ቤኒ ሀርሻው በዙምባራ

ጥበብ እግሯ ረዥም፣ እጆቿ ለግላጋ፣ ጣቶቿም አለንጋ ናቸውና ከወዴት ታደርሺኝ አይባልም:: መድረስ ስንፈልግ ማድረሻዋ እልፍ ነው:: ዛሬን ወደ የኛዎቹ የምእራብ ፈርጦች (ምእራብ ኢትዮጵያ) መንደር በዘመን ጥበብ ሠረገላ ብንፈረጥጥ ኅልቁ መሳፍርት ጥበባት ከአበባ እቅፍ ጋር ቆመው በክብር ይቀበሉናል:: እናስ ለማን ብለን እንቅር … እንሄዳለን እንጂ:: ጢም ካለው ባህል ጢቅ ያለ ጥበብ እያነሱ ማየት ስንፈለግን ሊያሳዩን፣ መስማት ስንፈልግም ሊነግሩን ብዙ አላቸው::

ጥበብ እየቀዱ ጥበብ ቢያጠጡን እንሰክር እንደሆን እንጂ በቃኝ፤ ጠገብኩ አንልም:: አብረን በፈሰስን ቁጥር ሁሉ እነርሱ ብቻም ሳይሆኑ እኛም ከውስጣቸው የተቀዳን ስለመሆናችን እናጤነዋለን:: ከጥበባቸው ጥበብን ከፍቅራቸው ኢትዮጵያዊነትን ነስተን እንወጣለን:: ሀገራችን የባለ አራት የሙዚቃ ቅኝቶች እናት ብትሆንም፤ ቅሉ ግን ብቻቸውን አስቀረናቸው እንጂ ብቸኛ አይደሉም::

ያወቅነው ጥቂት የማናውቀው ግን ብዙ ነው:: ገና ብዙ ያልታወቁና ያልተነገረላቸው የጥበብ ማድጋዎች በየማኅበረሰቡ ጓሮ ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ:: ጥያቄው ግን ማንስ ቆፍሮ ያውጣቸው? ያው እኛው … እኛው እራሳችን ነን እንጂ ሌላ ማንንስ ልንጠብቅ…ቆፍረን ያገኘናቸው ዕለት ከወርቅ አልማዝ የገዘፉ ማዕድናት ስለመሆናቸው እንረዳለን:: ከብዙ ጥቂቱም እዚህ ናቸው፤ እዚያ በቤኒሻንጉሎቹ መንደር ውስጥ ማለት ነው::

ከዚያ ከጠረፍተኞቹ ዓለም ውስጥ ያልታዩና ያልተሰሙ በርካታ የጥበብ ፕላኔቶች አሉ:: ያልተማሩ፣ ገና ያላወቁ ቢመስሉንም ሕይወታቸውን ግን ለጥበብ የውል ቃልኪዳን አድርገው አስረዋታል:: እናም ጥንትም ዛሬም የሕይወት እስትንፋሳቸው ያለዚህች ነገር ለመኖር አትችልም:: ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ጀርባ ጥበብ በአክናፏ ትረብብባቸዋለች:: እንደ ህጻን ልጅ ያስፈነድቋታል::

ከሀገራችን ደረት ላይ ልጥፍ እንዳሉ ከጡቶቿ ላይ ወተቷን እየማጉ ከውብ የተፈጥሮ ልምላሜ ጋር ኖረዋል:: ባንመለከታቸውም የጥበብን ማድጋ እየሞሉ እልፍ ዘመናትን ተሻግረው፣ በእልፍ የዘመን ቅኝት ውስጥ ተጠበው ዛሬም ይኼው አቲቲሽ… አጱንጱኝ ይሉናል:: እነርሱ መንደር ውስጥ ለሙዚቃ ትንፋሽ አያጥርም፤ ምን በድባቴ ቢወቃ እንኳን ለጭፈራው ሰውነት አይለግምም:: ያላቸውንማ ማንስ ችሎ ይቆጥረውና…ዙምባራና አኖባ፣ አጸጸሁና ቢልተኛ፣ ቦሎና ነገራ፣ አለፌና ቁዋ፣ ሀርሻና ሂጸሌ … ብሎ ጀምሮ መዝጊያ መንገዱ ይጠፋልና ከዚያማ ተደምሞ ዝም ማለት ብቻ …

ምን አለሽ ቤኒሻንጉል? ከማለት የሌላትን መጠየቁ ይቀላል:: ወዲያ ግድም ሲያቀኑማ ጥበብ ከሙዳይዋ፣ ተፈጥሮም ከምድር ገጸ በረከቷ አትሰስትም:: ለጋስ ሕዝብ፣ ትኩስ ጥበብ፤ ሀድራው የተዋበ ምድረ ገነት … ከእነርሱ መንደር ጎራ ብለው ከዘለቁ ሥራ መዋያው፣ ጥበብም ማደሪያው ነው:: ሥራና ኪነ ጥበብ ትቅፍቅፍ ብለው ፍቅርን ይሠራሉ:: ማኅበረሰቡ ብዙ ነው፤ በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ግን የእነኚህ ሁለት ነገሮች ኮከብ ገጥሞ አንዱን ያለ አንዱ ለማሰብ አይሞከርም:: የልባቸው ወርቅ አልፎም ከከርሰ ምድራቸው ላይ ተቆልሏል::

ቤኒዎቹ በጥበብ የሚፈሱበት ረዥም ቅጽበት አንድም የዚህን ጊዜ ነው … የከርሰ ምድሩን የድንጋይ ወርቅ ለማውጣት የልባቸውን የጥበብ ሙዳይ ያንጠለጥሉታል:: ሃይለኛው ብረት በእሳት ወላፈን እንደሚቀልጥ ሁሉ ጥበብም የወርቅ ቁፋሮውን የብርታት መንገድ እየከፈተ ጋሬጣውንም አለት አንከባሎ ወዲያ ያሽቀነጥርላቸዋል:: ወርቁም ይህን የጥበብ አጀብ ለምዶ እንዲሁ በዋዛ የሚወጣ አይመስልም:: የጥበብን ወርቅ እየሰጡ ከአፈሯ የድንጋይን ወርቅ ይቀበላሉ:: ተፈጥሮን በጥበብ ያጌጠ እንደ እነርሱ ማን አለና …

ቤኒሻንጉል ሲሉ አንድ ዓይነት ጥበብ፤ አንድ ዓይነት ማኅበረሰብ ብቻ አይደለችም:: ቤኒሻንጉል ጉሙዝማ … በዋልታና ካስማ የቆመች፣ በማገርና ወጋግራ የታጠረች፣ በጥበብ ምሰሶ ተቃኝታ በኢትዮጵያ ጡቶች መሃል የተንፈላሰሰች ዋርካ ናት:: ኢትዮጵያዊ መልክን ሰጥቶ ከጠረኗ ጋር ቢያውዳት ጊዜ ብዙ ሳለች ተፈጥሮና ፍቅር በአንድ ኩለው እንደ አንድ አሳመሯት:: አምስቱም ማኅበረሰብ እንደ ገመድ ተጋምደው ውብ መልክና እጹብ አንድነትን ፈጥረዋል:: ጉሙዝ፣ በርታ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ በቤኒሻንጉል ልምላሜ ቆመው ለጥበብ እንኮይን ያረግፉላታል:: የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን በፍቅር ህብረ ቀለማት ነክረው የሀገራቸውን የጥበብ ጥለት በወርቃማ ሸንተረር እያሸመኑ ከአይንና ከጆሮ በላይ የሆነውን ሳምራ ውበት ይኖሩታል:: ባህላቸው ብዙ ኪናዊ ጨዋታና ሙዚቃዎቻቸው ደግሞ ውለው አድረው እየሰሙት ቢከርሙበት በሀሴት ነብስን ያስታል እንጂ በቃኝ ብለው የሚጠግቡት አይደለም::

በአምስቱም ማኅበረሰቦች ውስጥ ጥበብ የሕይወት እስትንፋስ ልኬት እንጂ ማድመቂያ ብቻ አይደለም:: እንደ አንድ የሚጠቀሟቸው ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች በርካታ ቢሆኑም በተናጠል ደግሞ መታወቂያቸው የሆነ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ይኖራቸዋል:: በየአካባቢዎቻቸው የሙዚቃና መሰል ጥበባት እንደ እጣን ጢስ እየተንቦለቦሉ መዓዛቸው ከሩቅ የሚጣራበት ጊዜም እንዲሁ አለ::

