የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ እርምጃው ተጠናክሮ ሲቀጥል

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ካሉ ቁልፍ ቃላት (ጽንሰ-ሃሳቦች) መካከል ሁለቱን የሚያክል የለም። በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችም ሆነ ዩኔስኮ፤ በተባበሩት መንግሥታትም ይሁን በሌሎች ገዥ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ውስጥ ሁነኛ ስፍራን የያዘ እንደ ሁለቱ ማንም የለም። በሀገራትም ይሁን መንግሥታት፣ በምሁራንም ይሁን ፖለቲከኞች ስለ ትምህርት ካነሱ ሁለቱን በምንም መልኩ ሊያልፏቸው አይቻላቸውም። በመሆኑም፣ ሁለቱ አንድም ሁለትም ናቸው ማለት ይቻላል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተደራሽነት በሌለበት ጥራት ስለማይኖር፣ ወይም ስለ ጥራት ማንሳት ስለማይቻል፤ እንዲሁም፣ ተደራሽነት ብቻ ጥራትን ስለማያመጣ ነው።

የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን በተመለከተ እንደ እኛ ሀገር አብዝቶ የተጨነቀ ያለ እስከማይመስል ድረስ በጉዳዩ ላይ የተብሰለሰለ ሀገርም ሆነ ሕዝብ የለም ማለት ይቻላል። ሁሉም በሚባል ደረጃ በተደራሽነቱም ሆነ ጥራቱ ላይ የሚችለውን ሁሉ ብሏል። በተቃውሞ ጎራም በመሰላለፍ ያልተከራከረ የለም። “መጀመሪያ ተደራሽነት ነው፤ ጥራት ቀጥሎ የሚመጣ ነው”፤ “አይ፣ ጥራት ከሌለ ትውልድ አለቀለት ማለት ስለሆነ ተደራሽነት ያለ ጥራት ዋጋ የለውም” እየተባባለ ሁሉ የመጀመሪያውን ሁለተኛ ሁለተኛውን የመጀመሪያ በማድረግ እሰጥ-አገባው ጣራ ነክቶ እንደ ነበር የሚዘነጋ አይደለም። ነገር አለሙ ሁሉ ተበለሻሽቶ ከነጥብ በኋላ ያለን ዲጂት ማንበብ የማይችል የአካውንቲንግ ምሩቅ አጋጥሞ እንደ ነበር በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀር ሲነገር ነበር።

የትምህርት ጥራት እንጦሮጦስ የመውረዱ ጉዳይ “ሀ” ብሎ የጀመረው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ40 በላይ መምህራን በ“ችሎታ ማነስ፣ የተባረሩ እለት ነው ከሚሉ ወገኖች ጀምሮ እታች ድረስ ተማሪና አስተማሪ ስፍራ እንዲለዋወጡ እስከ ማድረግ የተወረደ ጊዜ ነው የትምህርት ነገር በኢትዮጵያ በአፍጢሙ የተደፋው የሚል ከ“አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” በተቃርኖ የቆመ ሙግት ሲሰነዘር የነበረ ቢሆንም (ብዙዎች ሲሉት እንደ ነበረው) የሚሰማ ሊኖር ባለመቻሉ ሀገርና ሕዝብ፤ ከሁሉም በላይ ተመራቂዎችን ዋጋ አስከፍሏል። የስነልቦና ጉዳት ሳይቀር አላደረሰም ማለት አይቻልም።

ለሦስት አሰርት ጥቂት ፈሪ ለሆኑ አመታት ስራ ላይ ውሎ የነበረውን ፖሊሲ በተመለከተ፣ ከትምህርት ሚኒስቴርና ተዛማጅ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ“አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” ማስፈፀሚያ መሳሪያነት ሲካሄድ የነበረው የመማር-ማስተማር ሂደት በችግሮች የተተበተበና ፊደል እንኳን መለየት ያልቻሉ ተማሪዎችን ሲያመርቅ የነበረ ጉደኛ (ዮዲት ጉዲት) ፖሊሲ ነው። “መፃፍና ማንበብ የማይችሉ”፣ “3 ከመቶ ብቻ የማትሪክ ውጤት በማምጣት ያለፉ” ወዘተ ተማሪዎችን በማፍራት ነው በ“የተማረ የሰው ኋይል” ሲባል የነበረው።

እንደ እነዚሁ ተቋማት መረጃዎች ከሆነ የትምህርት ስርአቱ በ“አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” ስም ፍዳውን ሲያይና ሀገርና ወገንን ዋጋ ሲያስከፍል ነው የቆየው። በመሆኑም “አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ” እና ርዝራዦቹ በሌላ፤ የትምህርት ጥራትን በሚያረጋግጡ ሰነዶች መተካት አለባቸው በሚል ስር ነቀላዊ አካሄድ እየተሰራባቸው ይገኛል።

ችግሩ እያየለ መጥቶ ዛሬ የጥራት ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆን እያወዛገበ፤ ብዙዎችንም ተጠያቂ እያደረገ፤ በብዙዎች ላይም እየተወሰደ ያለው እርምጃ ብዙዎችን እያስደሰተ ይገኛል። ለትምህርት ጥራት መጉደል መደላድል ናቸው የተባሉ መመሪያና ደንቦች ሁሉ እየተከለሱና ጥራትን ሊያረጋግጡ ይችላሉ በተባሉ አዳዲስ ደንቦችና መመሪያዎች እየተተኩ ነው። እንደ እነዚሁ የመረጃ ምንጮች ከሆነ ይህ ተጠናክሮ የሚቀጥል አሰራር ነው።

የትምህርት ጥራት መጓደል ለበርካታ አዳዲስ ተቋማትና ባለሙያዎች ብቅ ብቅ ማለት ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ አንዱም “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን” እና የተቋሙ ሰራተኞች ናቸው።

በዚህም ሆነ መሰል የትምህርት አመራር ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራትን ርቆ ከተቀበረበት ለመታደግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፤ አንዱና ቀዳሚው ኢንስፔክሽን ነው። የአጠቃላይ ትምህርት የኢንስፔክሽን መረጃ ትንተና፤ የአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ቡድን እና የመሳሰሉት የስራ ዘርፎች ተፈጥረው በስራ ላይ እንዲገኙ ተደርጓል።

ወደ ሙያዊ ቃላት (ፅንሰ-ሃሳቦች)ም ስንመጣ ያው ሲሆን ለዚህም በግብዓት፣ በሂደትና በውጤት ተቋማት ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚለዩበት፣ የደረጃ ምደባ የሚሰጥበት፣ ተቋማቱ ያላቸውን ጠንካራ ጎን እና ክፍተት በግብረ-መልስ የማሳወቅ ስራ የሚሰራበት፤ እና ተቋማት ያላቸውን ክፍተት እንዲሞሉ እና የማልማቱን ተግባር ለሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጭምር እንዲያሳውቁ የሚደረግበት መሆኑ በሚመለከታቸው የተበየነው “ስታንዳርድ ኢንስፔክሽን” አንዱ ማሳያ ነው።

የእውቅና እድሳትና የአዲስ እውቅና ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ “በተደጋጋሚ የሚፈጸም፤ በየጊዜው ግን አዲስ የሚሆን” በማለት የሚገልጸው ባለስልጣኑ በድረ-ገፁ “ሙያ ብቃት ምዘና ምንድነው?” በማለት ከጠየቀ በኋላ፤

“ምዘና (Assessment):- አንድ ግለሰብ ባንድ በተወሰነ የሙያ መስመር በሚፈለገው ዕውቀት፣ ቴክኒካዊ ክህሎትና አመለካከት አኳያ በተቀናጀ አግባብ በብቃት ያለ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለመዳኘት ሲባል ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን (Evidence gathering tools) በመጠቀም መረጃ የመሰብሰብ እና ዳኝነት የመስጠት ሂደትን (Process) የሚያመለክት ጽንሰ-ሃሳብ ነው፡፡በማለት ያሰፈረውንም እዚሁ ላይ መጥቀስ ተገቢ ነው።

እዚህ ድረስ ይህንን ማለት ያስፈለገው የወደቀውን የትምህርት ጥራት መልሶ ለመትከል እየተደረገ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ትንሽ ለማለት፤ እንዲሁም፣ ጉዳዩን ወደ ኋላ አስታውሶ ወደ ፊት ለማመላከት ያህል ነው።

ሰሞኑን፣ በመዲናይቱ አዲስ አበባ የከተማው መነጋገሪያ (ቶክ ኦፍ ዘ ታዎን) ሆኖ የሰነበተው የትምህርት ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ዋና መነሻ ምክንያቱ ትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለ ስልጣን ለ2017 የትምህርት ዘመን የሚቀጥሉና የማይቀጥሉ የትምህርት ተቋማትን ለመግለጽ፤ ማለትም የትምህርት ጊዜ ሰሌዳ /ካላንደር/ የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ከሰኔ 24 ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ በትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2016 ዓ.ም የእውቅና ፍቃድ እድሳት ከተደረገላቸው የትምህርት ተቋማት ውስጥ በስታንዳርድ ማሟላት/አለማሟላት እና ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ በተሻለ የፈጸሙ/ያልፈፀሙ ለ2017 የትምህርት ዘመን የሚቀጥሉና የማይቀጥሉ የትምህርት ተቋማትን ለህብረተቡ ግልጽ በማድረግ ግልጸኝነትን ለመፍጠር (ወላጆች ለ2017 ልጆቻቸውን የት ማስመዝገብና የት አለማስመዝገብ እንዳለባቸው ለይተው እንዲያውቁ) በማሰብ የተሰጠው አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

በየአመቱ “የጋራ ግልጽነት ለመፍጠር” በሚል መነሻ ከትምህርት ተቋማት ባለቤቶች ጋር መድረክ በማመቻቸት የጋራ ውይይት በሚያደርገው፤ በባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የተሰጠው መግለጫ ፍሬ ነገር፡-

በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን መዝግበው የሚያስተምሩ 1ሺህ 332 ትምህርት ቤቶች የማስተማር ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን፤ 43 ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ጊዜ መቀጠል ስላልቻሉ ፈቃዳቸው ተሰርዟል። 150 ትምህርት ቤቶች ጉዳያቸው በሂደት ላይ በመሆኑ ወደ ፊት የሚገለጽ ይሆናል። 41 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ፖሊሲውን ባለመጠበቅና ስታንዳርዱን ባለማሟላታቸው ፍቃዳቸው ተሰርዟል የሚለው ሲሆን፤ ፈቃዳቸው የተሠረዘው የትምህርት ፖሊሲውን ባለመጠበቅና መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ምክንያት መሆኑ የተነገረላቸው እነዚህ የትምህርት ተቋማት ከላይኛው በተጨማሪም፣

  • ለ2017 የትምህርት ዘመን ባደረገው ቁጥጥር የፖሊሲ ጥሰት የፈጸሙና የትምህርት መመሪያዎችን ያላሟሉ 35 የግል ይዞታ ያላቸው የቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ እገዳ ተጥሏል፤
  • ከእነዚህ ተቋማት መካከልም፣ የካ፣ ልደታ ጉለሌና ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ሲሆን፤ የጊብሰን ትምህርት ቤቶች፣ የቅዱስ ሚካኤል አምስት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም የካ አፖሎ ትምህርት ቤት እርምጃው ከተወሰደባቸው መካከል ይገኛሉ፤
  • ዕገዳ በተጣለባቸው ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በመኖረያ አቅራቢያቸው በሚገኙ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ እንዲስተናገዱ ይደረጋል፤
  • የተዘጉት ትምህርት ቤቶችም የተማሪዎችን የተሟላ ማስረጃ እንዲሰጡ ይደረጋል፤
  • የቅዱስ ሚካኤል ትምህርት ቤቶች የስያሜ ለውጥ በማድረግ ለመቀጠል በመጠየቁም ጉዳዩ በመታየት ላይ ይገኛል፤

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ መግለጫውን ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ተቋማት በተደጋጋሚ፣ እስከ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ድረስ የዘለቀ መድረክ ተፈጥሮላቸው የተወያዩ ሲሆን፤ በተደረገው ውይይት መሰረት ወደ ህጋዊነትና ተገቢ አሰራር መምጣት ያልቻሉ ናቸው። ለዚህም እነ ጊብሰን አካዳሚ በማሳያነት አቅርበዋል።

