ኢትዮጵያ የበርካታ እሴቶች መገኛ ነች። ከ80 በላይ የሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት ይህቺ አገር በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባሕልና በልዩ ልዩ እሴቶች ባለቤትነት ትታወቃለች። ከእነዚህ አያሌ ሀብቶቿ ውስጥ ባሕላዊ ምግቦቿ ተጠቃሽ ናቸው። የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባላቸው ልዩ የምግብ አዘገጃጀት ይታወቃሉ። ይህም ሀገሪቱን በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ተወዳጅ ምግቦችና የአዘገጃጀት ሥርዓት ካላቸው ውስጥ ቀዳሚው ያደርጋታል። ይሁን እንጂ ባለው የምግብ አዘገጃጀት መጠንና ተወዳጅነት ልክ በዓለም ላይ ከጥቂቶቹ ምግቦች በስተቀር መታወቅ አልቻሉም፤ በሀገሪቱ ዘመናዊ ሆቴሎች ጭምር በስፋት የተለመዱ አይደሉም። ለዚህም ነው በማኅበረሰቡ ውስጥ ብቻ እንዲቀሩና በስፋት እንዳይተዋወቁ የሆነው።
የዚህ ዋንኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ባሕላዊ የምግብ አዘገጃጀትን በሚገባ አጥንቶ መሰነድና ወደ ዘመናዊው ትምህርትና ሥልጠና ሂደት አለማካተት ነው። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ተግዳሮት ለመፍታት እና ባሕላዊ ምግቦች ሳይበረዙ እሴታቸውን ጠብቀው የሚተዋወቁበትን መንገድ በተመለከተ እየተተገበሩ ስላሉ ሥራዎች ዳሰሳ አድርጎ ይዞ ቀርቧል::
የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ሥዩም ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ፣ የባሕል ብዝኃነት እና አስደናቂ የተፈጥሮ ሃብት ያላት ጥንታዊ ሀገር መሆኗንና ዓለም አቀፋዊ የቱሪዝም አቅም ያላቸው ልዩ ልዩ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባለቤትም እንደሆነች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በሀገራችን የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ በቂ ሥራ ባለመሠራቱ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።
በተለይ የብሔረሰቦች ባሕላዊ ምግቦች፣ የምግብ ጥሬ ዕቃ አያያዝና አጠቃቀም፣ የምግብ አቅርቦት ዝግጅትና ምርጫ፣ የምግብ አቀራረብና አመጋገብ፣ ለምግብ የሚሰጠው ትኩረትና ክብር የሀገራችን ውብ ባሕላዊ እሴቶች ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ አለመቻሉን አንስተዋል። የኢትዮጵያውያን ምግቦች ጣፋጭና ባሕላዊ መገለጫችን መሆናቸውን የሚያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ባሻገር በሀገሪቱ የተለያዩ ዓይነት ባሕላዊ መጠጦች ከምግቦቹ ጋር በተለይም በበዓላት ወቅት እንደሚዘጋጁና ይህም ልዩ የማኅበረሰቡ እሴት መሆኑን ያስረዳሉ።
የሀገራችንን ባሕላዊ ምግብ አዘገጃጀት መሰነድ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ከሚያካሂዳቸው የምርምርና የማማከር ሥራዎች አንዱ ነው የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዋና ዓላማውም በሀገሪቷ የሚዘጋጁ ተወዳጅ ምግቦች ባሕላዊ እሴታቸው ሳይቀንስ በሰነድ ለማስቀመጥ፣ ለሆቴሎችና ሬስቶራንቶች የምግብ ዝርዝር /የሜኑ/ ግብዓትነት እንዲውሉ ለማድረግ፣ በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ሥርዓተ ሥልጠና ውስጥ ለማካተት እንዲሁም ለምግብ ቱሪዝም እድገት ይረዳ ዘንድ ደረጃውን የጠበቀ እና ግልጽ የሆነ የምግብ አዘገጃጀት ሰነድ ለማዘጋጀት እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም በኢንስቲትዩቱ ምርምርና ማማከር እና ምግብና መጠጥ ትምህርት ክፍሎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ጋር በመተባበር እየሠሩ መሆናቸውንና ይህን መሠረት በማድረግም ይፋዊ ሰነድ ማዘጋጀታቸውን ይገልፃሉ።