ልክ የክረምቱ ወራት ሲቃረቡ ቤኒዎቹ ከመቼውም በላይ በጥበብ ዝናብ ይረሰርሳሉ:: ሰማይ ከላይ የደመና ጭጋጉን ለብሶ በመብረቅ ጉምጉምታ ድባቅ ሲያስመታ እነርሱ በዙምባራ ያጅቡታል:: የሚያስደነግጠውን ድምጽ በዜማ እያነኮሩ ወደ ውብ የዜማ ስልት ይቀይሩታል:: ለመውረድ አንድ ሁለት እያለ ጉምጉም ከሚለው የክረምት ዝናብ አስቀድሞ ለቤኒ ማህበረሰብ ታላቁ የሥራ ጊዜያቸው ነው:: ከማሳው እርሻቸውም ሆነ ከጋጥና ጉረኖው ከብቶቻቸው ጋር የዚህን ጊዜ የተለየ ቀጠሮ አላቸው::

ሁሉም በየፊናው ለሥራው ይሯሯጣል:: ምንም ይሥሩ ምን ያለሙዚቃና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ግን እንኳንስ እጅና እግራቸው ልባቸውም አይነሳም፤ ሃሳባቸው እሺ ብሎ ቀልባቸውም አይሰበሰብም፤ ገና ሳይጀምሩት ጉልበታቸው ዝሎ ሁለንተናቸው የሚለግም መስሎ ይሰማቸዋል:: ዘሩን ዘርተው አዝመራውም ሲያሽት ምርቱን ወደ ጎተራው ሲያግዙ ቆሚያ እየተነፋ ዜማው ወርዶ ጭፈራውም ይደራል:: ታዲያ በዚህ ሁሉ ግብር መሀል ለእነርሱ እንደ አበረታች መድሃኒት እየሆኑ ለጉልበታቸው ማንቂያ መቀስቀሻ ደወል እኚሁ በግጥምና ዜማዎች የሚታጀቡት የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ናቸው::

በዚህ ጊዜ በዋናነትም ዙምባራ ይገኝበታል:: እንደሊማሊሞ ዋሻ ክብልል ብሎ ከአፍ እስከ ቁርጭምጭሚት የሚምዘገዘውን ያን ረዥም ዋዛ ከአፋቸው ላይ ደግነው ከትንፋሻቸው ጋር ሲያዋህዱት ድምጹ ኩልል እያለ ይፍለቀለቃል:: ልክ የዙምባራን ድምጽ የሰሙ ጊዜ ነብሳቸው ከሞት መሀከል ፈልቅቃ ወደ ገነት ትነጥራለች:: ከባህላዊ ግጥሞቻቸውና ዜማዎቻቸው ጋር እያማሰሉ ሲያዋህዱት ደግሞ በቃ የሥራ ወኔያቸው እየገነፈለ ድካምና ድባቴዎቻቸውን ወደ እንጠረጦስ ያወርደዋል::

ከምስራቃዊ የሱዳን ጎድን ከሆነው የየገሪን ተራራማ ስፍራ ተነስተው እስከ ዓባይና ዳቡስ ሸለቆዎች ድረስ ተንሰራፍተው ከዝንተ ዓለሙ የኖሩት ጉሙዞቹ (የቀድሞዎቹ በርታዎች) ለባቡሩ እንደምትነጠፍ ሀዲድ እንግዳ ለመቀበል የእነርሱም ልብ በረዥሙ ትዘረጋለች:: አመለ ወርቅ ናቸውና ከላይ ከጸባኦቱ ምድራቸውን በወርቅ ማዕድን አንቆጥቁጦታል:: በዙምባራ የዜማ ደሴት እያዞነበሩ ይህንንም ያንንም ደስታቸውን ያጣጥሙታል:: ከጉሙዝዎቹ የደስታ ደሴት ውስጥም ሁሌም በየትኛውም ጊዜና ቦታ ዙምባራ የተሰኘው የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያቸው አለ:: ሁለት ክዋክብት በፍቅር ትዳር ገጥመው ሠርግና ምላሹን በፌሽታ ሲራጩበት ትንፋሻቸውን ከጥበብ ማሰሮ ውስጥ እየሳቡ በዙምባራው ጨረቃን ለምድር ያቀርቧታል::