ባለፈው አመት፣ ዘንድሮ የእውቅና ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ለሚሰጣቸው የግል የትምህርት ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ፣ አቶ አድማሱ ደቻሳ የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የጥራት ዘርፍ ኃላፊ ናቸው”

ዘንድሮ የእውቅና ፈቃድ እድሳት ለግል ተቋማት ይሰጣል። የግብአት ማዘጋጀት ደግሞ ለእውቅና ፈቃድ ሳይሆን ለተማሪዎች የተሻለ ትምህርት ለመስጠት እንዲያግዝ ተብሎ የሚደረግ ነው። በተዘጋጀው ቼክሊስት መሰረት ሁሉም ተቋማት ሊዘጋጅ ይገባዋል። ሁሉም ተቋም ህጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል ያስፈልጋል፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ግን አንድም ተቋም አይቀጥልም በማለት አስገንዝበው የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ እርምጃም ያንን ታሳቢ ያደረገ ስለ መሆኑ መጠራጠር ባይቻልም በወቅቱ ማሳሰቢያውን ልብ ያላሉ ተቋማት የዘንድሮ ተዘጊዎች ለመሆን መብቃታቸው የዘንድሮው ማሳሰቢያ ለሚቀጥለው ትምህርት ነውና በሚቀጥለው አመት የሚዘጉ የትምህርት ተቋማት አይኖሩ ዘንድ ምኞታችን መሆኑን እየገለፅን ወደ ዘርፉ ኃላፊ ማሳሰቢያ እንመለስ።

እዚህ ጋ አቶ አድማሱ ደቻሳ እንዳሉት ሆኗል ወይም/እና አልሆነም ለማለት አይቻለንም። መሆንና አለመሆኑን ለመወሰን እንቸገር እንጂ አንድ ነገር ማለት የምንችል ሲሆን፣ እሱም የአሁኑ ታጋቾች (የታገዱት) ቢያንስ እንዲህ አይነት ነገር ሊመጣ እንደሚችል መረጃው ነበራቸው ማለት ነው። ወይም፣ “ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ግን አንድም ተቋም አይቀጥልም” ተብሎ ተነግሯቸው ነበር። ችግሩ፣ ለትምህርት ጥራት ሲባል የተነገራቸውን ወደ ተግባር መቀየር አለመቻላቸው ነውና ለክፉም ለደጉም በህግ የበላይነት ማመን ተገቢ መሆኑን ከስሩ ማስመር ያስፈልጋል።

በመድረኩ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ይሆን ዘንድ የተዘጋጀውን ሰነድ አቅርበው የነበሩት የባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ካሳ ሲሆኑ፤ የእውቅና ፈቃድ የሚሰጠው ተቋማት በቂ ግብአትና አደረጃጀት መፍጠራቸውን ለማረጋገጥ፣ ከስታንዳርድ ጋር በማነፃፀር ያሉባቸውን ክፍተቶች በመለየት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ ለተስተዋሉ ክፍተቶች ግብረ መልስ በመስጠት በቀጣይ መታረማቸውን ለማረጋገጥ፣ የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ድጋፍና ክትትል ለሚያደርገው ባለድርሻ አካል በማሳወቅ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ከስታንዳርድ በታች የሆኑ ተቋማትን በመለየት የእርምት እርምጃ በመውሰድ ለማህበረሰቡ ለማሳወቅ፣ ዜጎች ጥራቱ በተረጋገጠ የትምህርት ተቋማት የመማር መብታቸውን ለማስጠበቅ መሆኑን አስረድተው ነበር። ይህም የሚያመለክተው በባለ ተቋሟቱ ዘንድ እንዲህ አይነት ጉዳይ ሊመጣ እንደሚችል አስቀድሞ ግንዛቤው ነበር ማለት ነውና አሁንም ለሚቀጥለው አመት ከወዲሁ ቆፍጠን ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ማሳሰብ እንወዳለን።

ለትምህርት ጥራት ሁሉም ዘብ ይቁም!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You