አቶ ጌታሁን ደሳለኝ በቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት የምግብና መጠጥ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኢንስቲትዩት የጥናት፣ ምርምርና ማማከር ዘርፍ በዕቅድ ይዞ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካካል ይህ የባሕላዊ ምግቦች ጥናት አንዱ ነው። በዚህም መሠረት ኢንስቲትዩቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ በየክልሉ የሚዘጋጁ ተወዳጅ ባሕላዊ ምግቦችን የባሕል እሴታቸውን ሳይለቁ ደረጃውን የጠበቀና የተመጠነ የአዘገጃጀት ሰነድ (Recipe) እየሠራ ነው። ሰነዱም የሥራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ከሚኖረው አስተዋፅዖ በተጨማሪ ለሆቴል ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማቶች፣ ለሆቴሎች፣ ለሬስቶራንቶች እና የምግብ ቱሪዝምን እንደ አንድ የቱሪዝም ምርት ለሚያቀርቡ ለቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ጥቅም ላይ እንዲውል የታሰበ ነው::
‹‹ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦችን እያጠናና እየሰነደ ለትውልድ ለማስተላለፍ ይሠራል›› የሚሉት ኃላፊው እስካሁን ድረስ ወደ አስር የሚደርሱ የባሕል ምግቦችን በሳይንሳዊ መንገድ ወደ ሥልጠና ሥርዓቱ መግባት እንዲችሉ መደረጉን ይናገራሉ። ባሳለፍነው ዓመት ከተጠኑት የብሔረሰብ ምግቦች ውስጥ በዘንድሮው አስራ አንደኛ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ሳምንት በዓውደ ርዕይ የቀረቡትን ጨምሮ የሲዳማ፣ የስልጤ፣ የዳውሮ፣ የኮንሶ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላ (የአምስቱም ብሔረሰቦች) እንዲሁም የጋሞ ብሔረሰቦችን በማጥናት መሰነድ መቻሉን ይናገራሉ።
የጥናቱ ዋና ዓላማ የብሔር ብሔረሰቦች ባሕላዊ ምግብ ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር ብቻ እንዳልሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፤ በትምህርትና ሥልጠና ካሪኩለም ውስጥ በማካተት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውንም ማስፋት እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ በምግብ ቱሪዝም የሚገኘውን አቅም ለማሳደግ ተቋሙ እያጠናቸው የሚገኙ ባሕላዊ ምግቦች ትልቅ ድርሻ እንደሚኖራቸው ያስረዳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ባለድርሻ አካላትን (ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን) በማሳተፍ ምግቦቹ ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲተዋወቁና በየእለት የምግብ ዝርዝር ውሰጥ እንዲካተቱ እየሠሩ መሆኑንም ይገልፃሉ።
በኢትዮጵያ በሚገኙ በርካታ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ላይ በብዛት የአውሮፓና የሌሎች ሀገራት ምግቦች ዝርዝር እንደሚበዛ የሚገልፁት አቶ ጌታሁን፤ ይህንን ልምድ ለመቀየርና የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የብሔረሰብ ምግቦች እንዲካተቱ ተቋማቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹አብዛኛዎቹ ባሕላዊ ምግቦች አይታወቁም›› የሚሉት የትምህርት ክፍል ኃላፊው፤ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በሳይንሳዊ መንገድ ስለማይጠኑ፣ በትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ውስጥ ስለማይካተቱ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ የተነሳ ባሕላዊ ምግቦቹ በዚያው በራሱ በብሔረሰቡና በጥቂት አካባቢዎች ጥቅም ላይ ከመዋል ባሻገር ያለፈ ውጤት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ይህንን እውነታ ለመቀየርም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም አብራርተዋል።
የምግብና መጠጥ ትምህርት ክፍል ኃላፊው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውብ የባሕል እሴቶች መካከል የብሔረሰቦች ምግብ አዘገጃጀት፣ የምግብ ጥሬ ዕቃ አዘገጃጀት አያያዝና አጠቃቀም፣ የምግብ ማቅረቢያዎች አሠራርና አመራረጥ፣ የምግብ አቀራረብና አመጋገብ፣ ለምግብና ገበታ የሚሰጠው ትኩረትና ክብር የተለየ በመሆኑ፤ ተዘጋጅተው የሚቀርቡ ምግቦች ጣፋጭና በኢትዮጵያዊ ባሕል አገላለጽ ጣት የሚያስቆረጥሙ ናቸው:: በሀገራችን ኢትዮጵያ ከምግብ ውጤቶች በተጨማሪ አልኮል ይዘት ያላቸውና ከአልኮል ነፃ የሆኑ ባሕላዊ መጠጦች በተለይም በበዓላት ወቅት ይዘጋጃሉ:: ይሁን እንጂ እነዚህ ባሕላዊ ምግብና መጠጦች በሚፈለገው መጠን ተጠንተው፣ ተሰንደውና ለቀሪው ዓለም ተዋውቀው በቱሪዝም ዘርፉ ላይ እንዲመጣ የሚታሰበው እድገት ላይ አስተዋጽፆ ማድረግ አልቻሉም።
‹‹አገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት የታሪክ ባለቤት ናት›› የሚሉት የትምህርት ክፍል ኃላፊው፤ ሰፊ ውብና ድንቅ ባሕል ያላት እንዲሁም አይን የሚያማልሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለች በመሆኗ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቱሪዝም እንቅስቃሴ እምቅ አቅም ያላት ብርቅ የቱሪዝም መዳረሻ ናት:: ይሁን እንጂ በቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ በቂ ሥራ ባለመሰራቱ ቱሪዝም ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አንፃር አገራችን አመርቂ ጥቅም አላገኘችም:: ቱሪዝም እንደ ሀገር ውድድርን የሚጠይቅ በመሆኑ በየጊዜው ወቅቱን ያማከለ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል:: ከእነዚህ ተግባራት አንዱ በቀሪው ዓለም የማይታወቁ ተወዳጅ ባሕላዊ ምግቦችን ማጥናት፣ መሰነድ፣ በምግብ ዝርዝር ውስጥ በማካተት እንዲሁም ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት በየዓመቱ ‹‹የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ሳምንት›› ያከብራል። ይህንን ተከትሎ ዓውደ ርዕዮችና የክህሎት ውድድሮች ይካሄዳሉ። ዘንድሮም ይህንን ዝግጅት ለ11ኛ ጊዜ አካሂዶ ነበር። በዚህ መድረክ ላይ ከቀረቡ ሁነቶች መካከል የብሔር ብሔረሰቦችን ባሕላዊ ምግቦችና ተወዳጅ መጠጦች የሚያስተዋውቅ ዓውደ ርዕይ ይገኝበታል። በዓውደ ርዕይው ላይ የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ክፍል ቦታው ድረስ በመሄድ በሳይንሳዊ መንገድ ያጠናቸውና የሰነዳቸው የምግብ አይነቶች ለእይታ ቀርበው ነበር። ባሕላዊ ሥርዓቱን የጠበቀ እና የማኅበረሰቡን እሴት በትክክል ያሳየ እንዲሆን ደግሞ ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን አቶ ጌታሁን ደሳለኝ ገልፀዋል። ለትዕይንት ከቀረቡት ባሕላዊ ምግቦች ውስጥም ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበውልናል።
የትምህርት ክፍል ኃላፊው እንደሚገልፁት በ11ኛው የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ከቀረቡት የባሕል ምግቦች አንዱ የሐረሪ ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግብ ነው። ኃላፊው ሲገልፁ በሐረሪ ክልል የሚገኙ ብሔረሰቦች ልዩ ልዩ የምግብ ምርቶችን ያዘጋጃሉ። በተለይም ሑልበት መረኽ (መረቅ)፣ ዱባ መረኽ፣ አኪል መረኽ እና እናይ ገበታ ጣፋጭና ተወዳጅ ምግቦች ናቸው። የሐረሪ ምግብ አሠራር ከ10ኛው-16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንግድ መስቀለኛ መንገድ ስለነበረች የዓረብ ነጋዴዎች እና የኢትዮጵያ ደጋማ ነዋሪዎች ቅይጥ መሆኑን ያነሳሉ። በተጨማሪም ለምግብ ማቅረቢያ ለአገልግሎት የሚውሉ እንደ ገበታ (የእንጨት ጎድጓዳ ሳህን) ያሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች መገለጫዎቿ መሆናቸውን ነግረውናል። ኢንስቲትዩቱ እነዚህን ዝርዝር ምግቦች አሠራራቸውን በጥልቀት ማጥናቱንና መሰነዱንም ነግረውናል።
ሌላኛው ኢንስቲትዩቱ ካጠናቸው ባሕላዊ ምግቦች መካከል የጋምቤላ ክልል ምግቦች ይገኙበታል። የትምህርት ክፍል ኃላፊው፤ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኑዌር፣ የአኙዋክ፣ የኦፖ፣ የማጃንግ እና የኮሞ ብሔረሰቦች የሚገኙ ሲሆን፣ የአምስቱ ብሔረሰቦች ባሕላዊ ምግቦች እንዳላቸው ይገልፃሉ። ከእነርሱም መካከል የኑዌር ብሔረሰብ ባሕላዊ ምግቦችን ይጠቅሳሉ። የኑዌር የአመጋገብ ባሕል በአብዛኛው በግብርና ምርቶች (በቆሎ እና ማሽላ) እና በእንስሳት ምርቶች (ሥጋ እና ወተት) ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ከጥናታዊ ውጤታቸው ማግኘታቸውን ያስረዳሉ። በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ማኅበረሰብ ደረጃዎች የሚዘጋጁ ምግቦች መኖራቸውንም ይናገራሉ። ለምሳሌ ‹‹ኞምክዋር›› የሚባል ባሕላዊ ምግብ የንጉሥ ምግብ ሲሆን በብዛት የሚቀርበው ለተመረጡ ግለሰቦች ወይም እንግዶች መሆኑንም ይገልፃሉ። ምግብ በሚመገቡበት ሰዓት የኑዌር ቤተሰብ አስኳል እንደሆኑ የሚታመኑ አባቶች መጀመሪያ፣ ከአባቶች ቀጥሎ ልጆችና እናት ደግሞ በመጨረሻ እንደሚመገቡና ይህም የባሕሉ አንዱ አካል መሆኑን ይገልፃሉ።
ከላይ የተዘረዘሩት በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የብሔረሰቦች ባሕላዊ ምግብና የአዘገጃጀት ሥርዓት ይሁኑ እንጂ ኢንስቲትዩቱ በርከት ያሉ ባሕላዊ ምግቦችን በሳይንሳዊ መንገድ እያጠና በየዓመቱ ያሳትማል። የዚህ ሳይንሳዊ ጥናት ዋና ዓላማም የማኅበረሰቡን ባሕል መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ ሲሆን፤ ከዚያ ባሻገር ወደ ንግድ ሥርዓቱ እንዲገቡ በትምህርትና ሥልጠና ውስጥ ማካተት ነው። ሆቴሎች እንዲሁም አገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻዎችም ለመላው ኢትዮጵያውያን ብሎም በጉብኝት ወደ ሀገሪቱ ለሚገቡ ቱሪስቶች እንዲያስተዋውቁት መንገድ የሚከፍት ጭምር ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም