ካልተዘመረላቸው አርበኞች

አንዳንድ አርበኞች በኪነ ጥበብ ሥራዎችና በተለያዩ ታሪካዊ ሰነዶች ላይ ስማቸው ተደጋግሞ ይጠቀሳል። በዚህም ምክንያት በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ደምና አጥንታቸውን ለአገራቸው ገብረው ብዙም ሲዘመርላቸው አይሰማም። በእርግጥ የአርበኛ ዓላማውም አገሩን ማዳን እንጂ ዝማሬ እና ዝና ማግኘት አይደለም። ያም ሆኖ ግን አገራችንን ክብሯን አስጠብቀው አስረክበውናልና ሕይወትና ሥራዎቻቸውን እናስታውሳለን።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ109 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 2 ቀን 1907 ዓ.ም የተወለዱትን አርበኛ ኪዳኔ ወልደመድኅን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ።

ከ13 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም ጎረቤታችን ደቡብ ሱዳን 98 በመቶ ድጋፍ ባገኘ ሕዝበ ውሳኔ ከሱዳን ተለይታ ሉዓላዊት አገር ሆነች።

ከ22 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 2 ቀን 1994 ዓ.ም የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተካው የአፍሪካ ሕብረት በደቡብ አፍሪካ ደርባን ተመሰረተ። ስያሜውም ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ ዛሬው ስሙ አፍሪካ ሕብረት ተቀየረ። ዋና መቀመጫው ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ቢኖሩም በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ጠንካራ ትግል ባለበት እንዲጸና ተደርጓል። አቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ ብለው ነበር።

‹‹…ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ለአፍሪካ ሉዓላዊነትና ነፃነት ቆራጥ ናት!

ማንዴላን ያሰለጠነው ማን ነው? አጼ ኃይለሥላሴ!… ሙጋቤ ሩዲዝምን በሚፋለምበት ጊዜ ማነው የደገፈው? መንግሥቱ! መንግሥቱ በአገር ውስጥ ገዳይ ነው፤ ዳሩ ግን በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ልክ እንደ አጼ ኃይለሥላሴ ቆራጥ አቋም ያለው ነው። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት አቋም በመንግሥት መቀያየር ላይ ምንም ለውጥ አይኖረውም! በኃይለሥላሴ፣ በመንግሥቱ፣ በእኛ፣ በአፍካ ጉዳይ ላይ ምንም ለውጥ የለም! ሁሉም አፍሪካዊ ይህን የኢትዮጵያውያን ስሜት ማወቅ አለበት!..››

ከ8 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ነባሩንና ጥንታዊውን የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ይዘቱን ሳይለቅ ከዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ ጋር ለማዋሃድ በተደረጉት ጥረቶች ውስጥ የመሪነት ሚና የነበራቸው ታላቁ ሠዓሊ አለ ፈለገሰላም ኅሩይ አረፉ።

ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከጥር 1864 ዓ.ም እስከ መጋቢት 1881 ዓ.ም የመሩት ንጉሰ ነገሥት አጼ ዮሐንስ 4ኛ ተወለዱ። ባለፈው ዓመት በዝርዝር ማስታወሳችን ይታወሳል።

ከ74 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የስነ ጽሑፍ ተመራማሪ ደበበ ሰይፉ ተወለደ።

