ሀገራችን በብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ብትሆንም እነዚህን ሀብቶች ወደሚጨበጥ ልማት መለወጥ ባለመቻሏ የድህነት እና የኋላ ቀርነት መገለጫ በመሆን ረጅም ዓመታትን አሳልፋለች። በየጊዜው ከሚያጋጥሟት ችግሮች ለመውጣትም እጆቿን ዘርግታ የሌሎችን ምፅዋት ስትጠብቅም ኖራለች።
ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመሻገር በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም፣ በዘመናት ከሚከተለን የግጭት አዙሪት መውጣት ባለመቻላችን፣ ጥረቶቹ ውጤት አምጥተው የምንመኛትን ያደገች፣ የበለፀገች፣ ለዜጎቿ የተመቸች፣ የትምክህት ምንጭ የሆነች ሀገር ለመፍጠር ሳንችል ቀርተናል።
ባለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ያሉትን ሀገራዊ ትርክቶች እንኳን ብንመለከት፣ በነዚህ ዓመታት ውስጥ እንደ ሀገር የጀመርናቸው የለውጥ ንቅናቄዎች ዋነኛ ዓላማ ሀገርን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት የመታደግ፣ ሀገራዊ የማደግ፣ የመበልፀግ መሻትን እውን ለማድረግ ከፍ ባለ መነቃቃት የተጀመሩ ናቸው።
በተለይም እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረጉ ጥረቶች በየዘመኑ ከፍ ያለ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ሆነዋል። የ66 ለውጥ ሀገር ከፍተኛ በሆነ የድርቅ አደጋ የተመታችበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ለሞት የተዳረጉበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት እናደርጋለን” የሚል መፈክር የተስተጋባበት እንደነበር የሚታወስ ነው።
በርግጥም ሀገሪቱ ካላት ከፍተኛ የውሀ ሀብት፣ ለእርሻ ተስማሚ አየር፣ የሚታረስ መሬት እና ሰፊና የሚተጋ የሰው ጉልበት አንጻር፣ “ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት እናደርጋለን” የሚለው የዘመኑ ትውልድ መነቃቃት፣ ወደ ተግባር ተለውጦ ተጨባጭ ፍሬ የማያፈራበት ምንም ተጠየቅ አልነበረውም። መነቃቃቱም እንደተባለው ሀገረቱን የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ የነበረው አቅም ከፍያለ ነበር።
ይህም ሆኖ ግን ለውጡና ለውጡ የተገዛበት ሀገራዊ መንፈስ በተለያዩ ቡድናዊ ፍላጎቶች እየተቀዛቀዘ፣ ፍላጎቶች የሚስተናገዱበት የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አስተሳሰቡን የሚሸከም ሀገራዊ አእምሮ መፍጠር ባለመቻላችን ነገሮች ወዳልታሰበ አቅጣጫ ሄደው፣ ሀገር እና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት ታሪካዊ ክስተት ተፈጥሯል።
በዘመነ ደርግ ሀገርን የዳቦ ቅርጫት የማድረጉ መነሳሳትን ተጨባጭ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። አረንጓዴ የምርት ዘመቻ በሚል ሀገራዊ አቅሞችን በማቀናጀት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል፣ ዘመናዊ የመንግሥት እርሻዎችን በማስፋፋት ሀገራዊ ችግሩን ለመሻገር የተደረገው ጥረትም የዚሁ እውነታ አካል ነበር።
ጥረቱ በመንግሥት እና በተለያዩ ቡድኖች መካከል በነበሩ የተቃርኖ ፍላጎቶች እና፣ ፍላጎቶቹን በኃይል ተግባራዊ ለማድረግ በተፈጠሩ አውዳሚ የእርስ በርስ ግጭቶች/ጦርነቶች የተነሳ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ሳይሆን ቀርቷል። ያም ሆኖ ግን ጥረቱ እንደ ሀገር ያሉንን አቅሞች አቀናጅተን መንቀሳቀስ ከቻልን ስኬታማ መሆን እንደምንችል ተጨባጭ ማሳያ መሆን ችሏል ።
በዘመነ ኢሕአዴግ የተሻለ ሀገራዊ ሠላም ቢኖርም፣ ኢሕአዴግ መራሽ መንግሥት እንደ ሀገር ግብርና መር ኢኮኖሚ ተግባራዊ እንደሚያደርግ በፖሊሲ ደረጃ ቢያስቀምጥም፣ ከፖሊሲ አቅጣጫ ባለፈ ለዘርፉ ተገቢውን ስትራቴጂክ ትኩረት ባለመስጠቱ እንደ ሀገር በምግብ እህል ራስን የመቻል የስድስት አስርተ ዓመታት ጉዟችን ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት ሳይችል ቀርቷል።
ከለውጡ ማግስት በሕዝብ አዎንታ ወደ ሥልጣን የመጣው ብልፅግና መንግሥትም ቢሆን ይህን በትውልዶች መካካል ከፍ ያለ ራዕይ ሆኖ የቆየውን በምግብ እህል ራስን የመቻል፣ ከዚያም አልፎ ለሌሎች የመትረፍ ሀገራዊ መሻት ተጨባጭ እውነታ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። እየተመዘገበ ያለውም ውጤት ተስፋ ሰጭ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
የለውጥ ኃይሉ በምግብ እህል ራስን ለመቻል ከዚያም አልፎ በልማት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመረው ሀገራዊ ጥረት፣ በሕዝብ ውስጥ አዲስ መነቃቃት በመፍጠር፣ ትርጉም ያለው ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ለዚህም በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት ወዘተ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ተጠቃሽ ነው።
ይህ አሁናዊ የጅማሮ ስኬት አጠቃላይ ለሆነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ ጉዞ ሆነ፣ በምግብ እህል ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ሀገራዊ መነቃቃት እየፈጠረ ነው። ሀገሪቱ ካላት ከፍተኛ የውሀ ሀብት፣ ለእርሻ ተስማሚ አየር፣ የሚታረስ መሬት እና ሰፊ የሰው ጉልበት አንጻር፣ “ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት እናደርጋለን” የሚለው የቀደመው ዘመን ትውልድ መነቃቃት፣ ወደ ተግባር ተለውጦ ተጨባጭ ፍሬ ማፍራት እንደሚችልም እያመላከተ ነው።
አሁን ላይ ተስፋ ሰጭ የሆነው ሀገርን የዳቦ ቅርጫት የማድረግ የትውልድ መሻት፣ በምግብ እህል ለራሳችን በቅተን ለሌሎች የምንተርፍ ራዕይ በዚህ ትውልድ ተፈጻሚ እንዲሆን፤ ዛሬ ላይ ከትናንት ስህተቶቻችን ቆም ብለን መማር፤ የትናንቱ ትውልድ ይህን መሻቱን ለምን ተጨባጭ ማድረግ አቃተው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። እንደ ትውልድ የሚጠበቅብን ተወጥተን እንድናልፍ ያለን ተስፋም ይኼው ነው።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በየዘመኑ የነበሩ ትውልድ ስለሀገራቸው ያለሟቸው ትላልቅ ሕልሞች እውን እንዳይሆኑ ፈተና ለሆነው የፖለቲካ ባሕላችን ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን፤ እንደ ሀገር በሰከነ መንፈስ እና በጠራ አእምሮ ልንቀሳቀስ ይገባል። ይህን ማድረግ ባለመቻላችን ሊፈጠር ለሚችለው የሕልም መጨናገፍ ትውልዱ የታሪክ ተጠያቂ መሆኑ የማይቀር ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2016