ዙምባራም ያለ ህብራዊ አንድነት ተነጥሎ ለብቻ አይሆንለትም:: ትክክለኛውን የዙምባራ ጣፋጭ ድምጽና ዜማ ለማግኘት በአንድ ሆነው ጥምረት የፈጠሩ 12 አባላት ያስፈልጉታል። አሊያ ግን የዜማ ምቱ ተጓድሎ ውበቱ ይጠፋል:: አንዱ ቢጎድል አንድ አካል የጎደለ ያህል ነውና ትርጉም የማይሰጥ ጩኸት ብቻ ይሆናል:: የሙዚቃ ጠበብቱ የዙምባራ ሊቆች ያልተነገረለትን የዜማ ቀመር ቀምረው በአሥራ ሁለት የትንፋሽ ውህደት ላይ አሳርፈውታል:: የቤኒዎቹ በርታዎች ሴቶቹ ቶብ፤ ወንዶቹ ደግሞ ጀለቢያቸውን ለብሰው በሠርግና በዓላቱ ሁሉ ከአንድ የሙዚቃና የባህል ጨዋታ ላይ ሽር-ብትን ሲሉ መመልከትማ ማንነትን ያስረሳል:: ገንፎውንና ቄንቄሱን ከሸክላው፣ ጥበብን ከዙምባራው እያነሱ ጠግበው ያጠግባሉና ከእነርሱ ጋር ዘላለምን ያስመኛሉ::

ቤኒ ቤኒሻንጉል ብለው ከሮጡማ መንገዱ ወደ ጀግናዎቹና ጎበዛዝቱ የጉሙዝ ቁልቁለት ያደከድከናል:: መሄድ፣ መሮጥ ያስመኘናል:: ደርሰው የተመለከቷቸው እንደሆነ ባህላዊ የፍቅር ጥበብና የአኗኗር ዘያቸው ከዓይንና ልባችን ላይ ያበራል:: የልባችንን ጽለመት ገፎ ጸአዳውን የሕይወት ነጠላቸውን ያከናንበናል:: ድንገት ከተፍ ስንል፤ ጠላት አልፎ ከግዛት ላይ ሲገባ እንደሚጎሰመው ያለ የነጋሪት ድምጽ አያሰሙንም:: ይልቅስ ቆሚያቸውን ብድግ አድርገው በአፋቸው ትንፋሽ ልባችንን በፍቅረ ጥበብ ይማርኩታል:: የስሜት በራችንን በርግደው በደስታ ሀሴት ይሞሉናል:: በምን ካልን ደግሞ፤ ቆሚያ በተሰኘው ባህላዊ የትንፋሽ መሳሪያቸው … በጉሙዞቹ መንደር ውስጥ የቆሚያ ድምጽ ሳይፍለቀለቅ ጀንበር ወጥታ ጀንበር አትጠልቅም::

በርከት ያሉ ባህላዊና መንፈሳዊ ክብረ በዓላትን የሚያዘወትሩት ጉሙዞቹ፤ ከእነዚህ ትውፊታዊ ክዋኔዎቻቸው መሳ ለመሳ ቆሚያ የነብስ አዱኛቸውን እየሰበሰበ የሕይወትን ዜማ ያዜምላቸዋል:: ለሙዚቃ መሣሪያው ያላቸው ክብር ገዘፍ ያለ በመሆኑ እንደተፈለገው በየትኛውም ሰዓት ማንም እየተነሳ አይጫወተውም:: የተቀመጠለት የራሱ የሆነ ጊዜና ቦታ አለው:: በብሔረሰቡ ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና ያለው ሰው ሲሞት ቆሚያ የነጠላውን ጥለት ሽቅብ ሰቅሎ ይነሳል:: የዘመን መለወጫን ጨምሮ ልዩ ልዩ ክብረ በዓላት ሲኖሩም ድምጹ እረፍት አይኖረውም:: ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ሌላ የጥበብ ጽላሎት አላቸው:: ለሙዚቃዊ ጭፈራና ጨዋታው ማድመቂያ በሴቶቹ እግር ላይ ኤፂፃ ይታሠራል:: የጉሙዝ ሶታና ኮረዳ አንዴ ከጥበብ ትንፋሽ የሳቡ እንደሆን መላው እንቅስቃሴዎቻቸው ሁሉ ባህል ጥበብ … ጥበብ ሙዚቃ … ሙዚቃና ጨዋታ ነው::

ሴቶቹ ጨፋሪዎች ኤፂፃን እንደ እግር አልቦ ከቁርጭምጭሚታቸው አካባቢ በማሰር ዘለል • • • ዘለል • • • እያሉ እግራቸው ከመሬት ተነስቶ ወደ መሬት በተመለሰ ቅጽበት ሁሉ ልዩ ህብረ ዜማዊ የሙዚቃ ድምጽን ይፈጥራሉ:: ድምጹም ጽናጽል ከሚሰጠው ድምጸት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው:: በብዛት ሴቶቹ ቆመው የሚታዩት በሁለት ረድፎች ለሁለት ሁለት በመጣመር ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ሌላኛው ያልተመለከቱት የኬሮግራፊ ጥበባቸው ነው:: ትዕይንቱ ሲጀምር ተወዛዋዦቹ የድምጻዊውንና የቆሚያውን የሙዚቃ ምት እየጠበቁ ዘለል ዘለል በማለት በሆድ አሊያም በደረት ይነካካሉ:: ከስር ቅጭል! ቅጭል! ክሽ! ክሽ! የሚለው ኤፂፃው ደግሞ ውበትና ድምቀቱን ያፈካዋል:: በጉሙዞቹ ሰማይ ላይም ማራኪው የባህል ጥበብ ከምድር ሽቅብ እንደ እንፋሎት እየተንፎለፎለ ህብረቀለማዊ የጥበብ ቀስተደመናን ሠርቶ እየተዥጎረጎረ ያብረቀርቀዋል::

የዓባይን ወንዝ ሰማያዊ ጢስ እየተከተሉ በጉም በደመናው መሀል ከቀዘፉ መሄድን እንጂ መመለስን አያስመኝም:: ከወርቃማው የጉም ጢስ መሀል እልፍ ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ እየተመሙ ሲታዩማ ሺህ ናቸው ስለተባለላቸው ስለ ሺናሻዎቹ የጥበብ በረከት ካላነሱማ ምኑን አወሱ… “ሺኒ” የመጀመሪያ ወይም ቀደምትነትን የምታመለክት የእነርሱው ቃል ናት:: “አሻ” ማለት ደግሞ ሕዝብ ነው:: ቀደምቱ ሕዝብ ምንስ ጥበብ ይኖራቸው ይሆን … እነዚህም በበዓላት ጊዜ ልዩ ትውፊታዊ የጥበብ ክዋኔ አላቸው:: በበዓሉ ቀናትም ዘመድ፣ ወዳጅና ጎረቤቱ ተሰባስቦ ጭምቦ የተሰኘውን ምግባቸውን ሲመገቡ በቦርዴ ጠላው ብቻ አይወርድላቸውም:: ይልቅስ የገበታውና የጨዋታው ማንሸራሸሪያ፤ ሙዚቃና ጥበባዊ ትዕይንት የተሞላበቱ ጭፈራ ነው::

አራተኞቹን የጥበብ ፈርጦች ፍለጋ ለወጣ አቅጣጫውን ተከትሎ በመሄድ ከሱዳን ድንበር አካባቢ ደርሶ ቆም ብሎ ማሰብና ማነፍነፍ ይጠበቅበታል:: የዚያን ጊዜ የኦሮሚያን ክልል ተዋስነው የሚገኙት የማኦዎቹ ገዳሾላና ሽጎጎና፣ ጫንጋላና ፓሽማ፣ ውስኩና ሸንታ በፍቅር እቅፍ ጥበብ ይቀበሉናል:: እነዚህኛዎቹ በየጊዜው ከተፍ እያሉ የጥበብን ጮቤ የሚያስረግጧቸው ፌስቲቫሎቻቸው በርከት ያሉ ናቸው:: እጅን ከጥበብ ላይ አሳርፈው የሚሠሯቸው የእደጥበብ ሥራዎቻቸው አካል ሰውነታችንን እያሞቀ በውበት ወላፈን ያቀልጠናል:: በሠርጎቻቸው ላይ የመታደምን ዕድል ያገኘን እንደሆነማ ሙሽራይቱ እራሷ ጥበብ ስላለመሆኗ እርግጠኞች አይደለንም::

በጺል ጌጣጌጥና በጨሌዎች አምራና አሸብርቃ የጨረቃን እኩሌታ ከመሰለችው ሙሽሪትና ከጎምላሌው ሙሽራ ዙሪያ የሚከወኑት ትውን ጥበባት መደነቅ ያንሳባቸዋል:: ባህላዊ የሠርግ ዘፈኖቻቸውን መስማት ያነሆልላል:: የጭፈራ ስልታቸው ሲታከልበት ደግሞ አቧራው ብቻውን አይጨስም:: ወንዞች ሽቅብ እየፈሰሱ ፏፏቴዎች እንደ ሰው ቆመው ያጨበጭባሉ፤ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ከንፋሱ ጋር እየተውረገረጉ በኬሮግራፈር ተጠንቶ የተሰናዳ የሚመስል የዳንስ ስልት ያሳያሉ፤ የሚንቀለቀለው እሳት እንኳን ከቤኒዚን ጭዱ ጋር እየተስማማ ብርሃን ብቻ ይሆናል:: በእነርሱ ጥበብ፤ በእነርሱ ፍቅር የማይሆን የማይታይ የለም:: አምስተኛዎቹ ኮሞዎችም ሁሉንም ከሌሎቹ ጋር የሚጋሩ፣ በጎበዝ ገበሬ የተዘሩ ውብ አዝመራዎች ናቸው::

የሀገራችን የሙዚቃ ጥበብ ተዝቆ የሚያልቅ፤ ተነግሮም የሚያበቃ አይደለም:: ከፊት ዓይኖቻችን ላይ ያሉትን እንጂ ከውስጣችን እንደ ከርሰ ምድር ወርቅ ተቀብረው ያሉትን ገና ምኑንም አልነካናቸውም:: ሌላውን ሁሉ ትተን በዛሬውን ትኩርታችን የቆምነው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎች መስታየት ፊት ቢሆንም፤ የተመለከትነው ግን ፊትን የመመልከት ያህል ብቻ ነው:: በአሁኑ ሰዓትም ካሏት የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ዙምባራ ዘውዱን ጭኖ እናገኘዋለን:: በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል በሆነው በዩኔስኮ ተቋም ውስጥ ለማስመዝገብ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችም በሂደት ጉዞ ላይ ናቸው:: ቀጥሎም ሌላ ታላቅ የጥበብ መዝገብ እንከፍት ይሆናል::

ወርቃማዎቹ የጥበብ ጀልባዎች ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተሰባጠሩ ብሔር ብሔረሰቦችን አሳፍረው “ቤኒ ቤኒ … ቤኒ ሀርሻው … አለፌ ቁዋ በዙምባራ” እያሉ ከዓባይ ወንዝ እስከ ስናር ሱዳንና መላው ኢትዮጵያ በፍቅር ይሽከረከራሉ:: ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል፤ ሙዚቃዊ የጥበብ ማር ልውሳቸውን ግን ጆሮ ሰምቶና አጣጥሞ አይጠግበውም:: ከሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው ጠብ እያለ የሚፈሰው ትኩስ የጥበብ ወተታቸው እንኳንስ ሌላውንና ቄሱንም ጾም ያስፈታል:: ሲያወሩም መሽቶ ይነጋልና ከብዙ ቃላት በጥቂቱ ይህችን ስንኝ ቋጥሬ ልቋጭ::

ወርቃ ድንቁን እዩ ከጉሙዝ-ከበርታ፤

በኮሞ ሺናሻ የጥበብ እንቢልታ፤

በማኦ ጠበብት ደጅ ጦማሩ ሲፈታ፤

ይኼኔ ነው ጀባው አኖባው ለማታ::

አጱንጱኝ አጸጸሁ በዙምባራ ቁዋ፤

አቲቲሽ አጀረግ ቢልተኛው መረዋ፤

ዜማው ስልቱ ሀርሻ ኮዎ በጉብልዋ፤

ደጭ! ደጭ! ማለት ነው ይዞ ጥበብ ጽዋ::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2016 ዓ.ም

Recommended For You