አንድ ትልቅ ደራሲ ነበር፤ ንባብ ለዚህ ትውልድ እርግማን ሆኗል ሲል ሰማሁት። አባባሉ አጥንቴን ሰብሮ ስለገባ ቃሉን ተውሼ ብዙ ላሰላስልበት ፈለግኩኝ። እንዴትስ ያለው እርግማን ይሆን? በማንና እንዴትስ ተረገምን? ያ የረገመንስ ማነው? እያልኩ ስብሰለሰል በእርግጥም መረገማችን ወለል ብሎ ታየኝ። በፊት የማውቀውና በጊዜው እንደዋዛ ይታይ የነበረ አንድ ጉዳይ ነበር።
በሆነ ሰዓት ላይ ግን አብዛኛዎቻችን እርግፍ አድርገን ተውነው። በመጨረሻም ጭራሹን እንደጣልነው ሁሉ ረስተን ተላምደነው። ለዚህ ነው ዛሬ ላይ በእጁ መጽሐፍ የያዘ ሰው ያስገርመናል። “ታነባለህ! ታነቢያለሽ?” እያልን በግርምትና በአድናቆት ሁሉ መጠያየቅ ጀምረናል። በንባብ መነጽር ውስጥ ስንታይ ሁላችንም ዳሽቀንና ላሽቀን መታየታችን ሀቅ ነው።
ዛሬ ላይ አንባቢ የለም ማለት ሳይሆን እንደ ሀገር ግን አስቀያሚ መልክ ይዘናል። የምናቤን በር ሲያንኳኩ የነበሩ ጥቂት ጥያቄዎችን ጨብጬ ከአንዳንድ ሥፍራዎች ጎራ እያልኩ ቢያንስ የእውነታውን ጫፍ ለመመልከት ያስፈልገኝ ነበርና ከዚህም ከዚያም ማለቴ አልቀረም።
ከዓመታት በፊት የማውቀው አንድ መጽሐፍ እያከራየ የሚተዳደር ሰው ድንገት ትዝ አለኝ። በመንደራችን ውስጥ በዚህ ሥራው የማውቀው ገና በልጅነቴ ዘመን ነበር። በወቅቱ በረከትን የማያውቀውም ሆነ የማይፈልገው ሰው አልነበረም። ያ የመጽሐፍት ማከራያ ቤቱ ከአንድ የመጽሐፍ መደብር የሚበልጥ እንጂ የሚተናነስ አልነበረም። ይኼን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ከሀሳቤ ላይ ከተፍ አለና አድራሻውን አፈላልጌ አገኘሁት።
ነገሩ በስልክ ጥሪም ቢሆን ስለመጽሐፍቱ ዓለም የቀድሞና የአሁን ሥራው፣ እንዲሁም ስለአንባቢው ጥቂት ነገር ልጠይቀው ሞከርኩ። “ወይ መጽሐፍ…ወይ አንባቢ! …የመጽሐፍ ኪራዩንማ ከተውኩት አራት ዓመታት አለፈኝ እኮ። ሥራውን የጀመርኩት ገና ከ11 ዓመቴ ጀምሮ በጋዜጣ አዟሪነት ነበር። የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ከነበረው የመጽሐፍ ኪራይ ሥራዬ በእውነት የያኔው ጋዜጣ ማዞር እጅግ የተሻለ ነበር።
ስለ አንባቢው ካልከኝ እውነተኛ አንባቢ የነበረበት፣ ከተማሪው እስከ አዛውንቱ ያለ መጽሐፍት የማይንቀሳቀስበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። አዳዲስ መጽሐፍቶችን ባመጣሁ ቁጥር ሁሉ ቁጥሩ አልበቃህ እያለኝ ወረፋ ለማስያዝ እንዴት እጨናነቅ እንደነበረም አልረሳውም።
