ተሰማ መንግስቴ በሚያየው ነገር ተደንቋል። ከሰው የስራ ትጋት ባሻገር የስራው ፍጥነትና ጥራት አስደምሞታል። በአይኑ በብረቱ አይቶ የታዘበውን እና ውስጡ እርካታ የፈጠረበትን የኮሪደር ልማት ለጓደኞቹ በዝርዝር ለማስረዳት ተቻኩሏል። እናም ማምሻ ጉሮ ሰሪ ለመድረስ እየገሰገሰ ነው። ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ሲደርስ ዘውዴ መታሰቢያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም አፍ ለአፍ ገጥመው የሞቀ ጨዋታ ይዘዋል።
በያዙት ጨዋታ በመመሰጣቸውም የተሰማን መምጣት እንኳን ልብ አላሉትም ነበር። በሁኔታቸው ተገርሞ ‹‹እረ እባካችሁ፤ የእግዘኣብሄር ሰላምታ ይቀድማል፤ እንዴት አመሻችሁ ብል እንኳን የሚሰማኝ ጠፋ እኮ ››ብሎ በግርምት ተመለከታቸው። ሁለቱም ከመቀመጫቸው ተነስተው በይቅርታ ስሜት ‹‹ውይ ተሰማ ደርስሃል እንዴ፤ ይቅርታ ገብረየስ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ሄዶ የገጠመውን ውጣ ውረድ እያጫወተኝ፤ በጨዋታው ተመስጠን፤ አላየንህም፤ ይቅርታ፤ ቁጭ በል፤ በእግዜር ›› ብለው ቁጣውን አበረዱት።
እሱም ውስጡን ሲያስገርመው የነበረውን የኮሪደር ልማት ስሜቱ ሳይጠፋ በአይኑ በብረቱ ያየውን ግርምት የሚያጭር ስራ የስራ በዓል፤ ፍጥነትና ጥራት ሊያጋራቸው አንደበቱን ሞረደ። ሆኖም ገብረየስ የገጠመው ውጣውረድ ደግሞ ስሜቱን ስለተቆጣጠረው በሙሉ ቀልቡ አይሰማኝም ብሎ ስጋት አደረበት።
ተሰማ እንደተቀመጠ ገብረየስ እና ዘውዴ የጀመሩትን ጨዋታ ቀጠሉ። ገብረየስ በስሜት እየተናገረ ነበር። ‹‹አንዳንድ ተቋማት እኮ ከሚኖሩ ባይኖሩ ይሻላል። በመኖራቸው ሕዝብ ከሚጠቀመው ይልቅ የሚጎዳው ይበዛል። አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ያለው ቢሮክራሲ የተገልጋይ ወገብ ይቆርጣል።
በተለይ አሁን አሁን ኔት ወርክ የለም በሚል ሰበብ ተገልጋዩ መከራውን እየበላ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሄደ ሰው በተደጋጋሚ ከሚያደምጣቸው ቃላት መሃል ‹‹ኔት ወርክ የለም ››የሚለውን አባባል የሚስተካከል ያለ አይመስለኝም። ግብር ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ የኤሌትሪክ ቢል ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ የውሃ ቢል ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ የቤት ኪራይ ለመክፈል ኔት ወርክ የለም፤ ብር ከባንክ ለማውጣትና ለማስገባት ኔት ወርክ የለም ብቻ በአጠቃላይ ኔት ወርክ የለም የሚለው ቃል ሀገሩን አጥለቅልቆታል።
በእርግጥ ይህ ሁሉ ኔት ወርክ የለም የምር ኔት ወርክ ስለሌለ ነው ወይስ ሰነፎችና ሙሰኞች የፈጠሩት ማምለጫ ? የሚለውን መፈተሽ ይገባል። እንደ እኔ ግን አልፎ አልፎ ከሚያጋጥመው የኔት ወርክ መቆራረጥ ውጪ በረባ ባልረባው ኔት ወርክ የለም በሚል ሰበብ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ‹‹ነገ ና፤ ከነገ ወዲያ ና›› በሚል ተገልጋይን ከፊት ለማራቅ የሚደረግ ሙከራ የሚበዛ ይመስለኛል።
አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞቻችን ለደንበኛ አገልግሎት ክብር ስለሌላቸው ተገልጋይን ከፊት ማራቅን እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ነው። ለተቸገረ ደንበኛ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን ተሸክሞ ከቢሮ ወጥቶ እንዲርቅ የማድረግ የማድረግ ስልትን ይጠቀማሉ። በአግባቡ ከመነጋገርና ችግርን ከመፍታት ይልቅ ‹‹አይሆንም፤ አይቻልም ›› የሚሉ ሃሳቦችን በመደርደር ደንበኛ መፍትሄ ሳያገኝ እንዲሄድ ማድረግ የተለመደ ነው።
አብዛኞቹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አርፍዶ በመግባትና ቶሎ በመውጣት፤ ሕዝብን በማጉላላት፤ ምልጃ በመጠየቅ፤ በትውውቅና ዘመድ አዝማድ መስራት፤ በማመናጨቅ ጭምር የተገልጋይን ቆሽት የሚያደብኑ መሆኑን የደረሰበት ያውቀዋል። ብዙዎችም ‹‹ሰው ጤፉ›› የሚባሉ አይነት ናቸው። ››ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ።
ዘውዴ መታሰቢያ በጥሞና ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ እሱም የግሉን ሃሳብ አከለ። ‹‹ልክ ነህ ገብረየስ። እኔም መስማት የማልፈልገው ቃል ኔት ወርክ የለም የሚለውን ነው። በርካታ ተቋማት የስነምግባር መርሆች ብለው መግቢያ በራቸው ላይ ዝርዝር ነጥቦችን በማስታወቂያ መልኩ ይለጥፋሉ። 12 ስነ ምግባር መርሆች ተብለውም ይታወቃሉ። ከእነዚህ ስነ ምግባር መርሆች ውስጥ በተራ ቁጥር አንድ የሚቀመጠው ቅንነት ነው። ቅንነት የሁሉም ነገር መሰረትና መነሻ በመሆኑ ቅድሚያ መሰጠቱ አግባብ ቢሆንም አተገባበሩ እና ክትትሉ ላይ ግን ጥያቄ የሚነሳበት ነው።
ቅንነት ተራ ቁጥር አንድ ሆኖ እንደመቀመጡ የትኛው ሰራተኛ ነው በዚህ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ በቅንነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ የሆነው። እንደፋሽን በየቦታው የበዛው ‹‹ኔት ወርክ የለም›› የሚለው ምላሽስ ምን ያህል እውነተኛ ነው። ወይንስ ተገልጋይን ለማራቅና ለሙስና ለማመቻቸት ከቅንነት ውጪ እየተሰራ ያለ ስራ ነው።
በየቦታው ተዘዋውሮ ለተመለከተው ሕብረተሰቡ ከተማረረባቸው ቃላት ውስጥ ‹‹ኔት ወርክ የለም ›› የሚለው ቀዳሚው ነው። ‹‹ኔት ወርክ የለም ››የሚለውን ቃል የሚሰማ ተገልጋይ ወሽመጡ ቁርጥ ይላል። ጉዳዩን ጨርሼ ቶሎ ወደ ስራዩ እመለሳለሁ ብሎ ያሰበ ሁሉ ፊቱ በሀዘን ድባብ ይዋጣል። ኔት ወርክ እስኪመጣ ድረስም ወዲህ እና ወዲያ እያሉ መጠበቅም ግድ ይሆንበታል። በአጠቃላይ ኔት ወርክ የለም የሚለው ከንግግሩ ጀምሮ ይዟቸው የሚመጣው መዘዘም ሁሉ አሰልቺዎች ናቸው። ››ብሎ ሃሳቡን አሳረገ።
ተሰማ መንግስቴ የሁለቱንም ሃሳብ በአንክሮ ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ። ‹‹ልክ ናችሁ የሚያማርሩ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው እርግጥ ነው። እነዚህን ተቋማት ሁላችንም ታግለን ማስተካከል ይጠበቅብናል። ነገር ግን በእነዚህ ተቋማት ተሸፍነን አሁን፤ አሁን እየተሰሩ ያሉ በጎ ጎኖችንም ከመመልከት እንዳንሸሽ እሰጋለሁ።
ቀደም ሲል አንድ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ዓመታት መውሰድ የተለመደ አሰራር ነው። እኛም ሆንን መንግስት ለምደነው ቆይተናል። ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የሚዘገዩት በመንግሥታዊ ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራር፣ ቀና ትብብር አለመኖር፣ በፕሮጀክት አስተዳደር ችግርና በዕቅዶች የተፈጻሚነት ጉድለት መሆኑ በጥናት ከተረጋገጠ በኋላ በኢትጵያ አዲስ የፕሮጀከት አፋጻጸም መመዝገብ ጀምሯል።
አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶችም አስገራሚ በሆነ ፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ መታየታቸው ሀገሪቱ በፕሮጀክቶች መጓተት ስትከፍል የነበረው ኪሳራ ከፍተኛ እንደነበር ለመገንዘብ ያስችላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጓተቱትም ሆነ አዲስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ብዙ መሻሻሎች ታይተዋል። የግንባታ ሂደት በሪፖርት ብቻ ሳይሆን በቦታው በመገኘትም ጭምር ያሉባቸውን ተጨባጭ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ረገድ አዲስ የፕሮጀክት አጨራረስ ምዕራፍ ላይ መድረስ ተችሏል። አሁን አሁን እኮ ሌሊት 8 ሰዓት ጭምር ኃላፊዎች በየቦታው በመዞር የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ሲገመግሙ ማየት የተለመደ ሆኗል። ለዚህ ዕውቅና መስጠት ይገባናል።
የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ከመጣ ወዲህ ለዘመናት ሲጓተቱ የበሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ከማብቃት ባሻገር የተጀመሩትን በፍጥነት የማስቀጠልና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በሚገርም ፍጥነት ለውጤት ማብቃት ተችሏል። ከዓመታት በፊት ተጀምረው በመጓተት ብሎም በመክሰም ሂደት ውስጥ የነበሩትን የአባይ እና የኮይሻ ግድቦችን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ተችሏል። የንግድ ባንክን ሕንጻ ከመቆም ታድጎ ለአገልግሎት በቅቷል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የኢንሳ መስሪያ ቤቶች አምረውና ደምቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
አሁን ደግሞ የኮሪደር ልማት ተብሎ በአምስት የከተማዋ አካባቢዎች የተጀመረው ልማት በፍጥነትም ሆነ በጥራት የሚስተካከለው የለም። ይህ ሊሆን የቻለው በፕሮጀክት ክትትልና በኃላፊዎች ትጋት ጭምር ነው። ይህንን ሁላችንም በአይናችን አይተን የምንመሰክረው ነው።
የ137 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ አዲስ አበባ መልኳን እየለወጠች ነው። አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል።
ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከቦሌ ድልድይ በመገናኛ ወደ ሲኤምሲ፣ ከቦሌ ተርሚናል ወደ ጎሮ፣ ከሜክሲኮ ወደ ወሎ ሠፈር፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አራት ኪሎ የሚወስዱ ኮሪደሮች ባማረ መልኩ እየተሰሩ ነው።
በአምስት አቅጣጫዎች እየተከናወነ ያለው ኮሪደር ልማት ከተማዋን ከመሰረቱ የሚቀይር ነው። የተሽከርካሪ መሄጃ አስፋልቱን እና የእግረኛ መንገዱን ስፋት ለተመለከተውም ዓለም አቀፍ ደረጃን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መሆኑን ያመላክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ካሉ ዋና ከተማዎች ከኬፕታውን በስተቀር የሚወዳደራት ከተማ እንደማይኖር በተግባር የምናሳያችሁ ጉዳይ ነው።›› ሲሉ አዲስ አበባ እንደስሟ ውብ እና አዲስ የምትሆንበት ጊዜ መቅረቡን ተናግረዋል።
ይኸው ጉዳይ አሁን በተግባር እየተገለጸ ነው። ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያሉት መንገዶች እጅግ ባማረ ሁኔታ ተገንብተዋል። ዛሬ ፒያሳንና አራት ኪሎን የተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን እስኪጠራጠር ድረስ መገረሙ አይቀሬ ነው። የአስፋልቱ ጥራት፤ የእግረኛ መንገዶቹ ስፋትና ጥራት፤ የመናፈሻዎቹ እና አረንጓዴ ስፍራዎቹ ውበትና ድምቀት፤ የዘንባባዎቹ ማራኪነት በሙሉ እጅን አፍ ላይ ለመጫን የሚያስገድዱ ናቸው።
ለወትሮው በአቧራና በእርጅና ብዛት ተጎሳቁለው የነበሩ ሕንጻዎችና ፎቆች ዛሬ ታድሰው አዲስ ሙሽራ መስለዋል። በየስርቻው ተወትፈው የነበሩ ቅራቅንቦዎች ተወግደው የፒያሳና የአራት ኪሎ ውበት ወለል ብሎ እንዲታይ ሆኗል። ብዙዎች እሪ ይሉበት የነበረው እሪ በከንቱም ዛሬ ስሙን አድሶ ሰላምና ውበት ፈሶበታል።
አፍን በሚሰነፍጥ ሽታው የሚታወቀው ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ያለው መንገድም ጽዳቱ ተጠብቆለታል፤ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችም ተገንብተውለታል። በአጠቃላይ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ዓለም ከደረሰበት የዘመናዊ ከተማ መስፈርት አንጻር አዲስ አበባም መሰለፍ ጀምራለች።
ሆኖም አንዳንዶቻችን ባለማወቅ ሌሎቻችን አውቀን ይህንን ልማት ስንቃወም እንሰማለን። በተለይም ደግሞ የፖለቲካን ፍለጎት ቅርስ ፈረሰ በሚል ሽፋን የሚቃወሙና ድህነትን ቅርስ አድርገው መኖር ሚፈልጉ አውቃለሁ ባዮች በርክተዋል።
እርግጥ ነው በአዲስ አበባ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠሩና የቱሪዝም መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ ቅርሶች ባለቤት ነች። ነገር ግን ያረጀ እና ያፈጀ ቤት ሁሉ ቅርስ ነው ማለት አንድም የቅርስን ትርጉም አለማወቅ አሊያም ደግሞ ድህነትን ታቅፎ የመኖር አባዜ ነው።
የአዲስ አበባ ድህነት ደግሞ እንኳን ታቅፈውት ሊኖሩ ቀርቶ ለሰዓተራትም ሊቆዩበት የሚመኙት አይደለም። የሰው ልጅ ከሰው ስብዕና በታች ወርዶ የሚኖርበትና ሰው መሆን እስኪያስጠላ ድረስ ድህነት ሰውን የፈተነበት ነው።
ስለዚህ ይህ አካባቢ አይፍረስ፤ ሰዎች በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይኑሩ ብሎ መፍረድ ከጭካኔም በላይ ነው። አንዳንዶችም ይህን ፍርደ ገምድል ውሳኔ የሚሰጡት በአማረ ቪላ ውስጥ ነው። አለፍ ሲልም በውጭ ሀገራት ዘመናዊ አውቶሞቢል እያሽከረከሩና በቅንጡ ቤት ውስጥ እየኖሩ ነው።
ሆኖም ችግሩን በሩቅ ሳይሆን አብሮ በመኖር ጭምር የሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቼ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ አይኖሩም በማለት አዲስ አበባንም ለማደስ፤ የዜጎቹንም ሕይወት ለመቀየር ቆርጦ ተነስቷል። እኛ ነዋሪዎችም አድናቆታችንን ችረናል። በነካ እጁም አሁን እየተጓተቱ ያሉና ዘመኑን የማይመጥኑ የመንገድና መሰል ፕሮጀክቶች የኮሪደር ልማቱ መንፈስ ይጋባባቸው›› የሚል ምርቃት በማከል ሃሳቡን ቋጨ።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም