የግብር አሰባሰባችን የቤት ሥራዎች

ዜና ትንታኔ

መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት:: ይሄን ኃላፊነት ለመወጣት የራሱ ገቢ ያስፈልገዋል:: ይሄንኑ ሥራ የሚያከናውንበትን ገቢ ከሚያሰባስበብበት የገቢ ምንጭ መካከል ግብር አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል::

ለዚህም ነው ግብር ወይም ታክስ ዋናው የመንግሥት የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ልማትን እና እድገት የጀርባ አጥንት ነው ሲሉ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልጹት::

በሌላ በኩል ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት በሀገራችን ግብር የሚከፍለው ማህበረሰብ ቁጥር ከ 64 ሺህ ያልዘለለ ነው:: በሌላም በኩል የግብር ሥወራም አንዱ የዘርፉ ፈተና ነው::

በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም በሀገራችን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አንጻር የሚሰበሰበው ገቢ ከሰባት ከመቶ ያልዘዘ ሲሆን ይህ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድም ጭምር ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል::

ከዚህ አንፃር ሀገራችን ከገቢ አሰባሰብ አንጻር ያላት አቅምና እየሰበሰበች ያለው ሲነጻጸር ምን ያህል ጠንካራ ነው? የገቢ ምንጮችን አሟጦ ከመጠቀምስ አንጻር ምን ጥንካሬዎች አሉ? የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? ስንል የዘርፉ ባለሙያዎችን ጠይቀናል።

የፐብሊክ ፖሊሲና ምጣኔ ሀብት ምሁር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ መንግሥት የታክስ ሥርዓቱን ለማጠናከር እና የገቢ ግብር አማሯጮቿን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታታ ነው። በተለይም ደግሞ ንብረት ላይ ለመጣል በቅርቡ የተወሰነው ግብር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራት የሚሰበስቡትን ገቢ ከፍ ለማድረግ የታክስ ሥርዓታቸውን ማጠናከር እና የታክስ አማራጮችን ማስፋት ይገባል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በመደበኛ ታክስን ከማጠናከር ባለፈ ኤክሳይስ ታክስን ለማዘመን እያከናወነችው ያለው ተግባር በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቱኒዚያና ከሞሮኮ አንፃር ስናየው ደካማ ነው ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ታክስን ወይም ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ የማህበራዊ አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ ባህልን ለማሳደግና ፍትህን ለማስፈን፣ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ሀገርን ለማበልፀግ የሚወጡ ፖሊሲዎችንና እቅዶችን በአግባቡ ለመፈፀም የታክስ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑ ለሕዝብ ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የንብረት ግብር አንድ ግለሰብ ወይም ሕጋዊ አካል ለሚጠቀምበት ማንኛውም ንብረት ለመንግሥት የሚከፍለው ገንዘብ ማለት ነው ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ መንግሥት በኢትዮጵያ ከተሞች ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚሰበሰቡት የንብረት ገቢ ለማሳደግ እየሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የንብረት ታክስ የሚሰበሰበውን የገቢ ግብር ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የገለጹት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ያም ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ በሀብት ክፍፍል ረገድ የሚስተዋሉ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶችን በማጥበብ ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ጠቁመዋል።

ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) አክለውም፤ መንግሥት ለክልሎች የሚያደርገው ድጎማ ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ የክልሎችን የታክስ መሰብሰብ አቅም ሊያዳክም ይችላል። ስለዚህ ይህንን ድጎማ መቀነስና ማቆም የክልሎችን የገቢ አሰባሰብ ሂደት ሊያጠናክር ይችላል ሲሉም ተናግረዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኃይለመስቀል ጋዙ በበኩላቸው፤ የመንግሥት የገቢ አሰባሰብ ሂደትን ደካማ ያደረገው የታክስ ኦዲተሮች ሕገወጥ አሠራር ነው። ስለዚህ መንግሥት የታክስ ኦዲተሮች ላይ ልዩ ክትትል ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ ግብር ከፋዮች ግብር ለመክፈል ወደ ሰብሳቢዎች ሲያቀኑ ለአብነት ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ከምትከፍሉ 200 ሺህ ብር ለባለሙያ ሰጥታችሁ፤ 200 ሺህ ለመንግሥት ከፍላችሁ የተቀረውን 600 ሺህ ብር ለምን አታተርፉም?›› የሚሉ ግብር ሰብሳቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት አሠራር በድብቅ እንደሚካሄድ ገልጸው፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጠራራ ፀሐይ የሚሠራ ወንጀልና የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን አስረድተው፤ እንዲህ ዓይነት ሥነ ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎችና የግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎች፣ ስለግብር ምንነት ግንዛቤ ቢሰጣቸውና አለፍ ሲልም ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋት ይገባል ብለዋል።

ይህንንም ለመቅረፍ ዲጂታል አሠራሮችን መጠቀም እና የታክስ ኦዲተሮች ኦዲት ያደረጉትን ድጋሚ ኦዲት የሚያደርግ ቡድን ማቋቋም መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ይህን ማድረግ መንግሥት አሁን የሚሰበስበው ገቢ ላይ የአሥር በመቶ ጭማሪ እንዲኖር እድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አሁን አጠቃላይ የሚሰበሰበው ገቢ ከሀገሪቱ አቅምና ፍላጎት አኳያ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በእጥፍ ቢያድግ ለትውልድ የሚጠቅሙ በርካታ ፕሮጀክቶችን መገንባትና የሀገርን እድገት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

የገቢ ዘርፍ ተቋማት ዘመኑን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓትን በመከተል የግብር ስወራና ማጭበርበርን የመግታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሠራር የተላቀቀና በቴክኖሎጂ የሚመራ ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት መከተል ይገባል ብለዋል።

አቶ ኃይለመስቀል ጋዙ አክለውም፤ አሁን ላይ ግን የገቢ ምንጭን ለማስፋት ሲባል የሚወጡ የታክስ መጠን ተከራዮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

ስለዚህ የታክስ ምንጮችን የማስፋቱ ሥራ ሕዝብ ላይ ጫና እንዳያሳድር ትኩረት በማድረግ የታክስ መጠኑን ተመጣጣኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በተለይ የጣራና ግድግዳ ተብሎ የተጨመረው የታክስ መጠን ነዋሪው ላይ ጫና በማሳደሩ የታክስ መጠኑን በድጋሚ በማጤን ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአጠቃላይ ሁለቱም የምጣኔ ሀብት ምሁራን የኢትዮጵያ ገቢ አሰባሰብ ደካማ እንደሆነ፣ የገቢ አማሯጮቿን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን እና የቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ የሚታየውን ድክመት በቴክኖሎጂ መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ የግብር ወይም የታክስ ሥርዓት ስናይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገመንግሥት እና በታክስ ሕግጋት መሠረት መንግሥት የተለያዩ የግብር ወይም ታክስ አይነቶችን የሚጥል እና የሚሰበስብ ሲሆን እነዚህን የግብር አይነቶች ስናይ ፣ የገቢ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስ፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ እና ኤክሳይስ ታክስ ይገኙበታል::

እያንዳንዱ የግብር አይነት የራሱ የሆነ ባህርያት ያሉት ሲሆን ድምር ግቡ የመንግሥትን ገቢ ከፍ በማድረግ መንግሥት መሠረተ ልማት በማስፋፋት እና አጠቃላይ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ከፍ እንዲያደርግ ማስቻል ነው:: ግብር መክፈል ግዴታ መሆኑ በሕግ ተደንግጎ ይገኛል::

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You