የሀገር በቀል አምራቾችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በዘላቂነት የማሳደግ ጥረት

በአሁኑ ወቅት በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። እነዚህ ሀገራት ባለሀብቶቻቸውን በማገዝና በመጠበቅ ያከናወኑት ተግባር የአምራችነት አቅማቸውን አሳድጎ የምጣኔ ሀብት እድገታቸው ዘላቂ እንዲሆን አስችሏቸዋል። ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሰረት ከሆናቸውና ከውጭ ጥገኛነት ለመላቀቃቸው ተጠቃሽ ከሆኑት መካከል ይሄው የውስጥ አምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይጠቀሳል። እነዚህ ሀገራት አሁንም ቢሆን ባለሀብቶቻቸውን የሚያበረታቱባቸው ልዩ የድጋፍና ጥበቃ መርሃ ግብሮች አሏቸው።

የምጣኔ ሀብት ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉ የልማት አንቀሳቃሾች ናቸው። ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ ነው የሚባል ሳይሆን ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚታየው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ ግን ተስፋ ሰጭ ሆኗል።

የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች መደረጋቸው፣ ለኢንቨስትመንት እድገት መሰናክል የነበሩ ሕጎችና መመሪያዎች መሻሻላቸው፤ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ዘርፎች እየተተገበረ ያለው ቀልጣፋና ፈጣን አሰራር እና የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራዎች በመሰራታቸው ምክንያቶች ሆነው ይጠቀሳሉ። በተጨማሪ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ በመንግሥት ልዩ አቅጣጫ መቀመጡና ትኩረት መሰጠቱ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለሙ የሪፎርም ስራዎች መተግበራቸው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ ማደግ ትልቅ ሚና አላቸው።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያለሙ የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው። በቅርቡ በሌላ ኃላፊነት ወደ ሌላ ተቋም የተዛወሩት የቀድሞው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ፣ በ2016 ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ አምራቾች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው ሲሉ መግለጻቸውም ይታወሳል።

እንደ አቶ አክሊሉ ማብራሪያ፣ ባለፈው አንድ ዓመት በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን የማነቃቃት፣ የማበረታታትና ወደ አምራች ዘርፉ ገብቶ ውጤታማ ስራዎችን እንዲሰራ የማድረግ ስራ ነው። በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ አምራች ዘርፉ እንዳይገቡ መሰናክል የነበሩ ችግሮች ተለይተው መፍትሄ እያገኙ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፣ ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚሰጠው ቦታ አነስተኛ ነበር። በ2015 እና 2016 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲነቃቁ ባለሃብቶቹ ያሉባቸውን የፋይናንስና ሌሎች ክፍተቶችን የሚሞሉ ተግባራት ተከናውነዋል። በመሆኑም በ2015 እና ዘንድሮ ከተመዘገቡት ባለሀብቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው።

አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ ጓዙን ጠቅልሎ የሚሄድ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ጥገኛ ሆኖ መቀጠል ተገቢ ስላልሆነና ተወዳዳሪ የሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብት ማሳተፍና መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል። ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅማቸው አድጎ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ አመላካች ነው።

‹‹ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገቡ ያስደስታል›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ ‹‹ሀገር በቀል ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው በምርት ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ የኩባንያዎቹ የማምረት አቅማቸውና ተወዳዳሪነታቸው ማደጉን ከማመላከቱም በተጨማሪ የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በሽርክና (Joint Venture) የሚሰሩበት የቢዝነስ ሞዴል እድገት እያሳየ እንደሆነም ጠቋሚ ነው›› ይላሉ።

አቶ አክሊሉ እንደሚያስረዱት፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የታሪፍ እና የቅድመ ክፍያ ማሻሻያዎች ይጠቀሳሉ።‹‹ተጨባጭ ለውጥ መፍጠር የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ለአንድ ሺ ካሬ ሜትር የለማ መሬት የሚከፍሉት የኪራይ ክፍያ 14ሺ ብር ነው። ቀደም ሲል በዶላር ይከፈል የነበረውን የኪራይ ክፍያ በብር እንዲከፍሉ ተወስኗል። ቅድመ ክፍያ (Down Payment) ከ20 በመቶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል›› በማለት ባለሀብቶቹን ለማበረታታት ስለተወሰዱት እርምጃዎች ይናገራሉ።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ የተወሰዱት እርምጃዎች ቀደም ሲል የነበረውን 10 በመቶ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎ ከአምስት እጥፍ በላይ እንዲጨምር አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገኙ ኢንቨስተሮች መካከል 55 በመቶዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። ‹‹የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት ብዙ ጥቅም አለው። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ባበረታታን ቁጥር ካፒታሉ የሀገር ውስጥ ካፒታል ሆኖ ይዘልቃል። የስራ እድል የሚፈጠርበት እንዲሁም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የሚስፋፋበት ካፒታል የሀገር ውስጥ ካፒታል ሆኖ ይቀጥላል። የውጭ ባለሀብቶች ትንሽ ችግር ሲፈጠር ጥለው ይሄዳሉ። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን ችግር ቢኖርም እንኳን ተጋግዞ በማለፍ ስራቸውን ይቀጥላሉ›› ይላሉ።

እነዚህን ለውጦች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያግዝና ለሁለት ወራት የሚቆይ ‹‹መሬታችንን ለባለሀብቶቻችን›› የተሰኘ ንቅናቄ በቅርቡ ተጀምሯል። ንቅናቄው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው የለሙ መሬቶችን ቅድሚያ ለሀገር በቀል አምራች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በመስጠት አምራች ባለሀብቶች ለማስያዝና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሚፈፀም እንደሆነ አቶ አክሊሉ ያስረዳሉ።

‹‹ኢትዮጵያውያን ኢንዱስትሪያሊስቶችን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ ትልቅ ራዕይ ተይዞ እየተሰራ ነው›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ ወጣት ጀማሪዎችን እና የማምረቻ ቦታ ያጡ ኢትዮጵያዊ አምራቾችን ለመደገፍና የበለጠ ለማበረታታት ከ70 በላይ የሚደርሱ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመጀመሪያ ዙር በማሳተፍ በቦሌ ለሚና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ንቅናቄ መጀመሩን ይገልፃሉ።

በቅርቡ ‹‹ሶሎ ሰብ›› የሕክምና መሳሪያዎች ማምረቻ ኩባንያ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት መሰረት በማድረግ ወደ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ለማምረት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። የኩባንያው ባለቤት አቶ ሰለሞን ሰብስቤ የመንግሥት እርምጃ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን እንደሚያበረታ ይገልፃሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሌሎች የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኩባንያቸው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ለማምረት ላቀረበው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠቱ፣ ሌሎች ድርጅቶችም ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲያመርቱ ያበረታታል። ‹‹የማምረቻ ቦታ እጥረት ነበረብን፤ ክፍያ የሚፈፀመውም በውጭ ምንዛሪ ነበር። በአጠቃላይ ቀደም ሲል የነበረው አሰራር የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ አልነበረም። አሁን ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉት ማሻሻያዎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጉታል›› ይላሉ።

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ጥረት በብዙ መልኮች ሊገለፅ ይችላል። ባለሀብቶቹን የሚያበረታቱ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ፣ ፋይናንስን ጨምሮ ግብዓቶችን በማቅረብ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሟላት እንዲሁም ቢሮክራሲያዊ የአሰራር ውጣ ውረዶችን በማቃለል ለባለሀብቶቹ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል። ባለሀብቶቹ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማቅረብ ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርቶችን በመተካት እና የወጪ ንግድን በመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸው ይህን ሚናቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ በመንግሥት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።

በተለይ ኢትዮጵያ በስራ አጥነትና በዋጋ ንረት እየተፈተነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። መንግሥት ለባለሀብቶቹ የሚያደርገው ድጋፍ ምጣኔ ሀብቱን በማነቃቃት፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ የገቢ ንግድ እቃዎችን በመተካት፣ የወጪ ንግድን በማሳደግ ጥቅል ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲኖረው ያደርጋል። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ሀገር በራሷ አምራቾች ላይ እንድትተማመን ያስችላል። ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ከሚከሰት አደጋ ለመዳንም ይረዳል። አምራችነቱን ያላሳደገ እና ፍላጎቱንና አቅርቦቱን በራሱ የማምረት አቅም ላይ ያልመሰረተ ምጣኔ ሀብት ደግሞ ዘላቂ እድገትን ሊያስመዘግብ አይችልም። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት እንድታስመዘግብ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ ይገባል።

ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ድርሻ በየጊዜው እየተሻሻለ እንደመጣ ባይካድም በቂ የሚባል ግን አይደለም። ስለሆነም ለዘላቂ የሀገር ልማትና እድገት አስተማማኝ ዋስትና መሆን የሚችሉትን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍና ተወዳዳሪ የማድረግ ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ትብብርና በእርዳታ ስም የሚደረግን የሀብታም ሀገራትንና ተቋሞቻቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት ሉዓላዊነትን እስከማስከበር ድረስ የዘለቀ ትርጉምና ፋይዳ አለው። ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ደግሞ ሁነኛው መፍትሄ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው ዋነኛ ተዋንያን እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም

Recommended For You