ታዲያ አሁን አሁን እንኳንስ ሥራዬ ብሎ ገንዘቡን ከፍሎ ለመከራየት ቀርቶ ከፍለኸው አንብብ ብትለው እንኳን ሦስት ገጽ ለመግለጥ ጊዜ የሌለው በዝቷል። በመጨረሻም ለኑሮዬም አልሆን ቢለኝ ጊዜ መጽሐፍቱን ሸጥኳቸው። ስንት ዘመን ሳስነብብ የኖርኩበትንም ቤት ቢሆን አሁን ትልቁ ልጄ ቪዲዮ ቤት ከፍቶ ፊልም ያከራይበታል” እያለ ብዙ ነበር ያጫወተኝ። ታዲያ በእርግጥም ይኼ እርግማን እንጂ ሌላ ምን ሊባል።
በዓለም ዓቀፍ የንባብ መነጽር ውስጥ ስንታይ ምን እንደመሰልን ለማወቅ ፈልገን ከወዴት ነን? ካልን…የሀፍረት ማቅ ከሚያስለብስ፣ የውርደት ሸማ ከሚያስደርበው የመጨረሻው እንጥፍጣፊ ደረጃ ላይ ነን። በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የየሀገራቱ የአንባቢና የንባብ ልምድን መሠረት አድርጎ በተሠራ አንድ ዓለም ዓቀፍ ጥናት ላይ ትልቋ ኢትዮጵያ በትንሽዬ የንባብ ዱካ ላይ ተቀምጣለች።
ካሉት የዓለም ሀገራት በሙሉ ከሁለት ሀገራት ብቻ በልጣ ከመጨረሻዎቹ ሦስተኛ ላይ ጭራ ሆና ተገኝታለች። እና ይኼ እርግማን አይደለም? ከኛም የባሰ አለ በማለት አብረውን የወደቁትን እየተመለከትን ተጽናንተን እንዳንኩራራ እንኳን የበለጥናቸው ሁለቱ ሀገራት በታሪክም ሆነ በምንም ዓይነት መስፈርት ከኛ ጋር ሊነጻጸሩ የሚችሉ አይደሉም። በጣም ትንንሽ ሀገራትና ደሴቶች ናቸው። እንግዲህ ከማንም በፊት የራሷን ፊደላት ቀርጻ፣ ከድንጋዩም አልፎ በግዙፍ ብራና ላይ በመጻፍ የዓለም ዓይን የነበረች ሀገር ወርዳ ከጫማ ስር ተረከዝ ላይ ስትቀመጥ በእውነቱ ይህ ትልቁ የትውልድ እርግማን ነው።
“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” የሚል ባዶ ዲስኩር ይዘን ስንደሰኩር ብቻ እስከመቼ እንደምንኖር…ስለ ማንበብ ካነሳን ማንበብ ማለት ልቦለድ መጽሐፍትን ብቻ መኮምኮም እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ማንበብ ማለት ለቀጣዩ ፈተና የሚሆኑንን የፊደላት ኳኳታና የቁጥሮችን ሒሳባዊ ሽውሽውታ መቅለብ ማለት እንዳልሆነም ማወቅ ወሳኝ ነው።
ማንበብ ሁለቱንም አጣምሮ ይይዝ ይሆናል እንጂ፤ ከአስኳላው ቤት አሊያም ከፍልስፍናና ከምናብ አለም ውስጥ ብቻ ቁጢጥ ብሎ የሚቀር አይደለም። ማንበብ ሙሉ ሰው የሚያደርገው የአንዲት ዐረፍተ ነገርን ዳና ተከትለን ስንዝር ሀሳብ፣ ጭብጦ ዕውቀት ስላገኘን አይደለም። ማወቅ የምንፈልገውን ብቻ ፈልገን መጽሐፍትን ብናገላብጥ ሙሉ ምላሽ እንጂ ሙሉ ሰውነትን አይሰጠንም። ብዙ ስንገልጥ ብዙ ይገለጥልናል።
መጽሐፍ የሁል ጊዜም የሰው ልጆች የነብስ ምግብ ነው። ምግቡ ተትረፍርፎ በዪው መጥፋቱ ግን አስገራሚው ጉድ ነው። ደራሲው እንደ ውቅያኖስ ሰፍቶና እንደ ባህር ጠልቆ ሳለ አንባቢው ግን በኩሬ መቅረቱም ያሳዝናል። በዚህም የድሮ አባዜ የኋልዮሽ ናፍቆት አልቀረምና ላለፉት ብዙ ዘመናት የሚነበብ እንጂ የአንባቢ ችግር አልነበረም። የተማረው ትንሽ የሚያነበው ግን ብዙ ነበር።
“አያ ኤገሌ!…ኤገሊት!.. እታለም!…ወንድማለም!” እያሉ ተጠራርተው “ከተማ ስትወጪ፣ ከተማ ስትወጣ በእግረ መንገዱ ጋዜጣውን አሊያም መጽሔቱን ከተቻለም መጽሐፉን ያምጡልኝ። አምጣልኝ።” እየተባለ በፍቅርና በናፍቆት የተነበበት ጊዜም አለ። አሁን ወዲህ ሞልቶ ሲፈስ የሚቀዳ ጠፋና እርግማን ይሁን…እርግማን ተባለ። መጽሐፍቱ ሲበረክቱ አንባቢው ሲመናመን ሲመነምን ተሟጦ ከቋፍ ላይ ደረሰ። 30 እና 40 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብንል ድንቅ ነው እንላለን። በቅርብ ከነበረው በ90 እና 2 ሺህ ድንበር ላይ እንኳን ሀገራችን በንባብ የምትታማ አልነበረችም። በባለፈው የወጣውን መረጃ ተከትለን የአሁኑን ስንመለከት ግን ከጠላት መሳቂያና መሳለቂያነት ያለፈ አይደለም።
የአንባቢያኑ ቅዝቃዜ ደራሲያኑንም ጥሩ ስሜት እንዳይሰማቸውና ወደፊት እንዳይንቀሳቀሱ ጋሬጣ ሆኖባቸዋል። ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል መጽሐፍት በተመረቁባቸው መድረኮች ሁሉ እሮሮው ብዙ ነው። ጉዳዩ ሳይነሳ ታልፎ አያውቅም። እዚህ ውስጥ የሚታየው ውስብስብ የችግር ገመድ ብዙ ነው። በመሀል ተጠልፎ የሚወድቀውም እንደዚያው። በእርግጥ ደራሲያን የሚጽፉት ትርፍ ለማጋበስና ህይወታቸውን ለመቀየር አይደለም። ደራሲ ጽፎና አትርፎ ህይወቱን ቀይሮም አያውቅም።
መቀየሩ ቀርቶ ነገሩ ከትልቅ ኪሳራ ጋር ነው። በቅርቡ አንድ መድረክ ላይ መጽሐፉን ለማሳተም ወደማተሚያ ቤት የላከ አንድ የቅርብ ወዳጄ ገና ከአሁኑ የ90 ሺህ ብር እዳ መጥቶበታል ሲል ሰማሁ። በአጋጣሚ የእርሱን አነሳው እንጂ ይህ የሁሉም ደራሲያን ማጥ ነው። በሀገራችን ውስጥ ለዘመናት በካፍቴሪያና ሻይ ቡና ሥፍራዎች ሳይቀር ጋዜጣና መጽሔቶች ሳይቀሩ ተቀምጠው እንመለከት ነበር።
ሌላው ቀርቶ እንደዛሬው ሶፍትና ማስቲካ ብቻ አጭቀው ሳይቀመጡ በፊት ሊስትሮዎች እንኳን ደንበኛው የሚነበውን ነገር ይዘው ነበር የሚቀመጡት። ጸጉር ቤቶች ውስጥ ሰው እንዲሁ ተቀምጦ አይታይም። በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ በባለጉዳዮች ማረፊያ ጋዜጣና መጽሔት አይጠፋም። በዚህ ፈንታ ዛሬ ላይ ህዝበ አዳሜ ከስልኩ ፊት ላይ ፈጦ ይታያል። የለመድነው ሁሉ ቀርቶ ባዶ መቅረት እናስ እርግማን አያስብልም?
