ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትና አደረጃጀት በኮንሶ

ኢትዮጵያውያን የበርካታ እሴቶች ባለቤት ናቸው። ከእነዚህ እሴቶች መካከል ደግሞ በግለሰቦች፣ በቡድኖችና በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ግጭቶች በሚፈጠሩበት ወቅት እርቅና ሠላም ለማስፈን የሚጠቀሙባቸውን ባሕላዊ መንገዶች በቀዳሚነት መጥቀስ ይቻላል።

ሀገሪቱ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን በዚያው ልክም የግጭት አፈታት ዘዴ መንገዶቹም ይለያያሉ። የሁሉም ዓላማ እርቅ ማስፈን፣ የሠላም በሮች እንዲከፈቱ ማድረግ ቢሆንም አፈፃፀምና አካሄዳቸው ግን ይለያያል። ይህም የማኅበረሰቡን የሥነ ልቦና ውቅር እንዲሁም ባሕል ያማከለ የእርቅ ሥርዓት እንዲኖር ያስቻለ ነው።

የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው ሀገርኛ ዓምድ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች መካከል አንዱ በሆነው በኮንሶ ብሔረሰብ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ላይ ያተኩራል።

ወጣት ቀለሟ መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፎክሎር ትምህርት ክፍል ተመራቂ ነች። የመመረቂያ ጽሑፏን በኮንሶ ብሔረሰብ ባሕላዊ ግጭት አፈታት ዙሪያ ሠርታለች። እርሷ እንደምትጠቅሰው፤ የፍላጎቶች አለመጣጣም በሚኖርበት በማንኛውም ቦታና ጊዜ ቅራኔና ግጭቶች ይኖራሉ። በእነዚሁ ፍላጎቶች አለመጣጣም ሳቢያ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ደግሞ ከባድ ወይም ቀላል ግጭቶችን ሲጭሩ ይስተዋላል።

ግጭቶች በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ በአንድ ወይም በሁለት አሊያም ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች መካከል በተከሰተ አለመግባባት የሚነሱ ክስተቶች ሲሆኑ መንስኤዎቹም የተለያዩ ናቸው። እነዚህ ግጭቶች የሚፈቱበት ባሕላዊ ሥርዓትም እንደየማኅበረሰቡ እንደሚለያይ ባደረገችው ጥናት ላይ መለየቷን ትናገራለች። ከእነዚህ ውስጥ በጥልቀት የዳሰሰችውን የኮንሶ ብሔረሰብ የግጭት አፈታትን እንደሚከተለው ትጠቅሳለች።

‹‹ሀገር በቀል ከሆኑ ባሕላዊ ተቋማት መካከል የኮንሶ ብሔረሰብ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ተቋማት ‹ፓሌታዊ(ሞራ-ከንታ እና ሞራ-ፓሌታ)› የዳኝነት ሥርዓትና ጐሳዊ የዳኝነት ሥርዓት ተጠቃሾች ናቸው›› የምትለው ወጣት ቀለሟ፤ በኮንሶ የሚፈፀመው የግጭት አፈታት (የዕርቅ) ሥነ-ሥርዓት በብሔረሰቡ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነት እንዳለው ትገልጸለች።

አስታራቂዎቹም በሕዝቡ ዘንድ ልዩ አክብሮትና ተሰሚነት አላቸው ትላለች። ‹‹በፓሌታዊ›› አደረጃጀትና በጐሳዊ አደረጃጀት የሚፈፀሙ የዕርቅ ሥነ-ሥርዓቶች ጊዜ የማይወስዱና በማኅበረሰቡ የተፈጠሩ ግጭቶችን አስወግደው ዘላቂ ዕርቅና ስምምነት በማምጣት ረገድ ለብሔረሰቡ ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ መሆናቸውን ባደረገችው ጥናት እንዳረጋገጠች ታስረዳለች።

