ጉምቱው የጥበብ ሰው ነብይ መኮንን

ዕውቁ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ የቴአትርና የቴሌቪዥን ድራማ ጸሃፊ ነብይ መኮንን ወደዚህች አለም የመጣው በ1964 ዓ.ም በናዝሬት ከተማ ነው። ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰም ናዝሬት በሚገኘው አጼ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ተከታትሏል። ጉምቱው የጥበብ ሰው ገና ከመነሻው በቀለም አቀባበሉ የተዋጣለት ነበርና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት አልፎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀለ። አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታም ኬሚስትሪ አጥንቶ ለመመረቅ በቅቷል። ሆኖም ይህ የስነ-ጽሁፍ ሰው ነፍሱ ያለችው ከጥበብ ጋር በመሆኑ የተመረቀበትን የትምህርት ዘርፍ ትቶ ቀልቡን ከጥበብ ጋር አቆራኘ። የነፍሱን ጥሪ በመከተሉም ዘመን አይሽሬ ስራዎችን አበረከተ።

ነብይ መኮንን “ነገም ሌላ ቀን ነው” የትርጉም ስራ፣ ተከታታይ የግጥም መድብሎች፣ የጉዞ ማስታወሻዎች እንዲሁም የተውኔት ስራዎችን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል። ነብይ መኮንን ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ መሥራቾች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ጋዜጣዋን በዋና አዘጋጅነት መምራቱን የህይወት ታሪኩ ያስረዳል። ነብይ መኮንን በ1960ዎቹ በኢህአፓ ውስጥ ነበረው በተባለው ተሳትፎ ተይዞ ለእስር ተዳርጓል። በእስር በነበረው ቆይታም በርካታ ውጣውረዶችን ቢያልፍም ዘመን አይሽሬ ስራዎችንም ለማበርከት ዕድል ፈጥሮለታል።

አዲስ ማለዳ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ በአንድ ወቅት ስለገጣሚ ነብይ መኮንን የሚከተከለውን አስፍሮ ነበር። እስር ቤት ውስጥ ነው። በዚህ እስር ቤት ውስጥ ለወትሮው ከወረቀት እና ከመጻፊያ ብዕር ተለይቶ የማያውቅ ሰው ገብቷል። መቼ ከአካል እስር እወጣለሁ ሳይሆን መች እጽፋለሁ፣ መች በሐሳቤ የሚመላለሰውን በብዕር ወደ ወረቀት አጋባለሁ የሚለው ጭንቁ ሳይሆን አልቀረም! መላ ፈለገ። የሐሳቡን ጥያቄ ለመመለስ ምንም ነገር ላይ ከመጻፍ ወደኋላ የሚል ዓይነት አይደለም። አወጣ አወረደ። እናም በቅርቡ የታየውና ያገኘው የሲጋራ ወረቀት ነው። ብቸኛው አማራጭም ብዕሩን በዛ ላይ ማሳረፍ ነበር። እንዳሰበውም አደረገው።

እናም በሐሳቡ የሚመላለሰውን ከማስፈር ባሻገር በጊዜው በእጁ የነበረውን ‹Gone with the Wind› የተሰኘውን መጽሐፍ ይተረጉም ጀመር። እነዛ ቁርጥራጭ የሲጋራ ወረቀቶችም የመጻፍ መሻቱን ያስታግሱ ዘንድ ባለውለታው ሆኑ። ውለታ የዋሉት ለእርሱ ብቻ አይደለም። በኋላ ሁሉም አልፎ ‹ነገም ሌላ ቀን ነው› የሚለው መጽሐፍ ለአንባቢዎችም እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል። የዚህ ታሪክ ባለቤትና 10 ዓመታትን በእስር ላይ ሆኖ ይህን የትርጉም መጽሐፍ ለንባብ ያቀረበው ደራሲ፣ ተርጓሚና አርታኢ እንዲሁም ጋዜጠኛው ነብይ መኮንን ነው።

‹Gone with the Wind› የተሰኘው መጽሐፍ በፈረንጆቹ 1936 ማርጋሬት ሚሼል በተባለች አሜሪካዊት ጋዜጠኛ የተጻፈ ነው። ጋዜጠኛዋ በአንድ አጋጣሚ እግሯ ላይ ሕመም ገጥሟት አልጋ ላይ ውላ ነበር። በዚህን ሰሞን ነበር በአገሯ አሜሪካ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ በገጸ ባህርያት መልክ ውስጥ ስላ መጻፍ የጀመረችው። በመጽሐፏም የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ምን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዳደቀቀው ጠቅሳና ተያያዥ ነጥቦችን አንስታ የጦርነትን አስከፊ ገፅታ አሳይታለች።

ነብይ መኮንን በእስር ቤት ሳለ በዛ መልክ ተርጉሞ ያዘጋጀው ይኸው መጽሐፍ በ1980ዎቹ ለንባብ ቀረበ። የጊዜው ሳንሱር ታድያ ርህራሄ ያለው አልነበረም። የተርጓሚውን ድካም ከመጤፍ ሳይቆጥር ቆራርጦ አቀረበው። ከዛ ባይብስም ቀጥሎ ደግሞ መጽሐፉ <ከነበረው ስርዓት ጋር የሚስማማ ስላይደለ> ተብሎ ዳግም እንዳይታተም፣ በመጀመሪያ እትም ብቻ እንዲቆይ ተደረገ።

ነብይ መኮንን ለአገር የሚሳሳና አብዝቶ የሚጨነቅ መሆኑን ማሳያም በርካታ ሥራዎች አሉት። ይህንንም በሚመለከት ሐያሲ እና ፀሐፊ አብደላ ዕዝራ (ነፍስ ኄር) ‹የገጣሚ ነብይ መኮንን እማይነትበው ስውር-ስፌት› በሚል በጻፈው ሐተታ ላይ ‹በጥሞና ስለ አራት ግጥሞች› ሲል ባሰፈረው አንድ ጽሑፍ ያነሳል። በዚህም ላይ አያሌ ገጣምያን ስለ አገር በተለያየ መንገድ የጻፉ መሆናቸውን አውስቶ፣ ነቢይ መኮንን ከአማርኛ ገጣሚያን የሚለየው አንድ ወይም ሁለት ሳይሆን፣ በአገር ጉዳይ ከሃያ ግጥሞች በላይ መቀኘቱ ነው›› ይላል።

ነብይ መኮንን በእርግጥም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ፣ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ በኩራትና በክብር የሚቀመጡ ድንቅ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን ማበርከት የቻለ ሰው ነው። መለስ ብለን ሥራዎቹን ስናወሳ፣ የግጥም ስብስብ መጻሕፍቱን እናገኛለን። እነዚህም ስውር ስፌት (ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት) እንዲሁም ነፍሰ ጡር ግጥሞች የተሰኙትን መጥቀስ ይቻላል።

<ነገም ሌላ ቀን ነው> ከተሰኘው የትርጉም ሥራው ባሻገር በ1994 ለንባብ የበቃው <የእኛ ሰው በአሜሪካ> የተሰኘው የጉዞ ማስታወሻ እንዲሁም በ2014 መጀመሪያ አካባቢ ለንባብ የቀረበው <የመጨረሻው ንግግር> (The Last Lecture) የተሰኘ የትርጉም ሥራ የሆነ መጽሐፍም አለው። በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ግን እነዚህ መጻሕፍት እስከ አሁን ድረስ ከአንድ ጊዜ በላይ ሳይታተሙ የቆዩ ናቸው።

ከዚህም ባሻገር ነብይ የቴአትር የጽሑፍ ሥራዎች አሉት። ከእነዚህም ጁሊየስ ቄሳር፣ ናትናኤል ጠቢቡ እና ማደጎ የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው። በዚህ አያበቃም፣ ነብይ የሙዚቃ ግጥም ሥራዎችም አሉት።

አንጋፋው የሥነ-ጽሑፍ ሰው ነብይ መኮንን፣ <ነብይ በአገሩ ተከበረ> በሚል መነሻ ሃሳብ መጽሐፉን ከመመረቅ ጎን ለጎን የቀደመውም ሆነ አሁን ያለው የሥነ-ጽሑፍ ቤተሰብ ለነብይ ያለው አክብሮትና ፍቅር የተገለጸበት ተዘጋጅቶ ነበር። በዝግጅቱም የነብይ ሁሉም ሥራዎች በሚባል ደረጃ ለአንባብያን የቀረቡ ሲሆን፣ ሦስቱ የተመረቁት መጻሕፍትም በአንድ ላይ ተዳብለው ቀርበዋል።

ሸገር ሬዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ከገጣሚ ነብይ መኮንን ጋር ለ11 ሳምንታት በነበረው ቆይታ ነቢይ መኮንን ሁለት ዓመታትን የፈጀው “Gone with the Wind” “ነገም ሌላ ቀን ነው” የሚለውን መፅሐፍ በማዕከላዊ እስር ቤት ታስሮ በነበረበት ወቅት እንዴት እንደተረጎመውና ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች ደብቆ ያወጣበትን መንገድ ተርኳል ።

ይህ መፅሐፍ ማእከላዊ እስርቤት የገባበት ምክንያት አንድ “የሲ.አይ.ኤ ተላላኪ” በተባለ እስረኛ ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከቦሌ ቀጥታ ከነ ሻንጣው ወደ እስር ቤት ስላመጡት ነው ነቢይ ይህንን መፅሐፍ ሲተረጉም የሚፅፈው ሲጋራ ከሚያጨሱ እስረኞች የፓኮውን ብልጭልጭ በመሰብሰብ ሲሆን ቦታ ለመቆጠብ ብሎ ምስር ምስር በሚያካክሉ ፊደሎች እየፃፈ ተርጉሟል። ማታ ማታ የተረጎመውን ለእስረኞች ያነብላቸው ነበር እስረኞችም በታሪኩ እጅግ ተመስጠው ለመፅሐፉ መተርጎም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጉ ነበር።

ሌላው ይህን ሲተረጉም ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች እይታ ውጪ መሆን አለበት። አብዛኛውን የሚተረጉምበት ሰዓት ለሊት ሲሆን የተረጎመውን በሲጋራ ብልጭልጭ የፃፈውን ፅሑፍ ለደፋር ተፈቺዎች ብልጭልጩን አጣጥፎ መልሶ ፓኮ ውስጥ በመክተት ፓኮውን መልሶ በማሸግ ያልተፈታ ሲጋራ በማስመስል ነበር ስራውን ሲቀጥል የነበረው ።

ነብይ ይህን ያህል ኃላፊነት ወስዶ የሚተረጉመው ነገ ይፈታ ወይ ይገደል በማያውቅበት ወቅት ነው። ታዲያ እንዲህ እያደረገ አብዛኛውን የተተረጎመበት ብልጭልጭ ወረቀቶች በተለያዩ ሰዎች ከእስር ቤቱ ካስወጣ በኋላ እሱም ከእስር ሲፈታ እነዚህን ሰዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ፈላልጎና ሰብስቦ ለመጽሃፍነት የበቃ መፅሐፉ ብቻ ሳይሆን የተተረጎመበትም መንገድ አስደናቂ የሆነ ድንቅ መፅሐፍ ነው።

ሌላው ነብይ አስር ቤት የሚፅፋቸውን ግጥሞች አንድ እስረኛ በቃሉ የመያዝ ችሎታ ነበረው :: ነብይም ሁልጊዜ ያነብለት ነበር ከዛም ይህ እስረኛ የመፈቻው ቀን ሲደርስ አብዛኛውን የነብይን ግጥሞች ለእስር ቤቱ ጠባቂዎች በማይታየው በዓይምሮው ይዞት ከእስር ቤት ወጣ፤ ተፈታ።

ከዛም የመኪና አደጋ ደርሶበት ሆስፒታል እንደተኛ ከጎኑ ካለው እንደሱ በመኪና አደጋ ደርሶበት አልጋ ለይ ከተኛው ከሌላ ታካሚ ጋር ሲጨዋወቱ ስለነዚህ ግጥሞች ይነግረዋል። ይህም እስረኛ ለስነ ጥበብ የቀረበ ነበርና ከሆስፒታል ሲወጡ ግጥሞቹን በሙሉ በታይፕ ፅፎት ነብይ መኮንን ከታሰረ ከስምንት ዓመታት በኋላ ሲወጣ በስጦታ አበርክቶለታል። ይህ ግጥሙን በታይፕ የፃፈለት ሰው በሃይሉ ገ/መድህን ነው። ሌላው አሰፋ እንዳሻው የሚባል የቦረና ልጅ የኦሮምኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ፅፎ ጠርዞ ሊያስወጣው ሲል የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ይዘውበት ቀዳደው ጥለውበታል።

በአጠቃላይ ነብይ መኮንን ባህር ነው። ህይወቱ ተጨልፎ አያልቅም። ሆኖም ከሞት የሚቀር የለምና የሶስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ደራሲ ነብይ መኮንን ባደረበት ህመም ምክያት በመኖሪያ ቤቱ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ደራሲ እና ወግ አዋቂው ነብይ ህይወቱ ያለፈው በተወለደ በ68 ዓመቱ ነው።

ይህንን ጽሁፍ ስናዘጋጅ በማጣቀሻነት አዲስ ማለዳ ፤ሸገር ሬዲዮና ሌሎች ድረገጾችን ተጠቅመናል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2016

 

Recommended For You