ትንሽ ብቻ ዞር…

ማንበብ ስወድ ለጉድ ነው። ከዕለት ተዕለት ሱሶቼ መሐል በኩሩ ሆኖ እንደቡናና ትንባሆ ያዳክረኛል። የእውቀት ማረፊያው አእምሮ ነው። በልብ በኩል ደግሞ ስር ይሰዳል። የአእምሮ ብቻ መሆንና የአእምሮና ልብ መሆን የተለያዩ ማንነቶች ናቸው። የአእምሮ ብቻ መሆን እንደአሜሪካና ሰሜን ኮርያ እየተዛዛቱ መኖር ሲሆን፤ የአእምሮና ልብ መሆን ግን ከዛ የገዘፈ ነው።

ይህንን ከሚያክል ፍልስፍና ጋር እየተሟገትኩ ወዳንድ ካፌ ሰተት አልኩ። ቡና አዘዝኩ። በስኳር ብያት በጨው፣ በጤናዳም ብያት በሌጣው፣ ለዛውም በሸራፋና በገባጣ ስኒ፤ ይሄ ሳያንስ ግማሹን ሳህኑ ላይ አፍስሳ ድርበብ የሆነ ቡና አቀረበችልኝ። እስኪ ይሁን ስል ወደ አፌ አስጠጋሁት። ቡናው ቀዝቅዞ ነበር። አንዳንድ ቀኖችን እንዲህ ናቸው የሆነ ቦታ፣ የሆነ ሰው ላይ ይጥሉንና ያጎድሉናል።

በዚህ ስሜት ውስጥ ሳለሁ ሎተሪ አዟሪና ጋዜጣ ሻጭ፣ እኔ እበልጥ እኔ በሚመስል የብኩርና ፉክክር ይመስለኛል፤ ሰፊውን በር ለአንደኛነት ተቀራምተውት እኩል በሚባል ፍጥነት ወደ ውስጥ ተማገዱ። ከሁለቱም ከንፈር በላይ የንፍጥ ድርቆሽ ይታያል።

ለሃያ አመት ሎተሪ ቆርጬ ከማስተዛዘኛ ባለፈ ዕድል ያልቀናኝ ባተሌ ነኝ። ለዛሬ ግን ሎተሪውን አልደፈርኩም። ወደ ጋዜጣው ዞሬ ባለላባሙን አፍንጫ ልጅ በምልክት ጠራሁት። አፌ የነበረውን ስኒ ወደ ጠረጴዛው ልመልስ አፍታ በወሰድኩበት ቅጽበት እንዴት እንደደረሰ እንጃ፣ ጎኔን ሲታከክ አገኘሁት። ምንም አላልኩ። የራሴን ልጅነት ከእሱ ልጅነት ጋር በላመሉ አነካክቼ ወደ ታቀፈው የጋዜጣ ክምር ተላለፍኩ። ተራችን እስኪደርስ ድረስ አቃቂር አውጪዎች ነን፤ ተራችን ሲደርስ አቃቂሩ በእኛ ላይ ነው።

ጋዜጣውን መዝዤ ፊት ለፊቴ ዘረጋሁት። ሰከን ብዬ ፍሬ ሀሳቡን ለመረዳት ሞከርኩ። በትምህርት ዘርፉ ላይ የተጻፈ መረጃ ተኮር ጥናታዊ ጽሑፍ ሆኖ አገኘሁት። በአንድ ሁነኛ ሊቅ የተጻፈ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ እንድመሰጥበት አደረገኝ። የእኛን ሀገር መነካካቱ፣ ከቴክኒክና ሙያ ይልቅ ዩኒቨርሲቲ ተኮር ትውልድ መፈጠሩን በመተቸት ያወሳል። አንዳች እንዳያመልጠኝ አይኖቼን ወደ ጽሑፉ መግቢያ በመስደድ ጀመርኩ።

ከንባቤ በኋላ ጋዜጣውን ዘግቼ ስለሀገሬ መብሰልሰል ጀመርኩ። ልቤ መንደራችን ወዳለው ለብዙ ሥራ አጥ ወጣት የሥራ ዕድል ወደ ፈጠረው ወዳጄ ሸፈተ። በሥራና በክሂሎት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ወደ ተረፉ፤ ከመንግሥት እጅ ሽልማት እስከመቀበል ወደ ደረሱ ጓደኞቼም ተዛመትኩ። ራሴን ሸፍኜ እንጂ ቴክኒክና ሙያ ተምረው ከተሳካላቸው መሐል አንዱን ነኝ። የእኔ ይቆይና ስለሁለቱ ወዳጆቼ ላውጋችሁ።

የብዙዎቻችን ሕልም ፕሪፓራቶሪ መግባት፤ ከዛም ዩኒቨርሲቲ ሰንብቶ መመረቅ ስለነበር፤ አጋጣሚ ሆኖ እኔና አራት ጓደኞቼ ቴክኒክና ሙያ ገባን። ያን ጊዜ ሳስበው በብዙ ኅዘን ነው። ሕይወት ቀጠለ..እየመረረንም ቢሆን በእንጨት ሥራ፣ በሥራ ፈጠራ ክሂሎት እና በኤሌክትሪክ ዝርጋታ ላይ ሰንብተን ተመረቅን። ነገሮች ሁሉ ባልጠበቅነው መንገድ መሄድ ጀመሩ። ጊዜው የእኛ የሆነ እስኪመስለን ድረስ የታጠፍንባትን ያቺን የሕይወት እጥፋት እያሰብን ጮቤ ረገጥን።

አብረውን የገቡ ሰባት ልጆች በላቀ ውጤት እዛ ሲቀሩ እኔና ወዳጆቼ ግን በሙያችን የግል ሥራችንን ለማስቀጠል ወጣን። አንደኛው በተማረው የእንጨት ሥራ መዲናችን ላይ ስመጥር ቢሊየነር ሆኗል። ከሀገር አልፎ ከዱባይ በሚያስመጣቸው ዘመናዊ ፈርኒቸሮቹ ለብዙዎች የእንጀራ ገመድ በመሆን ስሙን በወርቅ ቀለም ጽፏል። ሁለቱ በተማሩበት የልብስ ስፌት ሙያ ሰፊ የገበያ አማራጮችን በመዘርጋት ከታማኝ ግብር ከፋዮች ተርታ ተሰልፈዋል። እኔም በተመረቅሁበት የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ስራ ትላልቅ ሆቴሎችንና ሕንጻዎችን በጨረታ በመውሰድ ለብዙዎች ተርፌአለሁ። በጣም የሚገርመው ዛሬ ለበርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሥራ እድሎች ሆነናል፤ በርካቶችንም ቀጥረን አብረውን በመሥራት ላይ ናቸው።

አሁን ላይ ለትውልዱ የማስተላልፈው፣ ትውልዱ ቢያውቀው የምላቸው ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው አእምሯችንን በእውቀት እንደምናፋፋ ሁሉ እጆቻቸውን በሥራ የምናፍታታበትን የሙያ መቅሰሚያ ኢንስቲትዩት መድፈር..ሌላው ከዩኒቨርሲቲ አስተሳሰብ ወጥተን ሕይወት በከፈተችልን መንገድ ስኬታማና ውጤታማ በመሆን ከባላሻራዎች ጎን መቆም የሚሉት ናቸው።

ሰፊ ሀገር..ግዙፍ ታሪክ በብዙኃነት የታጨቀ እሴትና ባሕል ዋነኛ መጠሪያችን ነው። በሥርዓት የዳበረ፣ በወንድማማችነት የቆነጀ ከዚህ እስከዛ የሌለው የኅብረብሔራዊነት ውሕድ ሌላኛው ቅጥያ ስማችን ነው። በዚህ ደማቅ ስም ውስጥ ድህነትን ጠሪ፣ ኋላቀርነትን ዘካሪ ሀሳብና ብስለት ያልተቃኘባቸው ማኅበራዊ ልምምዶች ውበታችንን አጠይመውታል። እነዚህ ልምምዶች ሀሳብ የገዘፈበትን ልዕለሰብ ሽረው ለድህነት በር ከፋች ሆነው አብረውን ከሰነበቱ ከራርመዋል። እንደመነሻ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ተሞክሮዎቻችንን ቃኘን እንጂ ከመማር ማስተማሩ ጋር በተያያዘ የውጤት ማሽቆልቆልንና ስንፍናን ከሙያ ሥልጠናና ከተግባረዕድ ጋር የማያያዝ ችግሮች አሉብን።

ከዚህ ሁሉ የሀሳብ ንውዘት ወጥቼ ወደ ራሴ ስመለስ..አይ የኔ ነገር! ያን ባለላባም አፍንጫ ጋዜጣ ሻጪ ሂሳብ አልከፈልኩት ኖሮ ፊቴ እንደተገተረ አገኘሁት። በእውነቱ ጸጸተኝ። ልክ እንዳይደለሁ ከመሰማት ባለፈ የጥፋተኛነት ለበቅ ሸነቆጠኝ። ስንት ደቂቃ ዝም አልኩ? ለምን ያክል ጊዜ አርምሞ ውስጥ ነበርኩ? በዛ ሁሉ ዝምታ ውስጥ አብሮኝ ዝም እንዳለ ሳስብ፣ ለሆሳሴን ሳይገረስስ ወደራሴ እስክመለስ መጠበቁን ሳስብ፣ ከዓላማው አስተጓጉዬ ስሬ እንደገተርኩት ሲገባኝ በራሴ አፈርኩ። አይኔን አተራምሼ ንፍጣሙን ጓደኛውን ሻትኩት .. አልነበረም። ጓደኛው ትቶት እንደሄደ ሳውቅ ደግሞ የበለጠ በዳይ መሆኔ ተገለጠልኝ። አንዳንድ ከነፍስ ማጥፋት እኩል የማይተናነሱ ይሄን መሳይ ጥፋቶች በእያንዳንዳችን እጅ ላይ አሉ። ለእኛ ምንም የማይመስሉን ሌላው ጋ ግን እንደፓስፊክ የገዘፉ ባዶነቶች።

እንደእኔ ያሉ በቴክኒክና ሙያ በልጽገው ራሳቸውን የቀየሩ አእምሮዎች ሕይወትን በተመለከተ ከጊዜ ጋር የሚያቆራኙት መልስ አላቸው። ደፍሮ አይናገረኝ ወይም አይክሰሰኝ እንጂ ከዚህ ብላቴና ላይ ብዙ እንዳጎደልኩ አውቃለው። ሕይወት ለእኔ ጊዜና ስኬት የተሰሉበት እውቀት፤ አሊያም አረዳድ፤ አሊያም ፍልስፍና ወይም ተሞክሮ ነው። የቆመበትን በማስላት ከዋጋው በለጥ አድርጌ በመክፈል ልክሰው እና ቀን ሙሉ ላስፈነድቀው አሰብኩ። ከዚህ ውጪ ምንም መካሻ እንደሌለኝ ሳውቅ ና ወደዚህ ስል በአይኔ ጋብዤው ከፒጃማዬ ውስጥ መዝዤ እጁ ላይ አስጨበጥኩት። አምጣ የምለው መስሎት ባለማመን እስከ ውጪ በር ድረስ የኋሊት እየተራመደ ሲያየኝ ነበር። የውጪውን በር እንዳለፈ በሳቀ ፊት እንዴት ፈጥኖ እንደሮጠ ለሁልጊዜ ይገርመኛል። ሩቅ ደርሶ ዞሮ ሲያየኝ በበሩ በኩል ሳስተውለው ነበር። መጨረሻው ናፍቆኝ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ቃኘሁት … ልጃገረድ ነፍሱ ራሷን በፀደይ ሰማይ ስር ደብቃ እንደመብረቅ ስትብለጨለጭ አየኋት። ጸጸቴ ድራሽ አባቱ ጠፋ . . አንድ እኩል ሆንን።

መጥፎ ልምምዶቻችንን ሽረን እጆቻችንን ሙያ ማስለመድ ከነበርንበት ፈቀቅ የምንልበት የቀጣዩ ጊዜ ትንሳኤአችን ነው› በሚል መቋጫ ሀሳብ ለዛ መራራ ቡና 25 ብሬን ገብሬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ባለላባሙ አፍንጫ ጋዜጣ ሻጪ በሄደበት መንገድ ዓይኔን ስሰድ ከርቀት አየሁት … ብርሀን ለብሶ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016

Recommended For You