ጥናቱ የተደረገበት ዋና ዓላማ በሰገን አካባቢ ሕዝቦች አስተዳደር ዞን በኮንሶ ብሔረሰብ የሚከናወነውን ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቱን በመመርመር አስታራቂዎች (የግጭት መፍቻ ተቋማት) በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖራቸውን የጎላ ሚና፣ ግጭቶችን ለመፍታት የሚጠቀሙበትን ስልትና ሂደት ወይም የግጭት አፈታት ሂደቱ ምን እንደሚመስል በመተንተን ማሳየት እንደሆነ ገልፃለች። በዚህ መነሻ የሚከተለውን ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ሂደት ታስረዳለች።

‹‹ሞራ- ከንታ››

በብሔረሰቡ ‹‹ከንታ›› ማለት ንዑስ መንደር ወይንም ሰፈር እንደማለት ነው። ‹‹ከንታ›› በፓሌታ ስር ያለ የአነስተኛ መንደሮች መጠሪያ ነው። በኮንስኛ ‹‹ፓሌታ›› በአማርኛ ቀበሌ (መንደር) ማለት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ፓሌታ (መንደር) በስሩ ከሁለት እስከ አስር የሚደርሱ ከንታዎች (ንዑስ መንደሮች) አሉት። እነዚህ ንዑስ መንደሮች የየራሳቸው ባሕላዊ የዳኝነት ስፍራ (ሞራ) አላቸው። ይህም ‹‹ሞራ-ከንታ›› ተብሎ ይጠራል።

‹‹በሞራ-ከንታ›› ደረጃ ባሕላዊ የግጭት መፍታት ሂደት ለማከናወን የሚቀመጡት የሥርዓቱ አስታራቂዎች ‹‹ፖርሺታ››፣ ‹‹አፓ-ከንታ››(የከንታ አባት)፣ ‹‹ቂሞታ-ከንታ›› (የከንታ ሽማግሌ) እና ‹‹ኸሊታ-ከንታ›› (የወጣት ትውልድ ቡድን አባል) ናቸው። እነዚህ አካላት በዚህ ደረጃ የሚቀርቡ ቀላል ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የየራሳቸው ተግባር ወይንም ኃላፊነት አላቸው።

‹‹ሞራ -ፓሌታ››

በኮንሶ ብሔረሰብ ‹‹ፓሌታ›› አሮጌ ከተማ ወይንም አምባ መንደራት እንደማለትም ነው። ‹‹ፓሌታ›› ከከንታ ከፍ ያለ፣ ሰፊና በርካታ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው። ኮንሶዎች ሞራ-ፓሌታን “ካርሞቴ” ይሉታል። ትልቁ ሞራ እንደማለት ነው። በዚህ ‹‹ሞራ›› የሚታዩት ግጭቶች በሞራ-ከንታ ደረጃ መፈታት ያልቻሉና በዚህ ደረጃ እንዲታዩ ተላልፈው የመጡ ቀላልና ከባድ ግጭቶች እንደ ድብደባ፣ (ደም መፍሰስ ካለበትና ደም በማለት ቃሉን መጥራት ከሆነ)፤ እንዲሁም ሴቶችን ማስኮብለልና ማባለግ፣ መድፈር ያሉት ናቸው።

በዚህ ደረጃ የግጭት መንስኤ የሆነውን ጉዳይ ለማየትና ዕርቀ-ሠላም ለማውረድ የሚቀመጡት ‹‹ቂሞታ-ፓሌታ›› (የፓሌታ ሽማግሌ ከየትኛውም ከንታ ሊሆን ይችላል)፣ ‹‹ኸሊታ-ፓሌታ››፣ ‹‹ሰንቀሊታ›› (የወጣት ትውልድ ቡድን መሪ)፣ ‹‹አፓ-ቲንባ›› (የከበሮ አባት) ወይንም ‹‹የፓሌታው የበላይ መሪ ዳውራ›› (መንፈሳዊ አባት)፣ ‹‹ሳራዎች›› (የጐሳ መሪ መልዕክተኞች)፣ ‹‹ፖቃላ ሙግላ›› የዋናው ጐሳ መሪ ምክትል ናቸው።

በዚህ ደረጃ የሚቀርቡ ግጭቶች ከባድ የግጭት ዓይነቶች በመሆናቸው በግጭት አፈታት ሥርዓቱ ወቅት እነዚህ አካላት የየራሳቸው ኃላፊነትና ተግባር አላቸው። ‹‹በሞራ-ፓሌታ›› ደረጃ መፈታት ያልቻሉ ግጭቶች ‹‹በፖቅላ›› ደረጃ እንዲታዩ ወደ‹‹ፖቅላ›› ይተላለፋሉ።

‹‹ፖቅላ››

‹‹በኮንስኛ ፖቅላ›› የሚለው ስያሜ ለጎሳ መሪዎች የሚሰጥ የማዕረግ ስምን ያመለክታል። ጉዳዩ ወደ ‹‹ፖቅላ›› ተላለፈ ማለት በጐሳ መሪ ደረጃ ዳኝነት ይሰጥበታል ማለት ነው። በዚህ ደረጃ የሚታዩት ጉዳዮች በየደረጃው ‹‹በሞራ-ከንታ›› ደረጃ ታይተው እልባት ያላገኙ፣ ወደ ‹‹ሞራ-ፓሌታ›› ደረጃም ተሸጋግረው መፈታት ያልቻሉ ጠንከር ያሉ ጉዳዮች (ከባድ ግጭቶች) እና ወንጀሎች ናቸው። በዚህ ደረጃ ጉዳይ ለማየት የሚቀመጡት ‹‹አፓ-ካፋ›› (የጐሳው /የቤተሰቡ አባት)፣ ‹‹ቂሞታ-ካፋ›› (ከጐሳው በዕድሜ ከፍ ያለ ሽማግሌ)፣ ‹‹ፖቃላ ሙግላ›› (ቱራይታ) የጐሳ መሪው ምክትልና ‹‹ፖቅላ ቱማው›› (ዋናው የጐሳ መሪ) በመሆን ጉዳዩን በጋራ ይመለከታሉ። በዚህ ደረጃ እነዚህ አካላት የየራሳቸው ድርሻና ኃላፊነት አላቸው።

በዚህ ደረጃ የሚቀርቡ ጉዳዮች ‹‹በሞራ-ፓሌታ›› ደረጃ ታይተው እልባት ያላገኙና ተደጋጋሚ ስርቆት መፈጸም፣ አካል ማጉደል፣ ድንገተኛ ነፍስ ግድያ፣ ውጉዝ ጋብቻና መረጃ የሌላቸው ጉዳዮች በቀጥታ ‹‹በፖቅላ›› ደረጃ ታይተው የሚፈቱ ናቸው፤ በድርድር አይታዩም። ማስረጃም ሆነ ምስክር አይጠየቅም። ጉዳዩ በልዩ ዘዴ ይጣራና የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል። ከዚህ ካለፈና መተማመን ካልተቻለ ወደ “ሞራ-ኻኻ” ተሸጋግሮ እልባት ያገኛሉ።

‹‹ኻኻ›› ወይም የመሐላ ሥርዓት

ከላይ ከተገለጹት በኮንሶ ብሔረሰብ የባሕላዊ ግጭት መፍቻ ተቋማት ደረጃ በደረጃ በተለይም ‹‹በፖቅላ›› ያልተፈቱ ጉዳዮች የሚፈቱት ‹‹ኻኻ›› ወይም የመሐላ ሥርዓት በመፈጸም ነው። ‹‹ወደ መሐላ የሚያስኬዱ ጉዳዮች ዋነኛ ምክንያት ዕውነታ ፍለጋ ሲሆን አንድን ጉዳይ አጣርቶና አስመስክሮ ውሳኔ ለመስጠት ወይም መንስኤያቸው የማይታወቁ ወይንም ደግሞ በምስጢር የተፈጸሙ ድርጊቶች ለምሳሌ የእርሻ መሬት ክርክር፣ የድንበር የንብረት መካካድና ስውር ደባዎች ሲፈጸሙና መረጃ የማይገኙላቸው ጉዳዮች ሲከሰቱ እንዲውጣጡ ለማድረግ ነው።

የመሐላ ሥነ ሥርዓቱ በሚፈጸምበት ቦታ ላይ በመገኘት መሐላውን የሚያስፈጽሙት በብሔረሰቡ ‹‹አፓ-ኻኻ›› ይባላሉ። የመሐላ ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸሙባቸው ቦታዎች በየሞራዎች ላይ የሚተከሉ የትልልቅ ድርጊቶች ማስታወሻ ትክል ድንጋዮች ዳጋ ዳሩማዎች ‹‹በየፖቅላ›› ወይም ‹‹ቱራይታ›› መኖሪያ ግቢዎች ውስጥ በተለይ እናቶች ሲወልዱ የሚታረሱበት ቤት መሰል ሆኖ ‹‹አክታ›› በመባል የሚታወቅ ‹‹ፖቅላዎች ወይም ቱራይታዎች ››ባሕላዊ የእምነት ሥርዓቶች የሚያከናውኑባቸው ቤቶች መሆናቸውን ጥናት አድራጊዋ የፎክሎር ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ወጣት ቀለሟ መኮንን ትገልፃለች።

የግጭት አፈታት ሂደት

እንደ ቀለሟ ገለፃ፤ በብሔረሰቡ አንድ ግጭት እንደተከሰተ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ከአነሳሱ እስከ ውሳኔው የሚኬድበት የራሱ የሆነ መዋቅር አለው። ይህ አካሄድ እንደተፈጠረው የግጭት ዓይነት ክብደትና ቅለት፤ እንዲሁም የተፈጠሩት ግጭቶች እንደሚዳኙበት መዋቅር የሚታይ ሆኖ፣ ግጭቱ (ጠቡ) እንደተከሰተ በየደረጃው የሚሄዱበት አግባብ አላቸው። በባሕላዊ ሥርዓቱ ለተለያዩ የግጭት ዓይነቶች በየደረጃው የሚካሄደው የድርድር ሂደት የራሱ ስያሜ አለው፤ የእርቅ አፈጻጸም ሁኔታውም የየራሱ ሥርዓቶችና ስያሜዎች አሉት። ለምሳሌ ‹‹በከንታ ደረጃ›› የሚካሄደው ድርድር ‹‹ዴኻ-ከንታ››፣ ‹‹በፓሌታ››ደረጃ የሚካሄደው ድርድር ‹‹ዴኻ-ፓሌታ››፣ እንዲሁም ‹‹በፖቅላ›› ደረጃ የሚደረገው ሥርዓት ‹‹ዴኻ-ካፋ›› ይባላል።

ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ ደግሞ በይቅርታ ወይም ይቅር በመባባል፣ በቅጣት፣ በእርድና በመሐላ የሚፈቱ የግጭት ዓይነቶች አሉ። ሥርዓቶቹ በአጠቃላይ ‹‹አራራ›› ሲባሉ በስያሜ ረገድ ግን ይለያያሉ። ይኸውም በይቅርታ ወይም ይቅር በመባባል የሚፈታው የግጭት ዓይነት ሥርዓት ‹‹ዴኻ-ዴባይታ›› ይባላል። በቅጣት የሚፈቱ (የሚደመደሙ) ‹‹ዴኻ-ኾራ››፣ በእርድ (የሚፈጸሙ) የሚፈቱ ‹‹ኮዴታ›› ቃልኪዳን ነውና፣ እንዲሁም በተለያየ የመሐላ ዓይነት የሚፈቱት ‹‹ሬቃ-ኾርባይታና አኩታ›› በመባል ይታወቃሉ።

ከዚህ ውጭ ጠበኞች ያለሽማግሌ ጣልቃ ገብነት በራሳቸው ሠላም የሚፈጥሩበት ሥርዓትም አለ። ይህ ሥርዓት በብሔረሰቡ አጠራር ‹‹ቱታ› ›በመባል ይታወቃል፤ ሥርዓቱም ሰኔ አጋማሽ ላይ የሚከናወን ነው። ይህ ወቅት እሸት የሚደርስበት እንደመሆኑ የብሔረሰቡ ተወላጆች በጋራ ተሰባስበው እሸት በእንኩቶ መልክ እየጠበሱ በመብላት የሚያከብሩት ትልቅ ሥርዓት ነው። በዚህ ሥርዓት ጠበኞች በተለይ ባልና ሚስቶች ሚስት ጋለሞታ ላለመባል፤ ባልም የቀደመ ክብሩን ላለማጣት ሲል፤ ለማንም ሳያሰሙ ሽማግሌም ሳያስገቡ በራሳቸው ሠላም የሚያወርዱበት ወቅትና ሥርዓት አለ።

በብሔረሰቡ አንድ ግጭት ምንም ይሁን ምን ሲከሰት ጉዳዩ የሚታይበት ወይም የዕርቅ ሥርዓቱ የሚከናወንበት የተለየ ስፍራ ወይንም ቦታ አለው። የዕርቅ ሥርዓቱ ቦታዎች በአብዛኛው ገለልተኛ ስፍራዎች ናቸው።

የባሕላዊ ሥርዓቱ ፋይዳ

የጥናቱ አድራጊ ቀለሟ መኮንን ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቱ የሚከተሉት ፋይዳዎች እንዳሉትም ትናገራለች። ኮንሶዎች ባለፉት አምስትና ስድስት መቶ ዓመታት ከዚያም በላይ በሆነ የዕድሜ ዘመናቸው በውስጣቸው የሚፈጠሩ ከቀላል እስከ ከባድ ግጭቶቻቸውን በራሳቸው እልባት በመስጠት በባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓታቸው ይታወቃሉ ፤ ዛሬም ድረስ በዚሁ እየተገለገሉበት እንደሚገኙም ትገልፃለች። ማኅበረሰቡም ሥርዓቱን ከልጅነት ጀምሮ በተለያዩ ሕዝባዊ መድረኮች እየተማረው ተዋሕዶት አብሮት ያደገ መሆኑን ጠቅሳ፣ ከልጅ አስከ አዋቂ ጠንቅቆ እንደሚያውቀውም ታነሳለች። ይህ በመሆኑ ደግሞ ለባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቱ ተገዢ በመሆን ለዘላቂነቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ታስረዳለች።

እንደ ቀለሟ ማብራሪያ፤ የኮንሶ ብሔረሰብ ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ይልቅ በባሕላዊ ሥርዓቱ መዳኘትን ይመርጣሉ። ለዚህ ደግሞ እንደመሠረታዊ ምክንያት የሚያስቀምጡት ባሕላዊ ሥርዓቱ በዲሞክራሲያዊ መርሕ የሚመራ፣ አድሎ የሌለበትና ፍትሐዊ መሆኑ፣ ምስክሮች በባሕላዊ ሥርዓት መሐላ ስለሚፈጽሙና ትክክለኛ የምስክርነት ቃል ስለሚሰጡ፣ የዕርቅም ሆነ የዳኝነት ሥርዓቱ ብዙ የሥራ ጊዜ የማይሻማ መሆኑ፣ የዕርቅም ሆነ የዳኝነት ስፍራው ከመኖሪያ ሰፈር አለመራቁ፣ በቋንቋው መዳኘቱ፣ ሥርዓቱ በዕርቅ መደምደሙ፣ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ቦታዎችም በባሕላዊ እምነት ተፅዕኖ ስላላቸው እንዲሁም ‹‹ፍርዶች ሁሉ በአብዛኛው ትክክለኛ ናቸው›› ተብሎ ስለሚታመን ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አስረድታለች።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You