መቼ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ፣ ለምን እና ማንን? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ስሌትና ቀመር የለውም። ከቁጥጥር በላይ በመሆኑ ድንገት አሊያም በሂደት ይፈጠራል፤ ከዚያማ ሁለት ልቦችን ያጣምራል፤ ፍቅር። አልፎ ተርፎም፤ ጎጆ ቀልሶ ለሶስት ጉልቻ ያበቃል።
ተፈጥሮ ከለገሰችን ጸጋዎች መካከል አንዱ የሆነውና በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚፈጠረው ይህ ስሜት የምድሪቱም ሚዛን ነው። በርካቶች የተከዙለት፣ ያዜሙለት፣ የደረሱለት፣ የተቀኙለትና ብዙ ያሉለት ፍቅር ታዲያ እንደ ደራሽ «መጣሁ» ይል ይሆን እንጂ በትምህርትና ዝግጅት ስለመምጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
በቻይና የሚገኝ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ግን «ፍቅርን እና ትዳርን አስተምራለሁ» ማለቱን ግሎባል ታይምስ አስነብቧል። በምስራቃዊው የቻይና ክፍል ዢጃንግ ግዛት የሚገኘው ተቋሙ ይህንን ትምህርት የሚሰጠው ለሴቶች ብቻ ሲሆን፤
የሃሳቡ ጠንሳሽና አጋዥም የሃገሪቷ የሴቶች ፌዴሬሽን መሆኑ ታውቋል። ትምህርቱ ባሳለፍነው ሳምንት ሲጀመር፤ ሴቶች ወደ ጾታዊ ግንኙነት እና ትዳር እንዴት መግባት እንዳለባቸው ዕውቀት ይገበያሉ የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
አንድ ደርዘን በሚሆኑ ወጣት ሴት ተማሪዎች የተጀመረው ትምህርቱ፤ ስሜትን እንዴት መግለጽ እንደሚቻልና በምን መልኩ ፍቅርን መምራት እንደሚቻል ያስተምራልም ተብሎለታል። አስደናቂውን ትምህርት ያስጀመሩት መምህርም «ተማሪዎች እንዴት ማፍቀር እንደምትችሉ ታውቃላችሁ?» የሚል ጥያቄ ነበር ቅድሚያ ያቀረቡት። ለጥያቄውም «አሁን መልስ ፍለጋ የእጅ ስልካችንን አንጠነቋቁልም፤ እኔ እንዴት እንደሆነ አስተምራችኋለሁ» ማለታቸውንም ድረገጹ አስነብቧል።
በልበ ሙሉነት ፍቅርን እና ስለ ትዳር ሊያስተምሩ የተሰየሙት መምህራን የስነልቦና ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ ትምህርቱ ሶስት ክፍሎችን የሚያጠቃልልም ይሆናል። የፕሮጀክቱ ርዕሰ መምህር የሆኑት ዡ ያንፒንግ፤ ተማሪዎቹ ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ፤ ለመልካም የፍቅር ግንኙነት ብቁ ይሆናሉ፣ በትዳር ላይ ያላቸው መጥፎ እሳቤ ይቀረፋል። እንዲሁም ትክክለኛውን ፍቅር ያልማሉ ሲሉም ያረጋግጣሉ።
ስልጠናውን ወስዶ ለማጠናቀቅ ግማሽ ዓመት የሚፈጅ ሲሆን፤ በመጨረሻም «ለፍቅርና ትዳር ብቁ ናቸው¡» የሚል ምስክር የሚሰጥ መሆኑንም ርዕሰ መምህሩ ዡ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2011
ብርሃን ፈይሳ