት አላውቅም ነበር። ሌሎቹን በሚጥሚጣ እያጠንኩ ነበር ያሳደኳቸው እሷን ግን… በሰፈር ውስጥ እንኳን ሰው ቀና ብላ የምታይ አልነበረችም። ግን እንዴት እንዳገኘብኝ አላውቅም!…እኔ ከሞትኩ ልጄን የቀን ጅብ ነው የሚበላብኝ፣ እሷ ጠዋት ከሞተች እኔ ማታ ልሙት ነው ፈጣሪዬን የምለው…” በማለት እንባ ከዓይኖቻቸው እየፈሰሰ ልባቸው በሀዘን እየደማ ብሶታቸው ገንፍሎ በእናት አንጀት እንዲያ ሲብሰከሰኩ ለተመለከተ ልብን የሚሰብር ነበር። ከደረሰባት ከአዕምሮ ሕመም በተጨማሪ ኩላሊቶቿም ከጥቅም ውጭ ስለመሆናቸው እናት ገልጸውታል። ከዚህ በኋላ የነበራት ሕይወትም በሕክምናና በፀበል የቆመ ነበር።

ቤተልሔም መኮንን “አነጋግረኝ”ን ባወጣችበት ሰሞን ጤንነት እየተሰማት አልነበረም። ተጫዋችና በሳቅ የሚጥለቀለቀው የልጅነት ፊቷም እንደቀድሞው የሚያበራ አልሆነም። አልፎ አልፎ ድንገት ውልብ የሚልባት ሀሳብና ጭንቀት ፊቱን አጥቁሮና እሳት ለብሶ ከፊቷ ላይ ድቅን ያለ ይመስላል። ሕይወትም መልኳን ቀይረችባት። ቤተልሔም በአዕምሮ ጭንቀት ተይዛ፣ የአዕምሮ ሕመምተኛ ሆነች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከሙዚቃ ወዲያ እራቀች። ከደጅ ለመውጣት እንኳን አልቻለችም። ከቤት ውላ አድራ ከቤት ውስጥ ብቻ ቀረች። አጠገቧ የነበሩትና ስቃይዋን ሁሉ የተሸከሙት እናቷ ነበሩ። ከሕመሟ የተነሳ ማንነቷ ብቻም ሳይሆን መልክና ደምግባቷም ጭምር እርቋት ነበር። ጠቋቁራና አመዳይ ለብሳ ሌላ ሰው ሌላ ቤቲ ሆነች። በዚህ ወቅት ስሟ ገኖ ሀገር ምድሩ ቤቲ…ቤቲ እያለ የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን በድንገት ከደጅ ላይ ወጥታ የተመለከታት ጎረቤት እንኳን ማን እንደሆነች አያውቅም ነበር። ምክንያቱም በሰዓቱ ባደገችበት ሰፈር ውስጥ ባለመሆኗ ሙዚቃው ላይ ያለችውን ወፍ መሳይ ባለማራኪ ድምጽዋን ልጅ እንጂ እንዲህ በአዕምሮ ሕመም ተይዛ የምትጎሳቆለዋን ቤተልሔም መኮንን የሚያውቅ አልነበረም። ያ ጊዜ ለእርሷ የሰቆቃ፣ ለእናት ደግሞ የመከራ ዘመን ነበር። ጥቂት ወዳጆቿና የሙዚቃ አጋሮቿ ሊረዷት ቢሞክሩም ጤንነቷን መልሶ ዳግም እርሷን ከሙዚቃ ጋር መመልከት የሚቻል አልነበረም። እነርሱም ተስፋ ቆርጠው ሳይደክሙ አልቀረም። አሁንም ከእናት ጋር ብዙ ሕመም…ብዙ ስቃይ…ብዙ የተከረቸመ መውጫ አልባ ሕይወት ቀጠለ…

ከዘመናት በኋላ ችግሯ አደባባይ ወጥቶ ብዙኀኑ አወቀላት። “ለማመን የሚከብድ የቤተልሔም መኮንን ሕይወት፣ ቤቲ አነጋግረኝ ምን የገጠማት…” እየተባለ ከብዙ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተራግቦም ነበር። ትልቁ ችግራችን አስቀድሞ መፈለግና ቀድሞ መድረስ ላይ ቢሆንም፤ ነገር ግን የአንዱን ችግር ከሰማንና ከተመለከትን በኋላ ግን ጆሮ ዳባ ብለን ለማለፍ የምንችል አይደለንም። አስታውሶ የጠፋን ያለመፈለግና የመርሳት አባዜ እንጂ በሰብአዊ ማንነታችን ላይ የመደራደር አቅሙ የሌለን፣ በሁለት በኩል የተጠፈጠፍን ምስኪኖች ነን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን። ቤተልሔም መኮንን በሕመም መክረሟን የሰማ ሁሉ እርሷን ለመርዳት በየፊናው ያልተሯሯጠ አልነበረም። በሕክምና በነበረችበት ሰዓትም ኢትዮጵያዊነት ማለት መልካምነት ስለመሆኑ ያስመሰከሩ ብዙ ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ዶክተርና ሌሎች ጥቂት ወዳጆቿ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። አልጋ ይዛ ሕክምናዋን በመከታተል ላይ ሳለች ከውጭ እየተመላለሰ የሚያክማት አንድ ዶክተር ነበር። ወዳጆቿም ካሰባሰቡት ገንዘብ ለዶክተሩ ቢሰጡትም ገንዘቡን አልፈልግም በማለት “ወርም ይሁን ዓመት ሕክምናዋ የፈጀውን ጊዜ ያህል በራሴ ወጪ አክማታለሁ” በማለት ያለአንዳችም መታከት ሲረዳት ቆየ። ከዶክተሩ አልፎ ባለቤቱም ጭምር ድጋፍ ስታደርግ ነበር።

እጅግ ጭንቅ የበዛበት የመከራ ጊዜዋ ከሁሉም በተለየ በ2013 ዓ.ም ነበር። እርግጥ ነው በሕክምናው እንድትድን ከዶክተሩ ጀምሮ ብዙዎች የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። መልካምነት የተሞላበት ጥረት ሁሉ ስኬታማ ይሆናል ማለት አይደለም። ስኬታማ አለመሆኑም በጎ አድራጊውን ከበጎነቱና ከልፋቱ ዋጋን አያስቀንስበትም፤ ማድረግ ያለብንን የግል ድርሻችንን እስከተወጣን ድረስ ሁሌም መልካም ሁሌም ስኬታማ ነን። ቀሪው የሕይወትና የሕይወት ሠሪው ፈንታ ናቸው። በሕክምናው በነበረው ርብርብ ውጫዊ አካሏን እንጂ መንፈስና ማንነቷን ለማግኘት በጣሙን አስቸጋሪ ሆነ። ከዚህ በኋላ ቤተልሔም በቀጥታ ወደ አንጎለላ ተወሰደች። በዚያም በገዳም ውስጥ እንድትሰነብት ተደረገ። ወደ ሰሚነሽ ኪዳነምህረት ገዳም ገባች። ከ6 ወራት በላይ በእምነቷ አጽንታ ፀበሉን ስትወስድና እምነቱን ስትቀበልም ቆየች። ከዚያ በኋላ ነበር በአንድ ወቅት በኢቢኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርባ “አሁን ደህና ነኝ። ችግሬን ተረድታችሁ በገንዘብና በጸሎት አብራችሁኝ ከጎኔ ለቆማችሁ መልካም ወዳጆቼና መልካም አድራጊዎች በሙሉ ከልቤ አመሰግናለሁ። ውለታችሁን ሁሉ እርሱ ፈጣሪ ይመልስላችሁ” ስትል በደስታ ተሞልታ ወደ ጤንነቷ ስለመመለሷ ተናገረች። የእርሷ ወደ ጤንነቷ መመለስ ከማንም በላይ ለእናት ዳግም ውልደት ነበር። ያለ እንቅልፍ ያደሩባቸውን ሌሊቶች እያስታወሱ ከዚያ የልብ ስብራትና እንባ ተመልሰው በፈገግታ ቆሙ።

“…ብድር ይግባችሁ! ልጄም ደህና ሆና በጣም ጥሩ ለውጥ ነው ያየሁት። ከአሜሪካን ሀገር ብቻ ወደ 4 መቶ 50 ሰው ነው የደወለው። ከእንግሊዝ፣ ከጣሊያን የሰማ ሁሉ ከየሀገሩ እየደወለ ይጠይቃል። ሕዝቡ አሁን በቃ መደወል…መደወል ነው። ቤተልሔም መኮንን ግርማ እንወዳታለን፣ እናደንቃታለን፣ ልንረዳት እንፈልጋለን ነው። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም፣ ቀንቋውን የማይችለው ሁሉ ይደውላል። ስልኩ ሲጮህ ውሎ እንዲህቹ በሱ ተጠምጄ ሃሎ! ስል…ሃሎ! ስል ምግብ እንኳን ሳልበላ ጾሜን የዋልኩት ቀንም አለ” ሲሉ በደስታ ከምስጋና ጋር ቀርበው ታዩ። ቤተልሔም በሕመም በነበረችባቸው ጊዜያቶች እናቷ የተሸከሙትን አይቶና ሰምቶ፣ እንደ ሻማ እየቀለጡ በመስዋዕትነት ከቆሙበት ጨለማ አልፈው ዛሬ እንዲህ ለመታየት የሚበቁ አይመስሉም ነበር። “…ለእናቴ ቤት ገዝቼ ከፎቅ ላይ እሰቅላለሁ አልኩ እንጂ፣ መኪና ገዝቼ አንቺን ከገዳም አዞራለሁ ስል አስብ ነበር እንጂ፤ አንድም ቀን ጥርስና አይንሽን አጠፋለሁ፣ ላንቺ ስቃይ ሆኜ እንደዚህ እጎዳሻለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። …እናቴ ይቅር በዪኝ! ብላ ከጉልበቴ፣ ከጫማዬ ስር ተደፍታ አለቀሰች። እናቴ ገደልኩሽ ብላ ከስንት ዘመን በኋላ በዚህ ሰሞን ሳመችኝ። እኔም በጣም ደስ አለኝ!” በማለትም ከሕመሟ ካገገመች ወዲህ ስላሳየችው ትልቅ የማንነት ለውጥ አብስረዋል።

“አሁን ወደ ሥራዬ ለመመለስ እፈልጋለሁ። ከራቁት ሕዝብና የሙዚቃ አፍቃሪ ወዳጆቼ ጋር ዳግም ለመገናኘት እፈልጋለሁ። ግጥምና ዜማም የምሞክር ብሆንም በሥራው ደግፈው ከጎኔ ለመቆም የሚችሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ያስፈልጉኛል። በየትኛውም በኩል ሥራዎቻቸውን ሊሰጡኝና አብረውኝ ሊሠሩ ለሚፈልጉ ሁሉ እኔ ዝግጁ ነኝ” ስትል በቅርቡ ሚዲያ ላይ ቀርባ የቀጣይ ሕልሟን አጫውታለች። አሁን ሁሉም ነገር ሠላም የሆነ ይመስላል። ያጎደለችውን የጥበብ አካል መልሳ ሙሉ አድርጋዋለች። ደረቁ የሕይወት በጋ አልፎ ክረምቱም ይመጣል። የደረቀች ጽጌረዳም ትለመልማለች። ትላንት የተለየ፣ ዛሬም እራሱን፣ ነገም ሌላ ቀን ነው። ከእርሷም ብዙ ሌላ እንጠብቃለን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን  ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You