ከ45 ዓመታት በፊት ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ተገደሉ።

አሁን በዝርዝር ወደምናየው የደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ታሪክ እናልፋለን።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀ መንበር የነበሩት ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን በዕለተ ዓርብ ሐምሌ 2 ቀን 1907 ዓ.ም ቡልጋ በከሰም ወረዳ፤ የለጥ ቀበሌ፤ ልዩ ስሙ ቡሄ አምባ በሚባለው ሥፍራ፤ ከእናቱ ከወይዘሮ አስካለ ደጀን እና ከአባቱ ከቀኛዝማች ወልደመድኅን አይደረስ ተወለደ። አባቱ ቀኛዝማች ወልደመድኅን በትውልድ አገራቸው በዘመኑ የታወቁ ስመጥር ጠበቃ ነበሩ። ኪዳኔ እስከ 12 ዓመት ዕድሜው ድረስ እዚያው ቡሄ አምባ አካባቢ በአያቱ አቶ ደጀን ደብሩ ቤት ሆኖ የቄስ ትምህርት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከታትሏል። በመቀጠልም ከወላጆቹ ጋር ሆኖ የአማርኛና የግዕዝ ትምህርቱን አጠናቋል።

ኪዳኔ በ18 ዓመቱ በ1925 ዓ.ም አዲስ አበባ የክብር ዘበኛ ሰራዊት አባል ሆነ። ወዲያው በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ከ69 አዲስ ወታደሮች ጋር ባሌ ተመድቦ እስከ 1927 ዓ.ም ድረስ በተራ ወታደርነት ከዚያም በሃምሳ አለቃነትና በባሻነት ማዕረግ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት በ1928 ዓ.ም በነደጃዝማች በየነ መርድ መሪነት ከጎባ ወደ ኦጋዴን ዘመተ።

ኪዳኔ ከባላምባራስ አየለ ወልደማርያምና ሌሎች አርበኞች ጋር ሆኖ በዚህ ግንባር በዋቢሸበሌና አካባቢው ለዘጠኝ ወራት ያህል ከጠላት ጋር ሲፋለም ከርሞ ወደ ጎባ ተመለሰ። ከሰኔ 1928 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 1929 ዓ.ም ድረስ ከአርሲ፣ ከሲዳማ፣ ከሐረርና ከኦጋዴን ወደ ጎባ የዘለቀውን የጠላት ጦር ሲዋጉ ከርመው፤ መጨረሻ ላይ ተማም ከሚባለው ሥፍራ ላይ በተካሄደው ጦርነት ማምለጥ በማይቻልበት ሁኔታ ኪዳኔና ሌሎች አርበኞች በጠላት እጅ ወድቀው ተማረኩ። ጠላትም ለአምስት ወራት በጽኑ እሥራት ከያዛቸው በኋላ፤ በጥር ወር 1930 ዓ.ም ከጎባ ወደ ወሊሶ አዛውሮ አሰራቸው።

ባሻ ኪዳኔም እዚሁ እስር ቤት እያሉ አብረዋቸው ከታሰሩት አርበኞች መካከል በምስጢር 100 ሰዎችን አደራጅተው እዚያ ያለውን የጠላት ጦር ፈጅተው ለመሸፈት ከወሰኑ በኋላ በወቅቱ ከስመ ጥር አርበኞች መካከል አንዱ ወደነበሩት ወደ ባላምባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪ ሰው ለመላክ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ አሳሪያቸው የፋሺስት ጦር ነገሩን በመስማቱ እጅግ ጥብቅ የሆነ ክትትል አደረገባቸው። ባሻ ኪዳኔም ይህን ሲገነዘቡ ካደራጇቸው 100 ሰዎች መካከል 55 ወታደር ከነመሳሪያው፤ አራት መትረየስ፤ አስር ሣጥን ጥይት፤ ስድስት ሽጉጥ ከጠላት እጅ ነጥቀው እየተታኮሱ ሲወጡ የጠላት ኃይል ሃያ ወታደርና አንድ መትረየስ ከሁለት ሣጥን ጥይት ጋር ብቻ ገንጥሎ ሲያስቀርባቸው ከተረፈው መሳሪያና ወታደር ጋር ድል አድርገው ሸፈቱ። ወዲያውም ኩሳ ኪዳነምሕረት ከሚባል ሥፍራ ላይ ከደጃዝማች ገረሱ ጋር ተገናኙ።