በማንበብ ብቻ ትልልቅ ነገሮችን ለማየት እንደቻልን ለማወቅ የተለየ ምርምርና ዕውቀት አያስፈልገውም። በሀገራችን ውስጥ የኪነ ጥበብ አብዮት በተቀሰቀሰባቸው 1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምናስታውሰው ምንድነው? አስቀድሞ ታላላቅ ጸሐፊያን ነበሩ የተነሱት። የስነ ጽሑፉ ዓለምም በርከት ያሉ አንባቢያንን እየፈጠረ በትንሽ ጊዜ ውስጥም በየጥበባት ዘርፉና በጥበብ አፍቃሪው ዘንድ ትልቅ ነገር ተቀሰቀሰ። በቲያትሩም ትልልቅ ጸሐፊያን ተነሱና እያበበ መጣ። የስነ ጽሑፉ ማበብ የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲያንን እንዲወለዱ ሆነና ሙዚቃውም በሌላኛው አቅጣጭ ከፍ ማለት ጀመረ። ሁሉም በየአቅጣጫው በሚያደርገው ሩጫ የኪነት ባንድ ኦርኬስትራዎችና ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ቡድኖች ተጧጧፉ። እናም ይሄ ትውልድ ሲነሳም ሆነ ሲጨርስ ከንባብ ጋር ነበር።
ወደ ሀገራችን የፖለቲካ ማጀት ብንገባ የማንበብ ሀይል ምን ያህል እንደሆነ ይገለጥልናል። ውጤቱንም ሆነ መነሻውን እንደየራሳችን እንቀበለውና መነሻውን ግን እንደ አብነት እናውሳው። በዚያው የኪነ ጥበብ አብዮት በተቀሰቀሰበት ሰሞን የፖለቲካውም ምሰሶ መወዝወዙ አልቀረም ነበር። በወቅቱ የነበረው የሀገራችን ፖለቲካ ለህዝቡ ጥቅምና ፍላጎት እንዲቆም በምክንያታዊነት ከቆሙት መሀከል የተማሪዎች ፍትጊያ ዋነኛው ነበር፤ የኋላ አካሄዱን ቢስትም። ጥያቄዎችን አንግቦ ለምን? ሲል የተነሳው የተማረ ሀይል ስለነበረ ብቻ ሳይሆን ጭራውን ከንባብ ጋር የቆለፈ ስለነበረም ነው።
ቀጥሎም ሲያካፋ የነበረው የማንበብ ነገር ብሶ እንደ ዶፍ መውረድ ጀመረ። ከዚያ ኋላም በነበረው በእጁ መጽሐፍ ይዞ የተገኘ እስከመታሰርና ቅጣት ድረስ ደረሰ። ምክንያቱም ንባብ ሙታንን ከየመቃብሩ ይቀሰቅሳል። ያነበበ ትውልድ የመኖር አላማው ለራሱ ሳይሆን ለሀገርና ለህዝቡ ነው። ይህቺ ትንሽ የምትመስለው ንባብ መላውን የሰው ማንነት፣ መላውን የሀገር ንቃትና ዕድገት ቀስቃሽ መርፌ ናት።
መማርና የተማረ ትውልድ ብቻ ከሆነ የምንፈልገው በደረቁ ከማወቅ አያልፍም። ዕውቀትን ወደ ጥበብ መቀየርና ለውጥ ፈጣሪ መሆን ነው ትልቁ ነገር። በሀገራችን ውስጥ ቀድሞ በነበረው የንባብ አብዮት ከተወለዱ ሰዎች መሀከል ለአብነት ጳውሎስ ኞኞን ሳናነሳው አናልፍም። አዎን ጳውሎስ ኞኞ ማስትሬት ዲግሪ፣ ዲግሪ አሊያም ዲፕሎማ አልጫነም። ኮሌጅ አልበጠሰም። እንዲያውም ከአራተኛ ክፍል አላለፈም። ግን ጳውሎስ ኞኞን በዕውቀት፣ አውቆ በመኖር ማንስ ይበልጠው ነበር? ማንም። ይኼ ሁሉ የማንበብ ሀይል የሠራው ተአምር ነበር።
በመቀጠል ከዘመን ዙረታችን ተመልሰን ወደዚህኛው የኛ ዘመን ስንመጣ ነገሮች ሁሉ ተቀያይረዋል። የነበሩ ነገሮች ዛሬ ከቦታቸው የሉም። እንደቀድሞው በየመንገዱ የሚሯሯጥ ጋዜጣ አዟሪ፣ ሻጭ የለም። ጫማውን ለማስወልወል ተቀምጦ ጋዜጣና መጽሔት ይዞ ጫማውን የሚያስወለውለው እንኳ አይታይም። ከተማው ሙሉ በእጁ መጽሐፍትን አንጠልጥሎ በአውቶብስና በየባቡር ፌርማታው፣ በታክሲና በመንገድ የሚታይ ሰው የለም። በገዢ ተጨናንቀው “እትን መጽሐፍ…ያ መጽሐፍ…የዛሬ ጋዜጣ…የሳምንቱ መጽሔት አልቋል።
የለም።” የሚሉት መጽሐፍት መደብሮችና ኪዮስክ የንባብ ግብአት መሸጫ ሱቆች የሉም፤ ዛሬ ላይ አፋቸውን ከፍተው የገዢና የአንባቢ ያለህ በማለት ላይ ናቸው። ታዲያ እኚህ ሁሉ ነገሮችን እንደ ቀልድ ስናልፋቸው ቀልድ መስለውን ነበር። ውጤቱን ግን ይኼው በሀገሪቱ የፊት መልክ ላይ እየተመለከትነው ነው። የዛሬው የፖለቲካ ሩጫችን በፌስቡክና ዩትዩብ ሆኖ ያመከነው ጥይት ብዙ ነው። ኑሯችን በቲክቶክና ዋትስአፕ ሆኖ የጣልነው እልፍ ነው። ህይወት በቴሌግራምና ኢንስታግራም ሆኖ የረገፈው ትውልድ አሸን ነው። እኚህ ሁሉ ነገሮች ጥሩ ሆነው ሳለ ግን መጥፎ አደረግናቸው።
ከማንበብ ዕውቀት ይገኛል፤ ከዕውቀት ደግሞ ጥበብ ይመዘዛል። ከጥበብ ደግሞ ውስጣዊ መንፈስና ስሜቶች ይወለዳሉ። በውስጣዊው መንፈስም ደግሞ ውጫዊው የሰው ልጅ ስብዕና ይገነባል። የምንበላውን ምግብ ከጎረስንበት ቅጽበት ጀምሮ የራሱን ሳይንሳዊ ኡደት ተከትሎ ሰውነት እንደሚሆነን ሁሉ የምናነበውም ነገር ስብዕናና ማንነታችንን የሚገነባው እኚህን የራሱን ኡደቶች በመጨረስ ነው። ስላነበብን ብቻ አዋቂ አሊያም ጠቢብ አንሆንም። በኬሚካል የተጨማለቀና በተፈጥሮ የበለጸገ ምግብ ሲበላ የኖረ ሰው እኩል አይደለም። የሚጠቅመውን ያነበበ የሚጠቅም የህይወት ስንቅ ያገኛል። ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ከሚለው አባባል ጀርባ አለማንበብ ደግሞ ጎዶሎ ሰው ያደርጋል የሚል አመክንዮ እንዳለ ይነግረናል። ያ ነው ትልቁ የሀገር ገደልና የህይወት ዝብርቅርቅ።
ከአራት ሳምንታት በፊት ነበር… አንዱን ወዳጄን ፍለጋ ወደቤታቸው አመራሁ። በሰዓቱ ከቤቱ በረንዳ ላይ አባት አንድ መጽሔት ከእጃቸው ላይ ይዘው በማንበብ ላይ ነበሩ። በእርግጥ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሳገኛቸው የዚያን ዕለት የመጀመሪያቸው አልነበረም። በተለይ ከሥራ ጡረታ ወጥተው መንደር ላይ መዋል ከጀመሩ ጊዜ ወዲህ ከመጽሐፍና ከማንበብ ተለይተው እንደማያውቁ በጨዋታ መሀል ቀደም ሲል ባለንጀራዬ አጫውቶኝ ነበር።
ጓዴ ከሥራ ቦታው ወጥቶ በቀጠሯችን ሰዓት ከቤት ለመድረስ ባልመቻሉ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ግድ ብሎኝ ነበር። በዚያ ሰዓት ከእኚያ ትልቅ ሰው ፊት ተቀምጦ ከአንደበታቸው ለመማር በመቻሌ አጋጣሚው ጥሩ እንጂ መጥፎ አልነበረም። እንደዋዛ በአንዲት ጥያቄ ምላሽ ጀምረው እጅግ አስተማሪ ከሆነው ከጣፋጩ የህይወት ልምዳቸው እያነሱ ካጠገቡኝ በኋላ “ለመሆኑ ታነባለህ?” ነበር ያሉኝ።
እሳቸውን ተመልክቶ አዎ አነባለሁ ማለቱ ቅጥፈት መስሎ ስለተሰማኝ አነባለሁም አላነብም ለማለቱም ግራ ገብቶኝ ሳመነታ ሳለሁ ምላሼንም ሳይጠብቁ “ለነገሩ የዘንድሮ ወጣት ጸሐይ ወጥታ ጨረቃ እስክትጠልቅ ድረስ ስልክ ላይ ፈጦ መጠቅጠቅ እንጂ ምን ማንበብ ያውቅና…” በማለት ጥቂት አሰብ ካደረጉ ኋላ መነጽራቸውን ከዓይናቸው ላይ አነሱና…
“ሰው እንዴት ያለንባብ ይኖራል..እኛ እኮ በናንተ ዕድሜ ሳለን እንግሊዝኛው አይቀረን የራሺያ፣ የምንችል ጣሊያንኛውንም ጭምር እናነብ ነበር። በእርግጥ እኔ አልችለውም ነበር እንጂ አንድ የሥራ ባለደረባዬ በስፓኒሽ የተጻፉ መጽሐፍቶችን ሁሉ ሲያነብ ሳይ በውስጤ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኝ ነበር። ሁሉንም ችለን ሁሉንም ብናነብ ደስ ይለን ነበር፤ ምክንያቱም ብዙ ተጠቀምንበት እንጂ አንድም የተጎዳንበት ነገር የለም። እኔ እንኳን በዚህ እርጅና ላይ ከመቃብሬ አፋፍ ላይ ሆኜ ከዓይኔ ጋር እየታገልኩ ዛሬም አነባለሁ። መብላትና መጠጣት፣ መተንፈስ እስካላቆምኩ ድረስ እያነበብኩ ስጋዬን አዝናንቼ፣ ነብሴንም አስደስትበታለሁ። ዛሬ ቤቴ ሙሉ መጽሐፍት ናቸው። መደርደሪያው ሞልቶ በየካርቶኑ ላይ ታጭቋል።
ግን አቧራ ሲጠጡና ሲበላሹ እንጂ የሚያነባቸው የለም። ከስድስቱ ልጆቼ መሀከል የ…ታናሽ እንዲያው እሷ በማንበቡ ሻል ትል ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው ማንበብ የሚገድለው ሙት ብቻ!… ባዶ ዘመን፣ እንቶፈንቶ ትውልድ መጣ…” በምትለው ንግግራቸው ውስጥ እራሴን አይቼ፣ ራሴን ተመልክቼ አቀረቀርኩበት። እርግማኑን አላቆና ጨፍልቆ፣ ከመጽሐፍትና ከንባብ ክንድ ጋር ተጣብቆ መኖር ሁላችንንም ግድ ይለናል። የዓይናችንን ቅርፊት እናንሳው እንጂ እንዲነሳልን በመጠበቅ ዛሬ ላይ ሆነን ነገን አናርፍድ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም