የአብዛኛውን ልብ የሚያሰክንና ከቁጣ የሚመልስ የሽግግር ፍትሕ

የሽግግር ፍትሕ የሰብዓዊ መብትን መከበር ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሁም በሕዝቦች መካከል እርቅ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል። በአንድ ሀገር ውስጥ ዘላቂ ሠላምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በመደበኛው ሕግ መፍታት የማይቻሉ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታትና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማስቻል የሽግግር ፍትሕ ሁነኛ መሣሪያ መሆኑን በዘርፉ ምሑራን ይገለፃል።

የሽግግር ፍትሕ ባለፉት ጊዜያት ከሕግ አግባብ ውጪ የተፈፀሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመለየት ችግሮችን በምሕረት፣ በይቅርታ እንዲሁም ተጠያቂነትን በማስፈን የመፍታት ዓለማቀፍ አሠራር ነው።

በሰው ልጆች ላይ አሰቃቂ ግድያዎችን የፈጸሙ፣ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ ሰብዓዊ መብቶችን የጣሱ፣ ዜጎችን ያፈናቀሉ፣ ጅምላ ግድያ የፈፀሙ፣ የሰዎችን ንብረት ያወደሙና የመሳሰሉት ሁሉ በሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መሠረት ካሉ አማራጮች ተጠያቂ ሆነው በይቅርታና በምሕረት የሚታለፉትን እንዲታለፉ፤ የግድ መታለፍ የለባቸውም መጠየቃቸው የተሻለ የፍትሕ መድኅን ነው የተባሉትን ደግሞ በመጠየቅ እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ለመካስና የተበደሉትን እንባቸውን ለማበስና ተመሳሳይ ጥፋት ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይደገም ለማድረግ ይጠቅማል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈፀሙ በደሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በፍትሕ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ አዘጋጅ የባለሙያዎች ቡድንም ሰነዱን በማዘጋጀት የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ማጠናቀቁን አስታውቋል። አሁን ላይ የባለሙያ ቡድኑ ተግባርና ኃላፊነቱን በመወጣት ሥራውን አጠናቆ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ በማዘጋጀት ለፍትሕ ሚኒስቴር አስረክቧል።

የሽግግር ፍትሕ ባለሙያ ቡድኑ ከኅብረተሰቡ ባሰባሰበው ግብዓት በኢትዮጵያ የተበዳዮችን እንባ ለማበስ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጧል። የሽግግር ፍትሕ የኢትዮጵያን ውጣ ውረዶችና ችግሮች ለመፍታት፣ ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት፣ እርቅን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ፍትሕን ለማስፈን አንዱ አስፈላጊ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ብዙዎች አምነውበታል።

ኅብረተሰቡ በሽግግር ፍትህ ሂደቱ እነማን ይጠየቁ፣ በየትኞቹ በደሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ተጠያቂ ይሁኑ የሚለውን ጉዳይ ከነአማራጩ ሀሳብ ሰጥቷል። በዚሁ መሠረት አብዛኛው በሀገር ደረጃ ግብዓት የሰጠው ሰው ሲታይ ከፍተኛ ተጠያቂነት ያለባቸው፣ የችግሩ ወይም የበደሉ፣ የወንጀሎቹ ጠንሳሾች ዋና ፈፃሚዎች፣ መከላከል እያለባቸው ያልተከላከሉ ሰዎች፣ ከጊዜ፣ ከሀብት፣ ከኃላፊነት አንፃር ኃላፊነት ያለባቸው ላይ ማተኮሩ የተሻለ መሆኑን ሀሳብ ሰጥተዋል።

የባለሙያዎች ቡድኑ የትኞቹ ጉዳዮች ላይ የሚለውን በተመለከተ ሁለት አማራጭ አቅርቧል። ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች/ከባድ ወንጀሎች የሚል አንዱ አማራጭ ሲሆን ሁሉም ጥሰቶች የሚል ደግሞ ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። በአብዛኛው የተደገፈው ሀሳብ አማራጭ አንድ ጉልህ/ከባድ ወንጀሎች ላይ ቢተኮር እንደሚሻል ነው።

የተጠያቂነት ሂደቱ በየትኛው ተቋም በኩል መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ከኅብረተሰቡ ግብዓት ተሰብስቧል። የትኞቹ የፍርድ ተቋማት/የፍርድ አደረጃጀቶች፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ ፖሊስ በጠቅላላው በየትኛው የተቋም አደረጃጀት የተጠያቂነት ሂደቱን እናከናውነው የሚልም ጥያቄ ለሕዝቡ ቀርቦለት ከነአማራጩ ሀሳብ ሰጥቷል። አማራጮቹ ላይ ብዙ ግብዓቶች ተሰብስቧል።

ሌላው እውነት ማፈላለግ የትኞቹ ጉዳዮች ላይ ይካሄድ፣ የትኛው ተቋም እውነት ያፈላልግ የሚል ሀሳብም ላይ ግብዓት ተሰብስቧል። ኅብረተሰቡ እውነትን ሊያፈላልግልን የሚገባው አዲስ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አቋቁመን ሊሆን ይገባል የሚል ሀሳብ ሰጥቷል፡፡

ብዙ ጊዜ የሽግግር ፍትሕ ላይ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ይኖራል። ይህ ኮሚሽን የተፈፀሙ ቅሬታዎችን በደሎችን ከማኅበረሰቡ፣ ከግለሰቦችም ይሰበስባል። የራሱ ሂደትም አለው። እነዛን ሂደቶች ተከትሎ ያረጋግጣል ወይም ደግሞ ወደ ፍትሕ የሚገባውን ወደ ፍትሕ ያቀርባል፤ ካሳ የሚገባውን ካሳ ይሰጣል የመሳሰሉትን ነገሮች ያደርጋል፡፡

ሌሎቹም የሽግግር ፍትሕ ዓምዶች ላይ ለምሳሌ ምሕረት፣ ማካካሻ፣ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ከየት ጊዜ ይጀምር የሚለው ላይ የባለሙያ ቡድኑ ባቀረባቸው አማራጮች ሕዝቡ የተለያየ ሀሳብ አንዳንዴም አዲስ አማራጭ ሰጥቶ ግኝቶችን በዝርዝር የባለሙያ ሃሳቦችን በሚያካትት መልኩ ቀርቧል።

የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች ቡድን ከሕዝቡ ያሰባሰበውን ግብዓት በመቀመርና የባለሙያዎችን አስተያየት በማካተት ያዘጋጀውን ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ለፍትሕ ሚኒስቴር አስረክቧል። ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ ይፋ አድርጓል። በተለያዩ ቋንቋዎችም ተርጉሞ ለመንግሥት አስረክቧል። የአማርኛውን ሪፖርት እና የአማርኛውን ረቂቅ ፖሊሲ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ለፍትሕ ሚኒስቴር አስረክቧል። በመሆኑም ይህ የባለሙያዎች ቡድን የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር አጠናቆ ለመንግሥት ረቂቅ ፖሊሲውንና ሪፖርቱን አስረክቦ ሥራውን ጨርሶ ባለሙያዎቹም ተበትነዋል፡፡

በቅርቡም ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የዓለማቀፍ ወንጀሎችና የሽግግር ፍትሕ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ አዋጆችን እንደሚያወጣ አስታውቋል። በፖሊሲው መሠረት ሕጋዊ ተቋማት እስኪቋቋሙ፣ የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር መድረክ ኃላፊነቱን ተረክቦ እንደሚቆይ ሚኒስቴሩ ገልጧል። ሰው የማሰቃየት፣ መሰወር፣ ፆታዊ ጥቃትና የጦር ወንጀሎች በአዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚቀረጹና በፌደራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጉልህ ጥሰቶችን ማየትን በተመለከተ አዋጅ እንደሚወጣ ሚኒስቴሩ ገልጿል ።

በተከሰቱ ነገሮች ከቤት ውስጥ ሁለትና ሦስት ልጆችን ያጡ ወላጆች፣ ለዓመታት ያፈሩትን ሀብት ያጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ ‹‹ሁሉን ነገር ትተነዋል፣ ይቅርታ ነው፣ እርቅ ነው፣ ሁሉ ነገር ቀርቷል፣ ሁሉ ነገር ተካክሷል›› ተብሎ በአዲስ እንቀጥልበት የሚባል አይደለም። ፍትሕ፣ ካሣ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያካተተ የሽግግር ፍትሕ ያስፈልጋል።

በአብዛኛው የሚስተዋለው እርቅን ለብቻው መዞ ማውጣትና ፍትሕን የመዘንጋት ጉዳይ ቢሆንም ሁለቱን ጎንለጎን ማካሄድ ይቻላል። ይህም በእርቅ ታልፎ ሳይጠየቅ የሚያልፈውን እንዲሁም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠረውን ቁርሾ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እልባት ለመስጠት ያስችላል። በተለይም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚሄድበት እርቀት ውይይትን በውስጡ ያካተተ ሊሆን ይገባል።

የሽግግር ፍትህ አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ አብዛኛውን የሚያስማማ፣ ለነገ የተሻለ መሠረት የሚጥል የሀገር ካስማ ያስገኛል። ሙሉ በሙሉ ፍፁም የሆነ እርቅ፣ ፍፁም የሆነ ፍትሕ፣ ፍፁም የሆነ ካሣ እናገኛለን የሚል እምነት ሊኖር አይችልም። ዓለምም እንደዚህ አይነት ሕግ የላትም። ነገር ግን አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ አብዛኛውን የሚያስማማ፣ የአብዛኛውን ልብ ሰከን የሚያደርግ ከቁጣ የሚመልስ እርቅ ማድረግ እንችላለን፡፡

ሩዋንዳም ላይ የሆነው ተመሳሳይ ነው። በደቡብ አፍሪካም ከአፓርታይድ መንግሥት የሀገሩ ባለቤት የሆኑት ደቡብ አፍሪካውያን/ጥቁሮች የሚገባቸውን ካሣ ላያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን ለነገ መሠረት የሚሆናቸውን ሀገር አስቀምጠዋል። ከዚህ በኋላ በሚሠሩት መንግሥታዊ መዋቅር በደላቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ። እኛም ያንን ልምድ ማምጣት እንችላለን። በሚመጣው የሽግግር ፍትሕ እና በምናቋቁማቸው ተቋማት ተበደልኩ የሚል ዜጋም ይሁን ቡድን ጥያቄውን ተዓማኒ ለሆኑ ተቋማት በኩል አቅርቦ ፍትሕን ማስፈን እንችላለን።

በእርግጥ መንግሥት ፖሊሲውን ከማውጣት ባለፈ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል። ሕጉን ማውጣቱና ማዘጋጀቱ በቂ አይደለም። ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ውሳኔ የዜጎችን ሠላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ የቤት ሥራዬ ነው ብሎ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች የመመርመር፣ ይቅርታና ምሕረትን የመለየት፣ በበቂ ማስረጃ አስደግፎ ተጠያቂ የሚሆኑትን ወደ ፍርድ ወስዶ ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም ተጎጂዎችን ወይም የተበደሉትን መልሶ የማቋቋም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ዜጎችም እውነትን በማፈላለግ ሂደቱ ትክክለኛውን መረጃ ለመንግሥት በመስጠት የተፈፀሙ በደሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ መፍትሔ እንዲያገኙ በቅንነት ሊሠሩ ይገባል። ዜጎች ስለሽግግር ፍትሕ ምንነትና ጠቀሜታ ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መገናኛ ብዙኃንና ባለድርሻ አካላት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሕግን ማስከበር ብቻውን በራሱ ሁልጊዜ ግብ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ለሕግ መጣስ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ነገሮች የታዩበት ሁኔታ ላይ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ በመጫወቻ ሕጉ ብቻ ከመጫወቻ ሕጉ ውጪ ማንኛውንም ተግባር ያከናወነ የሕግ ኃላፊነት ይኑርበት የሚል መደምደሚያ ይዘን የምንነሳ ከሆነ ይሄ ቀጣይነት ያለው መፍትሔ አያመጣም። ሆኖም ግን ሁሉም አይነት ጉዳዮች በእርቅ፣ በሀገራዊ መግባባት ስም ሁሉም አይነት የሕግ ጥሰቶች በይቅርታ የሚታለፉበት አግባብ ሊኖር አይችልም።

በይቅርታም በምሕረትም ሊሰረዙ የማይችሉ ነገሮች ወንጀሎች እንዳሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 28 ተቀምጧል። ሰው ተኮር ሰብዓዊ ወንጀሎችን የፈፀሙ አካላትን ለምሳሌ ዘር ተኮር ጥቃቶችን፣ ግድያዎችን፣ ስቃዮችን የመሳሰሉ ድርጊቶችን የፈፀሙ ሰዎች በእርቅም በይቅርታም በምሕረትም ሊታለፉ አይችሉም። ስለሆነም አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ ሀገራዊ መግባባት ሀገራዊ የልዩነታችን ነጥቦችን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡

ጦርነቶችም ሆኑ ግጭቶች በአብዛኛው የሚቋጩት በሠላም ስምምነት ነው። ከጦርነት በፊት ለገላጋይ ያስቸገሩ ተፋላሚዎች ለንፁሐን ዜጎች እልቂትና ለሀገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆነው በመጨረሻ የሚገናኙት የሰላም ስምምነቱን የሚፈራረሙበት ክብ ጠረጴዛ አጠገብ እንደሆነ የብዙዎች ታሪክ ምስክር ነው። ይህ ታሪክ ለኢትዮጵያ አዲስ ባይሆንም ሀገሪቱን ወደተሻለ የታሪክ ምዕራፍ ለማሻገር እንደየሁኔታው የሕግ የበላይነትንና እርቅን በቅደም ተከተል ተግባራዊ ማድረግ ይገባል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You