ባሻ ኪዳኔ ከባላምባራስ ገረሱ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላም እስከ ጥቅምት 1931 ዓ.ም ድረስ በደንዲ፤ በሶዶ፤ በበዳቄሮ እና በሌሎች ሥፍራዎች በአርበኝነት ሲዋጉ ቆዩ። በዳቄሮ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ሳሉ ሙሴ ሰባስቲያኖ ካስታኛ (ሙሴ ቀስተኛ) የሚባለው ጣሊያናዊ ከፋሺስት አመራሮች ተልኬያለሁ ብሎ ከሦሥት ባላባቶች ጋር መጣ። አርበኞቹም ይህ ሰው ቀደም ሲል በ1930 ዓ.ም ወደ ራስ አበበ አረጋይ ዘንድ ሄዶ የጦሩን ኃይል ከተመለከተ በኋላ ብዙ አርበኛ እንዳስገደለ ሰምተው ስለነበር እነሱንም እንደዚሁ ለማስፈጀት እንደመጣ ስለተገነዘቡት ባሻ ኪዳኔ ወልደመድኅን በመውዜር ጠመንጃ ሲመቱት ‹‹ኢጣልያ ለዘለዓለም ትኑር! ለኢጣሊያ ስል ሞትኩላት›› ብሎ ሲናገር በሽጉጥ ራሱን መትተው ከገደሉት በኋላ የለበሰውን ሙሉ ገበርዲን ልብስና ካፖርት እንዲሁም የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ስዕል ያለበትን የብር ሰዓቱንና በቅሎውን ከነኮርቻው ማረኩት። ከሙሴ ካስታኛ ጋር አብረው የመጡት አባላባቶች የሙሴን መገደል ለፋሺስት ጦር መሪዎች አሳወቁ። ከ25 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ያሉበት በርካታ የፋሺስት ጦር ወደ በዳቄሮ ዘመተ። አርበኞቹም ለሦስት ቀናት ሙሉ ሲከላከሉ ከቆዩ በኋላ ከሥፍራው ሸሽተው ሶዶ ላይ ለስምንት ቀናት ያህል ተዋጉ።

ባሻ ኪዳኔ በኅዳር ወር 1931 ዓ.ም አርበኞቻቸውን አስከትለው ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ቡልጋ ገቡ። በዚያም ከፊታውራሪ ኃይለማርያም ማናህሌ እና ከፊታውራሪ ተረፈ ማናህሌ ጋር ተቀላቅለው እስከ መጋቢት 1931 ዓ.ም ድረስ በውሽንግር፤ ጨፌ ዶንሳ ምሽግ፤ ነጭ ድንጋይ ምሽግ፤ ልዝብ ድንጋይ በተባሉ ቦታዎች ላይ ከጠላት ኃይል ጋር ሲዋጉ ከረሙ። በዚህ ወቅት ታመው በነበረበት ጊዜ የፋሺስት ጦር በሦስት አቅጣጫ ከበባቸው። የጠላት ኃይል እጅ እንዲሰጡ ቢጠይቃቸውም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ከፋሺስት ጋር ተፋለሙ። በወቅቱ ባሻ ኪዳኔ ከፋሺስት ጦር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ እጅግ መራራና እልህ አስጨራሽ እንደነበር ስለአርበኞች ታሪክ የተፃፉ መዛግብት ይመሰክራሉ። ከህመም ጋር እየታገሉ ከፋሺስት ጦር ጋር የተፋለሙት ባሻ ኪዳኔ የጠላት ጦር እርሳቸው መሽገውበት የነበረውን ጫካ በእሳት ነበልባል ግራና ቀኙን ሲያቃጥልው እሳቸው በተዓምር ተረፉ። ከሦስት ቀናት በኋላ የጠላት ኃይል አካባቢውን ለቆ ሲሄድ ባሻ ኪዳኔ ህመሙና ድካሙ በርትቶባቸው ስለወደቁ በብዙ ፍለጋ ነበር የተገኙት።

ከዚህ በኋላ ክረምቱን ቡልጋ ውስጥ በነጭ ድንጋይ፣ ፍልፍል አፈር፣ ጦስኝ ምሽግ እና በመስኖ ከነደጃዝማች ኃብተ ሥላሴ በላይነህ፣ ፊታውራሪ በለጠ ሳሴ፣ ፊታውራሪ አጎናፍርና ሌሎችም ስመጥሩ የቡልጋ ልጆች ጋር ሆነው ጠላትን ሲያጠቁና ሲከላከሉ ቆይተው በመስከረም 1932 ዓ.ም በሰገሌ በኩል ተጉዘው ገሊላ ከሚባል ሥፍራ ላይ ከራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ሲቀላቀሉ ባሻ ኪዳኔ የግራዝማችነት ማዕረግ ተሾሙ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ጎጃምና ወደ ጎንደር እስከዘመቱበት 1933 ዓ.ም ድረስ ከራስ አበበ ጋር ጠላትን በየቦታው ሲዋጉ በአርበኝነት ቆዩ።

ከብዙ ውጊያዎችና ጀብዱዎች በኋላ በየካቲት 1933 ዓ.ም መሶቢት ከሚባለው ቦታ ላይ በመሪነት የጠላትን ጦር ድል አድርገው ወደ ዋናው ሰራዊት ከተቀላቀሉ በኋላ ራስ አበበ የቀኛዝማችነት ማዕረግ ሾሟቸው።

ቀኛዝማች ኪዳኔ ከሌሎች አርበኞች ጋር ሆነው በ1933 ዓ.ም ዳውንት፣ ተንታ እና ደብረታቦር ላይ የሰፈረውን የፋሺስት ጦር እየማረኩ በመስከረም 1934 ዓ.ም ጉማራ ላይ ከፍ ያለ ውጊያ አድርገው ጠላትን ድል አደረጉ። በኅዳር 1934 ዓ.ም ከጎንደር ወደ ቁልቋል በር ላለው ለጠላት ጦር ስንቅና ትጥቅ አቀብሎ ሲመለስ ጥቃት ከፍተውበት ብዙ ባንዳዎችን ገደሉ።

በዚያው በኅዳር ወር 1934 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ውስጥ ጄኔራል ናሲ የተባለው የፋሺስት ጦር አዛዥ ከብዙ ሺህ ሰራዊት ጋር አካባቢውን በሽቦ አጥሮ በሽቦው ውስጥና ውጭ ፈንጂና ቦንብ ቀብሮበት ነበር። ቀኛዝማች ኪዳኔ ይህንኑ የተቀበረ ቦንብ እየቆረጡ ሌሊቱን ተጉዘው ምሽጉ ደረሱ። ሲነጋ ተኩስ ተከፈተ። ጠላትም ከከፍተኛ ተራራ ላይ ወደታች ወደነ ቀኛዝማች ኪዳኔ በቦምባርድና ከባድ መትረየስ ሲያጠቃቸው በተራራው ሥር አድርገው ወደ ጎንደር ከተማ የሚወስደው መንገድ ላይ ሲደርሱ ከጎንደር ከተማ የሚመጡ አስመስለው ከኋላው በጨበጣ የእጅ ቦንብ እየጣሉ ብዙ የጠላት ኃይል ደመሰሱ። እንዲሁም መትረየሶችን ማርከውና ምሽጉን አስለቅቀው ከያዙ በኋላ ጀኔራል ናሲ ወዳለበት ወደ ጎንደር መጓዝ ቀጠሉ። ጎንደር ሲገቡም ፋሲል ግንብ ምሽግ ሲደርሱ ምሽጉን ለመድፈር የእጅ ቦንብ ምሽጉ ላይ በብዛት ሲጥሉ ጠላት ተሸንፎ የሰላም ባንዲራ አውለበለበ። ወዲያውኑ 500 የጠላት ወታደሮችን ማረኩ። በከተማው የሚገኙትን የአረብ ተወላጆች ሱቅና ገንዘብ እንዳይዘረፍ በወታደር አስጠብቀው ወደ ቀጣዩ ዘመቻቸው አቀኑ።

ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ራስ ብሩ ወልደብርኤል ከእንግሊዛዊው ሜጀር ጀኔራል ፎክስ ጋር ወደ ጎንደር ገቡ። ‹‹ባለህበት እርጋ›› ተባለና ሁሉም ተረረጋ። ጀኔራል ናዚ ያለድርድር እጁን ሰጠ። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ። በማግሥቱ ኅዳር 20 ቀን ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ጎንደር ገቡ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ የነበረው ቆይታ ተደመደመ! የጎንደሩ ውጊያና ሽንፈት የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአፍሪካ ምድር ያካሄደው የመጨረሻው ውጊያና የተከናነበው የመጨረሻው ሽንፈት ሆኖ ተመዘገበ። ቀኛዝማች ኪዳኔ ከአልጋወራሹ ጋር ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት እንዲሄዱ ተደርጎ እዚያው ብዙ ወታደርና መሳሪያ ለመከላከያ ሚኒስቴር አስረከቡ።

በየካቲት 1934 ዓ.ም የፊታውራሪነት ማዕረግ አግኝተው መጀመሪያ በወረዳ አስተዳዳሪነት ከዚያም በ1936 ዓ.ም የየጁ፤ የዋድላ ደላንታ፤ የመቄት፤ የሸደሆና የዳውንት ብሔራዊ ጦር አዛዥና የጠቅላይ ግዛቱ ጦር አማካሪ በመሆን አገለገሉ። ከዚያም እስከ 1943 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በወሎና በከፋ ውስጥ በአውራጃ አስተዳዳሪነት ተመድበው ሲያገለግሉ ቆዩ። በዚሁ ወቅት ነው የደጃዝማችነት ማዕረግ የተሰጣቸው።

ደጃዝማች ኪዳኔ ከፋ ውስጥ እንደተሾሙ ከጠቅላይ ገዢው ጋር ባለመስማማታቸው ተሽረው ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን እስከወረዱበት ጊዜ ድረስ በእስራትና በግዞት እንዲቆዩ ተደርገዋል። ንጉሠ ነገሥቱ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ደጃዝማች ኪዳኔ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ አገራቸውንና ማኅበሩን ወክለው ሮም ላይ በተካሄደው የዓለም አቀፍ ጸረ ኑክሊየር መሣሪያ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ ሞስኮ ላይ፣ ጥቅምት 9 ቀን 1972 ዓ.ም አረፉ። ስርዓተ ቀብራቸውም ጥቅምት 15 ቀን 1972 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።

ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ከአርበኛነታቸው በተጨማሪ በማኅበራዊ ኑሯቸውም ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በ1949 ዓ.ም በትውልድ ስፍራቸው በቡልጋ የየለጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን አሰርተዋል። በ1964 ዓ.ም ‹‹ከልደት እስከ ሞት›› የተሰኘች አጭር ኃይማኖታዊና የፍልስፍና መጽሐፍ አሳትመዋል።

ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በርካታ የውጭ አገራት ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን ባለአምበል፣ የአርበኝነት ሜዳይ ከአራት ዘንባባ ጋር፣ የድል ኮከብ ሜዳይ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የከፍተኛ ጀብዱ ሜዳይ ከአንድ ዘንባባ ጋር፣ የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ታላቅ መኮንን ከደረት ኮከብ ጋር፣ የአፍሪቃ ኮከብ ሜዳይ (ከእንግሊዝ መንግሥት)፣ የአፍሪካ የድል ሜዳይ (ከእንግሊዝ መንግሥት) እንዲሁም ሦስት ልዩ ልዩ የሶቭየት ኅብረት ኒሻኖች ይጠቀሳሉ።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You